Saturday, 28 January 2023 21:13

አሳፋሪና አስደንጋጭ ክስተቶች!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(2 votes)

“ህገ ወጥ ተግባራትን የፈፀሙ የሀይማኖት አባቶች ከሥልጣነ ክህነት እንዲነሱ ተወሰነ”

  አንዳንድ ሳምንት ጨፍጋጋ ነው። በአስደንጋጭና  አሳፋሪ ክስተቶች የተሞላ። (“አንዳንድ ቀን አለ ኮረኮንች የበዛው” የሚለው የነ.መ  ግጥም ትዝ አለኝ!) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ትንሽ የሰላም አየር መተንፈስ ስንጀምር፤ ከእልቂት ዜና እፎይ ያልን ሲመስለን፣ ዱብዳ የሚመስል መዓት  ይገጥመናል። ግጭት፣ ግድያ፣ ውድመት፡፡
ከሰሞኑም እንዲሁ ነው የሆነው። ታላቁ የጥምቀት በዓል በሰላምና በድምቀት ተከበረ ብለን ፈጣሪያችንን አመስግነን ሳንጨርስ፣ አሳዛኝና አስደንጋጭ ክስተቶችን ለማስተናገድ ተገደናል፤ በአስፈሪውና አሳፋሪው ሳምንት።
ሦስት አባቶች ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አፈንግጠው በመውጣት ፈጸሙ የተባለው ህገወጥ ድርጊት ምዕመኑን አስደንጧል፤ ሲኖዶሱን አሳዝኗል ተብሏል። በነገራችን ላይ አባቶቹ ህገወጥ የተባለውን ድርጊት ከመፈጸም ይልቅ ችግራቸውን በውይይት ቢፈቱት የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ለቤተ ክርስቲያኗም፣ ለምዕመኑም፣ ለአገርም፣ ለሲኖዶሱም፡፡ ለሁሉም፡፡
እስቲ ከእሁድ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ  የተከሰቱትን  ጉዳዮች  እናስታውስ።  ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ተከሰተ የተባለውን “ህገወጥ-ሲመተ-ጳጳሳት” ተከትሎ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ “በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኙ አበው ሊቃነ-ጳጳሳት፣ በቤተ ክርስትያናችን ላይ በተፈጸመው የቀኖና ጥሰትና ህገ-ወጥ ድርጊት ዙሪያ ለመወያየት በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ብፁአን አበው ሊቃነ-ጳጳሳት ወደ አገራቸው እንዲገቡ ጥሪ ተደርጎላቸዋል፡፡
“ቤተ ክርስቲያናችን በረዥም ዘመን አገልግሎቷና  በታሪኳ ገጥሟት የማያውቀውን ችግር በጋራ ሆነን እንፍታ” ሲሉም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሃፊና የኒውዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። (ልብ በሉ! “በታሪኳ ገጥሟት የማያውቅ ችግር ነው” ነው ያሉት ጳጳሱ!)  ይህ አባባላቸው የችግሩን ጥልቀትና ክብደት በግልጽ ይጠቁሟል፡፡
እንደሚታወቀው “ህገ-ወጥ ሲመተ ጳጳሳት” ፈፅመዋል የተባሉት አባቶች ከየትም  አልመጡም። ከራሷ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ነው የወጡት። ለቤተ ክርስቲያኒቱ ቅርበት ያላቸው የሃይማኖት ልሂቃን በአባቶቹ የተፈጸመው ሌላ ሳይሆን “መፈንቅለ ሲኖዶስ” ወይም “መፈንቅለ ቤተ-ክርስቲያን” ነው ይላሉ።
“ህገ-ወጥ ሲመተ ጳጳሳት” ፈጽመዋል የተባሉት ሦስቱ አባቶች ባለፈው እሁድ በሰጡት የቪዲዮ መግለጫ፤ “በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር አልቻልንም፤ ሲኖዶሱ ከአንድ አካባቢ ብቻ የተዋቀረ ነው።” ብለዋል።
