Saturday, 18 February 2023 19:38

ራሺያና ዩክሬን በከንቱ የደሙበት ጦርነት

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

እንደ ዘበት በሁለት ሳምንት ይጠናቀቃል ተብሎ የተጀመረው ጦርነት፣ በየወሩ የእልፍ ሰዎችን ሕይወት እያረገፈ፣ ዩክሬንን እያፈራረሰ፣ ራሺያን እያቆሰለና እያዳከመ፣… ይሄውና ዓመት ሊሞላው ነው። 16 ሚሊዮን የዩክሬን ዜጎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው ለስደት ተዳርገዋል። 8 ሚሊዮኑ ከአገር ሸሽተው ሄደዋል።
350 አውሮፕላኖች እንደተመቱና እንደተቃጠሉ አስቡት። ግማሾቹ የዩክሬን ግማሾቹ የራሺያ ናቸው። ይሄ ብቻ የጦርነቱን ውድመት አይገልፅም? ከ50 ሺ በላይ ሰዎች መሞታቸውስ? “ቢያንስ ቢያንስ” የተባለለት ቁጥር ነው ይሄ። የቁስለኞች ቁጥር ደግሞ፣ ከ200 ሺ አያንስም ተብሏል። የኢኮኖሚ ውድመትና የኑሮ ቁም ስቅል፣… ለቁጥር ያስቸግራል። ከተሞች ከዳር እስከ ዳር እየፈረሱ፣ ምኑንና ከምኑ ቆጥረው ይዘልቁታል!
መች በዚህ አበቃ? እንዲያውም ዘንድሮ፣ ከአምናው የባሰ ጦርነት ለማካሄድ ሲዘጋጁ ነው የከረሙት።
ውጊያው ለአፍታ ሳይቋረጥ፣ እንደ አዲስ ከአምናው በእጥፍ የሚበልጡ የራሺያ ወታደሮች ለሰፊ ጦርነት ወደ ዘመቻ ገብተዋል።
የዩክሬን ጦርም፣ ከአምናው በእጥፍ የሚበልጥ የጦር መሣሪያ በዓይነትና በብዛት እየታጠቀ ነው። የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት፣ በየሳምንቱ ተጨማሪ መሣሪያና ተተኳሽ እየሰጡ፣ ተጨማሪ ለመላክ ቃል ሲገቡ ሰንብተዋል። በእርግጥ፣ አንዳንድ የመሣሪያ ዓይነቶች ላይ፣ ማመንታታቸው  አልቀረም። ጦርነቱ የተጀመረ ሰሞን፣ አሜሪካና አውሮፓ፣ ለዩክሬን ከባባድ መሣሪያዎችን ለመስጠት ፈቃኛ አልነበሩም። ወር ሁለት ወር ካንገራገሩ በኋላ ነው፣ መድፎችን መላክ የጀመሩት። ትንሽ ቆይተው ደግሞ ዘመናዊ የአጭር ርቀት ሮኬቶችን ሰጥተዋል።
እንዲም ሆኖ፣ “ታንኮችን ግን አንሰጥም፤ አይሞከርም” ማለታቸውና ማንገራገራቸውን  አላቋረጡም። ይሄውና ዓመት ሊሞላቸው ሲቃረብ፣ በመጨረሻ አሁን፣ ታንኮችን ለመላክ ወስነዋል። ከወሰኑ በኋላም ግን ነገሩን እንደቀላል አልቆጠሩትም። “ዛሬም፣ ሰበብ ከመደርደር አልተመለሱም” ይሏቸዋል ተቺዎች።
ሰበብ የተባለው የትኛው እንደሆነ ተመልከቱ።
የእንግሊዝ መንግስት፣ ለዩክሬን ጦር ታንኮችን እልካለሁ ለማለት የቀደመው የለም። ነገር ግን፣…
“ነገር ግን” ምን? የእንግሊዝ አገር ስሪት የሆኑ ታንኮችን ለዩክሬን ለመስጠት አይፈልግም። ምን?
