Saturday, 08 October 2022 09:48

ሙሾ አውራጅነት ቢቃጣኝ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ሙሾ አውራጅነት ቢቃጣኝ
ለማዲንጎ ላውርድ ብዬ፣ የገጣሚ ቃል ቢወጣኝ
እንዲህ ነበር የሚያሰኘኝ፡-
ወይ ዋይ ዋዮ- ዋይ
ዋይ ዋይ ዋዮ- ዋይ
እሱ ከመሬት፣ ድምፁ ከላይ!
*    *    *
እናንት ቀባሪዎች፣ ዝቅ አርጋችሁ ማሱ
አይበቃውምና፣ ለድምፁና ለሱ!
*    *    *
አይ ያቀንቃኝ ነገር፣
አይ የቀን-ቃኝ ነገር፣
ልቡ የሸፈተ፤
ውርስ ስጠን ቢባል፣ ድምፁን ትቶ ሞተ!
*    *    *
አያዋጣም ስለው፣ እያዜሙ መኖር
አልበም ሰጥቶኝ ሄደ፣ የአዝመራውን መከር!
*    *    *
አይ የዘመኑ ሰው
አወይ እንዳንድ ሰው
ደስ እንዳለው መስሎ፣ ደስ እንዳለው ሆኖ
አለሁኝ እያለ
ጨረስኩኝ እያለ
እሱው ያልቃል ዘፍኖ
ክለቡን አድምቆ
ክቡን አሙቆ
ይሄዳል መንኖ!

እንደ መግቢያ
ማዲንጎ!
እንዲህ ነወይ ዜና ማለት?
እንዲህ ነወይ መርዶ ማለት?
እንዲህ ነወይ ድምጽ ቅጭት?!
ያ ከሆነ ሞትም ይሙት!
ያ ከሆነ አብሮህ ይሙት!
ተዘፍኖ እንጂ፣ ተለቅሶ አይደል
ያንተን መሳይ ሰው ስንብት!

ዋ! ማዲንጎ!
ማዲንጎ፤
አንተ የዜማ ዐይነ- በጎ!
ማን ፀነሰህ እጥበብ ቤት ማን ወለደህ አሳድጎ?!
 ማዲንጎ! አድጎ መወለድ ብሎ ቃል፣ አሁን እሄ አማርኛ ነው?
ሆኖም ያ ባንተ አየነው!
የቅላፄህ ስጋ- መንፈስ
እንዳሻህ በቦዩ ስንዲፈስ
ማን ቃኘህ ድምፀቱን ክኖ በሙዚቃ ግብር ድግስ?
ስትጠል መረዋ ቃጭል፣ የነጥላሁን ቡቃያ
ስትገዝፍ ብራቅ ነጎድጓድ የካሣ ተሰማ እኩያ፡-
“ከባልንጀራው ማታ የተለየ
እንደ አጥቢያ ኮከብ ሲነጋ ታየ!
… አባረርካቸው በቃ ተመለስ
ማንን ይተኳል አንተ ብትጨረስ!”
የሚባልልህ… አንት አንጀት አርስ
ማዲንጎ!
ምነው ጀምበርህ ዘመመ?
ያንገት በላይ ህመም እንጂ፣ የድምፅ ቅጭት የታለ?
የዘመን ትዝታህ እንጂ፣ ጠርህ መች ጎላ ተባለ?
ማዲንጎ!
ሬንጀ-ብዙ ሬንጀር መሰል፣
የጥበብ ጦር ልዩ ደወል
ወራጅ- ውሃን የሚያባብል
(የ) ደወል-ምላስ፣ የደዋይ ድል
ሰዓት ደርሷል “ንቁ” እምትል፣
የአንተም ሰዓትህ ደረሰ?
የድምፅህ ምት ለሰለሰ?
ያ እስግምግምታው ቀነሰ?!
ዋ ማዴዋ!
ነበርክ እኮ ቅን መለከት፣
ሲሻህም ድምፀ- ነጋሪት፣
አሊያም ደግ አንጎርጓሪ
ማልደህ እንደ ወፍ ዘማሪ፣
ነግተህ እንዳዝማሪ ጥሪ፤
ቃል ውሃ ልክህ ምጥን… ሆኖም ንፍገትን እማይዋጅ፤
ጠብታ- ጎርፍህ ገደል-ናጅ
ለስንት ወጣት ፈርእሚያበጅ
የስንቱ ወጣት አዋላጅ
አንት የጠዋት የጥበብ አዋጅ።
ጉሮሮ አንጀትን ሲስበው
ትንፋሽ ስንኝን ሲቃኘው
ማወቅ ለሚሻ ለገባው ያተ ፍሰት ነው ማስረጃው!
ሲመቸው  በደንገላሳ፣ እንደፈረሰ በሶምሶማው
ወይ እንደሰጋር በቅሎ ስግረት፣  ዘለግ ባለ ጅናኔው
ከበገናም ክራር አውታር በተሸረበ ምጣኔው
ድርብ- ነጠላ ሲያስኬደው
ምን ይላል ያ ያሬድ ሲሰማው
ዋይ ዜማ! ሲል የዘመረው
ዋ ዜማ! ሲል የዘፈነው
ማዲንጎ ላንተም እኮ ነው!
መጥኔ ለቅላፄህ ጠረፍ
ካጣሱት ለማይገኝ ፅንፍ!
እንደክት ልብስ ብርቅ ሆኖ፣ ሁሌ አሲድ ስንኝ ለሚያመጥቀው
ፅርሃርያም ለሚከትተው!
አወይ ለማዲንጎ /መጥኔ፣ ሰምና ወርቅ ---- በሰው!!
በድንገት ሄድክ አሉኝ እንጂ
አለህ ማዲንጎ ከኛ ጋር፣ ድምፅ እንደ ዕድሜ አይቀጭም።
እንደ ጠጅ ሣር፣ ለም ቄጤማ፣ ይለመልማል ዝንተ ዓለም!
አይገርምህም ማዲንጎ?
ክፉን ዘመን ተገን አርጎ
ለክፉ ዕጣ አደግድ
ሞት እኳን ዘፈን አማረው
የወሰደህ… ትዘፍንለት፤ ወይ ታንጎራጉር መስሎት ነው
ሞትስ ይሙት- ፍግም ያረገው!
እኛስ በድምፅህ ኗሪ ነን
እያሰብንህ እንኮራለን
ዛሬም ቃኖህ ኑርልን!
ዋ!ማዲንጎ!
አንተ ዜማ ዐይነ-በጎ!...
ከነቢይ መኮንን (ለማዲንጎ አፈወርቅ መታሰቢያ በሰይፉ በኢቢኤስ መነሻነት የተሸፈ)
መስከረም 22 ቀን 2015


Read 1740 times