Saturday, 14 January 2023 10:46

ሦስቱን ፈተናዎች የማሸነፍ ጥበብ? (ለግልና ለአገር፣ ለስጋና ለነፍስ)

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)


         “ድንጋዩን ዳቦ የሚያደርግ” አንዳች ተዓምር ወይም አንዳች ቴክኖሎጂ ቢመጣልንና፣ የተሟላ መፍትሔ ቢሆንልን እንዴት ጥሩ ነበር? ግን አይሆንም። ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሏላ።
ታዲያ፣ የኢኮኖሚና የመተዳደሪያ ጉዳያችንን ለማናናቅ አይደለም። የኑሮና የዳቦ ሃሳባችንን ሁሉ ለማሳነስ ወይም “አለማዊ” ብሎ ለማጥላላት አይደለም። በእርግጥ እህል ውሃን አቅልሎ፣ የኑሮ ጉዳይን አናንቆ መናገር፣ የተለመደ ነው። “አዋቂነት” ወይም “መንፈሳዊነት” የሚመስላቸው አሉ።
በምግብ እጦትና በኑሮ ችግር፣… በረሃብና በጥም “ከነዋሪነት ተራ” መውጣትና መውደቅ እጅግ አሳዛኝ መሆኑን ስለማያውቁ ነው? አሳዛኝነቱ ያነሰ ይመስል፣… የኑሮ ጉዳይን እንደ ተራ እንደ አላስፈላጊ ነገር ማጣጣል፣ ተጨማሪ እጦትና የባሰ ውድቀት ነው - (የእውቀት እጦት፣ መንፈስን የሚያራቁት ውርደት)።
ግን ደግሞ፣ “የደላ ኑሮ” ማለት፣… ጥሩ ነገር ቢሆንም፣ ጭማሪ የማያስፈልገው የሕይወት ሁሉ ጉልላት ነው ማለት አይደለም።
በእርግጥ፣ “የሰዎችን መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት፣… ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ማግኘት”… የሁሉም ነገር መጨረሻ፣ የሕይወት ሁሉ ብቸኛ አላማ እንደሆነ የሚሰብኩ ሞልተዋል።
ከዳቦ በስተቀር፣ ከእለት ኑሮ ውጭ፣… ሌላው ነገር ሁሉ፣… ትርፍ ነው ይላሉ። ቅንጦትና ቅብጠት ነው ብለው የሚያጥላሉም አሉ። እንዲያውም፣… የግል ንብረት ሁሉ፣ ከየትም ቢመጣ፣ በየትኛውም መንገድ የተፈጠረ ቢሆን፣ የግል ጥሪትና ሃብት፣ ቁሳቁስና ቅያሪ ልብስ መያዝ፣… “ዝርፊያና ብዝበዛ ነው” ብለው የሚያወግዙ አልጠፉም።
ምንም ሆነ ምን፣ ማንም ቢሰራ ሌላው ባይሰራ፣ አንዱ በብርቱ እየጣረ ቢደክም፣ ሌላው በስንፍና ቢደክም፣ ግድ የላቸውም። ዋናው ነገር እህል ውሃ መሟላቱ ነው ብለው ይናገራሉ። ምንም ተባለ ምን፣… የትኛውም ሃሳብና እውቀት ቢታተም፣ ዲስኩር ከዳርዳር በጩኸት ቢያስተጋባ፣ ልዩነት አይታያቸውም። እልፍ የመርህ ዓይነት ቢፈለሰፍ፣ የትኛውም ቃል ቢሰበክ፣ ከቁብ አይቆጥሩትም።… “ዳቦ ለሁሉም እኩል መዳረስ አለበት” ይላሉ።
“በባዶ ሆድ ፍልስፍና አያጣፍጥም፤ ዲስኩር ዳቦ አይሆንም” ባይ ናቸው።