“የእንግሊዝ ታንኮች፣ ለአስቸጋሪ መልክዐምድር የሚያገለግሉ እጅግ አዝጋሚ ታንኮች ስለሆኑ፣ ለዩክሬን ጦር ብዙም አይጠቅሙም” ብለዋል - የእንግሊዝ ባለስልጣናት።
የአሜሪካ ባለስልጣናት በበኩላቸው፤ ታንክ ለመላክ ፈቃደኛ መሆናቸውን እየገለፁ፣ “የአሜሪካ ታንኮች ግን እጅግ ግዙፍ ከመሆናቸው የተነሳ የነዳጅ ፍጆታቸው አይቀመስም” በማለት ተናግረዋል። አሜሪካ ሰራሽ ታንኮችን ላለመላክ የቀረበ ሰበብ መሆኑ ነው።
የጀርመን ባለስልጣናት ደግሞ፣ ለዩክሬን ጦር የብረት ቆብ በመርዳት አጋርነታቸውን እንደሚያሳዩና እንደሚያግዙ ነበር የተናገሩት። በዚህም፣ ወዳጅ መንግስታትን አስቆጥተዋል። የብዙዎች መሳለቂያም ሆነዋል። ከትከሻ የሚተኮሱ ጸረ ታንክና ጸረ አውሮፕላን ሮኬቶችን ለመላክ የፈቀዱት፣ የሚወቅሳቸውና የሚያላግጥባቸው እየበዛ ሲመጣ ነው። ታዲያ፣ “ታንክ መስጠት ግን አይሞከርም” ከሚል ማስጠንቀቂያ ጋር የተሰጠ እርዳታ ነው።
በዚህ አቋማቸው ለበርካታ ወራት እየተከራከሩ ዘልቀዋል። በዚሁ ፀንተው መቀጠል ግን አልቻሉም። እንዴት ብለው?
ለዩክሬን ጦር እጅግ የሚስማሙና ለአካባቢው የሚመቹ ታንኮች፣ የጀርመን ታንኮች እንደሆኑ የጦር መሣሪያ አዋቂዎችና ጀነራሎች ከአለም ዙሪያ በየእለቱ ይናገራሉ። እየደጋገሙ ያብራራሉ።
 የጀርመን መንግስት ከየአቅጣጫው በሚጎርፍ የነቀፋ መዓትና ውትወታ እንቅልፍ አጣ። የውሃ ኮዳ የብረት ቆብ እልካለሁ ብሎ መልስ መስጠት አልቻለም።
መቼስ ምን ይደረግ? የወዳጅ መንግስታት ወቀሳና ተግሳፅ በላይ በላዩ እየተደራረበ ሲመጣ፣ ማምለጫያሳጣል። ከበርካታ ሳምንታት ድርድርና ውትወታ በኋላ፣ የጀርመን ባለስልጣናት፣ እሺ አሉ። እሺታቸው ግን በቀጥተኛ መንፈስ በመሉ ልብ አይደለም። በሰበብ የታጀበ ነው።
ታንኮችን ለመላክኮ ፈቃደኛ ነን፤ ነገር ግን አሜሪካና እንግሊዝም በየፊናቸው የራሳቸውን ታንኮች ለዩክሬን መስጠት አለባቸው። የጀርመን ታንኮች ብቻ ከተባለ ግን አይሆንም አሉ።
“አንተስ? አንቺስ? እኔ ላይ ብቻ ነው የምትበረቱት!” ምናምን የሚል ሙግት ሲወራወሩ ሰንብተው ነው ሁሉም የተስማሙት። የጀርመን መንግስት 14 ታንኮችን እሰጣለሁ ብሏል። በሚቀጥለው ወር ወደ ዩክሬን እንደሚደርሱም ገልጿል።
ይህም ብቻ አይደለም። ሌሎች አገራት በመላክ የተሰማሩ እና በመጋዘን የተቀመጡ የጀርመን አገር ስሪት ታንኮችን ለዩክሬን መስጠት ይችላሉ። የጀርመን መንግስት ካልፈቀደ ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው መስጠት አይችሉም ነበር። እንዲያውም “ፈቃድ ስላገኘን እንጂ ለዩክሬን ታንኮችን ለመላክና ለመርዳት እንፈልጋለን” እያሉ የጀርመን መንግስትን ሲተቹና ሲያሳጡ ቆይተዋል።
