Saturday, 04 March 2023 11:42

ፍካሬና ናትናኤል ግርማቸው

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(2 votes)

    ‹‹አውቃለሁ ነክቼ፣ የርግብ ላባ ስሱን፣
                          ግን እንዳንቺ ገላ፣ እንጃ መለስለሱን፤››
                      
         መነሻ፡-
ግጥምን በሁለት ጎራ መድበን ብንመለከት መልካም ነው፤ ውበት-ዘመም እና ሀሳብ-ዘመም ብለን፤ በመጀመሪያው ጎራ የሚመደቡ ገጣሚያን የውበት ልክፍተኞች ናቸው፤ በግጥሞቻቸው ተፈጥራዊ ውበትን፡- ጸዳልን፣ ብርሃንን፣ ፍቅርን፣ ጽጌያትን፣ ጨረቃን፣ ፀሐይንና መልካም መዓዛን ማጣቀስ ያዘወትራሉ፤ ይኼንን ሲያደርጉ ታዲያ በሌጣ ዘገባ ሳይሆን ከሚስሉት ገጸ-ባሕርይ/ከባለድምጽ ልምድ፣ ተሞክሮ፣ አሁናዊ ሁናቴና ሥሜት ጋር እየመሰሉ በማቅረብ ነው። የቃላትንና የሐረጋትን ፈሊጣዊ ፍቺ ከእውኑ ዓለም እውነትና ከባለድምጹ ልምድ ጋር በማዛመድ ይፈክራሉ፤ ነገር ግን ‹ውበት ተኮር› ናቸው ማለት የግጥም ሀሳባቸው ለሚዛን የቀለለ ነው ማለት እንዳልሆነ መዝግቡልኝ፤ የግጥም ሀሳባቸውን በሥነ-ውበት መፈከር ላይ ትኩረት ይሰጣሉ፤ እናም ሀሳባቸው ሥነ-ውበት ታክሎት ይገዝፋል እንደማለት ነው፡፡
ሀሳብ-ዘመሞቹ ደግሞ ሀሳብ ላይ ያተኩራሉ፤ የግጥም ሀሳባቸው ግልጥልጥ ሊል፣ ወይም ፍዝና ግልብ ሊሆን ይችላል፤ መምከርና መዝከር ጠባያቸው ሊሆንም ይችላል፤ ሆኖም በውበት ተኮሮቹ በኩል ሀሳብ አለ፣ በሀሳብ ተኮሮቹም በኩል ውበት አለ፡፡
በአሁን ወቅት ብቅ ካሉ የዘፈን ግጥም ደራሲዎች መካከል ስለ ናትናኤል ግርማቸው ገ/ሥላሴ ጥቂት ልበል። ናትናኤል ግርማቸው የሥነ-ውበት ልክፍተኛ እንደሆነ ከምሰላውና ከቃላት አጣጣሉ ያስታውቃል፤ ግጥሞቹ በሥነ-ውበት የበለጸጉ ናቸው፤ በተምሳሌታዊ ቋንቋ ተራዳኢነት ሀሳብ ይመረምራል፤ ሀሳብ አይዘግብም/አይናገርም። ፍካሬ፣ ወይም መፈከር ማለት ሕይወትን በሥነ-ውበት መተርጎም ማለት ነው…
ገጣሚና መምህር ዮሐንስ አድማሱ፡-
‹‹ከሰው መርጠው ለሹመት፤
ከእንጨት መርጠው ለታቦታ፤
