Saturday, 21 January 2023 20:22

በየቀኑ በሀገር ደረጃ ወደ 35 እናቶች ይሞታሉ፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

  የዚህ እትም እንግዳችን አቶ ፈቃዱ ማዘንጊያ ናቸው አቶ ፈቃዱ ማዘንጊያ በአዋላጅ ነርሶች ማህበር ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ በአዋላጅ ነርስነት ሙያቸው ለ19 አመት ያህል ሰርተዋል፡፡ አቶ ፈቃዱ በተለይም በኢትዮጵያ የነበረውንና አሁን ያለውን የእናቶች ሞት እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡
‹‹…በኢትዮጵያ የነበረውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ ባለፉት ሀያ አመታት ብዙ የተሰራ ሲሆን ብዙ ለውጥ ተገኝቶአል፡፡ በፈረንጆቹ 2000 ዓ/ም በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1992 ዓ/ም አካባቢ በ100.000 በሕይወት ከሚወለዱ ህጻናት ውስጥ 1035/እናቶች ይሞቱ ነበር፡፡ አሁን ግን በ100.000 በሕይወት ከሚወለዱ ወደ 401/ዝቅ እንዲል ተደርጎአል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በየአመቱ ወደ 3.5 ሚሊዮን ህጻናት ይወለዳሉ፡፡ በዚህ መሰረት ሲሰላ ከ12.000-14.000 እና ቶች ይሞታሉ ማለት ነው። በቀን ሲሰላ ደግሞ በየቀኑ በሀገር ደረጃ  ወደ 35 እናቶች ይሞ ታሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ በመቀጠልም እዚህ ላይ የእናቶች ሞት ሲባል የሴቶች ሞት ማለት አለመሆኑን እና የእናቶች ሞት ማለት ህይወትን ለመስጠት ስትል ለህልፈት የምትዳረገውን ከእርግዝናው ወይንም ከወሊድ ጋር በተያያዘ ወልዳም ቢሆን በ42 ቀን ውስጥ በአራስነት ጊዜዋ የምትሞተውን የሚመለከት ነው ብለዋል አቶ ፈቃዱ፡፡››
አቶ ፈቃዱ በመቀጠልም እንደተናገሩት የእናቶች ሞት የሚከሰተው መከላል በሚቻሉ ምክ ንያቶች ሁሉ ነው፡፡ ለምሳሌ ባደጉ ሀገራት ያሉትን የእናቶች ሞት ቁጥር ለመመልከት ቢሞከር በስዊድን ከ1000.000 በሕይወት ከሚወለዱ 3 እናቶች፤ በአሜሪካ ከ100.000 በሕይወት ከሚወለዱ 7 እናቶች በአረብ ኢምሬቶች ከ1000.000 በሕይወት ከሚወለዱ 7 እናቶች ብቻ ይሞታሉ፡፡ ይህንን ቁጥር  በኢትዮጵያ ከሚሞቱት 401 ጋር ሲነጻጸር እጅግ በጣም የተራራቀ ነው፡፡ ይህንን ከፍተኛ የሆነ የእናቶች ሞት ቁጥር ግን አሁንም ማውረድ ስለሚቻል ጠንከር ያለ ትኩረትን ይፈልጋል፡፡
አንድ ሰው በሰውነቱ ውስጥ 5 ሊትር ደም አለ። ይህ ደም በምን ደረጃ ሲፈስ ነው የደም መፍሰስ ገጥሞት ተጎዳ የሚባለው ለሚለው ጥያቄ አቶ ፈቃዱ ሲመልሱ ‹‹…እናቶችን ከሚገድሉት ምንያቶች መካከል ከዋና ዋናዎቹ ውስጥ የደም መፍሰስ አንደኛው ነው፡፡ ከዚያ ሲቀጥል የደም ማነስ አለ፡፡ ከዚያ ደግሞ የምግብ እጥረት አለ፡፡ ሌላው እናቶች የሚሞቱበት ምክንያት ደግሞ የማህጸን ወይንም የዳሌ መጥበብ የሚባለው ይገኝበታል፡፡ ስለዚህ ከእነዚህና መሰል ነገሮች ተነስተን እናቶች ለምንድነው የሚሞቱት የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ድህ ነት፤ ያለእድሜ ጋብቻ፤ የሴቶች መብት አለመከበር፤ አለመማር የመሳሰሉት ሲሆን ብዙ ጊዜ ደም የሚፈሳቸው ሴቶች በርከት ያለ ልጅ የወለዱ፤ የቤተሰብ ምጣኔ ያላገኙ ናቸው፡፡ እንደ ዚህ ያሉት ሴቶች ትምህርት ያልተማሩ ስለሚሆኑ ልጅ ወልጄ ይጦረኛል ከሚል ልጅን እንደ ኢንሹራንስ የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ ሴቶቹ ይህንን ባይሹም እንኩዋን ወንዶቹ ወይንም ባሎቹ ልጅ እንዲወለድላቸው ስለሚፈልጉ የቤተሰብ እቅድ ዘዴ ተጠቃሚ አይሆኑም፡፡ ይህ በከተማ በመጠኑም ቢሆን መልኩን ይለውጣል። ልጅን አራርቆ እና በፕላን በእቅድ የመው ለድ ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ስለዚህም እናቶች በአብዛኛው ለሞት የሚዳረጉት ከድህነትና ከማህ በራዊ ፍትህ መጉዋደል የተነሳ መሆኑ በግልጽ ይስተዋላል፡፡
አንዲት እናት በእርግዝና ላይ እያለች በየደቂቃው ወደ አንድ ሊትር የሚጠጋ ደም ወደ ልጅዋ ትልካለች፡፡ ልክ ልጅዋን ስትወልድ እና የእንግዴ ልጁ ከማህጸንዋ ሲለያይ ያ ደምን ወደልጅዋ የምታስተላልፍበት የደም ስር መዘጋት ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ተፈጥሮ በራሱ ዝግጁ ነው፡፡
በመጀመሪያ ወዲያውኑ የሚመነጨው ሆርሞን ወይንም ቅመም በመመንጨት እነዚያን ደም ሲያስተ ላልፉ የነበሩ ክፍት የሆኑትን የደም ስሮች ይዘጋቸዋል፡፡
ሁለተኛው ወደላይ ከፍ ብሎ የነበረው ማህጸን ወደታች በመውረድ ጭነት አድርጎ የድም ስሮቹን እንዲዘጉ ያደርጋል፡፡
ሶስተኛው በማህጸን የደም ስሮቹ እርስ በእርስ በመቆላለፍ ደም መፍሰሱ እንዲቆም ያስችላሉ፡፡
ከማህጸን ጋር ተያይዞ የነበረው የእንግዴ ልጅ ሲለያይ እስከ እሩብ ሊትር ደም ሊፈስ ይችላል። ይህ ተቀባይነት አለው፡፡ ነገር ግን ወላድዋ የደም ማነስ ወይንም የደም ግፊት አስቀድሞውኑ ከነበረባት ለመቋቋም ሊያቅታት ይችላል፡፡ ጤነኛዋ ሴት የእሩብ ሊትሩ ደም መፍሰስ የማይጎዳት ሲሆን ከዚያ በላይ እስከ ግማሽ ሊትር ደም የፈሰሳት ከሆነ የደም ሽክር ክሪቱን ተፈጥሮአዊ ሂደት ሊያውክ ይችላል፡፡ደም በልብ አማካኝነት በሰውነት ውስጥ ደምን የማመላለስ ተግባርዋን ማከናወን እየተሳናት ስለሚመጣ ሴትየዋ እየተጎዳች ትሄዳለች፡፡ በዚህ ጊዜ በሰውነት ውስጥ ዋና ዋና ክፍሎች የሚባሉት ኩላሊት፤ ጉበት፤ ሳምባና አእምሮ ጉዳት ሊርስባቸው ይችላል፡፡ በተለይም ኩላሊት የደም ድርቀት ሊያጋ ጥማት ሲችል ልብ ደግሞ የደም መጠኑ ሲያንስባት ለማካካስ በፍጥነት መምታት ትጀም ራለች፡፡ ስለዚህ ልብ መድከም ትጀምራለች፡፡ ሳምባና አእምሮም ተመሳሳይ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ ከዚያም በተጨማሪ የደም ዋናው ተግባር ኦክስጂን መሸከም ስለሆነ ይህች እናት የደም መፍሰሱ ሲገጥማት ኦክስጂን ሊያጥራት ይችላል፡፡ በዚህም እስከሞት ልትደርስ ትችላ ለች። ደም ሌላው ተግባሩ በሽታን መከላከል ነው፡፡ ቀዩ ኦክስጂንና ምግብ ሲሸከም ነጩ ደግሞ በሽታን መከልል ስራው ነው፡፡ ይህች እናት ደም ሲያንሳት በሽታን መከላከል ያቅታታል፡፡ ስለዚህ ምናልባት ወሳኝ ከሆኑት ጉዳቶች ለጊዜው ብትተርፍም ኢንፌክሸን ሊይዛት ይችላል፡፡ይሄ ተደማምሮ ሴትየዋን ለሞት ያጋልጣታል ማለት ነው ብለዋ አቶ ፈቃዱ ማንያዘዋል የአዋላጅ ነርሶች ማህበር ስራ አስኪያጅ፡፡
