Monday, 09 January 2023 10:26

የገና ሥጦታ - አጫጭር ታሪኮች

Written by  ዳንኤል ወርቁ
Rate this item
(8 votes)

አርበኛው
ሰአቱ ከምሽቱ  አራት ሰአት ገደማ ነዉ። የከተማዉ አስፓልት ጭር ብሏል። ሰማዩ ድንግዝግዝ ያለ ቢሆንም እንኳን የመንገድ ዳር መብራቶች ብርሃናቸዉን እየፈነጠቁ ከአስፓልቱ ላይ ለመጋደም የሚሻዉን ጽልመት ያባርራሉ። ገና ከባድ ዝናብ ጥሎ ማባራቱ ስለሆነ ከመንገዱ ዳርና ዳር ጎርፍ እየፈሰሰ ወደ ቦይ ዉስጥ ይገባል። የሚሰማዉም እርስ በራሱ የሚተራመስ የጎርፍ ድምጽ ብቻ ነዉ።
አንድ አርበኛ የነበሩ አዛዉንት ከእግረኛዉ መንገድ ላይ ደጋን ወገባቸውን አቆልምመዉ መሬት መሬቱን  እያዩና እርምጃቸዉን እየቆጠሩ በሚመስል መልኩ በእርጋታ ይራመዳሉ። አልፎ አልፎ ፊታቸዉን እያዞሩ ኋላቸዉንም ይገላምጣሉ። ሰዉ  እየፈለጉ ነዉ። የሚለምኑት ሰዉ። ላለፉት ሁለት ቀናት እህል የሚባል ነገር አልቀመሱም። በእድሜ መግፋት ሳቢያ ከስራ ሲባረሩ ለመጨረሻ ጊዜ የተሰጣቸዉን ገንዘብ ከሶስት  ቀን በፊት ነዉ የጨረሱት። አሁን ከቤታቸዉ ዉስጥ ምንም የሚላስ የሚቀመስ ነገር የላቸዉም። ቀኑን ሙሉ ረሃቡ ቢጠናባቸዉም፤ ጨጓራቸዉ እሳት እየተፋ ቢያነዳቸዉም፤ አንጀታቸዉ እንደ ማሲንቆ ክር ቀጥኖ ረሃብ ቢገዘግዘዉም፤ ክብራቸዉን ዝቅ ላለማድረግ ብለዉ ለልመና ከቤታቸዉ ላለመዉጣት ምለዉ ነበር የዋሉት። አስራ ሁለት ሰአት ካለፈ በኋላ ነዉ በህይወት ማደር ከፈለጉ እህል መቅመስ እንዳለባቸዉ የታወቃቸዉ። ከዛን በኋላ ከቤታቸዉ አልጋ ላይ እንደተኙ ወጥቼ ‘ልለምን ወይንስ ከነክብሬ ልሙት?’ ሲሉ ከራሳቸዉ ጋር  ተሟግተዋል። በመጨረሻ ግን ወጥቶ መለመኑ ሚዛን የሚደፋ ስለመሰላቸዉ ከምሽቱ ሁለት ሰአት ገደማ ልክ ከቤታቸዉ ሊወጡ ሲሉ ከባድ ዝናብ መዝነብ ጀመረ። ዝናቡ እስኪያልፍ ተቀመጥዉ  ቢጠባበቁም ዝናቡ በቶሎ ሊቆም አልቻለም ነበር። በመጨረሻም ልክ ለአራት እሩብ ጉዳይ ሲሆን ዝናቡ ጋብ አለና ከቤታቸዉ ወደ ከተማዉ ጎዳና ሲወጡ መንገዱን ያገኙት ጭር ብሎ ነዉ።
ከየመንገዱ ዳር ያሉት መሸታ ቤቶችና ሱቆች ያለወትሯቸዉ በጊዜ ስለተዘጉ አንድም የሚለምኑት ሰዉ ማግኘት አልቻሉም። ከጎዳናዉ ላይ መቶ ሃምሳ ሜትር ያህል ከተጓዙ በኋላ  ከአስፓልት ዳር የቆመ አንድ መኪና አዩና ወደ መኪናዉ ተጠግተዉ በጋቢናዉ መስታወት በኩል ሲመለከቱ፣ ሁለት እድሜያቸዉ በሰላሳዎች ዉስጥ የሚገኝ ወጣቶች ዉስኪ እየጠጡ ነበር። አርበኛዉ ምን ብለዉ እንደሚለምኑ ግራ ተጋብተዉ  ከመኪናዉ መስታወት አጠገብ ከቆሙ በኋላ አንድ እጃቸውን ዘረጉ። ያ ጦር  የሰበቀ፤ ዘንግ የመዘዘ፤ ልጓም የጨበጠ፤ ሻሞላ የሰነዘረና የመከተ እጅ ለልመና ተዘረጋ።
