Saturday, 25 February 2023 13:56

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

      የአውቶብሶች ግዢው በገለልተኛ ኦዲተር ይጣራ!!
                              ሙሼ ሰሙ

          የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግዢ የፈጸመባቸው አውቶብሶች ዋጋ እጅግ አወዛጋቢ ከመሆኑ የተነሳ አስተያየት ለመስጠት እንኳን የተጸየፍኩት አጀንዳ ነበር። የአውቶብሶቹ ዋጋ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ የከተማውን ነዋሪ ያስደነገጠ፣ ግራ ያጋባና ዘረፋ ለይቶለት ነፍስ ዘርቶ ስጋ ነስቶ በቅ ብሏል ያሰኘ አነጋጋሪ ክስተት ሆኖ ሰንብቷል።
የአውቶቡስ ግዢውን በሚመለከት ከተለያየ ገለልተኛ አካላት በሚቀርብላቸው መረጃ መሰረት፣ የከተማችን ነዋሪዎች በከፍተኛ ደረጃ የመዘረፍና የመነጠቅ ስሜት አድሮባቸዋል። ተመዝብሯል የሚባለው የአውቶብሱ ግዢ የተፈጸመው ላባቸውን አንጠፍጥፈውና ከልጆቻቸው ጉሮሮ ነጥቀው ለጋራ ልማት ከሚገብሩት ግብር ላይ ተዘግኖ ስለሆነ ቁጭታቸው ፍትሐዊና ጥያቄያቸውም  ከገለልተኛ አካል መልስ የሚሻ ጉዳይ ነው።
የከተማዋ አስተዳደርም መረጠኝ ለሚለው ነዋሪ ታማኝነቱ የሚረጋገጠው ከቀረበለት ጥያቄ እራሱን ከመጋረጃ በስተጀርባ ደብቆ ወፈ ሰማይ ካድሬ በማሰማራት፣ ሀቁን በርብርብ በማድበስበስና ሕዝብን ለማሸማቀቅ በመሞከር ሊሆን አይገባም።
ጥያቄው ከሕዝብ የመነጨ የሕዝብ ጥያቄ ነው። ገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ የጨረታ ሂደቱ፣ አሸናፊው የተመረጠበት መስፈርት፣ ተገኘ የተባለው የውጭ ምንዛሪ ምንጭ፣ የአውቶብሶቹ ዋጋና የጨረታ ኮሚቴው ገለልተኝነት ወዘተ ኦዲት ሊደረግ ይገባል። ሂደቱ ኦዲት ተደርጎና ሀቁ ተጣርቶ ውጤቱ በግልጽ ለሕዝብ መቅረብ አለበት።
ይህ ሳይሆን ቀርቶ መርጦናል የምትሉት ሕዝብ ላቀረበው ፍትሐዊ ጥያቄ፣ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለትና በካድሬ ትርክት ጥያቄውን ለማድበስበስ መሞከር፣ ጥርጣሬውን በሐቅ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ከማረጋገጥና ብሶትና ጥላቻውን ከማባባስ ውጭ የሚያመጣው ፋይዳ የለም፡፡
ይህ ደግሞ ለዘመናት የለመድነው “የምን ታመጣላችሁ” ማን አለብኝነት ስለሆነ፣ ጊዜ ይፍጅ እንጂ ትናንት በሌላው ላይ የጠቆመ ጣታችሁ ተራውን በራሳችሁ ላይ ጠቁሞ፣ በሙስና እንደሚፋረዳችሁና ታሪክ እራሱን እንደሚደግም ጥርጥር የለኝም ?!
በመሰረታዊነት የሚነሱና ሕዝብን ለበቂና አስተማማኝ ጥርጣሬ ከሚዳርጉ መነሻዎች በጥቂቱ ፡-
-ቻይና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ባላት ኢኮኖሚያው ትብብርና (Bilateral ) የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት መሰረት፣ ቀጥታ ከአምራቹ ጋር ተደራድሮ አውቶብሶቹን መግዛት እየተቻለ ከሁለተኛ አቅራቢ መገዛቱ?
- መንግስት ማቅረብ ያልቻለውን ከ70 ሚሊየን በላይ (በብሔራዊ የምንዛሪ ተመን መሰረት) የሆነ ዶላር የጨረታ አሸናፊው ማቅረባቸው፣ እንደ ብቸኛ አቅራቢ መወሰዳቸውና የዶላሩ ምንጭ አለመጠቀሱ ?
- ከ3.8 ቢሊየን ብር ወይም ከ70 ሚሊየን ዶላር በላይ ለወጣበት የ200 አውቶቡሶች  ግዥ ዓለም ዓቀፍ ጨረታ አለመውጣቱ፣ ወጥቶም ከሆነ ውጤቱ አለመገለጹ ?
- የተጠቀሱት ዓይነት የከተማ አውቶብሶች፣ አንድ አውቶብስ ብቻ ለመግዛት ለሁለት የቻይና አምራች( Higer, dongfeng,) ላቀረብኩላቸው ጥያቄ የተሰጠኝ ዋጋ ከ 80 ሺህ እስከ 130 ሺህ ዶላር (ልዩነቱ በሚገጠምላቸው አክሰሰሪና አውቶማቲክና ማንዋል ይመሰረታል)  የሚደርስ ሲሆን መስተዳድሩ ግን የአውቶብሶቹ ብዛት 200 ስለሆነ የመደራደርና ዋጋ የማስቀነስ አቅም እያለው፣ ገዛኋቸው የሚለው ከ350,000 ዶላር በላይ ወይም ከ3 እጥፍ በላይ መሆኑ ? ወዘተ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።