ከቃል መርጠው ለኪነት፤››
…እንዳለው ናትናኤል ግርማቸው ቃላት ላይ ይራቀቃል፤ ባማረ ምሰላ እውነታን አዟዙሮ ይፈክራል/ይተረጉማል፤ ለምሳሌ፡- ፈሊጣዊ-ንግግርን፣ ሥነ-ቃልን፣ አፈ-ታሪክን፣ ተረት-ተረትን፣ የፍልስፍና ኅልዮቶችንና ጨዋታን እንደ ግብዐት ተጠቅሞ ወደተነሳበት ሀሳብ በመሰግሰግ ይመስላል፤ የዚህ ፋይዳ ሕይወትን፣ እውነትንና ልምድን በሥነ-ውበት መፈከር ነው፤ ለዚህ ነጥብ ሁነኛ ማስረጃ የሚሆነኝ፣ ግጥሙ በናትናኤል ግርማቸው ተደርሶ በዳዊት ጽጌ የተቀነቀነው ‹‹እትቱ›› የተሰኘ ዘፈን ነው፤ ዜማው የአበበ ብርሃኔ ሲሆን፤ አሬንጅመንቱ ደግሞ የአበጋዝ ክብረወርቅ ሺዎታ ነው፡፡ የሚከተሉ ስንኞችን መዝዘን እንመልከት፡-
‹‹በቀን መብራት ይዤ፣ ተቆጠርኩ እንደጅል፣
እኔስ ባንቺ ጉዳይ፣ ብልጠትን አልከጅል፤››
እያለ የገጸ-ባሕርይውን / የባለድምጹን አሁናዊ ሁናቴ ከዲዮጋን የፍልስፍና እሳቤ ጋር በመመሰል ተሰናኝቷል፤ ሀሳብ ይዞ ግብዐት መፈለግ ነው ምሰላ፤ በዚህ ድርሰት ፍልስፍናን እንደ ግብዐት እንጂ እንደ መነሻ ሳይጠቀም ቃላት ላይ እንደ ልቡ እየተራቀቀ የተነሳበትን ጭብጥ ውብ አድርጎ ገልጿል። የፍልስፍናው ፋይዳ ተምሳሌት ሲሆን፣ እንደ መቃንም/framework ሊያገለግል ችሏል ብዬ አምናለሁ፤ በእነዚህ ስንኞች ሊነግረን የተለመው በፍለጋ የባዘነን ሰው ታሪክ ነው፤ ‹በከንቱ መድከሙን› ለሚነግሩት ሁሉ ጆሮ ይነሳቸዋል፤ ይልቅ ከከንቱነቱ የሚያመልጠው ሲያገኛት እንደሆነ እሙን ነው (ቆነጃጅት አይገዱትም፤ የልቡ መሻት እሷ ናትና)። የፍለጋውን ጽናት ብቻ አይደሰኩርም፤ ማሕበረሰባዊ ሕጸጻችንንም ገሃድ ያሰጣዋል እንጂ፤ እዚህ ስንኝ ውስጥ ነፍሰ-ቀጭን ማሕበረሰብ ሰርክ ሲንከላወስ ማጤን ይቻላል፤ ‹በአንዲት የመንደር ውርጋጥ ተይዞ ነኾላ› ባይ ማሕበረሰብ፡፡ ታዲያ ናትናኤል ይህቺን መሳይ ዳፍንት ‹በጀ› ማለት አልፈቀደምና በእጃዙር ይናደፋል፤ ይኼ አመክንዮ ‹አንድ ይበልጣል ከምንትስ›ን ይወዳጃል። ዘለፋቸው ጉዳዩ አልነበረም፤ ከተዐምራቱ መስዋዕትነቱ እንዲልቅ፣ ከንቱ መባሉ አይጎረብጠውም፤ በጽናት ይፈልጋታል እንጂ! ሌሎች ስንኞችን ጨምረን እንመልከት….
