Saturday, 03 December 2022 12:27

ለማመን የሚያዳግቱ የዓለም ዋንጫ ታሪኮች (ከኡራጋይ የዓለም ዋንጫ እስከ ኳታር)

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 የአርጀንቲናው የስፖርት ሊቅ ሊቺያኖ ወርኒኪ፤ ከኳታር  የዓለም ዋንጫ 2022 መክፈቺያ ጥቂት ቀደም ብሎ ባሳተመው “The Most Incredible World Cup Stories “ የተሰኘ መፅሐፉ ውስጥ ለማመን የሚያዳግቱ የዓለም ዋንጫ ታሪኮችን ብቻ አይደለም የሰነደው፡፡ ይልቁንም ከመጀመሪያው የኡራጋይ ዓለም ዋንጫ እስከ ኳታር ያሉትን አስደናቂ፤ አስደማሚ፣ አዝናኝና ትንግርት የሚመስሉ እውነታዎችንና ገጠመኞችንም  ጭምር እንጂ፡፡  
በ20 የተለያዩ ቋንቋዎች በታተመው በዚህ መፅሐፍ ውስጥ ከተካተቱት ለማመን የሚያዳግቱ ታሪኮች መካከል፤ አንድ ደቡብ አፍሪካዊ የ2010 የዓለም ዋንጫ ነፃ ትኬቶችን ለማግኘት ሲል፣ አዞዎች በሞሉበት ወንዝ ውስጥ ዘሎ መግባቱ፤ አንድ የኡራጋይ ተጫዋች በድንገተኛ የልብ ድካም ከተጠቃ በኋላ ወደ ሜዳ ተመልሶ መግባቱ፤ እንዲሁም የሩሲያ  ጥንዶች “አሪፉ ተጫዋች ማነው፤ ሊዮኔል ሜሲ ወይስ ክርስቲያኖ ሮናልዶ?” በሚል ከተከራከሩ በኋላ መለያየታቸውን፤ የሚተርኩት  ተጠቃሽ ናቸው፡፡  
ከሮይተርስ ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ የዓለም ትልቁን የስፖርት ኹነት ከተለየ አንጻር እንደሚመለከተው የተናገረው ወርኒኪ፤ “ትናንሾቹ ታሪኮችም ቢሆኑ ዓለም ለእግር ኳስ ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳዩ  ናቸው”  ብሏል።
ወርኒኪ እንዲህም ሲል ጽፏል፤ “እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም አንድ አልባኒያዊ ወደ ውርርድ ቤት ይሄድና፣ አርጀንቲና ቡልጋሪያን ታሸንፋለች ብሎ ይወራረዳል፤ሚስቱንም በቁማር ያሲዛል። የማታ ማታ ታዲያ ያቺ የተወራረደላት አገር  2ለ0 በሆነ ውጤት ተሸነፈች፤ እሱም ውርርዱን ተበላ፤ በቁማር ያስያዛትን ሚስቱንም በአሳዛኝ ሁኔታ አጣ::” ይሄ ለማመን የሚያዳግት ታሪክ ሳይሆን “ጉድ” ነው መባል ያለበት፡፡
ከ16 ዓመት በኋላ ደግሞ የአስተናጋጇ አገር የደቡብ አፍሪካ አንድ የሬዲዮ ጣቢያ፤ የመጨረሻውን የዋንጫ ጨዋታ ሁለት ትኬቶች፣ ያልተለመደ የእብደት ድርጊት ለፈፀመ ሰው እንደሚሸልም ያውጃል፡፡ አሸናፊው ማን ቢሆን ጥሩ ነው? አዞዎች የሚርመሰመሱበት ወንዝ ውስጥ ዘሎ የገባ አንድ ሰውዬ ትኬቱን ወስዷል፤ይለናል ጸሃፊው፡፡  
በእያንዳንዱ የአለም ዋንጫ አዲስ ምዕራፍ እየታከለበት የሚበለፅገው “The Most Incredible World Cup Stories“ መፅሐፍ፤ ያሁኑ ሦስተኛው ዕትም ሲሆን ፀሃፊው ከኳታር የዓለም ዋንጫም ገና ካሁኑ ትናንሽ ጮማ ወሬዎችን እያሰባሰበ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
“ከአድማዎችና ከሰብአዊ መብት ጉዳዮች አንስቶ አያሌ ትኩረት የሚስቡ ነገሮች አሉ” ያለው ወርኒኪ፤ “ከስፖርት ውጭ በእርግጠኝነት በርካታ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ማህበራዊ ኹነቱ በእጅጉ የሚያመዝን ይሆናል” ብሏል፡፡
የአለም እግር ኳስ አድራጊ ፈጣሪ የሆነው ፊፋ፣ በወግ አጥባቂዋ የሙስሊም አገር ስቴዲዮሞች ቢራ እንደማይሸጥ ማወጁ፣ ለወርኒኪ ቀጣይ ምዕራፍ እንደ መነሳሻ ሊያገለግለው እንደሚችል ሮይተርስ በዘገባው ጠቆም አድርጓል፡፡
 የ53 ዓመቱ ሉቺያኖ ወርኒኪ የተወለደው በአርጀንቲና ቦን አይረስ ሲሆን ከሳልቫዶር ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት ተመርቋል፡፡ ለ20 ዓመት ያህልም በ”Argentine University of Enterprise (UADE)” እንዲሁም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ጋዜጠኝነትን አስተምሯል፡፡ በበርካታ አገራትም መጣጥፎችን አሳትሟል፡፡ ከ20 በላይ የእግር ኳስና የስፖርት መፃህፍት ደራሲም ነው፡፡ ከመፃህፍቱ መካከልም የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡-
The Most Incredible world cup Stories(2010)
The Most Incredible World cup Stories(2012)
The most Incredible World cup Stories(2013)
Doctor and Champion (Autobiography of Carlos Bilardo-2014)
The Most Incredible Copa Libertadores Stories(2015)
Round Words (2016)
Why is Football played eleven against eleven? (2017)
Matador ( Autobiography of Mario Kempes -2017)
Duel Never Seen (2019)
Inside DIego (2021)
Football Drops (2022)
Dark Goals(2022)

Read 2299 times