____________________________________________


                   የማኅጸን ውስጥ ሸንጎ
                      ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ


         መንትያ ሕጻናት በእናታቸው ማኅጸን ውስጥ ተጸንሰው እየኖሩ ነው፡፡ አንደኛው ሕጻን ሌላኛውን ጠየቀው፤
‹‹ከማኅጸን ከወጣን በኋላ ሕይወት አለ ብለህ ታምናለህ?››
ሌላኛው መለሰ ፡-
‹‹እንዴታ! ከማኅጸን ከወጣን በኋላማ የሆነ ሕይወት ሳይኖር አይቀርም፡፡ ምናልባት አሁን ማኅጸን ውስጥ የምንቆየው ለዛኛው ሕይወት ራሳችንን እያዘጋጀን ሊሆን ይችላል፡፡›› አለው፡፡
‹‹የማይመስል ነገር!!›› አለ የመጀመሪያው ሕጻን፤ ‹‹ከማኅጸን ከወጣን በኋላ ሕይወት የሚባል ነገር የለም! እስቲ አስበው ከማኅጸን ውጪ የሚኖረው ምን ዓይነት ሕይወት ነው?›› አለ እየሳቀ፡፡
 ሁለተኛው መለሰለት፤
‹‹እኔም አላውቀውም ግን እዚህ ካለው የተሻለ ብርሃን እዚያ ያለ ይመስለኛል፡፡ ምናልባት በዚያኛው ሕይወት በእግራችን ለመሔድ፣ በአፋችን ለመጉረስ የምንችል ይመስለኛል። ምናልባት አሁን ልንረዳቸው የማንችላቸው ሌሎች ስሜቶችም ሊኖሩን ይችሉ ይሆናል››
የመጀመሪያው ሕጻን በብስጭት ቀጠለ፤
‹‹ይኼ ቅዠት ነው፡፡ በእግር መሔድ የማይቻል ነገር ነው፡፡ ጭራሽ በአፍ መጉረስ? የማይሆን ነገር ታወራለህ እንዴ?! የምንበላውንና የሚያስፈልገንን ነገር የምናገኘው በእትብታችን በኩል ነው፡፡ እትብታችን ደግሞ በጣም አጭር ነው፡፡ ከማኅጸን ከወጡ በኋላ ሕይወት አለ የሚለው ነገር አሳማኝ አይደለም››
ሁለተኛው ሕጻን ግን ውትወታውን ቀጠለ፤
‹‹እኔ ግን የሆነ ነገር የሚኖር ይመስለኛል፡፡ ምናልባት ማኅጸን ውስጥ ካለው ነገር የተለየ ነገር የሚኖር ይመስለኛል፡፡ ምናልባትም እትብትም ላያስፈልገን ይችል ይሆናል፡፡››
የመጀመሪያው ሕጻን ግን አልተረታም፤