‹‹ወንዙ ዳር አትጥሪኝ፣ መልክሽ ይታየኛል፣    
አንቺን አሳስቆ፣ እኔን ይወስደኛል፤››
በማለት እያሳሳቀ ስለሚወስድ ፍቅር ይነግረናል፤ በፈሊጣዊ ንግግር ‹‹ውኃ እያሳሳቀ ይወስዳል›› ሲባል እንጂ ‹‹እያሳሳቀ የሚወስድ ፍቅር›› ሰምቼ አላውቅም፤ በውል የምናውቀውን ፈሊጣዊ-አባባል ዐውዱን ባማከለ መልኩ አዟዙሮ ተጠቅሟል፤ ድንቅ ትልምና ሙከራ ነው! የገጣሚ መብቱን (poetic license) በመገልገል ቃላት ላይ እየተራቀቀና ባልተለመደ መልኩ እየመሰለ የሕይወትንና የዓለምን ፍካሬያዊ መልክ በሚገባ ለማሳየት ችሏል። ይበል ያሰኛል! ይኼ የሚያመለክተው ናትናኤል የሥነ-ግጥምንና የሥነ-ውበትን ዝምድና ተንትኖ ከተረዳ በኋላ በሥራዎቹ ማሳየት መቻሉን ነው፤ ብሎም በዚህ ዘፈን ባለድምጹ የናፈቃትን ሴትና ናፍቆትዋን ተፈጥሯዊ በሆኑ መገለጫዎችና በውበት ሲመስል እናያለን፤ አንዳንድ መገለጫዎቿን እየመደበና እየመሰለ፡- በውኃ፣ በአየር ጸባይ፣ በፏፏቴ፣ በንጋት…ወዘተ.።
‹‹እትቱ››ን ደጋግሜ ሰማሁ። ወዲያው አዕምሮዬን አንድ ነገር ጎበኘኝ፤ በአንድ ወቅት ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ) ገጠር ቆይቶ ደሴ ይከተትና ለውኃ ልኩ ውኃ ይቀማምሳል አሉ፤ ከዚያ ቴፑ የአረጋኸኝ ወራሽን ‹‹እስቲ ዘለል›› ማንቆርቆር ገባ፤ አያ ሙሌ ታዲያ ሰማና ወበራ፤ ብርክ ሆነ፤ በጊዜው እጁ አጭር ስለነበር ምን ልስጠው ብላ ነፍሱ ተጨነቀች፤ በኋላ ‹‹አምላኬ ሆይ ከእድሜዬ ላይ ሁለቱን ቀንሰህ ለአረጋኸኝ ወራሽ ስጥልኝ›› አለ አሉ፤ ‹‹እትቱ››ን ሳደምጥ እኔም እንዲያ ነበር ያልኩት!
ተጨማሪ ማባያ እንካችሁ፤ ‹‹ሼሙና›› በተሰኘ የሔዋን ገ/ወልድ ዘፈን ውስጥ ናትናኤል ግርማቸው ጨዋታን እና ሥነ-ቃልን እየመሰለ የፈከረበትን ስንኞች መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ግጥም፡- ናትናኤል ግርማቸው፤ ዜማ፡- ሔዋን ገ/ወልድ፤ ቅንብር፡- ዲጄ ሚላ ነው፤ እንሆኝ፡-
በመጀመሪያ፣ የልጅነት ጊዜ ጨዋታን በዘፈን ግጥም ውስጥ እየፈከረ በማስረግ የልጅነት ፍቅርዋ ያልወጣላትን ልክፍተኛ ያስተዋውቀናል፤ ጸሐፊው እንዲህ ይላል፡-    
‹‹ብስኩት አደባባይ፣ ሁለት ዛፎች አሉ፣
እነሱን የነካ፣ ልብ ይሰውራሉ፤››
ከላይ በተጠቀሱ ስንኞች ገላ፣ በልጅነት ልብዋ የመዘገበችው ፍቅር ዛሬ ድረስ ዘልቆ የሚያንቀጨቅጫትንና የሚያክለፈልፋትን እንስት መሳል አይከብድም፤ የስንኞቹ ምሰላ ጨዋታው ላይ ይታከካል፤ ልክፍቱም ወደ ኋላ ትዝታዋ የሚጎትታት ሲሆን ፍቅር ዘመን የማይሽረው ጸጋ መሆኑን ማመላከቻ ነው! ተብሰልስሎቷ ከልጅነት እስከ እውቀት ያልበረደላት መሆኑን ለማስዋብ የተጠቀሰው የልጅነት ጨዋታ በልኩ የተሰፋ ነው፤ ካላመንክ ደሞ ብዙ ሳትንጀረጀር እዚያው መልሱ አለልህና…
‹‹በጠዋቱ ተለክፌ፤
በከንፈርህ ተነድፌ፤
አልድን አልኩኝ፣ ወይ ፍንክች፤
ሐኪም የለው፣ ያንተ ምች፤›› የሚሉትን ስንኞች ልብ በል!   