“ምዕመናን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ወንጌልን ለመማርና ሥርዓተ አምልኮ ለመፈፀም እንዲሁም ለመገልገልና ለማገልገል ከአጥቢያ ቤተክርስቲያን ጀምሮ እስከ ፓትርያርክ ጽ/ቤት ድረስ ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ አላገኘንም” ነው ያሉት፤ ሦስቱ አባቶች በመግለጫቸው። ((ወንጌል በተለያዩ የብሄረሰብ ቋንቋዎች አይሰበክም እያሉ ነው እንዴ?) የቤተ ክርስቲያኒቱን አሰራር በጥልቀት የሚያውቁ አንድ የኦርቶዶክስ  ዲያቆን፤ በተለያዩ  ክልሎች በተለይም በኦሮምያ ወንጌል በአፍ መፍቻ ቋንቋ እንደሚሰበክ ለኢኤም ኤስ አረጋግጠዋል፡፡))
“አሁን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ከ85 በመቶ በላይ ከአንድ ወገን ተዋቅሮ የሚገኝ በመሆኑ ሁሉን አቀፍ ሲኖዶስ ነው ብሎ መቀበል ባለመቻሉ፣ ሁሉንም የአገሪቱን ህዝቦች ያዋቀረ ቅዱስ ሲኖዶስ አቋቁመን በይፋ ስራ ጀምረናል” ብለዋል፤ አባቶቹ።
እኒሁ አባቶች ታዲያ ለ26 የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶች የተለያዩ ሹመቶችን የሰጡ ሲሆን አብዛኞቹ ሹመቶች በኦሮሚያ ክልል፣ ጥቂቶቹ ደግሞ በደቡብ ክልል አካባቢዎች ለሚያገለግሉ አባቶች መሰጠቱ ተነግሯል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡ አንድ ምዕመን፤ ድርጊቱ የተፈጸመው በመንግስት ወይም በፓርቲ መዋቅር ውስጥ ቢሆኑ ኖሮ፣ ድርጊቱን ፈጻሚዎች ራሳቸውን የሚያገኙት ቂሊንጦ ነበር ብለዋል - “መፈንቅለ መንግስት” ወይም “መፈንቅለ ፓርቲ” በሚል ተወንጅለው፡፡ አሁን ግን አባቶቹ “መፈንቅለ ሲኖዶስ” ወይም “መፈንቅለ ቤተ ክርስቲያን”  ከፈጸሙ በኋላም  ከመሸጉበት ሆቴል ውስጥ ሆነው መግለጫ ሲሰጡ ሰንብተዋል፡፡ (የሃይማኖት አባቶች ከሆቴል መግለጫ ሲሰጡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል፡፡) ፈረንጅ እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲገጥመው ነው  Weird የሚለው፡፡
አባቶቹ በተለይ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ፤ “ፓትርያርኩ የ26ቱን አባቶች ሹመት እንዲያፀድቁ መጠየቃቸውን ጠቅሰው፤ ካልሆነ ግን  አዲስ ፓትርያርክ ለመሾም እንደሚገደዱ አስጠንቅቀው ነበር፡፡
በነገራችን ላይ ህዝበ ምዕመኑ እነርሱን እንደሚቀበላቸውና እንደሚከተላቸው የገለጹት አባቶቹ፤” ካልተቀበላቸው ግን አንድም ህዝቡ ሃይማኖቱ አልገባውም አሊያም ደግሞ ሌላ ችግር አለ ማለት ነው”  ሲሉ ተናግረዋል።
እርግጥ ነው ቤተ ክርስቲኒቱ ሁሌም ስትፈተን ነው የኖረችው። በለውጡ ማግስት “የኦሮሚያ ክልል ቤተ-ክህነት” የመመስረት እንቅስቃሴ ሲካሄድ እንደነበር ይታወሳል - በኋላም በቤተ ክርስቲያኗ አባቶች መካከል በተደረጉ ውይይቶች እልባት አግኝቷል፡፡
የሰሜኑ ጦርነት በተፋፋመ ወቅት ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ በትግራይ የሾመቻቸው ጳጳሳት፤ የትግራይ ቤተ ክርስቲያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መነጠሉን በአደባባይ አውጀው ነበር፡፡
“ስለዚህ ለቤተክርስቲያኒቱ  ፈተና ብርቋ አይደለም፤ በድል ትወጣዋለች” ሲሉ  ምዕመናን ተናግረዋል።