የኢኮኖሚ ጉዳይ፣… የዳቦ ጥያቄ፣… አልፋና ኦሜጋ እንደሆነ ይናገራሉ። እንዲያውም፣ የሰዎች እውቀትና መርህ፣ ፍልስፍናና ስብከት፣ ቃልና ሕግ፣… “የኑሮ ልሳናት” ናቸው ይሉናል። ሃሳብና ንግግር ሁሉ፤ ከኢኮኖሚ ቅኝት የሚወጡ የእልልታ ወይም የሙሾ ዜማዎች እንደሆኑ ይነግሩናል። ሰው፣ እንደ ኑሮውና እንደ ጓዳው መጠን ያስባል። እንደ መሶቡ፣ እንደ ምጣዱ ዓይነትና መጠን ይናገራል ይላሉ።
ኢኮኖሚውን የተቆጣጠረ ሃይል፣ የመጋዘንና የዳቦ ጌታ፣… የአገር ምድሩ አዛዥ አናዛዥ፣ አድራጊ ፈጣሪ ይሆናል ባይ ናቸው።
በቃ፣ የሃያልነት ምልክት ብቻ ሳይሆን ዋና ማረጋገጫ ሆኖ ይታያቸዋል - “የዳቦ ጌታ” መሆን!
“የእግዚሄር ልጅ ከሆንክ፣… እነዚህ ድንጋዮች ዳቦ እንዲሆኑ ተናገር” ብሏል የኢየሱስ ፈታኝ።
ኢየሱስ የዳቦ ጌትነቱን ካሳየ ሃያልነቱ አይረጋገጥም። በዚህም በዚያም ተብሎ፣ በተዓምርም ሆነ በምትሃት፣ በጉልበትም ሆነ በአዲስ አዋጅ፣ ድንጋዮች በቅጽበት ዳቦዎች መሆን አለባቸው። ከዚያስ?
ለምን ዳቦ ብቻ? ብልፅግናና ሥልጣኔ ጥበብና ትልቅነት፣ ፍቅርና ክብር የሰፈነለበት አገርንና ዓለምን በቅጽበት የመፍጠር ምኞትስ ማን ይከለክለናል? በተቃናም ሆነ በጠማማ መንገድ ምኞታችን ቢሳካ ምን ቸገረን! ወደ ሁለተኛው ፈተና ተሸጋግረናል ማለት ነው።
“የአለምን መንግስታትና ክብራቸውን አሳየውና፣ ብትሰግድልኝ ይሄን ሁሉ እሰጥሃለሁ” የሚል ነው ሁለተኛው ፈተና።
ከዚያስ? የምንመኘውን የምንሆነውን ነገር ያሳጣናል። “ከፎቅ አናት ላይ ካልተወረወርኩ!” እያለ ወላጅን የሚያስቸግር ልጅ ይመጣል። ከታች ህዝቡን አሰልፎ፣ እሱ ከላይ እየተወረወረ ሲወርድባቸው፣ እነሱ አቅፈው እንዲቀበሉት በትዕዛዝ የሚያስገድድ አምባገነንስ? የክብር ጉዳይ ሆኖ ይታየዋል። ይሄ ሦስተኛው ፈተና ነው - “ከመቅደሱ አናት ጫፍ ላይ ራስን ወርውር። መላእክት አቅፈው ይቀበሉሃል” የሚል ሃሳብ።
በዳቦ የተጀመረው ሌጣ ምኞት ወደዚህ ያመራል። ችግሩ ምንድነው? በሌጣው መግነኑ እንጂ፣ መጥፎ ምኞት ስለሆነ አይደለም።
ሰዎች፣… ምግብና መጠጥ፣ ልብስና ማደሪያ ካላገኙ መኖር አይችሉም። ነገር ግን፣ እነዚህ የኑሮ መተዳደሪያዎች ስለተገኙ ብቻ፣ “ሕይወት ተሟላ” ማለት አይደለም። የዱር አራዊት፣ እፅዋትና ነፍሳት፣… ምግብና ማደሪያ ካገኙ ሕይወታቸው ይሟላ ይሆናል። ለሰው ግን፣ የኑሮ ጉዳይ፣ ምግብና መጠጥ ሞልቶ ቢትረፈረፍላቸው እንኳ፣… በቂ አይደለም።
አዎ፣ ምንም አያጠራጥርም፣ የተደላደለ ኑሮ ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ፣ “ጥሩ ነገር” በቂ አይደለም። ጎን ለጎን ተጨማሪ ጥሩ ነገሮች ያስፈልጉታል።
