Saturday, 17 December 2022 14:13

“ጩኸት የሸመነው የዝምታ ጥበብ”

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(5 votes)

 የመኪናውን ጥሩምባ  እያ’ንባረቀ...  ለመብረር በከፊል ጎድሎ  ሲነጉድ ለቅፅበት የጨው ዓምድ ሆኜ ቀረሁ። ምክንያቱም ህይወቴ ከፊል የሚጎድል መብረር፣ ከፊል የሚጎድል የጩኸት ዝምታ ነው። መኪና አልወድም። መኪና የሰይጣን ፈረስ ነው ብዬ በዚህ ዘመን የማምን፣ የባልቴት ስነ ልቦና የማያጣኝ ወጣት ተባዕት ነኝ.... ትንሽ ድምፅ ልቤን የሚበሳኝ ድንጉጥ፣ ሰው ሲበዛ መግቢያ የሚጠፋኝ የዘመን መናኝ።  ህልሜ መሃል አብቤ፣ ተስፋዬ ግርጌ  ልከስም አንድ ሀሙስ የቀረኝ አበባ አይደለሁ? ሳቄ ውስጥ ስለተንጠባጠቡ እንባዎቼ የምጨነቅ፣ በደስታዬ ሽንቁር ስላለፉ ሃዘኖቼ የምተክዝ፣  እብደት ከጤና ጋር የተዛነቁብኝ ውል አልባ ሰው ....
እራመዳለሁ!
እኔ ጩኸት የሸመነኝ የዝምታ ጥበብ ነኝ።
እርምጃ 9 [ብዙ መጠጥ ቤትና ስጋ ቤት ታልፎ]
(ሞሳዎች የጠቧትን የእናታቸውን ጡት ያስታውሳሉ? በዓይናችን ላይ የሚመላለሰው ምን ያህል ቀለም ነው በቀን? ሃዘን ለስንት ቀን ልባችን ላይ ይቆያል? ደስታስ ቅፅበት ነው ዘላለማዊ? ከተፈጠርን የሄድንባቸው መንገዶች ምን ያህል ናቸው? የቃምነው አቧራ ንፋስ ከምዕራብ አመጣው ከምስራቅ? ያልቋጨነው  ህይወት ተደምድሞ አያውቅም? እንዲህ አይመስልህም? ህይወት ያጋጣሚዎች ክስተት ናት።)
እራመዳለሁ።
እርምጃ 2 [ፋርማሲውን ገላምጬ፣ የአትክልት መሸጫውን  አቋርጬ]
(መንገደኛ እንጂ መንገድ ፍፁም አያልቅም)
እራመዳለሁ።
ጠባቧ የእግረኛ መንገድ ላይ እጓዛለሁ። ፀሃይ ለመጥለቅ ስትግደረደር ጠጅ ቤት የመሄድ ልማድ አለኝ። ብዙ አልጠጣም። ... ትንሽ ብቻ... በከፊል የጎደለ ስካር .... ሌላ አልፈልግም። በከፊል ትንሽ የጎደለ እብደት፤ ሌላ አልፈልግም። በህይወቴ የሚመጡት ነገሮች ሁሉ በከፊል መጉደል አለባቸው። የምፈልገው ብዙ የለኝም። ካለኝ ግን እሱም በከፊል ጎድሎ እንዲመጣ እሻለሁ።
በከፊል የጎደለ ህይወት፣ በከፊል የጎደለ ፍቅር ፣ በከፊል የጎደለ  ተንኮል፣ በከፊል የጎደለ ጅልነት...እምነትና የዋህነት... በከፊል የጎደለ እውነት... ህይወት የምታጠጣን ሙሉ ፅዋ እንደሌለ አውቃለሁና ....