 የጠ/ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ- ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በሰጡት አስተያየት፤ “የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያንን በዘር ለመክፈል የተሄደው ርቀት አደገኛም አሳዛኝም ነው” ሲሉ ወቅሰዋል።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፤ ”በሲኖዶስ ህገወጥ የተባሉት አባቶች የጀመሩትን እንቅስቃሴ  ከጥቂት ዓመታት በፊት “የኦሮሚያ ክልል ቤተ-ክህነት” ለመመስረት ሲደረግ ከነበረው እንቅስቃሴ ጋር  ያገናኙታል - ካለፈው የቀጠለ እንቅስቃሴ ነው በማለት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤  ቅዱስ ሲኖዶስ ከትናንት በስቲያ  ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፣ ህገ ወጥ ተግባራትን የፈፀሙ የሀይማኖት አባቶች፣ ከሥልጣነ ክህነት እንዲነሱ ወስኗል፡፡
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንደገለጹት፤ ሕገ ወጥ የኤጴስ ቆጶሳት ሹመት ያስፈጸሙ ሦስት  ሊቃነ ጳጳሳት የነበሩ ግለሰቦችና በሕገ ወጥነት ሹመቱን ለመቀበል የሄዱ 25 መነኮሳት፣ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የአንድነት ጉባኤ ተለይተው እንዲወገዙ ተወስኗል።
ባለፈው አስፈሪና አስደንጋጭ ሳምንት፣ በሸዋ ሮቢት በተፈጸመው ጥቃት ከፍተኛ ውድመትና ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡   
ሥፍራው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ በሚገኙ የአማራና የኦሮሞ ብሄረሰብ አባላት መኖሪያ በሆኑ አካባቢዎች ነው። ከቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው ግጭት ወደተለያዩ ዞን አካባቢዎች ተስፋፍቶ፣ ባለፈው ማክሰኞም የአጣዬ ከተማን ጨምሮ በሌሎች ሥፍራዎች ጉዳት ማድረሱን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢው ሃላፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ ለቀናት ዘልቆ ለበርካቶች ሞትና ውድመት ሰበብ የሆነው ግጭት የተቀሰቀሰው ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም ነው። በዕለቱ ታጣቂዎቹ በክልሉ የጸጥታ ሃይል አባላት ላይ በፈጸሙት ጥቃት፤ ከ20 በላይ የአማራ ልዩ ሃይል፣ አምስት የፌደራል ፖሊስ አባላትና ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰላማዊ ሰዎች እንዲሁም የጀውሃ ቀበሌ አስተዳዳሪ መገደላቸውን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ አህመድ አልይ እና አንድ ነዋሪ ደግሞ፤ “ሸኔ ብለው የጠረጠሯቸውን፣ ነገር ግን ቤት ውስጥ ተቀምጠው ጫት ሲቅሙ የነበሩ ሰላማዊ ሰዎችን የአማራ ልዩ ሃይሎች መግደላቸው” ለግጭቱ ሰበብ መሆኑን ለቢቢሲ ጠቁመዋል።
ባለፈው ቅዳሜ የተቀሰቀሰው ግጭት ማክሰኞ ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ወደ ኤፍራታና ግድም ወረዳ አጣዬ ከተማ ተስፋፍቶ ውድመት መድረሱን ነዋሪዎች ጠቁመዋል። በእነዚህ አካባቢዎች ባለፉት ዓመታት ተመሳሳይ ግጭቶች ተከስተው በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፤ አጣዬ ከተማም የአሁኑን ጨምሮ ቢያንስ ለሦስት ጊዜ ያህል አስከፊ ግጭቶችንና ውድመቶች አስተናግዳለች። በእነዚህ ግጭቶችና ጥቃቶችም የከተማዋ ነዋሪዎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለመፈናቀል እንዲሁም ለንብረት ውድመት መዳረጋቸው ይታወቃል።