ሁለተኛው ደግሞ ሥነ-ቃልን በምሰላ የተጠቀመበት ሙከራ ነው፤ በቦታው የዶሉት ሥነ-ቃል (ዐውዱን፣ የገጸ-ባሕርይውን ሥሜትና ጭብጡን ማዕከል ያደረገ) ግጥምን ለማጦንቸት ይረዳል። ያቺ ከልታማ እንስት እንዲህ ትሰኛለች፡-
‹‹ቢያፈሉት ከቡና፤
ቢሰፍሩት ከቁና፤
አያልፍ የሰው ነገር፣ ይሄድ ይሄድና፤››
ደራሲው በከንፈር ፍቅር የተነደፈችን ሴት ወክሏል፤ የያዛት ፍቅር አቅሏን ስላሳታት ‹ሰው ምን አለኝ›ን ወግድ ያለችና የወበራች አፍቃሪ ናት ታዲያ! ሥነ-ቃል ውልድ ምሰላው እንደሚጠቁመን ተጠቃሽዋ ‹ያላችሁትን በሉ!› ባይ አፍቃሪ ናት።
የልባችንን ገመና እንደ አባት ዳረጎት በብብታችን እንሸሽገውና፣ ውበትን ማን ይጠላል? የጠዋት ፀሐይ ጣዕም፣ ቢራቢሮ አበባ የምትቀስም፣ የሌሊት ዝናብ ከእንቅልፍ የማያናጥብ… ትፍስህት እንጂ ጣመን አይሆኑንም፤ ጨረቃ ውብ ፊቷን አጥልቃ፣ ወይም እናትን፣ ሙቀትን፣ የልብን ሰው ጥበቃ… ሐሴቱ አያበቃ። ታዲያ ውበት የተመሰለበትን ሙዚቃ ማዳመጥ ነፍስን ላይመግብ ነውን!
ከናትናኤል ድርሰቶች አንድ ተጨማሪ ማሳያ ላንሳ፤ የአዲስ ለገሠ ‹‹እንጃ›› ከሚል ሙዚቃ::
ግጥም፡- ናትናኤል ግርማቸው፤ ዜማ፡- እሱባለው ይታየው፤ ቅንብር፡- ሚካኤል ኃይሉ፤  
‹‹አውቃለሁ ነክቼ፣ የርግብ ላባ ስሱን፣
ግን እንዳንቺ ገላ፣ እንጃ መለስለሱን፤››
የሚሉትን ስንኞች እንመልከት፤ ደራሲው ሁለት የማይገናኙ ፍጥረትን ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መልኩ በማነጻጸር (simulation) የእንስቷን የውበት ጥልቀት አመላክቷል። በእውኑ ዓለም ከምናውቀው ከርግብ ውበት ይልቅ የተፈቃሪዋ እንዲልቅ መገንዘብ ይቻላል።
ከናትናኤል ግርማቸው ተወዳጅ ሥራዎች መካከል የሔዋን ገ/ወልድ ‹‹ምን ይጠቅምሃል›› ተጠቃሽ ነው::