ኪስና ቦርሳ፣ የባንክ ሂሳብና ካዝና፣ ቤትና ንብረት ቢሟላ፣… በድሮ አባባል፣ ጎተራና ጓዳ፣ አስቤዛና ማዕድ ቢበረክት፣ እሰየው ነው። ስለት በውን ሰመረ፤ ጸሎት በገሃድ ደረሰ ያስብላል።
ምርጥ ምርጡን ለመግዛት አቅም ባያንሰን፣ ባሰኘን ጊዜም እጥፍ ለመድገም ኪሳችን ባይጨንቀው አስቡት። እንዳሻንና ባስፈለገን ጊዜ እንደ ማብሪያ ማጥፊያ ማዘዝ ብንችልስ?
ያማረንን ነገር ሁሉ የሚያቀርቡና የሚያሟሉ፣ የሚያሞላቅቁና የሚያቀብጡ ወላጆች ወይም ሞግዚቶች ቢኖሩን እንደማለትም ሊሆን ይችላል።
ያሰኘንን ነገር በሙሉ ያመጡልናል። ለነገሩ፣ ባያሰኘንም እንኳ፣ እንዲሁ ለመቅበጥ ያህል፣ “ያንን አምጡልኝ፣ ያንን አቅርቡልኝ፣ ከየትም ወልዳችሁ፣ እንደምንም ፈጥራችሁ ስጡኝ” ብንል ምን ችግር አለው? ከኛ በላይ እንዲያስቡልን፣… እሳት ለኩሰን ካልያዝን፣ መስተዋት ሰብረን ካተራመድንበት እንል ይሆናል። “ከህንጻው አናት ላይ ብንወድቅ ወላጅ ይጭነቀው” እንደማለት ነው።
ሌጣ የዳቦ ምኞት፣ እንደዚህ ቅጥ እያጣ መረን ይለቅቃል። እና ምን ይሻላል?
ከሁሉ ከሁሉ በፊት፣ ከምኞት ጎን ለጎን ሁሌም መነሻ መሠረቱን መዘንጋት የለብንም። ምኞት በእውቀት መሆን አለበት።
ምኞታችን መሳካት አለመሳካቱን የምናረጋግጠው በምን ሆነና! ቀድሞውኑ፣ እውነትንና ሐሰትን፣ ጠቃሚንና ጎጂን፣ ጥሩና መጥፎውን ለይተን ማስተዋል የምንችል ከሆነ ነው - ወደ ምኞትና ወደ እልልታ የምንሸጋገረው።
በሌላ አገነጋገር፣… ምኞትና አላማችን፣… ከእውቀትና ከሃሳባችን ጋር ይዛመዳሉ፤ ይዋለዳሉ።
በእርግጥ የሰው ምኞቶች፣ ከሰው አካላዊ ተፈጥሮ የሚመነጩ፣ የመኖርና ያለመኖር ጉዳዮች ናቸው። ምኞቶች ለውጤት ሲበቁም፣ ጥቅማቸው፣ ለአካልና ለኑሮ ሊሆን ይችላል።
የምኞቶች መነሻቸውና እድገታቸው ግን፣ ከአእምሮና ከእውቀት ጋርም የተሳሰረ ነው።
ስለትና ጸሎት፣ የቃልና የሃሳብ ዘሮች ናቸው። የአእምሮ ግዛት ናቸው።
የስለታችንና የጸሎታችን፣ ወይም የምኞታችንና የአላማችን ልክ፣… በእውቀታችንና በአስተዋይነታችን መጠን ነው።
ከጊዜ በኋላ ምናዘወትራቸው ልማዶችና የምንላበሳቸው ባህርያትም፣ በምኞታችን ወይም በጉጉታችን ላይ የራሳቸው ድርሻ ወይም ተጽእኖ አላቸው። እንዲህ ሲባል ግን፣ ነገር ለማወሳሰብና ለማካበድ አይደለም።
የተደላደለና የተሟላ ኑሮን ከምር መመኘት፣ ጥረት የማይፈልግ በጣም ቀላል ነገር ይመስለን ይሆናል። እውነትም፣ የኑሮ ምኞት፣ በጥቅሉና በደፈናው ሲታይ፣ ብዙም ላያስቸግር ይችላል። ምን ዓይነት ምኞት፣ መቼና ለምን እንደመረጥነው እንኳ ትዝ አይለንም። በጣም ቀላል ጉዳይ ይመስላል።