አሁን ትችትና ሰበብ መደርደር አይችሉም። የእንግሊዝና የአሜሪካ ስሪት ታንኮችንም ለመላክ ተስማምተዋል- ዩክሬንን የሚረዱ መንግስታት።
“የጦር ጄት ግን አይቻልም” የሚለው የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት ውሳኔ ብቻ ነው እስካሁን ያልተቀየረው። እስከመቼ እንደሚቆይ አልታወቀም እንጂ። የዩክሬን መንግስት ደግሞ የጦር አውሮፕላኖችን ስጡኝ እያለ ከመጎትጎት አላረፈም።
ያው፣ አብዛኛው የማጥቃት ዘመቻ ሀ ተብሎ የሚጀምረው፣ በሚሳኤል፣ በአየር ኃይል እና በሩቅ ተጓዥ መድፎች ነው። ከባድ መሳሪያዎችና ትጥቆች፣ አንድም ምሽጎችን ለማፍረስ፣ የመከላከል አቅምን ለማዳከምና ለማስጨነቅ ያገለግላሉ። ሁለትም፣ ከግንባር በስተጀርባ የማዘዣ ማዕከላትን፣ የስንቅና የትጥቅ ማከማቻ ጣቢያዎችን እንዲሁም የማጓጓዣ ተሸከርካሪዎችንና መስመሮችን፣ የመገናኛ አውታሮችን ለመስበር ያገለግላሉ።
በእነዚህ ሁሉ፣ የራሺያ ጦር በሁሉም የትጥቅ ዓይነቶች ከፍተኛ ብልጫ አለው። በወታደሮች ቁጥርም እንዲሁ። አምና ለወረራ ያዘመታቸው ወታደሮች ቁጥር 200 ሺ ገደማ ነበር። ከመስከረም ወዲህ የዚያኑ ያህል አዳዲስ ወታደሮችን አዝምቷል። እንዲያውም 300 ሺ ይደርሳሉ ተብሏል- የአዳዲሶቹ ዘማቾች ቁጥር።
በእርግጥ በርካታ ሺ ወታደሮች ሞተዋል፤ ቆስለዋል። በራሺያ በኩል ብቻ፣ ከ320 ሺ በላይ ወታደሮች መሞታቸውን ከ50 ሺ የሚበልጡም መቁሰላቸው ተዘግቧል። ቢሆንም ግን፣ አሁን ለአዲስ የጥቃት ዘመቻ የተሰለፈው የራሺያ ጦር የአምናው እጥፍ ነው።
በሌላ አነጋገር፣ የዘንድሮው ጦርነት ከአምናውም የበረታና የከፋ ይሆናል።
ሁለቱም በየበኩላቸው፣….የራሺያ ጦር በወታደሮች ቁጥር፣ የዩክሬን ደግሞ በአዳዲስ የጦር መሣሪያዎች የጦርነት ዝግጅታቸው ላይ፣ በእጥፍ “እድገት” አሳይተዋል።
የዚህ ሁሉ አላማ ምንድን ነው? እልቂቱንና ውድመቱን በእጥፍ ለማሳደግ ነው?
አንዳንዴ፣ ለጦርነት የሰበብና የማመከኛ ሰበብ የሚደረድሩ ሰዎች፣..የቋንቋ፣ የዘር፣ የባህል፣ የሃይማኖት ልዩነቶችን እንደ መንስኤ ይጠቅሳሉ። ጭራሽ የጦርነት አላማ የኢኮኖሚ ጥቅም ለማትረፍና የበላይነት ለማግኘት ነው የሚል ምክንያት እስከማቅረብ ይደርሳሉ።
አገራችንን ተመልከቱ። ለእልቂትና ለውድመት በዳረጉን ጦርነቶች ላይ የትኞቹ የአገራችን ተፋላሚዎች  ትርፍ አገኙ? አገራችንና ዜጎቿ፣ ሌላ ሳይሆን፣  ሞትና ሐዘን፣ ውድመትና ድህነት ነው የተረፋቸው።
የጦርነት ክፋቱ፣… ማሸነፍም በኪሳራ መሆኑ ነው። በአፍጋኒስታንና በኢራቅ በተካሄዱ ጦርነቶችስ ማናቸው አተረፉ?