እኔ የምሞላው በከፊል የጎደልኩ ዕለት ነው።
እርምጃ 19 (ጠጅ ቤት ልደርስ ጥቂት ሲቀሩኝ)
(የተመኘነውን ሁሉ ማስታወስ እንችላለን?  ለምንድነው መኖር ወደ ትላንት የሚያላጋን? ትላንት የሚሉት፣ እንደ አይናፋር እንስት ተከናንቦ ዛሬና ነገን መስለብ የሚችል ታጣቂ እንዴት ሆነ? ..የደረቀ ቅጠል ድምፅ ህልውናዬን  ማንገቻ የልጅነቴ  ሞግዚት ነው።)
አራብሳ የሚባል ደባሪ ሰፈር ውስጥ በክርስቶስ ተዓምር ካልሆነ በቀር የምገኝ ሰው አልነበርኩም። ግን ያለ ምንም ተዓምር ተገኝቻለሁ። የተዓምር አስደንጋጭ ክስተት ያለ ተዓምር መገኘቱ ነው። ከጋዜጣና መፅሃፍ ውጪ ያለች ጠባብ የደንቆሮ ከተማ ጥራ ቢሉኝ አራብሳ እላለሁ። ስጋ እየደረደረች ምራቅ የምታስውጥ፣ ድራፍት ቤት የተንጣለለባት፣ መጠጪያና መጨፈርያዎች የዓይናቸውን ቆቦች ገልጠው የሚያፈጡባት... ለሳቅ እንጂ ለእንባ፣ ለተድላ እንጂ ለችግር ደንታ የሌላት፣ ... ኪስ እንደ ጨርቅ  የምታጥብ... “ብሉ፣  ጠጡ ምክንያቱም ነገ ሟች ናችሁ” የሚል ጥቅስ ግንባሯ ላይ የለጠፈች ወጣት ባልቴት ትመስላለች - አራብሳ። አራብሳ ውስጥ ጋዜጣ ማግኘት በበረሃ እንደፈለቀ ምንጭ  እጅን በአፍ የሚያስጭን ተዓምር ነው።
ወደ ጠጅ ቤቱ ገባሁ። ቦታዬ ላይ አንዲት ወጣት ተቀምጣለች። ይህቺን ወጣት እዚህ ቦታ ላይ ተቀምጣ፣ ብርሌ ጨብጣ ጠጅ ስትጠጣ አይቻለሁ። ቅላቷ ደብዛዛ ነው። ዓይኗ ወደ ህልሜ የሚሸኙኝ ትላንቶች ይመስላሉ። ጋዜጣ ታነባለች። ቀና ብላ አየችኝ። እንደሚያውቀኝ ሰው ፈገግ አለች። ምናልባት እሷም በህልሟ አይታኝ ይሆናል።
“ተቀመጥ እንጂ ሌላም ቦታ--” የአስተናጋጇ ድምፅ ነው።
አጠገቧ ተቀመጥኩ።
ሁለት ብርሌ ቃል ሳላወጣ ጨረስኩ።
ድንገት ይህቺ እንስት ድምፅ አወጣች።
“ታውቀዋለህ ይሄን ቀሽም ደራሲ? ደግሞ በፊት የሴት ሥም ነው የሚያስቀድመው እኮ... ሴት ትመስለኝ ነበር። ወንድ መሆኑን ያወቅኩት ከቅርብ ወዳጁ ነው። ወንድ መሆኑን ሳውቅ አብልጬ ጠላሁት” በእጇ ወደ ፅሁፍ እየጠቆመች...
“ማን ነው?” ከፅሁፉ ርዕስ ውጪ የደራሲው ስም አልተነበበልኝም።
“አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)... ዝም ብሎ ስቃይንና ሃዘንን በመፃፍ የተለከፈ... የህመም ዛር ብዕሩ ላይ ያረፈ እብድ ፀሃፊ  ነው። “
“አዲስ አድማስ ላይ ...አወቅኩት... አልወደውም። አልጠላውምም። አንዳንዴ የሱን ፅሁፍ እዘለዋለሁ። ፍፁም አላነበውም። ይደብተኛል። ያስጨንቀኛል።”
“እኔ የሚያዝናናኝ ልብወለድ ነው የምፈልገው። ... በህይወቴ የተከዝኩበት፣ ያዘንኩበት ይበቃኛል። ደግሞ በእሱ ገፀ ባህሪ ልተክዝ እንዴ? ብዙ ነገር አለብኝ። የተሸከምኩት ብዙ ነው አየህ?"