ግጥም፡- ናትናኤል ግርማቸው፤ ዜማ፡- ምሕረተአብ ደስታ፤ ቅንብር፡- ታምሩ አማረ፤…
‹‹ባወራው - አንተን ይጠሉሃል፤
ግን እኔ - ተጎዳው በመሀል፤››
የሚሉት ስንኞች ያወበሩኛል። ጣዕር ሲያንገላታት ዓይን-ዓይኗን እያዩዋት - ቤሳቤስቲን ቢያጡ እናት እንደማጣት ዓይነት አይችሉት ጉዳት፣ አይገገም ጸጸት ከጫንቃዋ የሰፈረባት አፍቃሪ በጎዳት ሰው ላይ ብድራት መጥራትን ችላ ብላ በዝምታ ትማቅቃለች። በጽኑ ያመነቺው ወዳጅ ይገፋታል፤ ምናልባትም ከእግዚሔር ቀጥላ ተስፋዋን የጣለችበት ጉብል ነበር ታዲያ፤ በእምነቷ ሰፈረችው፤ በክህደቱ በተናት፡-
‹‹የሆንኩልህ - የምንጭ ውኃ፤
የቆጠርከኝ - ከበረኃ፤
ተረዳሁት - ሞኝነቴን፤
ድንገት ሳጣው - ካንተ እምነቴን፤››
ጣይና ወዳቂ በአንድ ጎጆ ያድሩ ነበር፤ ጊዜ አይከሰስ፣ አይወቀስ ፍቅርንና እምነትን በነበር አስቀራቸው፤ አዪ እቴ! በአፏ ማር አይሟሟም፤ እምነቷ የጽድቅ በርዋ ነበር፤ የልብዋ ሰው በልቡ የቋጠረላትን ፍቅር በሂደት እንደ ጥሬ በተነው፤ መስከረሟ ጠብቶ ለማየት ስትጓጓ የልቧ አበባ ከሰመ፤ በእነ‹እኔ ልላበስሽ› ባዮች ደጃፍ ተዟዙራ ተምች ሆኖ ያደባያትን ጉብል ልታሳጣው አልቃተተችም፤ በሕመም እየቃተተች ትጠይቀው ያዘች እንጂ…  
‹‹ሕመምስ - ይጎዳል ምንኛ፤
ቢችሉት - እንደ ደስተኛ፤
ኀዘኔን - ደብቄው ሰው መሀል፤
ማረሬ - ቆይ ምን ይጠቅምሀል፤››
በዚህ ዘፈን ፍቅር ከፊት ይሰለፋል፤ ያሳለፉትን መልካም ነገር ስላስበለጠች ለሀሜተኞች አሳልፋ አትሰጠውም፤ የጓደኝነት ልኬትን በቅን ልቧ መዝግባ እምነት ያሳጣውን ምክንያት ትመረምራለች። ለመሆኑ የጉዳትዋ መጠን ስንት ነበር? ጽናትዋን ይስጠን እንጂ ምን ይባላል! አሁንም ሁለት ዓመት እንካ!