‹‹አይዋጥልኝም! እሺ የምትለውን ልቀበልህና እንዳልከው ከማኅጸን ውጪ ሕይወት ካለ እዚያ ደርሶ የተመለሰ ሰው ለምን አናገኝም? ከማኅጸን መውጣት የሕይወት መጨረሻ ነው፡፡ ከማኅጸን ከወጣን በኋላ በጨለማ ውስጥ በዝምታ ከመጣል በስተቀር ምንም ነገር የለም፡፡ ወዴትም አንሔድም!››
‹‹በእርግጥ ምንም አላውቅም›› ቀጠለ ሁለተኛው ሕጻን፤ ‹‹ነገር ግን ከማኅጸን ከወጣን በኋላ እናታችንን እናገኛለን፡፡ እስዋ ትንከባከበናለች››
‹‹እናት? በእናት መኖር ከልብህ ታምናለህ ማለት ነው? በጣም የሚያስቅ ነገር ነው!!! እሺ እናት ካለች አሁን የት ነው ያለችው?‘’
ሁለተኛው ቀበል አድርጎ፤
‹‹እናታችንማ በዙሪያችን አለች፡፡ በእርስዋ ተከብበን ነው ያለነው፡፡ የተገኘነው ከእርስዋ ነው፡፡ የምንኖረውም በእርስዋ ውስጥ ነው፡፡ ያለ እርስዋ ያለንበት የማኅጸን ውስጥ ዓለም ሊኖር አይችልም›› አለው፡፡
‹‹አላየኋትማ! የት አለች? ስለዚህ አለች የሚለው ነገር አሳማኝ አይደለም!›› አለ የመጀመሪያው ሕጻን
ሁለተኛው ሕጻን ግን ይህን አለ፤
‹‹በማኅጸን ውስጥ ስትኖር አንዳንድ ጊዜ በዝምታ ውስጥ ሆነህ በጥሞና የምታዳምጥ ከሆነ የእናትህን መኖር ትገነዘባለህ ፤ በፍቅር የተሞላ ድምጽዋን ከላይ ሆኖ ሲጠራህ ትሰማዋለህ›› ብሎ ክርክሩን ቋጨው፡፡
 ይህች ዓለም እንደ ማኅጸን ናት ፤ የዚህ ዓለም ኑሮ ለወዲያኛው ኑሮ የምንዘጋጅበት አጭር ጊዜ ነው፡፡ ብዙዎች ለማመን ቢቸገሩም ከሞት በኋላ ዘላለማዊ ሕይወት አለ ፤ በጥሞና በተመስጦ ከፈለግነው የዓለም መጋቢና ሠራዒ አምላክ  የፈጠረህም አለ፡፡ የምንሞትበት ቀን ከጠባቡ ወደ ሰፊው የምንሔድበት፣ ለዘላለም ሕይወት የምንወለድበት የልደታችን ቀን ነው፡፡

_____________________________________________


                   ከ10 በላይ ሴቶች በጋብቻ ቀኑ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡበት ቻይናዊ ሙሽራ
                       ዳጉ ጆርናል