ማንበብና መናገርስ መች እንደለመድነው መች እናስታውሳለን? ግን እንደ ዋዛ የተገኙ ነገሮች አይደሉም። ያለ ጥርት፣ በቅጽበት ጥበበኛ ልሳን አላበቀልንም። እንደ ዘበት ንባብን አልለመድንም። በጊዜው ብዙ ጥረንበታል።
የኑሮ ምኞትም፣ እንደዚያው ዛሬ ቀላል መስሎ ቢታየንም፣ በአንድ ጊዜና በድንገት የሚገለጥልን፣ ያለ እውቀትና ያለ ሃሳብ፣ በደመነፍስ የሚመጣ፣ በዘፈቀደ የሚታወጅ ጉዳይ አይደለም።
ለነገሩ፣ የምኞቶቻችንን ዝርዝር አንድ በአንድ እየተነተንን ልናሰላስላቸው ብንሞክር፣ ለራሳችን ሊገርመን ይችላል።
በዚያ ላይ የእያንዳንዱ ሰው እልፍ የምኞት ልዩነቶችንና የዝንባሌ ዓይነቶችን ስንመለከት፣ ነገሩ ቀላል እንዳልሆነ ይጠቁመናል። ከልጅነት እስከ አዋቂነት፣ የሕጻንነት ዘመን ምኞታችንን የአፍላነት እድሜ ፍላጎታችንን ብናስታውስ፣… ልዩነቶችን ማየታችን አይቀርም።
ምን ጥያቄ አለው?... በእውቀታችን፣ በአስተዋይነታችን፣ በልማዳችንና በባሕርያችን፣ በመንፈሳችን ብሩህነትና በነፍሳችን ልዕልና ልክ ነው - ምኞትም፣ ጸሎትም።
እንዲህም ሆኖ፣… የተደላደለ ኑሮን መመኘት፣ ያን ያህል እውቀትና ምርምር ሊጠይቅ ይችላል ብለን ለማሰብ እንቸገራለን። ያው፣ ማንበብና መራመድም፣… አንዴ ከለመዱት በኋላ፣… ጥረትና ትጋት እንደሚያስፈልገው እንዘነጋዋለን።
ለነገሩ፣ የተደላደለ ኑሮ ለተወሰነ ጊዜ ከተሟላ በኋላ፣ ለሁለት ለሦስት ዓመት ከተላመድነው፣ ምግብና ልብስ አሳሳቢ ጉዳይ አይሆኑብንም። ድሮም የነበሩ፣… ወደፊትም ለዘላለምም ተሟልተው የሚኖሩ ይመስለናል።
ቢሆንም ግን ብናምንም ባናምንም፣ ለተደላደለ ኑሮ የሚኖረን ምኞት፣ በእውቀታንና በባህርያችን ልክ ነው።
ይህም ብቻ አይደለም።
ወደ ምኞታችን የምንሄድበት የተቃና ወይም ጠማማ መንገድ፣ ጸሎታችንን በእውን የምናመጣበት የጥረትና የአዝመራ ወይ የሸፍጥና የዝርፊያ ጉዞም አለ።
ቆሞ መጠበቅ አንድ አማራጭ ነው።
በዘልማድና በዘፈቀደ መጣጣር መራመድም ይቻላል።
በልግስና በበጎ ምጽዋት ከጊዜዊ ችግር የእፎይታ እድል ማግኘትም ይኖራል።
ከመስረቅና ከማምታታት፣ በሸፍጥ ማጭበርበርና በሽፍትነት መዝረፍም አለ።
በሙያ ትጋት፣ በጥበብና በጥረት፣ በፍሬያማና በተቃና መንገድ የሚራመድ፣ የሚያዛልቅ መርህ ደግሞ አለ።
ምን ለማለት ነው? የመልካም ስብዕና፣ የማንነት ክብር፣ የስነምግባር መርህ ጉዳይ ነው-የኑሮና የእንጀራ ጉዳይ።
የተደላደለ ኑሮን መመኘትና ማግኘት እጅግ መልካም ነው። አለበለዚያማ ምኑን ኖርነው? የጽድቅ ጸሎት ነው- የእንጀራ ምኞት። ነገር ግን፣…