እልቂትንና ውድመትን ነው የተትረፈረፋቸው። የአሜሪካ መንግስት፣ የሽብር ጥቃት የፈጸሙበትን ጠላቶች ለማጥቃት ላይ መዝቱ አንድ ነገር ነው። ተሳክቶለታል ወይ የሚለው ጥያቄም አለ። በኢኮኖሚ በኩል ግን የአንድ ትሪሊዮን ኪሳራ ነው የተረፈው። ጥቃትንና ወረራን ለመከላከል ሌላ አማራጭ ሳያገኝ እየቀረ እንጂ፣ ጦርነት ሁሌም አክሳሪ ነው። መሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ ማሸነፍም እንኳ በኪሳራ ነው።
ጥቃትን ያለ አጸፋ ማለፍ፣ ወረራን በዝምታ መቀበል፣… ለባሰ ጥፋትና ኪሳራ የሚዳርግ መሆኑ ነው ችግሩ።
እናም ወረራንና ጥቃትን በአጭሩ ለመቅጨት፣ እንዲሁም ጥፋትና ኪሳራን ለመቀነስ ሌላ አማራጭ ከጠፋ ብቻ እንደሆነ እንጂ፣ በጦርነት ትርፍ አይገኝም። የሚታፈስ ፍሬ የለውም። የደም መአት እየፈሰሰ ነው መሸነፍና ማሸነፍ። ይኸውና እልቂቱና ውድመቱ እንደገና በዩክሬንና በራሺያ በየእለቱ እየታየ ነው።
የቋንቋና የዘር፣ የባሕልና የሃይማኖት ልዩነት?
አስገራሚው ነገር፣ ራሺያ፣ ከአጋሮቿ ከቻይናና ከሰሜን ኮሪያ፣ ከማሊና ከኢራን ይልቅ ከዩክሬን ጋር በብዙ ነገር ትቀራረባለች። በቋንቋም በትውልድም፣ በባሕልም በሃይማኖትም።
ዩክሬንም፣ እጅግ የምትቀራረበው፣ ከአሜሪካ ወይም ከፈረንሳይ ጋር ወይንም ከሌሎቹ የአውሮፓ አገራት ጋር ሳይሆን ከራሺያ ጋር ነው።
በእርግጥ የዘረኝነት ፖለቲካና የሃይማኖት ፖለቲካ፤… የጭፍን አስተሳሰብ አጥፊ መንገዶች ናቸውና፤ ወሰንና ልክ የላቸውም።
የዘረኝነት አስተሳሰብ ያልመረዛቸው ሰዎች፣ በትውልድ ሃረግና በቋንቋ ልዩነት ሰበብ አይጨፋጨፉም።
በዘረኝነት አስተሳሰብ የተበከሉ ከሆኑ ደግሞ፣ የቱንም ያህል ቢቀራረቡና ቢመሳሰሉ እንኳ፣ ለመጨፋጨፍ ሰበብ አያጡም።
ጥቁር እና ነጭ፣ የእገሌ ብሔርና የእከሌ ብሔረሰብ ተብሎ የሚናፈስ የዘረኝነት አስተሳሰብ፣… ብዙም ሳይቆይ ወደ መንደር ወደ ሰፈር ወርዳል። በዚህ ሰፈርና በአጎራቻቹ መንደር የተቧደኑ ሁለት የዱርዬ ቡድችን ያገዳድላል። የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካም፣ በጎሳና በወረዳ እየተቧደኑ የሚጨፋጨፉ ቡድኖችን ይወልዳል።
የራሺያና ዩክሬን ጦርነትም፣ በሃይማኖት ወይም በቋንቋ ልዩነት የሚሳበብ ከሆነ፣… በጣም ስለሚለያዩና ስለሚራራቁ ሳይሆን፣ የጭፍንነት አስተሳሰብ ጥፋት ወሰንና ድንበር ስለሌለው፣ ሰፊ ልዩነትን ብቻ እንጂ ጠባብ ልዩነትን አትመልከት ተብሎ ስለማይታጠር ነው።




Read 1143 times