“ሁላችንም የተሸከምነው ብዙ ነው። ብንቀያየር ምን ትያለሽ?”
“ሃሃሃሃ... ኪሎህ ስንት ነው?”
“75 ኪሎ ነኝ?”
“የስጋህን አይደለም የነፍስህን ነው የጠየኩህ። ደማቅ ሃዘን መቀመጫው  ነፍስ ናት። የስጋችንንማ ለመርሳት ስካር በቂ ነው። የነፍስህ ማለቴ ነፍስህ  ላይ የነበረውን  ሃዘን ግን አትሸሸውም። መደበቅያ ጥግ ታጣለህ። መሸሸግያ ይጠፋሃል። ዝምታህ ውስጥ ይጮሃል። ደስታህ ውስጥ ይንሰራፋል። ሳቅህ ላይ አየኸኝ እያለ ይላገዳል። እምነትህን ይሸረሽራል። ህይወት በጀብዱ የተሞላች የህመም ትግል ናት። እናት ነኝ ታምናለህ?”
“ትገርሚያለሽ...ማለት ሃሳቦችሽ! የነፍሴን ኪሎ ማወቅ ላይ ደደብ ነኝ። ነፍሴን መዝኜውም አላውቅም ኧረ! ሲጀመር ነፍስን መመዘን የሚችል ሚዛን መኖሩን አላውቅም። እናትነትሽ ግን ድንቅ ነው”
“ሰው እፈልጋለሁ። የማላውቀውን፣ የማያውቀኝን... ግን ሳይህ ትመስላለህ፣ ማንን እንዳትለኝ! .... ቆይማ ልንገርህ እስቲ” (ልሰማት ጆርዬን ከፈትኩ)...
“ነፍስህን መመዘን የሚችለው የልቦናህ ንቃት ነው። የአዕምሮህ ልህቀት ነው። ተወው...ይሄ የኔ ቅዥት ብቻ እንደሆነ አውቃለሁ። ሂሂሂሂ... ደስ የማይሉ ሳቆች አሉኝና ታገሰኝ።  ግን ልንገርህማ፣ አንዳንድ ድንቅነት ግልብነትን ያቅፋል። በመወለድ እንቁላል ውስጥ ያለው አስኳል ሞት ስለመሆኑ አታምንም? ሞትን መረዳት የህይወትን ፊደል ሀ ብሎ ቆጥሮ እንደመጀመር ስለመሆኑስ ትክደኛለህ? የብቸኝነትን ዘውድ መድፋት የሚችሉ ሙታን ብቻ እንደሆኑስ ታውቃለህ? አንዳንድ በረከቶች መረገምን በሕቡዕ ሰፍተዋል። ሳቆች የሃዘን ደመና የከበባቸው ሰማዮች ናቸው። ደስታ የሃዘን መለከት ካልተነፋ ከእንቅልፉ መንቃት ትቷል። ህልም የሚባል ድርሳን ውስጥ የተፃፈው ሃቅ ምናልባት ህይወት ውስጥ የለም። ማለት ... የምልህ ይገባሃል አይደል? መቀባጠሬን ይቅር በለው...ልንገርህማ!  ከወደድኩት ሰው መውለድ እፈልግ ነበር። የወደድኩትን ግማሽ አካል መታቀፍ ለእኔ ሃሴት ነበረው። እሱን ለማድረግ ለፋሁ። ወለድኩ ...ልጄ በሂደት የአዕምሮ ዝግመት እንዳለበት አወቅሁ... ጠላሁት ልጄን!  አይገርምም? እናት ልጇን መጥላት እኮ ትችላለች።  በዚህ ምክንያት የወደድኩትም ጠላኝ። ሃበሻ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻህን መቀጠል ይችላል። መልካምነትህ ወድቆ ሲለምን ያልመፀወተው፣ ክፋትህ ሲታረዝ ለማልበስ ይሽቀዳደማል።  በጥላቻ ብቻ ነገርዬው አልቀረም...ጥሎ እስከመጥፋት... አገር እስከመቀየር  ደረሰ። አንዳንዴ የሁለት ሰውን መስቀል ብቻህ እንድትሸከም ትታጫለህ። አንዳንዴ የህይወትን ፅልመት ብርሃን ብለህ በተቀበልከው በኩል ታገኛለህ። አንዳንዴ   ሰው ብቻ ትፈልጋለህ። ገባህ አይደል? ለምን ብዙ ለፈለፍኩ ግን (አፋራም ሳቅ ሳቀች... ዓይኗ ግን የእንባ ጭጋግ ጋርዶ ተሸፍኗል። ሳጓ ድምጿን ይቆራርጣል) ... ምንም አትበለኝ በናትህ። አዎ ልጄን እጠላዋለሁ። ታማሚ ስለሆነ ብቻ አይምሰልህ፤ ፍቅሬን ስላሳጣኝም ጭምር ነው።”
“ይገባኛል። ... ግን ማንን መሰልኩሽ?”