“ነገር ግን”፣… “ይሁን እንጂ”፣ “ግን ደግሞ” የሚሉ አባባሎች እዚህ ላይ ነው የሚያስፈልጉት። ጥሩ ነገሮች እጅግ መልካም የመሆናቸው ያህል፣ ያንን የሚመጥኑ ተጓዳኝ መልካም ነገሮችን ማሟላት እንደሚገባን ለማገናዘብ ይጠቅማሉ። “ዳሩ ግን”፣… “ቢሆንም ቅሉ” የሚሉ አባባሎችም ነበሩ።
ለማንኛውም፣ እንጀራና ኑሮ መልካም ናቸው። ግን ደግሞ፣… ሰው አውሬ አይደለም። ዘላለም ጨቅላ እንዲሆን፣… ወላጆችና ሞግዚቶች ከየትም አምጥተው ሁሌ እንዲመግቡት፣… ምኞቱን እንዲያሟሉለት አይደለም- የሰው አፈጣጠሩ።
ከወዲህም በእውቀት ምኞቱን በአሰተዋይት አላማውን እያስተካከለ እያሳደገ፣
ከወዲህም የተቃና ፍሬያማ መንገድን እየያዘና በትጋት እየተጓዘ፣
ለምኞቱ የሚመጥን የስነምግር መርህና የግል ማንነትን እየገነባ እንዲኖር ነው- የሰው አፈጣጠር።
ሰው በእግዚአብሔር ቃልም ጭምር እንጂ፣ በእንጀራ ብቻ አይኖርም የሚለው ሃሳብም እነዚህን የሰው ተፈጥሯዊ ገጽታዎችን አጣምረን እንድናገናዝብ የሚያስተምር ነው።
የማቴዎስ መጽሐፍ ምዕራፍ 4  እንዲህ ይተርክልናል።
ኢየሱስ በዲያብሎስ ሊፈተን፣ መንፈስ ወደ ምድረ በዳ መራው። አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ።
ፈታኝም ቀርቦ፣ “የእግዚሄር ልጅ ከሆንክ፣ እነዚህ ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ ተናገር” አለው።
እሱም መልሶ፣ “ሰው ከእግዚሄር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ፣ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ተብሎ ተጽፏል አለው።
ከዚህ በኋላም፣ ዲያብሎስ ወደ ቅድስት ከተማ ወሰደውና በመቅደስ አናት ጫፍ ላይ አቁሞ፤ “መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል። እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳይሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል” ተብሎ ተጽፏልና፣ የእግዚሄር ልጅ ከሆንክ ራስህን ወደ ታች ወርውር አለው።
ኢየሱስም፣ “ጌታ አምላክህን አትፈታተን” ተብሎም ተጽፏል አለው።
ደግሞ ዲያብሎስ እጅግ ረዥም ወደሆነ ተራራ ወሰደውና የዓለምን መንግስታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ፣ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው።
ያን ጊዜም ኢየሱስ፣ “ሂድ አንተ ሰይጣን። ለጌታህ ለአምላክህ ስገድ፣ እሱንም ብቻ አምልክ” ተብሎ ተጽፏልና አለው።
ከዚያም፣ ዲያብሎስ ተወው። ይሄውናም መላእክት ቀርበው ያገለግሉት ነበር።