ለድምጻዊ ማስተዋል እያዩ ‹‹ጀግና›› የተሰኘ ቱባ የዘፈን ግጥም ደርሷል ናትናኤል ግርማቸው፤ የዜማ ደራሲው ቢኒአሚር አሕመድ ነው። ምሰላው ትዳር ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን በካብትሽ-በካብቴ በተባባሉ ጥንዶች መካከል ድንገተኛ ማዕበል ይሰርጋል፤ መርከብ ትዳራቸው በእንስቷ በኩል መልሕቁን ባለመጣሉ መናወጽ ጸና፤ ተባእት መጠነኛ መፍጨርጨር ቢያከናውንም ትዳራቸው የባሕር እራት ከመሆን አልዳነም፤ እብለቷ ልቡን ይንጠዋል፤ ግና ፍቅር ቀዳማይ ነው ለእሱ፤ በኋላ ፈቅ እንደማትል የተረዳው ልቡ በከንቱ ሲበግን መኖርን ሊከላ ይቃትታል፤ ፍቅርን መርገጥ ባይሆንለትም ሚዛናዊነት ያልጎደለውን እውነታ ይፈትሻል…           
‹‹ፍቅርን ብዬ እንጂ - የምተናነሰው፤
ከመረረማ - በ‘ኔ ነው ‘ሚብሰው፤››  
የቆራጥ ሰው ውሳኔ የተወከለበት ነው ሙዚቃው፤ ባለ ድምጹ ሀኬተኛ አይደለም፤ ልቡ ፍቅርን ያስበልጣል፤ ነገሩ የግርንቢጦሽ ይሆንና ከአባይ እጅ ጣለው፤ እብለት ሽንፈት መሆኑን ስለሚያውቅ የቁብ ኀዘን ልቡን አይጎበኝም፡፡ ልብ መባል ያለበት ጀግንነት ፍቅርን መግፋት ሳይሆን ፍቅርን ማስበለጥ ነው ባይ ነው ባለ ድምጹ፤ በዚህ ዘፈን ውስጥ የተሳለው ባለ ድምጽ ፍቅርን ላሳጣቺው - ለውዳጁ ተስፋ እንጂ ለራሱ ተስፋ አያላዝንም፤ በሚከተሉት ስንኞች ገላ የጨዋታው አሸናፊ መሆኑን እየተኩራራ ያወጋል…
‹‹ብቻ ቀርቦ ጉርሻ - ልምዱን፣
           ባልኩራራበትም፤
ሰው ራቀኝ ብሎ - መቼም፣
        እጅ አፉን አይስትም፤››
ዘፈኑ ሌጣ ስሜት ብቻ ሳይሆን ዓለማዊ እውነትም አለው፤ ከዚህም የላቀ እቅጭ እውነት/real-fact ዓይነት ሀሳብ ነው፤ በወል ሥምና በፍዝ ግንዛቤ ‹ጀግንነት› ማለት መርታት ወይም መጣል ማለት ሊሆን ይችላል፤ ግና በዚህ ዘፈን ውስጥ የጀግንነት ጣዕሙ ከወደ-መጣሉ ሳይሆን ከወደ-መውደቁ ጽዋ በኩል ነው፤ ሂያጅ ሳይሆን ለማጅ፤ አባይ ሳይሆን ተበዳይ እንዲጀግን፡-      
‹‹ከንቱ ቢለፈልፍ - ተናግሮ አናጋሪ፣
የወደደ አይደለም - የጠላ ነው ፈሪ፤›› ብሎ ይሞግታል።
ከዚህ በተረፈ ናትናኤል ለተዐምር ግዛው ‹‹ምነዋ››፣ ለዳዊት ጽጌ ‹‹ደስ አለኝ››፣ ለሔዋን ገ/ወልድ ‹‹ትፈለጋለህ››- ግጥምና ዜማ፣ አዲስ አይደለም፤ ለግርማ ተፈራ ካሣ ‹‹መርጦ ማፍቀር የለም››፣ ለብስራት ሱራፌል ‹‹ዛሬም ከኋላ ነገም ከኋላ››፣ ከብስራት ሱራፌል ጋር በጋራ ‹‹የቤት ሥራ››፣ ለአብዱ ኪያርና ለአዲስ ሙላት ‹‹የውብ ዳር››፣ ለራሔል ጌቱ ‹‹ኢትዮጵያ››፣ ለማኪ ኬቢ (ከዓለማየሁ ደመቀ/ወፍጮ ጋር በጋራ) ‹‹ደነገጠ››፣ ለፍቅርዓዲስ ነቃጥበብ - ጌታቸው ኃ/ማርያም እና ሌሎች የተሳተፉበትን ‹‹የሀገር ካስማ›› እና የሌሎች ድምጻዊያንም የዘፈን ግጥሞችን ደርሷል።

Read 955 times