Saturday, 29 October 2022 20:49

22ኛው የዓለም ዋንጫ በኳታር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

22 አስደናቂ ሁኔታዎች

ከጨዋታ ውጭን የምትቆጣጠረው ኳስ
አል ሪሃላ Al Rihla ለ22ኛው የዓለም ዋንጫ በአዲዳስ የተሰራች ኳስ ናት፡፡ የዓለም ዋንጫዋ ኳስ  እውነተኛ መረጃን ለVAR ባለሙያዎች የምታስተላልፍ፤ ፊፋ ለመጀመርያ ጊዜ ተግባራዊ ከሚያደርገውና በከፊል አውቶሜትድ ከሆነ የኦፍሳይድ መቆጣጠርያ ቴክኖሎጂ ጋር በመናበብ የምትሰራም ነች፡፡ በሜዳው ዙርያ የሚገጠሙ  12 ካሜራዎችን ከኳሷ እንቅስቃሴ ጋር በማዋሃድ  የሚሰራ ቴክኖሎጂ ተለጥፎባታል፡፡ከጨዋታ ውጭ የሆኑ ኳሶችን ለመቆጣጠር ፊፋ ተግባራዊ የሚሆነው አዲስ ቴክኖሎጂ ዳኞች ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንዲሰጡ ያግዛቸዋል፡፡
ረጅሙ የብስክሌት ጎዳና
ኳታር የዓለማችንን ረጅሙን የብስክሌት ጎዳናም ገንብታለች፡፡ በዶሃ የሚገኘው የኦሎምፒክ ደረጃ ያለው የብስክሌት ጎዳና በ33 ኪሜ ርዝማኔው በጊነስ ሪከርድ ሬከርድ የተመዘገበ ነው፡፡ ከጎዳናው 25.3 ኪሜትር በአስፋልት ኮንክሪት መነጠፉም ክብረወሰን ላይ ሰፍሯል፡፡
ከዓለም ሃብታም አገሮች ተርታ
ኳታር በድፍድፍ ነዳጅ ና ተፈጥሮ ጋዝ በተገነባው ኢኮኖሚዋ ከዓለማችን ሃብታም አገራት ተርታ ትሰለፋለች፡፡    ነዳጅ የኢኮኖሚ ዋልታዋ ሲሆን በጥልቀት ከተቆፈሩ ጉድጓዶች አንዱ 12290 ሜትር ተለክቷል፡፡ ኳታር ከሉክሰምበርግ፣ ስዊዘርላንድና ሲንጋፖር በመቀጠል አራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ የዓለም ሃብታም አገር ናት፡፡  አንድ የኳታር ዜጋ የነፍስ ወከፍ ገቢ እስከ 100ሺ ዶላር ይደርሳል፡፡
አረቢያን አጋዘን
አረቢያን አጋዘን የኳታር ብሄራዊ እንስሳ ሆኖ ይታወቃል፡፡ ይሄው አጋዘን  መሰል እንስሳ የኳታር ኤርዌይስ ሎጎ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በ1972 እኤአ ላይ ከዱር የጠፋው እንስሳ ከ10 ዓመት በኋላ እንደገና ወደ ዱር እንዲመለስ በማድረግ በማድረግ የኳታር መንግስት ከምድር ገጽ እንዳይጠፋ ተረባርቧል፡፡
በዓለም ዋንጫ ታሪክ ከፍተኛው የገንዘብ ሽልማት
በዓለም ዋንጫው ታሪክ ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ የተመደበ ሲሆን አጠቃላይ መጠኑ 440 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከ4 ዓመታት በፊት ራሽያ ካስተናገደችው 19ኛው የዓለም ዋንጫ በ40 ሚሊየን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ የዓለም ዋንጫው አሸናፊ 46 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኝ ያገኛል፡፡ በ21ኛው ራሽያ ላይ 38 ሚሊዮን ዶላር፤ በ20ኛው ብራዚል ላይ 35 ፤ በ19ኛው ደቡብ አፍሪካ ላይ 30፤ በ18ኛው ጀርመን ላይ 20  እንዲሁም በ17ኛው በጃፓንና ደቡብ ኮርያ ላይ 8 ሚሊዮን ዶላር ለዋንጫው አሸናፊዎች ተሸልሞ ነበር፡፡
ሌሎች ተሳታፊዎች የሚሸለሙት
