Saturday, 04 March 2023 11:42

አፍላ ገጾች

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(3 votes)

     “--ግጥም የሰራችውን ምግብ እስከ ማጉረስ አትጓዝም፡፡ ምናልባት ምግቡን እስከ ምግብ ማቅረብ ድረስ ብትኼድ ነው። ሰርታ ፣ፈትፍታ ካጎረሰች ምኑን ቁጥብ ፣ምኑን ምሥጢር ሆነች ? በምንስ በስንኝ ከተዋቀረ የአጭር አጭር ተረክ ተለየች?--”
   
         በገጣሚው ግብዣ «አፍላ ገጾች»የተሰኘችዋን የግጥም  ስብስብ ለማንበብ ቻልኩ ።በ2015 ዓ.ም የታተመችዋ «አፍላ ገጾች»፤  የገጣሚ ዮናስ መስፍን ሥራ ነች። መጽሐፏን በAfro Read መተግበሪያ በኩል ሊያገኟት ይችላሉ። መጽሐፏን ባነበብኩና ሐሳቤን ለመሰንዘር በሞከርኩ ሰዓት፣ ለስሜቴ ለመታመን ሞክሬያለሁ።
አሁን፣ ነቀሳም፤ ሙገሳም መሳ ለመሳ ቆመዋል። «ድንጋይ እና ጭቃ ቢቀጣጠሉ ታላቅ ቤት፣ ረጅም ቅጥር ይሆናሉ» እንዲለን አለቃ ዘነብ፤ ተደጋግፈን፣ ተሞራርደን፣ ከመሸረፍ ድነን ...ስለት ሆኖ መገኘት የዘወትር መሻቴ ነው። “you are that man “የሚለው የPhrophet Nathanን አስደንጋጭ ጥቆማ፣ David የደነገጠውም ድንጋጤ እዚህ የለም።
«ኮሶና ክረምት ፊት ይመራ˙ል፤ኋላ ግን ደስ ያሰኛል» ይሉትን «ኂስ  ፊት ሲቀበሉት ያንገሸግሻል፤ ኋላ ግን በኹለት የተሳለ ሰይፍ ይሆኑበታል» ብለን እንጀምር።
Learning Arch በሚበለጽግበት መንገድ ግጥምም  ታድጋለች የሚል እምነት አለኝ።
1ኛ. ACT በማድረግ
2ኛ.Learn በማድረግ
3ኛ. Adapt በማድረግ
...በቅድመ ውልደቷ ከነፍስ የተዋሕደች ሥንኝ፣ ለአፍ ጥፍጥና አታጣም። ለውልደቷ በየኹኔታው ACT የተደረገች  ቋጠሮ ስሜት ነክ ለመሆን አታንስም። በዕድገቷ፤ ቢማሯት፣ ቢያጠኗት የልብ ማድረሷን አትተውም። Experience (ልምምድ) ያልተለየው ቃል ህብስት ነው። ጠንቋዩ ችግር በዛብኝ ያለችውን ደንገጡር፣ ለሰባት ዓመት ታገሽ ያላት፣ ለምን? ስትለው ትለምጅዋለሽ ለማለት ነበር። ይህን ሐሳብ ኢትዮጵያዊው  ግን UK’s leading literary figures የሆነው ለምን ሲሳይ፤ በ« my name is why »መጽሐፉ እንዲህ ያጠነክርልኛል ...
[[...My first footsteps were followed by click clack clack of a typewriter: ’The boy is walking’ .my first words were recorded,click clack clack:’ the boy has learned to walking ‘fingers were poised above a typewriter waiting for whatever happened next: ’The boy is adapting’]
«ኖር»
ዶ/ር ኢዮብ ማሞ «የጥበብ መንገድ» በተሰኘች መጽሐፉ፣ ረጅም ሀተታ የሰጠውን ሐሳባዊ ፍልስፍና እና ተግባራዊ ፍልስፍና ብሎ ያነሳውን ሐሳብ እንይ። በሐሳባዊ ፍልስፍና ሐሳብ የበላይ መሆኑንና በተግባራዊ ፍልስፍና መሬት ላይ የወረደ ሥራ ተከባሪነቱን ያትትልናል። ይህ ሐሳብ በአፍላ ገጾች የግጥም ቋጠሮ ሲደገፍ (ተግባራዊ የሚሆን ነገር ሲሻት) ...የሚከተለውን ተማጽዕኖ እናገኛለን።
«በጠቢብ ምናብ ውስጥ በእውቀት ከሚሰነኝ
በቀልን ማርከሻ ቂምን የሚገድል አንድ ጥበብ
