Saturday, 04 February 2023 18:48

ከግጭት አዙሪት እንዴት እንውጣ?!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(1 Vote)

 ያልሞከርናቸውን ነገሮች ብንሞክርስ ለህዝባችንና ለሃገራችን ብለን!
                     
           ባለፈው ሳምንት በሸዋሮቢትና አካባቢው የተከሰተው ግጭትና የደረሰው ጉዳት አስደንጋጭ ቢሆንም ከአሁን በፊት ተከስቶ የማያውቅ አይደለም። በቅርብ ዓመታት ብቻ ተመሳሳይ ግጭት እልቂትና ውድመት ቢያንስ ለሦስት  ጊዜያት ያህል መከሰቱ ይታወቃል። አጣዬ ከተማ ከሰሞኑ ጋር ለሦስተኛ ጊዜ በእሳት መጋየቷን ነው ነዋሪዎች የሚናገሩት።
መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ባደረጉት ርብርቦሽም የወደሙ መኖሪያ ቤቶችና ተቋማት ተመልሰው ተገንብተው ነበር።  ነገር ግን ይኸው ባለፈው ሳምንት ሌላ ግጭት ተነስቶ የጸጥታ ሃይሎችን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል፤ አያሌዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል። ብዙዎች ቤት ንብረታቸው በእሳት ወድሞባቸዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት ሰላምና መረጋጋቱ የተመለሰ ቢመስልም ነዋሪዎች ግን አሁንም ከስጋትና ፍርሃት እንዳልወጡ ነው የሚናገሩት። ባላሰቡትና ባልጠበቁት ጊዜና ሁኔታ ጥቃት እየተሰነዘረባቸው እንዴት ብለው ከስጋት ይውጡ?!
አማፂ ታጣቂዎች በየጊዜው ድንገተኛ ጥቃት እየፈጸሙ ነዋሪዎችን ይገድላሉ፤ ቤት ንብረት ያቃጥላሉ፤ የመንግስት ተቋማትን ያወድማሉ። በየጊዜው ዜጎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ይፈናቀላሉ። ስለዚህም ከስጋትና ፍርሃት ባይወጡ አይፈረድባቸውም። ከመንግስት ሁነኛ ዋስትና እስኪያገኙ ድረስ ነገ ከነገ ወዲያም መስጋታቸው አይቀርም።
በሌላ በኩል፤ የአካባቢው አመራሮች ስጋትና ፍርሃት የወለደው ዘላቂ መፍትሄ አበጅተው ህዝባቸውን ከእልቂት፤ ከተማቸውን ከውድመት የሚታደጉት መቼ ነው? አንገብጋቢ ጥያቄ ነው! በቸልተኝነትም ይሁን ሆን ብለው በአሻጥር ህዝቡንና አካባቢውን ለተደጋጋሚ ጥቃት የዳረጉ አመራሮች ተጠያቂ ሆነው አስተማሪ ቅጣት የሚያገኙትስ መቼ ነው? ሌላው ቢቀር ፓርላማ ቀርበው አፋጣጭ (አሳጭ) ጥያቄዎች እየቀረበላቸው ስለ ግጭቱ፣ ስለ ግድያው፣ ስለ ውድመቱ፣ ስለ መፈናቀሉ፣ ስለ ሰቆቃው ወዘተ እውነቱን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያስረዱ የሚገደዱበት አሰራር የሚፈጠረው መቼ ነው? እንዲህ ያለው ሃሳብና ፍላጎቱስ አለ? ወይስ ተሸፋፍኖ እንዲያልፍ ነው የሚፈለገው?! (ከሆነም አያዋጣም!)
መቼም በመንግስት መዋቅር ውስጥ “ኦነግ ሸኔ” ተሰግስጓል እየተባለ በግልጽ እየተወራ ጥቃትና ግድያ ደጋግሞ የሚጎበኛቸው አካባቢዎችን የመንግስት አመራሮች ተጠያቂ አለማድረግ ግራ አጋቢ ነው።
ዜጎች በተደጋጋሚ የሚገደሉባቸውን አካባቢዎች አመራሮች በፓርላማ አቅርቦ ተጠያቂ ማድረግ የሚቻልበት አሰራር ሳይዘረጋ በወር አንዴ የተቃዋሚዎች የክርክር ቀን በፓርላማ ለመጀመር ማሰብ እንቆቅልሽ ነው የሚሆነው። (ቅንጦትም ጭምር!) በዜጎች ላይ የሚፈጸም ማንነት-ተኮር ግድያና ማፈናቀል እንደሆነ ከክልል ብቻ ሳይሆን ከፌደራልም አልፎ የምዕራባውያኑን ትኩረት ጭምር እየሳበ መጥቷል- እንደ ሰሜኑ ጦርነት። (ሸፋፍኖ ማለፍ አያስኬድም ለማለት ነው!)