ከጥቀምት ማግስት የሚመጣው የኢየሱስ የፈተና ትረካ፣ በማቴዎስ መጽሐፍ ውስጥ ራሱን የቻለ ምዕራፍ ሆኖ ቀርቧል። በማርቆስ መጽሐፍ ውስጥ ግን በአጭሩ ነው የተጠቀሰው። ከጥምቀት በኋላ ምን እንደተከሰተ በጥቅሉ ያለዝርዝር ያስነብበናል። የማርቆስ ትረካ እንዲህ ይላል።
ወዲያውም፣ መንፈስ ወደ ምድረበዳ አወጣው። በምድረ በዳም ከሰይጣን እየተፈተነ አርባ ቀን ሰነበተ። ከአራዊት ጋር ነበረ። መላእክትም ያገለግሉት ነበር።
በቃ ዝርዝር የለውም። ከፈለጋችሁ ሌሎቹን መጻህፍት ማንበብ ትችላለች የሚል ይመስላል።
በእርግጥም፣ በሉቃስ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረው ዝርዝር ትረካ፣ ከማቴዎስ ጋር ተቀራራቢ ነው (የሁለተኛውና ሦስተኛው ፈተና ቅደምተከል ቢለያይም)። እንዲህ ይላል።
ኢየሱስም መንፈስ ቅዱስ መልቶበት፣ ከዮርዳኖስ ተመለሰ። በመንፈስም ተመርቶ አርባ ቀን ከዲያብሎስ ተፈተነ። በነዚያ ቀናት ምንም አልበላው። በመጨረሻም ተራበ።
ዲያብሎስም፣ “የእግዚሄር ልጅ ከሆንክ ይህን ድንጋይ እንጀራ ሁን ብለህ እዘዝ” አለው።
ኢየሱስም፣ ሰው በእግዚሄር ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፏል ብሎ መለሰለት።
ዲያብሎስም ወደ ረዥም ተራራ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት በቅጽበት አሳየው። ዲያብሎስም፣ ይህን ሥልጣን ሁሉ ክብራቸውም ለእኔ ተሰጥቷል። ለምወደው ለማንም እሰጠዋለሁና… አንተ በእኔ ፊት ብትሰግድ፣ ሁሉም ላንተ ይሆናል አለው።
ኢየሱስም መልሶ፣ ለጌታ ለአምላክህ ስገድ። እሱንም ብቻ አምልክ ተብሎ ተጽፏል አለው።
ወደ ኢየሩሳሌም ደግሞ ወሰደው። በመቅደስም አናት ጫፍ ላይ አቁሞ፣ “ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል። እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳይሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፏልና የእግዚሄር ልጅ ከሆንክ፣ ራስህን ከዚህ ወደ ታች ወርውር አለው።
ኢየሱስም፣ ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሏል አለው።
ዲያብሎስም ፈተናውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ እስከ ጊዜው፣ ከእርሱ ተለየ።
ይሄው ነው የሉቃስ ትረካ። ሦስቱ ፈተናዎች ተጠናቅቀዋል። ነገር ግን ለጊዜው ነው። ፈተናዎቹ ዘላለማዊ ናቸውና።

Read 1284 times