“ፈጣሪን”
“ሃሃሃሃሃሃሃ...ፈጣሪ እኔን ይመስላል?” ሳቅ ልዘራባት ተጋሁ።
“አዎ! ፈጣሪ ቆንጆ ነው። በቆንጆ እንዳይቀና እራሱን ቆንጆ አድርጎ ነው የሚፈጥረው!”
“ፈጣሪ እራሱን ፈጥሯል እያልሽኝ ነው?”
“አዎ! ሙሴ ያልዘገበው፣ ወይ አውቆ ቸል ያለው አሊያም በንቃታችን አቅም ልክ ይፈለግ ዘንድ የተወው የአምላክ አፈጣጠር አለ። ይሄን አፈጣጠር እኔ አንቤበዋለሁ። የት አልከኝ? የልቤ ንቃት ውስጥ! መመፃደቅ እይደለም። እንደውም ንገሪኝ ካልክ የፃዲቅ ፅድቅ የሚከሽፈው ፀደቅኩ ብሎ ያሰበ ዕለት ነው።  አምላክ እራሱን የፈጠረው ከነበልባል የእሳት ፍምና ከእልፍ  ዝምታ ነው።  ግን  ፍፁማዊ መፍጠር እንደሌለ የምታውቀው አምላክም እራሱን ሲፈጥር ለእራሱ ጎድሎንና ድክመትን አሸክሞ ነው..."
ሳቅኩኝ በጣም...
ተነሳችና ጋዜጣዋን ያዘች። መልሳ እያስቀመጠችው:-  “ይቅር አንብበው።  ብቻ አፀደ ኪዳኔን ከማንበብ ተቆጠብ" ብላኝ ወጣች።
ተከተልኳት....
ዞራ አየችኝ...
“አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ) እኮ እኔ ነኝ” ....
“እንግዲያውስ እንደምጠላህ እወቅ። ልንገርህማ... (አፋራም ሳቋን አሳየችኝ) ህይወቴ የአፀደ ኪዳኔ (ቶማስ) ድርሰት ሆኗል... እና ምናልባት ያንተ ድርሰት ሲለወጥ ህይወቴ ይለወጥ ይሆናል። እናም  ጥሩ ነገር ለመፃፍ ሞክር። ምክር አይደለም የነገርኩህ፤ ተግሳፅ ነው። የረባ ነገር ሳትፅፍ ሽበት ማውጣት ጀምረሃል...ህይወትን መርሳት ካላቆምክ ህይወትም አንተን መርሳት አታቆምም። ይገባሃል አይደል?...”
በፍጥነት መራመድ ጀመረች።
ዘመናት ነጎዱ፣  ዓለም ተጓዘች። ፀሃይ ደጋግማ ሰማይ ላይ እየታየች ጠፋች። ከዋክብት ታይተው እየቀሩ፣ ተናፍቀው ሲጠበቁ አመታት ተቆጠሩ።  እኔ ግን እዚህች  ሴት ንግግር ውስጥ የጨው አምድ ሆኜ ቀረሁ።
“ህይወትን መርሳት ካላቆምክ ህይወትም አንተን መርሳት አታቆምም”

Read 1017 times