(በጣም  ያሳዝናል። ማንም የውጭ ሃይል ሳይመጣብን- እንዲህ እርስ በርስ መተላለቃችን- መጨካከናችን በእጅጉ ልብ ይሰብራል።  በእጅጉ ያስፈራል። በእጅጉም ተስፋም ያስቆርጣል።)
ባለፈው ረቡዕ የሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደር በሰጠው መግለጫ፤ በሸዋ ሮቢት ከተማ በሸኔ ቡድን ለቀናት እየተፈጸመ ያለው ጥቃት፣ ከከተማው የፀጥታ መዋቅር በላይ መሆኑን አስታውቋል። ጥቃት አድራሾች በተደራጀ መልክ የሚንቀሳቀሱና ግዙፍ የጦር መሳሪያዎችን የታጠቁ መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ተስፋዬ መንግስቱ ተናግረዋል። በከተማዋ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ የጠቆሙት ከንቲባው፤ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማወቅ አስተዳደሩ መቸገሩን ተናግረዋል። የፀጥታ መደፍረሱ ከአቅም በላይ መሆኑን በመግለጽም፤ መንግስት ቋሚ ዕልባት በመስጠት በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ ሃይል እንዲያሰማራ ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።
--በነገራች ላይ ከሰሞኑ ጥቃትና ግጭት ጋር በተገናኘ መንግስት ከወትሮው በተለየ የከረረና የመረረ ትችት ቀርቦበታል - ያውም ቀድሞ የመንግስት ቀንደኛ ደጋፊዎች በነበሩ ወገኖች ጭምር። በተለይ “በሸዋሮቢትና አካባቢው የተፈጸመው ጥቃት፣ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ቢያንስ ለሦስተኛ ጊዜ ከመሆኑ አንጻር፣ እንዴት ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ይሳነዋል? እንዴት የዜጎችን ህይወት አይታደግም?” በሚል መነሻ ነው በመንግስት ላይ የትችትና ተቃውሞ መዓት ሲዘንብበት የሰነበተው፡፡
ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት ከዓለም ቀዳሚ መባሏን በመጥቀስም፤ የኢትዮጵያ መንግስት “ደካማ መንግስት ነው!” እስከ ማለት ያመረሩ ተቺዎችም  አልጠፉም። በእርግጥም  አይፈረድባቸውም። በዜጎች  ላይ በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ያለው አስከፊ ጥቃት  በእጅጉ ስሜታዊ ያደርጋል፤ ያስቆጣልም!
አሁንም ቢሆን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ግድያና መፈናቀል እንዳይፈጸም መንግሥት ቁርጠኛና ዘላቂ  መፍትሄ ማበጀት ይጠበቅበታል፡፡ የፖለቲካ ልሂቃንና አክቲቪስቶች በህዝቦች መካከል ግጭት ከሚቀሰቅስ ንግግራቸው መታቀብ ይገባቸዋል፤በተለይ ደግሞ በዚህ  ፈታኝ ወቅት። የሃይማኖት አባቶችና መሪዎችም ምዕመናኑን በማስተማርና ሰላምና ፍቅርን በመስበክ፣ ህዝቡንና አገሪቱን ከተጨማሪ ዕልቂት፣ ውድመትና  መፈናቀል  ሊታደጉ ይገባል። ለዚህ ደግሞ በመጀመሪያ እርስ በርሳቸው መግባባትና መከባባር ይኖርባቸዋል - በሳምንቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ ጳጳሳት መካከል  የተከሰተው ዓይነት አሳፋሪና አስደንጋጭ  ክፍፍልና ውዝግብ ዳግም እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ  ይሻል፡፡
በመጨረሻም፤ ከእንዲህ ያለ ጨፍጋጋ ሳምንት ይሰውረን!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!!   


Read 1112 times