በአገራችን በየቦታው ለሚከሰቱ ዘር-ተኮር ጥቃቶችና ግጭቶች በብሔር የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አስተዋጽኦ የላቸውም ማለት አይቻልም። እነርሱ እርስ በርስ በርቀት የሚወራወሩት ቃላት ነው ህዝባችንን ጥይት ሆኖ እየፈጀው ያለው። በሰላማዊ መንገድ ሊቀንቀሳቀሱ ተመዝግበው የጥላቻ ትርክት በማራገብ እሳቱ ላይ ነዳጅ  የሚያርከፈክፉ ብሄር ተኮር የፖለቲካ ድርጅቶችስ እንዴትና መቼ ነው ተጠያቂ የሚሆኑት? በዩቲዩብና በፌስቡክ አንዱን ብሄር ከሌላው ብሄር ጋር ለማጋጨትና ደም ለማቃባት በትጋት የሚንቀሳቀሱ አክቲቪስትና ልሂቃን ተብዬዎችስ አደብ የሚገዙት መቼ ነው? ማንንና የቱን ህግ ፈርተው? እነሱ እንደሆነ አሜሪካና አውሮፓ መሽገው ነው ድሃውን የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በርስ የሚያፋጁት-ሥራቸው ነዋ!
እናም ምን ለማለት ነው… ችግሮቹን እንዲህ ዘርዝረንና ለይተን ስናበቃ- ፊት ለፊት ተጋፍጠን፤ የወንጀል ተባባሪዎችን (በተለይም የመንግስት ባለስልጣናትን) ተጠያቂ አድርገን፤ ቸልተኞቹን ደግሞ በፓርላማ በህዝብ ፊት አፋጥጠን ካላሳጣናቸውና ከትላንቱ የተለየና የተሻለ ዘላቂ መፍትሄ ካላበጀን በቀር የሰላማዊ ዜጎች ግድያ አያቆምም፤ መፈናቀሉ አይቀርም፤ ንብረትና ሃብት ውድመቱ አይገታም። በአጭሩ የግጭት አዙሪቱ ይቀጥላል። የማታ ማታም ተመልሰን የማንወጣበት የአዘቅት ቀውስ ውስጥ እንገባለን። ያኔ ስንቶች የሞቱላት አገር ትፈራርሳለች፤ ህዝቦች ይበተናሉ-እንደ ሶርያ (ከዚህ መአት ይሰውረን!)
ከመዓቱ የምንሰወረው ግን በምኞት አይደለም። ቢያንስ አንድዬ ከመዓቱ ይሰውረን ዘንድ እኛ ምቹ መሆን አለብን። ከመፈራረስና ከመበታተን ለመዳን በሰዋዊ አቅማችን የተቻለን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅብናል። ከአቅማችን በላይ የሆነውን ለአንድዬ ትተንለት የድርሻችን ግን መወጣት አለብን።
እስቲ ከዛሬ ጀምሮ ለህዝባችንና ለአገራችን ብለን (ለራሳችንም ጭምር) እስካሁን ያልሞከርናቸውን ነገሮች እንሞክር፡-
 እስቲ በህዝቦች መካከል ጥላቻን የሚፈጥሩና ግጭትን የሚቀሰቅሱ የማህበራዊ ሚዲያ ጽሁፎችን ላይክም ዲስላይክም ከማድረግ እንቆጠብ- ለህዝባችንና ለአገራችን ብለን!!
እስቲ መረጃ ላይ ያልተመሰረቱ መሰረተ-ቢስ የፈጠራ ወሬዎችን አናራግብ- ለህዝባችንና ለአገራችን ብለን!!
እስቲ የሌላውን ባህል፣ ቋንቋና ሃይማኖት ከማጥላላትና ከማናናቅ እንታቀብ- ለህዝባችንና ለአገራችን ብለን!!
እስቲ ለልጆቻችን በጎነትን፣ ፍቅርን፣ መከባበርንና ወንድማማችነትን እንስበካቸው- ለህዝባችንና ለአገራችን ብለን!!
እስቲ “የእኔ” ማለቱን በእጅጉ ቀንሰን፣ “የእኛ” ማለቱን በእጅጉ እናብዛ- ለህዝባችንና ለአገራችን ብለን!!
እስቲ ከሥልጣንም፤ ከምድራዊ ሃብትም ከመሬትም በላይ ለሰው ልጅ ህይወት ዋጋ መስጠት እንጀምር- ለህዝባችንና ለአገራችን ብለን!!
እስቲ በራሳችን ላይ እንዲደረግ የማንሻውን በሌሎች ላይ ላለማድረግ ለራሳችን ቃል እንግባ- ለህዝባችንና ለአገራችን ብለን!!
እስቲ ለጎረቤቶቻችን፣ ለባልንጀሮቻችን፤ ለሚያውቁንም ለማያውቁንም ደግ ደጉን ብቻ እንመኝ፤ እናድርግም- ለህዝባችንና ለአገራችን ብለን!!
እስቲ የሚመለከተን ጉዳይ ላይ ብቻ እናተኩር- ለህዝባችንና ለአገራችን ብለን!!
ያኔ ከግጭት አዙሪት ያለጥርጥር እንወጣለን ብዬ አምናለሁ!! (በግሌ!)
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ይባርክ!!

Read 831 times