Saturday, 17 December 2022 14:11

አፍሪካ በዶላርም በውዳሴም ተንበሽብሻለች

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(2 votes)

ዓለም የአፍሪካ መሪዎችን ጥበብና ሃሳብ ትፈልጋለች ተብሏል
     - አሜሪካ ከአፍሪካ “አዲስ ፍቅር ይዞኛል” እያለች ነው
             
      የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባለፈው ሳምንት በዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው የዩኤስ- አፍሪካ ጉባኤ ላይ አገራቸው ለአፍሪካ በድጋፍና በኢንቨስትመንት 55 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ እንደምታደርግ አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ በአፍሪካ ንግድና መሰረተ-ልማቶችን በማሳደግና በማስፋት ላይ ያተኮሩ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችንም ይፋ ማድረጋቸው ተዘግቧል።
አሜሪካ ይህን የዩኤስ-አፍሪካ ጉባኤ ያካሄደችው ከ8 ዓመት በኋላ ሲሆን፤ ሃያሏ አገር ጉባኤውን የጠራችው በአህጉሪቱ እያደገ ለመጣው የቻይና ተጽዕኖ ምላሽ ለመስጠት በማለም ነው ተብሏል። (ይሳካላት ይሆን?!)
በአጭሩ አሜሪካ ከአፍሪካ “አዲስ ፍቅር ይዞኛል፤ እወቁልኝ” እያለች ነው።
ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፤ በዩኤስ- አፍሪካ የቢዝነስ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “አፍሪካ ስኬታም ስትሆን አሜሪካም ስኬታማ ትሆናለች። እውነት ለመናገር መላው ዓለም ጭምርም ስኬታማ ይሆናል።” ብለዋል። (ከመቼ ወዲህ?)
ባይደን አክለው ሲናገሩም፤ “ዓለም በአሁኑ ወቅት ከገባችበት ቀውስ ለመውጣት የአፍሪካ መሪዎች የመሪነት ጥበብና ሃሳብን ትፈልጋለች።” ብለዋል። (ጥበበኞች ሆኑ እንዴ?)
የፕሬዚዳንቱ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጃክ ሰሊቫን፤ አሜሪካ በቀጣይ ሶስት ዓመታት በድጋፍና በኢንቨስትመንት 55 ቢሊዮን ዶላር በአፍሪካ ፈሰስ እንደምታደርግ ገልጸዋል።
ይሄ ብቻ ግን አይደለም። በአህጉሪቱ የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማሳደግ 350 ሚ. ዶላር ወጪ እንደሚደረግም ሰሊቫን ጠቁመዋል። ይህም በማይክሮሶፍትና ቪያሳት ትብብር አማካኝነት ቢያንስ ለ5 ሚሊዮን የአህጉሪቱ ህዝብ የኢንተርኔት አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግን ያካትታል ተብሏል።
በተጨማሪም አሜሪካ በአፍሪካ ኢኖቬሽንና ስራ ፈጣሪነትን እንደምትደግፍ ጆ ባይደን በሰሞኑ ጉባኤ ተናግረዋል። ለሚሊዮኖች የንፁህ ኢነርጂ ተደራሽነትን ለማሳደግ፣ ለገበሬዎች ማዳበሪያን ለማድረስ እንዲሁም ለማህበረሰቦች ንፁህ ውሃን ለማቅረብ የሚተጉ ኩባንያዎችን ለማገዝ የአሜሪካ ዓለማቀፍ ልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን 370 ሚ.ዶላር በአህጉሪቱ ኢንቨስት እያደረገች  መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።
“አሜሪካ ለአፍሪካ የወደፊት ተስፋ ሙሉ ትኩረቷን ትሰጣለች” ያሉት ጆ ባይደን፤ “ማንም ወደ ኋላ የማይተውበት መጪ ዘመን በአንድነት መገንባት እንፈልጋለን” ብለዋል። (እመኑኝ በፍቅር ጦዘዋል!)
ከዚህ ጉባኤ ጎን ለጎን ባይደን እ.ኤ.አ በ2023 ምርጫ ከሚያካሂዱ 6 የአፍሪካ አገራት መሪዎች ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንቱ ከመሪዎቹ ጋር የተወያዩት በየአገሩ የሚካሄዱት ምርጫዎች ነፃና ፍትሃዊ እንዲሆኑ ጫና ለመፍጠር ነው ተብሏል። (ይሄ ግን ለአፍሪካ መሪዎች ቀይ መስመር ነው!)
ከዚህ ቀደም የእኛውን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ አፍሪካ ህብረት በተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ም/ቤት ቋሚ ውክልና እንዲያገኝ ደጋግመው መጠየቃቸው ይታወቃል።
49 የአፍሪካ አገራት መሪዎች በተሳተፉበት የዩኤስ-አፍሪካ ጉባኤ ላይ ደግሞ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ አፍሪካ ህብረት የG-20 ቡድንን በቋሚ አባልነት ይቀላቀል ዘንድ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ ተናግረዋል። (ከዚህ በላይ በፍቅር መውደቅ ካለ ንገሩኝ!)
በሌላ በኩል የዩኤስ-አሜሪካ ጉባኤው የአገራችንን ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን በሽልማት ነው የተቀበላቸው- በዓለማቀፍ ሽልማት!!
በዚያ ላይ በዋሺንግተን ቆይታቸው የቪአይፒ መስተንግዶ ነው የተደረገላቸው ማለት ይቻላል- ከባለቤታቸው ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር። ይህን ለማረጋገጥ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጩ ጥቂት ምስሎችና ቪዲዮዎችን መመልከት በቂ ነው። ከአንድ ምስል በታች የሰፈረው መግለጫ (Caption) እንዲህ ይላል፡- “ክብር ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ምሽቱን ፕሬዚዳንት ባይደን ባዘጋጁት የእራት ግብዣ ላይ ለመገኘት ከክብርት ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር ዋይት ሃውስ ሲደርሱ የአሜሪካ የክብር ዘብ ክብራቸውን የሚመጥን ታላቅና ታሪካዊ አቀባበል ሲያደርግላቸው።”
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ከጉባኤው ጎን ለጎን፣ ከዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጄቫና ከዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስ ጋር መወያየታቸው ታውቋል። (ውይይት ብቻ ሳይሆን ድጋፍም ተገኝቷል!)
ከሁሉም በላይ ብዙዎችን ያስገረመው ደግሞ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በዋሽንግተን ዲሲ የፈረንሳይና የሞሮኮን እግር ኳስ ጨዋታን ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና ከላይቤሪያው ፕሬዚዳንት የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ ጋር መመልከታቸው ነው። ለእኔ ግን ብዙም አልገረመኝም። ለምን ቢሉ? ኢትዮጵያ ስታሸንፍ እንዲህ ነዋ! (ገና ይቀጥላል!)
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!
ሰላም ለአገራችን! ሰላም ለዓለማችን!

Read 727 times