        በቻይና ዩ አን ግዛት ሄንግዲ መንደር ከ10 በላይ ሴቶች፤ “ቼን ሶንግ የእኛም ፍቅረኛ ነበረ” በማለት “እኛ የቼን ሶንግ የቀድሞ ፍቅረኞች  ነን፤ ዛሬ ይህ ጋብቻ መበላሸት አለበት” የሚል ትልቅ ቀይ ባነር ይዘው ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተዋል። መጀመሪያ ላይ በርካቶች ያልተለመደው ትዕይንት ቀልድ መስሏቸው የነበረ ቢሆንም፣ ሴቶቹ በእርግጥ የቼን የቀድሞ ፍቅረኞች መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።
ሴቶቹ ከቼን የሰርግ ቦታ በፀጥታ መንገድ ላይ ቆመው ቀይ ባነር ይዘው ታይተዋል።በሰርጉ እለት እንዲህ ዓይነት ክስተት የገጠመው ቼን ሶንግ፤ “በጣም አሳፍሮኛል፤ ባለቤቴና ቤተሰቧ ተበሳጭተውብኛል” ሲል ተናግሯል። ሙሽራው ከዚህ ቀደም በአንዳንድ የቀድሞ ፍቅረኛዎቹ ላይ መጥፎ ባህሪ እንደነበረው አልሸሸገም፣ ነገር ግን እድሜዬ እየጨመረ ሲመጣ አካሄዴን ለውጫለሁ ሲል ገልጿል። ያም ሆኖ  ግን ሚስቱና አማቶቹ ስለ አስገራሚው የሰርግ ትዕይንት አጥጋቢ ማብራሪያ እስኪያገኙ ድረስ እንደማያናግሩት አስታውቀዋል፡፡
“በወጣትነቴ ያልበሰልኩ ነበርኩ እናም ብዙ ልጃገረዶችን እጎዳ ነበር” ሲል ቼን ተናግሯል፡፡ ከዚህ በፊት ባደረገው ነገር  ማዘኑን በመግለጽም፤ ሌሎች ወንዶች ሴቶችን በአክብሮት እንዲይዙ መክሯል። “ለሴት ጓደኛህ እሷን ከማታለል ይልቅ ታማኝ መሆን አለብህ” ሲል ቼን ከተሞክሮው አጋርቷል።

__________________________________________


                   አሮጌ መኪናውን እየነዳ ቱርካዊያንን ለመርዳት የተጋው አዘርባጃናዊ፣ ቅንጡ መኪና ተሸለመ        በርእደ መሬት የተጎዱ ቱርካዊያንን ለመርዳት የመጣው የአዛርባጂያን ዜጋ ቅንጡ መኪና ይዞ ተመለሰ።
በቱርክ ከሁለት ሳምንት በፊት በታሪክ ከፍተኛ የተባለ ርዕደ መሬት አደጋ መከሰቱ ይታወሳል። ይህ አደጋ በደቡባዊ ቱርክና ሰሜናዊ ሶሪያ የተከሰተ ቢሆንም፣ አደጋው በአንጻራዊነት ቱርክን የበለጠ ጎድቷል።
በዚህ አደጋ ምክንያትም የሟቾች ቁጥር ከ50 ሺህ ያለፈ ሲሆን፤ ተጎጂዎችን ለመታደግ ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለም ሀገራት ተረባርበዋል።
ይሁንና የቱርክ ጎረቤት ከሆነችው አዛርባጂያን መዲና ባኩ ከተማ፣ በራሱ አሮጌ መኪና እርዳታዎችን ይዞ ወደ ቱርክ የመጣው ግለሰብ የብዙዎችን ልብ ነክቷል።
ግለሰቡ ድሀ የሚባል ቢሆንም ከቤተሰቡና ከጓደኞቹ ያሰባሰባቸውን አልባሳትና ምግብ በመያዝ መምጣቱ ቱርካዊያንን አስገርሟል።
በዚህ ደግ አዛርባጂያን ድርጊት ልባቸው የተነካው አንድ የቱርክ  ባለሀብት፣ አዲስ ቅንጡ መኪና ሸልመውታል ሲል አናዶሉ ዘግቧል።
ግለሰቡ የ1980ዎቹ ስሪት የሆነች አሮጌ መኪናውን እያሽከረከረ የርእደ መሬት አደጋ ወደ ደረሰባቸው አካባቢዎች መምጣቱና የያዛቸውን ቁሳቁሶች ለተጎጂዎች መስጠቱ ታውቋል፡፡   
ግለሰቡ የፈጸመውን በጎ ተግባር  ሚዲያዎች ማስተጋባታቸውን ተከትሎ ታዲያ፣ ዝናው ከቱርክ አልፎ ዓለምን አዳርሷል ተብሏል።
(አል ዐይን)

Read 597 times