ከወሊድ በሁዋላ የደም መፍሰስ የሚባለው ከወለደች በሁዋላ እስከ ስድስት ሳምንት የሚቆይ ነው፡፡ ይህም በሁለት ይከፈላል፡፡ የመጀመሪያው ሀያ አራት ሰአትና ከሀያ አራት ሰአት በሁዋላ ያለው ማለት ነው፡፡
የመጀመሪያው ሀያ አራት ሰአት ከሆነ ብዙ ጊዜ ማህጸን ወደ ቦታው ማለትም ከእርግዝናው በፊት ወደነበረበት ቦታ በሰአቱ አለመመለሱ ወይንም አለመውረዱ ነው፡፡ እናቲቱ ለልጁ ደም ስታቀብልበት የነበረውን የደም ስሮች ማህጸኑ ወደቦታው ካልተመለሰ የሚዘጋቸው ስለማያ ገኙ ደም ማፍሰሳቸውን ይቀጥላሉ ማለት ነው፡፡ ይሄ ሊሆን የሚችልት አጋጣሚ፡-
በማዋለድ ወቅት የእንግዴ ልጅ በአግባቡ ካልተወገደ፤
እንግዴ ልጁን የሚሸፍነው እንደፕላስቲክ ያለ ተፈጥሮ ወይንም ደግሞ የጉዋጎለ ደም ከውስጥ ከቀረ፤
ልጁ መጠኑ ትልቅ ሲሆን ወይም በማዋለድ ጊዜ የማህጸን ጫፍ ወይንም አካባቢው የመሰንጠቅ አጋጣሚ ካለው፤
ሌላው ደግሞ እናትየው ልክ ስታረግዝ ጀምሮ የሚኖረው የጉበት ዝግጅት ነው፡፡
ከወሊድ በሁዋላ ደም እንዳይፈስ ለማድረግ ያሉት ተፈጥሮአዊ ሁኔታዎች 1/ወዲያውኑ የሚመነጨው ሆርሞን ወይንም ቅመም በመመንጨት 2/ማህጸን ወደቦታው መመለሱ 3/ ማህጸን እራሱ መቆላለፉ 4/ እንደመረብ ነገር የሚሰራ አለ፡፡ ያ መረብ የሚሰራው ፕሮቲን ነው፡፡ ያ ፕሮቲን ትሮምቢን የሚባል ነገር ያመርታል፡፡ ጉበት የሚያዘጋጀው ይህንን ነገር ነው። ልክ ልጁ ተወልዶ ሲለያይ ያ ኬሚካል ከጉበት ይወጣል፡፡ ከዚያም ደምስሮቹ ላይ መረብ ይሰራል፡፡ ያ መረብ የደም ስሮቹን ይዘጋቸዋል፡፡ ነገር ግን የሽርት ውሀ ቀድሞ ከፈሰሰ፤ ከፍተኛ የደም ግፊት ካለባት፤ ልጁ በማህጸን ውስጥ እያለ ከሞተ እንደተወለደ ይቆጥረውና ጉበት ኬሚካሉን አስቀድሞ ይለቀዋል። ስለዚህም ተፈጥ ሮአዊ ሁኔታው ይዛባል፡፡ በዚህም የተነሳ በቂ መረብ የሚሰራ ነገር ሲጠፋ እናትየው ትደ ማለች፡፡ በሌላም በኩል ወላድዋ እናት የጉበት ታማሚ ከሆነች ጉበት መረቡን ለማዘጋጀት ስለማ ይችል አስቀድማ በሐኪም ክትትል ስር መቆየት ይገባታል፡፡
የደም መፍሰስ በ24 ሰአት ወይንም ከዚያ ውጪ ሊከሰት ይችላል፡፡ እንደ አቶ ፈቃዱ ማብራሪያ የደም መፍሰሱ ምክንያቶች ከላይ የተዘረዘሩት አራት ምክንያቶች ከሆኑ እናትየው ደም የሚፈሳት በ24 ሰአት ጊዜ ውስጥ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን አወላለድዋ ንጽህናው ባልተጠበቀ ሁኔታ ሲሆን፤ የሽርት ውሀ ቀድሞ ከፈሰሰ…ወዘተ የመመረዝ ወይንም ኢንፌ ክሽን ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ አጋጣሚው ይህ ከሆነ ደም የሚፈሳት ከ24 ሰአት በሁዋላ ይሆናል፡፡ ምክንያቶቹ ስለሚለያዩ ነው እንጂ የደም መፍሰሱ ያው አንድ አይነት ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ ወላዶቹም ይሁኑ ቤተሰብ የደም መፍሰስን መጠን ካለመረዳት የተነሳ እናቶ ቹን እያዩዋቸው የሚሞቱበት አጋጣሚ ይስተዋላል። ከግማሽ ሊትር በላይ እስከ ሁለት ሊትር ድረስ የሚፈስ ከሆነ ለመዳንም አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ነገር ግን ግማሽ ሊትር ያህል ደም ፈስሶ አል ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ በአስቸኳይ ለህክምናው እርዳታ መቅረብ ወይንም በተኙበት ሆስፒታልም ቢሆን ሁኔታውን በአስቸኳይ ለሐኪም ሪፖርት ማድረግ ይገባል፡፡      
Read 664 times