Saturday, 25 February 2023 13:40

ቅድመ እርግዝና የህክምና አገልግሎት

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

   “ጽንስ የተስተካከለ አፈጣጠር እንዲኖረው ቅድመ እርግዝና የህክምና አገልግሎት ጠቃሚ ነው” - ዶ/ር ተስፋዬ ሁሬሳ
እርግዝና ከተፈጠረ በኋላ ጥንዶች የቅድመ ወሊድ ክትትል ለማድረግ ወደ ህክምና ተቋም እንደሚሄዱ ይታወቃል። ነገር ግን ፅንስ ከመፈጠሩ አስቀድሞ ጥንዶች የህክምና ባለሙያ ቢያማክሩ እና የህክምና አገልግሎት ቢያገኙ ይመከራል። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ሁሬሳ እንደተናገሩት ቅድመ እርግዝና የህክምና አገልግሎት በኢትዮጵያ አልተለመደም። ጥንዶች ከእርግዝና ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጽንስ ከመፈጠሩ አስቀድሞ ወደ ህክምና ተቋም የሚያመሩት ልጅ ያለመውለድ ችግር ሲያጋጥም ነው። “በሀገራችን ቅድመ እርግዝና የህክምና ክትትል ማድረግ በሀሳብ ደረጃ አዲስ ነው” ብለዋል የህክምና ባለሙያው። ነገር ግን ሁሉም ጥንዶች እርግዝና እንዲፈጠር ሲያስቡ ወይም ሲያቅዱ የህክምና ባለሙያ ማማከር በሌሎች ሀገራት የተለመደ ነው። ይህም ፅንሱ ወይም ጥንዶቹ ላይ ችግር ካጋጠመ በኋላ ወደ ህክምና ተቋም ከመሄድ ይልቅ አስቀድሞ ችግሩ እንዳይፈጠር ያደርጋል። ዶ/ር ተስፋዬ ሁሬሳ “ጥንዶች ለማርገዝ (ፅንስ እንዲፈጠር) ሲያስቡ የህክምና አገልግሎት ማግኘት አስፈላጊ ነው” በማለት ተናግረዋል።
በቅድመ እርግዝና የሚሰጥ የህክምና አገልግሎት፤
የማማከር አገልግሎት; እርግዝና ስለሚፈጠርበት ወቅት(ቀናት)፣ በሽታ ካለ ስለሚኖረው ተፅዕኖ፣ አመጋገብ ምን መሆን እንዳለበት ምክር ይሰጣል። እንዲሁም በግብረ ስጋ ግንኙነት ላይ ችግር ካለ የማማከር አገልግሎት ይሰጣል።
ምርመራ; የድም ግፊት፣ ስኳር እና የመሳሰሉት በሽታዎች መኖር ወይም አለመኖሩ በምርመራ ይረጋገጣል።
እናቶች ፎሊክ አሲድ (ንጥረ ነገር) እንዲወስዱ ይደረጋል።
ጥንዶች ማድረግ ያለባቸው ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡፡
የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፤
የተመጣጠነ ክብደት እንዲኖር ማድረግ; ከመጠን በላይ ውፍረት እና አነስተኛ ክብደት ለእርግዝና አይመከርም ፡፡
ሲጋራ ማጨስ ማቆም፤
የአልኮል መጠጥ ማቆም፤
ማንኛውም መድሀኒት አለመውሰድ (አስገዳጅ ከሆነ የህክምና ባለሙያ ማማከር)
መደረግ ያለባቸው እና የሌለባቸው ጉዳዮች ለሁለቱም (ለባል እና ሚስት) የሚያገልግሉ ናቸው።
የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት ቅድመ እርግዝና የህክምና አገልግሎት ጥንዶች (ባል እና ሚስት) በጋራ ማግኘት አለባቸው። ይህም እርግዝናውን ውጤታማ ለማድረግ ይረዳል። ስለሆነም እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ እናት[ሚስት] ብቻ ሳትሆን አባት[ባል] ጥንቃቄ እንዲያደርግ ይመከራል።
ለጥንዶች የሚሰጠውን ቅድመ እርግዝና የህክምና አገልግሎት በማግኘት ወ/ሮ ታሪክ ከፍያለው ተጠቃሽ ናት። ነዋሪነቷን  በአዲስ አበባ ያደረገችው ወ/ሮ ታሪክ ይህን አገልግሎት ያገነችው ከባለቤቷ ጋር በጋራ በመሆን ነው። የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን የባለቤቷ አነሳሽነት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።
“ባለቤቴ ከእኔ በተሻለ ለህክምና ሙያ ስለሚቀርብ ለልጆቻቻን ተገቢውን ጥንቃቄ እንድናደርግ አድርጓል” ብላለች የ2 ልጆች እናት የሆነችው ወ/ሮ ታሪክ ከፍያለው።››
