Saturday, 19 November 2022 20:37

22ኛው የዓለም ዋንጫ በኳታር ተጀምሯል

Written by  ግሩም ሰይፉ ከዶሃ ኳታር
Rate this item
(2 votes)

22ኛው የዓለም ዋንጫ  በአልክሆር ከተማ በሚገኘው አልባይት ስታድዬም  አዘጋጇ ኳታር ከኢኳደር በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ይጀመራል፡፡  ለዓለም ዋንጫው በተዘጋጀው ልዩ የመክፈቻ ስነስርዓት ላይ ከቢቲኤስ የሙዚቃ ቡድን ጃንኮክ፤ የኮሎምቢያዋ ሻኪራ፤ብላክ አይድ ፒስ፤ ሮቢ ውልያምስና ኖራህ ፋቲህ ሙዚቃቸውን ያቀርባሉ፡፡
የኳታር መንግስት ከዓለም ዋንጫው ጋር በተያያዘ በከፍተኛ የፀጥታና ደህንነት አገሪቱን ማስተዳደሩን ቀጥሏል፡፡ ባለፉት 3 ቀናት በኳታር ከተማ ዶሃ በመገኘት እንዳስተዋልነው የኳታር ህዝብ ዓለም ዋንጫውን በጉጉት እየተጠባበቀው ይገኛል፡፡ ኳታሪያውያን በነጫጭ ባህላዊ አልባሳቶቻቸው ተውበው የዓለም ዋንጫውን እንግዶች ለመቀበል ዝግጅታቸውን  አጠናቅቀዋል፡፡


የኳታር መንግስት በመንግስት የስራ ሰዓቶች ላይ ለውጥ ማድረጉ ሲታወቅ ትምህርት ቤቶችም እንዲዘጉ ተወስኗል፡፡ የዶሃ ከተማ ዋና ዋና አውራጎዳናዎችና አደባባዮች  በታዋቂ ተጨዋቾች ግዙፍ ቢልቦርዶችና ምስሎች ተጥለቅልቀዋል፡፡  አመሻሽ ላይ የዶሃ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች  በዓለም ዋንጫ ተጨዋቾች ምርጥ የቪድዮ ምስሎች እንደ ቴሌቭዠን ስክሪን  እያሳዩ ናቸው፡፡
ትልልቅ ሱፕር ማርኬቶች፤ ህዝብ በብዛት የሚገኝባቸው አደባባዮችና  የከተማዋ መለያ የሆኑ ህንፃዎች በተሳታፊ አገራት  ሰንደቅ አለማዎች አሸብርቀዋል፡፡ ጨዋታዎች ወደ የሚካሄዱባቸው ስታድዬሞች አውራ ጎዳናዎች በልዩ ፅዳትና የተሟላ አቅም መስተንግዶውን በሚያሳምሩበት ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡  ዓለም ዋንጫውን ከስታድዬሞቹ ውጭ ለሚታደሙ  ወደተሰሩት  የደጋፊ መናሐርያዎች የሚወስዱ መንገዶች ከትራፊክ ነፃ ሆነው መስተንግዶውን እየተጠባበቁ ናቸው።
ለዓለም ዋንጫው ከ2.89 ሚሊዮን በላይ የስታድዬም መግቢያ ትኬቶች ተሸጠዋል፡፡ የምድብ ጨዋታዎችን ለመመልከት የስታድዬም መግቢያ ትኬቶች  ዋጋቸው ከ70 እስከ 220 ዶላር  ሲሆን የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎችን መመልከቻ ትኬቶች ዋጋቸው ከ600 እስከ 1600 ዶላር ነው፡፡
በግዙፉ ሃማድ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ያገኘናቸው የኢኳዶር ደጋፊዎች ለስፖርት አድማስ በሰጡት አስተያየት የመክፈቻ ጨዋታውን በድል እንደዲሚወጡት ተናግረዋል፡፡ ከሚኖርባት የአሜሪካዋ ግዛት ኬኔቲኬት ወደ ኳታር በመጓዝ የትውልድ አገሩን በዓለም ዋንጫ ላይ ለመደገፍ  የገባው ጆርጄየቺ  በሰጠው አስተያየት ቡድናቸው የኳታር አቻውን በሜዳው አሸንፎ፤ በአንድ ጨዋታ ተጨማሪ ድል በማስመዝገብና በአንዱ ጨዋታ አቻ በመውጣት ወደ ጥሎ ማለፍ ምዕራፍ ውስጥ ይገባል፡፡
ኳታራውያን ለዓለም ዋንጫው ከፍተኛ በጀት ማውጣታተቸው ብቻ ሳይሆን መላው ዓለም በመልካም መስተንግዶና ምቹ ሁኔታዎች የማይረሳ ትዝታ እንዲያገኝ መስራታቸውን ከአየር ማረፊያው አንስቶ መታዘብ ይችላል፡፡ በሃማድ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የተሰማሩት የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች፤ የዓለም ዋንጫን የመረጃ ዴስክ የሚመሩ ሰዎች ለዓለም ዋንጫ እንግዶች ሙሉ ልብ እየሰጡ ናቸው፡፡
በ22ኛው የዓለም ዋንጫ ላይ ለሚሳተፉ 32 አገራት የሚሰለፉ 826 ተጨዋቾች ዝርዝር በፊፋ ታትሟል። 32 ብሔራዊ ቡድኖች እያንዳንዳቸው 26 ተጨዋቾችን  በየስብስባቸው አስመዝግበዋል።


በትራንስፈርማርከት transfermarkt የዝውውር ገበያ ዋጋቸው እስከ 12.46 ቢሊየን ዮሮ ወይም 13 ቢሊዮን ዶላር ተተምነዋል። እስከ 693 ቢሊዮን ብር ይሆናል። በውድ ተጨዋችነት ግንባር ቀደም የሆነው የፈረንሳይ ኪሊያን ምባፔ 160 ሚሊዮን ዮሮ ነው። የብራዚሉ ቪንሸየስ ጁኒየር 120 ሚሊዮን ዮሮ፤ የእንግሊዙ ፊል ፎደን 110 ሚሊዮን ዮሮ፤ የጀርመኑ ጀማል ሞሳየላ 100 ሚሊዮን ዮሮ  እና የስፔኑ ፔድሪ 100 ሚሊዮን ዮሮ እንደ የዋጋ ተመናቸው እስከ አምስተኛ ደረጃ ወስደዋል። በተጨዋቾች ስብስብ በከፍተኛ ዋጋ የተተመነው በ1.26 ቢሊዮን ዮሮ የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ነው። ብራዚል በ1.14 ቢሊዮን ዮሮ፤ ፈረንሳይ በ1.08 ቢሊዮን ዮሮ ፖርቱጋል በ937 ሚሊዮን ዮሮና ስፔን በ902 ሚሊዮን ዮሮ እስከ አምስተኛ ደረጃ ወስደዋል።


Read 13698 times