መስታወቱ  በደንብ ስላልተዘጋ ሁለቱ ሰዎች የሚያወሩት ወሬ በደንብ ይሰማቸዋል።  የሚያወሩት ወሬ ለጆሮዋቸዉ ስለቀፈፋቸዉ አርበኛዉ መስማት አልፈለጉም። አማራጭ ስላልነበራቸዉ ግን የሰዎቹን ወሬ ከብርድ ጋር ተጋቱት። ተለማኝዎቹ ደግሞ አይተዉ እንዳላዩ ሆነዋል። አርበኛዉ ግራ ቢገባቸዉ የሚኪናዉን መስታወት በጣቶቻቸዉ  ሲቆረቁሩት ሁለቱም ሰዎች አንድ ላይ ወደ መስታወቱ ፊታቸዉን አዙረዉ አርበኛዉን ገላምጠዋቸዉ ጨዋታቸዉን ቀጠሉ። የሰዎቹ ግልምጫ አርበኛዉን ክፉኛ አሸማቀቃቸዉ። ከመኪናዉ አጠገብ እንደቆሙ የአስፓልቱን ላይና ታች ቢያዩ ምንም የተቀየረ ነገር የለም። ጎዳናዉ ጭር እንዳለ ነዉ። እርሳቸዉም ከመኪናዉ አጠገብ እንደቆሙ ሰዎቹም ዉስኪያቸዉን እየኮመኮሙና ወጋቸዉን እያወጉ ደቂቃዎች አለፉ። በመጨረሻም ከመኪናዉ አጠገብ የተቀመጠዉ  ሾፌር መስታወቱን ዝቅ አድርጎ “ቆይ ያሞታል! ለምን አይገባዎትም? ከሌለንስ? ከየት አምጡ ነዉ የሚሉን?  እንደሌለን ለማስረዳት  እንደ እርስዎ ልመና መዉጣት አለብን እንዴ? አቦ ይሄ ህዝብ ግን መቼ ነዉ የሚሻሻለዉ? መቼ ነው እንደ ሰዉ ሃገር ሰዉ ሰርቶ መብላትን የሚለምደዉ?” እያለ ፊቱን ወደ ጓደኛዉ አዙሮ ሲጠይቀዉ፤ ጓደኛዉ እኔንጃ በሚል አኳኋንና መሰላቸት በተሞላበት ስሜት መዳፉን አወራጨለት። ሰዉዬው ፊቱን ወደ አርበኛዉ መልሶ “ቆይ ይሄ ሁሉ ዘመኖን ምን ሲሰሩ ነበር? ነዉ ወይንስ ከመሃፀን የወጡት በሰባ አመትዎት ነበር?” አለና ከጓደኛዉ ጋር ተሳሳቁ። አርበኛዉ አይናቸዉ እንባ ለበሰ። ይናገር የነበረዉ ሰዉዬ ከኪሱ ብዙ የብር ኖቶችን አዉጥቶ፣ ከመቶ መቶ ብር መሃል ጣል የተደረገችን አምስት ብር ሳብ አድርጎ በመዳፉ ጭርምትምት  አድርጎ በመኪናዉ መስኮት በኩል ወደ ዉጭ ወረወረላቸዉ። አርበኛዉ ከመሬት ላይ የወደቀችዉን ብር አንስተዉ ዳቦ የሚገዙበትን ሱቅ ደግሞ ለመፈለግ መጓዝ ጀመሩ። ጥቂት እንደተራመዱም ከግንብ ጥግ ከተወጠረ ሸራ አጠገብ ደረሱ። ከሸራዉም አጠገብ አንዲት ሴት ሶስት ትናንሽ ልጆቿን ከአጠገቧ አስቀምጣ የምትለምነዉ ሰዉ እየተጠባበቀች ነበር። የአርበኛዉን መቃረብ እንዳየች ድምጿን ከፍ አድርጋ፤ “እባክህ ወገኔ በእኔ ብትጨክን በእነዚህ ህጻናት አትጨክን። ከዚህ ቀደም በረሃብ አንድ ልጄን የተነጠቅኩ ሰዉ ነኝ።  አሁን ደግሞ ረሀብ የተቀሩትን ልጆቼን ሊፈጃቸዉ ነዉ። ከነጋ እህል የሚባል ነገር አልቀመሱም።  