የ6 ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ገነት አበበ በበኩላቸው
‹‹ልጅ ከተጸነሰ በኋላ ለክትትል ወይም ለመውለድ አሊያም ለማርገዝ ችግር ሲያጋጥም እንጂ አስቀድሞ ህክምና ሰምቼ አላውቅም”›› ብለዋል።
ወ/ሮ ገነት በ1970ዎቹ እና 1980ዎቹ የቅድመ ወሊድ ክትትል ለማድረግ እንዲሁም ለወሊድ ወደ በህክምና ተቋም በሚሄዱበት ወቅት ስለ ቅደመ እርግዝና የህክምና አገልግሎት ሰምተው አያውቁም። በተመሳሳይ  በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም አይነት የምክር አገልግሎት ያልነበረ እና ስለ ቤተሰብ ምጣኔ ላይ ትኩረት ይደረግ ነበር እንደ ወ/ሮ ገነት ንግግር ። እኒህ አዛውንት 6 ልጆችን እና 3 የልጅ ልጆችን አፍርተዋል። ስለሆነም በአሁኑ ወቅት ወላጆች ለልጆቻቸው የተሻለ እንክብካቤ እና ትኩረት እንደሚሰጡ በልጅ ልጆቻቸው ማስተዋላቸውን ተናግረዋል።
“እናቶቻችን እና አባቶቻችን ከእርግዝና በፊት የህክምና አገልግሎት ሳያገኙ እዚህ ደርሰናል። ስለዚህ አስፈላጊ ነው ብዬ አላስብም”
በማለት የተናገረው ቃለመጠይቅ ካደረግንላቸው ሰዎች መካከል የሆነው ወጣት ዮሴፍ ቃለአብ ነው። አክሎም ዮሴፍ
“ከዘመናዊነት አንጻር ምናልባት ሊያስፈልግ ይችላል” ብሏል።
በተመሳስይ  ሊበን ጌታቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመጣ የህክምና አገልግሎት ነው ብሎ እንደሚያስብ ተናግሯል። በመቀጠልም
“ቅድመ እርግዝና የህክምና አገልግሎት በሌሎች ሀገራት መሰጠቱን በተወሰነ መልኩ አውቃለው። ለእኛም ያስፈልገናል” ብሏል።
 በተጨማሪም ሊበን እንደተናገረው ይህ ጉዳይ አስፈላጊ እና ጠቃሚ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እና ሁሉም ሰው ሊያውቀው ይገባል።          
ቅድመ እርግዝና የህክምና አገልግሎት ያለው ጥቅም
ፅንስ እንዲፈጠር ያደርጋል(ያግዛል)
ፅንስ[የተጸነሰው ልጅ] የሚያገኘው ጥቅም; የተስተካከለ አፈጣጠር እንዲኖር ያደርጋል፤ እናት ፎሊክ አሲድ እንድትወስድ ስለሚደረግ የፅንስ የነርቭ አካል በተገቢው መንገድ ይሰራል፤ እናት የምትወስደው ፅንስን ሊጎዳ የሚችል መድሀኒት ካለ ቅድመ እርግዝና ክትትል ሲደረግ መድሀኒት ስለሚቀየር ጽንሱን ከጉዳት ይታደጋል።
እናት የምታገኘው ጥቅም; ከእርግዝና በፊት የነበረ እና በእርግዝና ምክንያት የሚባባስ በሽታ ካለ ህክምና እንድታገኝ ይደረጋል፤ ከዚህ ቀደም መኖሩ ያልታወቀ በሽታ ለቅድመ እርግዝና በሚደረግ ምርመራ ሊገኝ[ሊታወቅ] ይችላል።
አባት የሚያገኘው ጥቅም; ከዚህ ቀደም መኖሩ ያልታወቀ በሽታ ለቅድመ እርግዝና በሚደረግ ምርመራ ሊገኝ[ሊታወቅ] ይችላል።
ቅድመ እርግዝና የህክምና አገልግሎት አለማግኘት ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት
የፅንስ የሰውነት አካላት የሚፈጠሩት ከ2 ወር በታች ባለው የእርግዝና ወቅት በመሆኑ እናት መፀነሷን ባለማወቅ ማድረግ የሌለባትን ነገሮች ስታደርግ ጽንስ ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል።
እናት ላይ የልብ ድካም፣ ስኳር፣ የሚጥል እና ሌሎችም በሽታዎች ካሉ ማርገዟ ሳይታወቅ በእርግዝና ወቅት መባባስ ሊኖር ይችላል። እንዲሁም ለእነዚህ በሽታዎች የሚወሰዱ መድሀኒቶች ፅንሱን ሊጎዱ ይችላሉ።
እርግዝና ሳይፈጠር አስቀድሞ ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ አካላዊ፣ ስነአእምሯዊ እና ስነልቦናዊ ጤንነትን የተስተካከለ እንዲያደርጉ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ሁሬሳ ለጥንዶች መልእክት እና ጥሪ አስተላልፈዋል።


Read 1273 times