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ለሁለተኛ ደረጃ 30 ሚሊዮን ዶላር፤ ለሶስተኛ ደረጃ 27 ሚሊዮን ዶላር፤ ለአራተኛ ደረጃ 25 ሚሊዮን ዶላር፤ ከአምስት እስከ 8ኛ ደረጃ ለሚያገኙት 17 ሚሊዮን ዶላር፤ ከ9 እስከ 16ኛ ደረጃ ለሚያገኙት 13 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ከ17 እስከ 32ኛ ደረጃ ለሚኖራቸው 9 ሚሊዮን ዶላር የሽልማት ገንዘብ የሚከፈል ይሆናል፡፡
የጭልፊት አደንና በረራ ስፖርት
በኳታር ጭልፊት ማልመድ፤ ልዩ የአደንና የበራራ ውድድር ማካሄድ የእግር ኳስን ያህል  አድናቂዎች እያፈራ ነው፡፡  የአየር ሙቀቱ ለጭልፊቶቹ ተስማሚ በሚሆንበት ጊዜ  ለአሸናፊዎች ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማቶች እየተዘጋጀ ልዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ይካሄዳሉ። ጭልፊቶች ከኳታራዊያን የእለት ኑሮ  ፈጽሞ የራቁ አይደሉም፡፡ በዶሃ ከተማ ያሉ የጭልፊት መሸጫ ሱቆች የቅንጦት መኪና ከሚሸጥባቸው ማዕከሎች ደረጃቸው ይስተካከላል፡፡ ዋጋቸው ከ2000 ፓውንድ ጀምሮ እስከ 200ሺ ፓውንድ ይደርሳል፡፡
የግምሎች ሽቅድምድም
በኳታር ተወዳጅ ከሆኑ ስፖርቶች የግምሎች ሽቅድምድም ዋንኛው ነው፡፡ ስፖርቱ በዶሃ ከተማ ውስጥ አልሻሃንያ የሚባል ዘመናዊ የመወዳደርያ ትራክ ተሰርቶለት የኳታር ባህል መለያ ሆኗል፡፡  የስፖርት አይነቱ የቱሪስት መስህብ ሆኖ ቆይቷል። ከዶሃ መሃል ከተማ የአንድ ሰአት የመኪና መንገድ ርቆ የሚገኘው አልሻሃኒያ በግመሎች የሚካሄዱ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ውድድሮችን ያስተናግዳል፡፡ በአንድ አመት ውስጥ ከ6000 በላይ ግመሎች በዚህ ውድድር ይሳተፋሉ፡፡ ተወዳዳሪ ግመሎች በሰዓት እስከ 40 ማይል ይሮጣሉ፡፡
ቡርጃ ዶሃ
በዶሃ ከተማ ከሚገኙ አስደናቂ  ህንፃዎች ቡርጃ ዶሃ ታወር አንዱ ሲሆን በፈረንሳዊው አርክቴክት ጂን ኖቭል የተሰራው ባለ 48 ፎቅ ህንፃ ነው፡፡
 ማቻቡስ
ማቻቡስ የኳታር ተወዳጅ ብሄራዊ ምግብ ነው፡፡ ከሩዝ፤ ስጋ፤ ሽንኩርት፤ ቲማቲም እና ከጀተለያዩ ቅመማ ቅመሞች ጋር ተዋህዶ ይሰራል፡፡
ስፖርት አዘጋጅነት በኳታር
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ መስተንግዶ ኳታር ከዓለማችን ታላላቅ የስፖርት መድረኮች የመጀመርያውን ማዘጋጀቷ ነው፡፡  በ2006 እኤአ ላይ ያዘጋጀችውን የኤስያ ኦሎምፒክ በ2030 እኤአ ላይም እንድታስተናግድ ተመርጣለች፡፡
አዳዲስ ታሪኮች የበዙበት የዓለም ዋንጫ
22ኛው ዓለም ዋንጫ  በታሪክ ትንሿ አገር የምታዘጋጀው፤ በፈረንጆች አዲስ አመት ዋዜማ ለመጀመርያ ጊዜ የሚካሄድ፤ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ እግር ኳስ አፍቃሪዎችና ቱሪስቶች የሚሳተፉበት፤ በድምሩ እስከ  5 ቢሊዮን ተመልካች እንደሚያገኝም የተገመተ ፤ እስከ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል የተጠበቀ ነው፡፡
የምንግዜም ውዱ የዓለም ዋንጫ
በ220 ቢሊዮን ዶላር ወጭው የምንግዜም ውዱ ዓለም ዋንጫ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከብራዚልና ከራስያ ዓለም ዋንጫዎች በ10 እጥፍ፤ ከደቡብ አፍሪካ ዋንጫ በ64 እጥፍ የሚልቅ በጀት ወጥቶበታል፡፡

Read 1229 times