መቼም ለወላድ የልጇን ረሀብ ከማየት የበለጠ አሰቃቂ ነገር እንደሌለ ሳያዉቁ አይቀሩም። ወገኔ ከባድ ሰቆቃ ዉስጥ ነኝ። እባክህ አትለፈኝ” ስትላቸዉ፤ አርበኛዉ ወደ ሴቲቱ ተጠግተዉ ከልጆቹ ፊት እንደ መንበርከክ አሉና ሶስቱንም ልጆች ተራ በተራ ጭንቅላታቸዉን ፍቅር በተሞላበት ሁኔታ ከዳበሱ በኋላ  “አባታቸው የለም እንዴ?” አሏት። ሴቲቱ እንባዋን እየጠረገች “ካረፈ ቆይቷል” አለቻቸዉ። ከዛም አንገታቸዉን ሰብረዉ ትንሽ ካሰቡ በኋላ  ይዘዉት የነበረዉን አምስት ብር አዉጥተዉ ሲሰጧት፣ አመስግናና እጃቸዉን ስማ ተቀበለቻቸዉ። ከዛም አርበኛዉ ከተንበረከኩበት ተነስተዉ ወደ ቤታቸዉ መመለስ ጀመሩ።
የዳቢሎስ ችሎት
የሲኦል  ከፍተኛ   ምድብ ችሎት ዳኛ የሆኑት ጋኔን በዳይን ለመካስ፤ ተበዳይን ለመቅጣት እንደወትሮዉ ከችሎታቸዉ  ላይ ተሰይመዉ ከሳሽና ተከሳሽ ወደ ፍርድ አዳራሹ እስኪ ገቡ ድረስ ይጠባበቃሉ። ብዙም ሳይቆይ የፍርድ ቤቱ አስተናባሪ የሆነዉ ከይሲ ሶስት ሰዎችን ወደ ፍርድ አዳራሹ አስገብቶ ከዳኛዉ ፊት ለፊት አቆማቸዉ።  ዳኛዉ ከፊት ለፊታቸዉ የቆሙትን ሶስት ሰዎችን አንድ በአንድ በደንብ እያስተዋሉ “ከሳሽ  ቀርበዋል? “ ሲሉ፤ ከተሰለፉት ሰዎች ከመጀመርያ የቆመዉ፤ “አዎ ክቡር ዳኛ ቀርቤያለሁ” አለ። ዳኛዉ በሰላ አይናቸዉ ከሳሽን በጥርጣሬ አስተያየት ጥቂት ከመረመሩት በኋላ አይናቸዉን ከፊታቸዉ ወደ ነበረዉ ወረቀት መልሰዉ፤ “ተከሳሽ ቀርበዋል?” ሲሉ ከመሃል የነበረዉ ተከሳሽ እጁን አዉጥቶ “አዎ ቀርቤያለሁ ክቡር ዳኛ” አለ።  ዳኛዉ፤ “በመጨረሻም ምስክር” ሲሉ፤  “ቀርቤያለሁ” አለ ሶስተኛዉ ሰዉ እጁን አወጥቶ።
“እሺ  ከሳሽ ምን ነበር የተፈፀመብዎት በደል?” አሉ ዳኛዉ። ከሳሽ  ከወገቡ ዝቅ ብሎ ለዳኛዉ እጅ ከነሳ በኋላ፤ “ክቡር ዳኛ ይሄ ሰዉ የመንግስታችን መተዳደርያ  የሆነዉን ህግና ደንብ ጥሷል። እንደሚታወቀዉ ህጋችን ‘ግራህን ለመታህ ግራዉን አጩልለት፤ ቀኝህን ቢልህ ደግሞ ቀኙን በለዉ ነዉ’ የሚለዉ። ይሄ ሰዉ ግን የቀኝ የጆሮ ግንዱን በጥፊ ሳጮለዉ፣ የእኔን የጆሮ ግንድ በጥፊ ማጮል ሲገባዉ እሱ ግን በአፀፋዉ  ግራዉን ሰጥቶኛል። ይሄም ለህጋችን ያለዉን ንቀትና አልገዛም ባይነቱን ያሳያል።” እንዳለ ዳኛዉ አይናቸዉን እያጉረጠረጡና ከመላ ፊታቸዉ የቁጣ ነበልባል  እያፈለቁ  ተከሳሽን፤ “ እዉነት ነዉ አንተ?” አሉት ህግ ከሚፈቅደዉ በላይ ስሜታቸዉን መቆጣጠር አቅቷቸዉ በንዴት እየጦፉና እየተወራጩ።
ተከሳሹም ሰዉ ድምፁን ከፍ አድርጎ፤ “ክቡር ዳኛ ይሄ ፍፁም ከእዉነት የራቀ ዉንጀላ ነዉ። ከሳሽ እንዳለዉ ግራዬን ስመታ ቀኜን የምሰጥ ወስላታና ነፈዝ ሳልሆን፤ ቀኜን ላለኝ ግራዉንም ቀኙንም ብዬ የማጠናግር ቆፍጣና ህግ አክባሪ ዜጋ ነኝ። ለዚህም በወቅቱ ከሳሽ ሲመታኝ የነበረዉ  የአይን እማኝ ምስክር ነዉ።” አለ።
ዳኛዉም  የአይን እማኙን “ምስክር ስለጉዳዩ የምትለዉ ነገር ይኖራል?” አሉት።
“ክቡር ዳኛ፤ ይሄ አሁን የምናገረዉ የእዉነት ቃሌ ነዉ። ከሳሽና ተከሳሽ በተጣሉ ጊዜ በስፍራዉ ነበርኩ። የሆነዉም እንዲህ ነዉ፥ በመጀመርያ ከሳሽ ተከሳሽን በጥፊ መታዉ። ወዲያዉም ተከሳሽ በአጸፋዉ ከሳሽን በጥፊ አጮለዉ። የፀጥታ አስከባሪዎች ከስፍራዉ ደርሰው ይዘው ወደዚህ ስፍራ አመጡን። ክቡር ዳኛ እኔ ያየሁት እንዲህ ነዉ። ይሄ የእዉነት ቃሌ ነዉ። አልጨመርኩም፤ አልቀነስኩም” ሲል የእዉነት ቃሉን ሰጠ።
ዳኛዉም እዛዉ በተቀመጡበት ሆነዉ በአይነ ህሊናቸዉ ወደ ኋላ ተመንጥቀዉ ፀቡ ወደ ተፈጠረበት ቦታ አምርተዉ ጉዳዩን ቃኙት። ሁሉንም ነገር ያገኙት የአይን እማኙ እንደተናገረዉ ነበር። ከገቡበት ሰመመን ከተመለሱ በኋላም እራሳቸዉን አረጋግተዉ  “ጥበባችንንም ተጠቅመን በአይነህሊናችን ወደ ኋላና ድርጊቱ ወደተፈፀመበት ስፍራ ተጉዘን የሆነዉን ሁሉ ቃኝተናል። የአይን እማኙ እንደተናገረዉ ከሳሽ በጥፊ ሲመታ ተከሳሽም አጸፋዉን መልሷል። ስለዚህ ተከሳሽ ምንም አይነት ህግ ባለመጣሱ እንደ ሽልማት በቅርቡ ሲኦልን የሚቀላቀሉ አንድ ሺህ ነብሳትን እንዲያሰቃይ  ይበርከትለት። ከሳሽም በሃሰት በመወንጀሉ ህጋችንን እንዳከበረ  አረጋግጠናል። የሚያስመሰግንና የሚያኮራም ተግባር ነዉ የፈጸምከዉ። ለዚህም በቀን ለስምንት ሰአታት ያህል በእሳት ትነድ የነበረዉ በሰላሳ ደቂቃ ዝቅ እንዲልልህ ተወስኗል።” ትንሽ ዝም ካሉ በኋላ ቀጠሉና “የአይን እማኝ” አሉ።
“አቤት” አለ የአይን እማኙ።
“የመሰከርከዉ እዉነቱን ነዉ አይደል?”
“አዎ’’ አለ የአይን እማኝ በሰራዉ መልካም ተግባር እየተኩራራ።
ዳኛዉ ብግን ብለዉ ከፊታቸዉ የነበረዉን ጠረጴዛ በቡጢ ነርተዉ፤ ‘’አዎ ይላል እንዴ ይሄ ጀዝባ! ማነዉ አንተን የእዉነት ተቆርቋሪ ያደረገህ? አሽቃበጥክ በጣም! ለእዉነት የቆምክ ብትሆን ቀድሞዉኑ እዚህ ምን ትሰራለህ? ለምን ገነት አልገባህም? አንተን ብሎ መስካሪ! ስለዚህ እዉነታዉን መመስከር ያስቀጣል የሚለዉን ወይንም በሃሰት መመስከር  እንዳለብን አበክሮ የሚገልጸዉን ህግ ተላልፈህ በመገኘትህ ወደ ደረጃ አንድ የጣርና የሰቆቃ ማረምያ ቤት እንድትገባ የእስከዘላለሙን ቅጣት አስተላልፌብሃለሁ።” ብለዉ በመዶሻቸዉ ከፊታቸዉ የነበረዉን ጠረጴዛ ወቁ። ተከሳሽም በደረሰበት ድንገተኛና ያላሰበዉ ቅጣት ተደናግጦ እያለቀሰ ከፍርድ ቤቱ ወለል ላይ ተንፈራፈረ።

Read 1009 times