ቢገኝ»
1.ርእስ እና ይዘት
«ርእስን» «ራስ» ይሉታል፤ ደስታ ተ/ወልድ። ርእስ ለሐሳብ ስምረት ሲበጅ፤ ያልሰመረ ርእስ አሰጣጥ  ግን  ጠፍቶ ያጠፋል (“ሙት ይዞ ይሞታል “እንደሚባለው)። ግጥሙ ራስ የለሽ ቢሆንስ? ያስብላል። ገጣሚ ዮናስ መስፍን ለመጽሐፉ አጠቃላይ መጠሪያ ቆንጆ ርእስ እንደመረጠ  ይሰማኛል። «አፍላ ገጾች» አፍላ..አፍለኛ ..ለጋ ለግላጋ ..ለንቀቦጭ (እኒህን ቃላት ሰምተን ያልጠነከረ ግጥም  በውስጡ ብናገኝ እንኳ ብዙም እንዳንገረም ያግዘናል። ምክንያቱስ ስያሜው አፍላ ነዋ፤ በአፍላ ዘመኑም የተጫረ።
ቀስቃሽ ሐሳቦችን (evocative ideas) መጠቀም፣ ቦታን ጊዜን፣ ትዝታን፣ ተስፋን ሌሎቹንም የኑሮ አጥቆችን እንድንቃትትባቸው ማድረግ እና  ነጠላ ቃል (single word) ራስ ሆኖ እንዲመጣ ይመከ˙ራል፤ ምሣሌ፦የሎሬቱ «ቢራቢሮ»ን መሰል። ነገር ግን «እሳት ወይ አበባ»፣ «እውነት ከመንበርህ የለህማ»፣ «መሸ ደግሞ አምባ ልውጣ»ን የመሰለ ረዘም ያለ ርእስም ተመርኩዞ ግጥም ላይረሳ ይጻፋል።
 ራስ የአካልን እንቅስቃሴ ካልተቆጣጠረ አንገት ሊሸከመው እንደማይፈልግ ይሰማኛል። የግጥም ይዘትም እንዲሁ ርእሱ ከይዘቱ እንዲሰምር ይጠበቃል። በአፍላ ገጾች ውስጥ ይኼን እሳቤዬን የሚገዳደር አወቃቀር ገጥሞኛል።
«ውዳሴ ለፍቅርሽ» ለተሰኘ ርእስ ...
ሌላ እስከማፈቅር
ቃልም ሆነ ዜማ ባሉበት ያድቡ
ዳግም ፍቅር ይዞኝ
ደጄ መጥተው ቆመው እስኪሰባሰቡ።
...የሚል የሐሳብ መቋጫ ይመጥነዋል አልልም፤ ምናልባትም ግጥሙ የተዋቀረው በምጸት (irony) ነው ብለን ራሳችንን ካላስተባበልን በቀር። መውደዱን አለመውደዷ እንደሸኛቸው ይናገራል። ታዲያ ለዚህ ውዳሴ? ምጸትነቱን የሚያሳይ ምልክት አለመኖሩ ተቃርኖውን አጉልቶብኛል።
2,ወደ ውጭ የተጻፈች መጽሐፍ
ግጥም ከራስ ትጀምር። በletters to a young poet መጽሐፉ [Rainer Maria Rilke] ...ይመክራል። ..write about what your everyday life  offers you; describe your sorrows and desires, the thoughts that pass through your mind, and your belief  in some kind of beauty_ describe all these with heartfelt, silent, humble sincerity.(page 10, letter one, Paris, february 17,1903).
ግጥም ከነፍስ ጋር ተዋሕዳ፣ወረቀት ላይ ተወልዳ፣ አልያም በሥነ-ቃል ተነግራ ...የተጣመመውን ትገራለች። መቼ? መነሻዋ ከውስጥ ሲሆን።
አፍላ ገጾች ወደ ውጭ የተጻፈች መጽሐፍ ነች። ተወቃሹም፣ ተሞጋሹም ሌላ ነው። ወደ ራስስ? በ«እኛ» መደብ ውስጥ ካልሆነ በቀር አዝማሚያውን ሳየው ገጣሚው ጻድቅ ነው። የራሱ ስህተቶች፣ ኃጢያቶች፣ ድክመቶች፣ወይም ሌሎች ሲንጸባረቁ አላየሁም (በጣት ከሚቆጠሩት በቀር)።  ለመዘርዘር እስኪያታክት ድረስ ግጥሞች ጠቋሚ ናቸው። «የዘመን ሽሚያ» ትቷት ስለሚኼድ ሰው፣ «የሚከስሽ የለም» ቃሏን ስለ ሳተች ፍቅረኛው፣ «ተልካሻ ስዕል» በcircular ending የተጻፈ ስለ ነቃፊ ሰው፣ «ጤዛ»፣ «የአፈር ምስል»ስለ አፈር ስሪት መሆኗ.... ወዘተ። attitude ከመመዘኛዎች አንዱ መሆኑን ልብ ይሏል።
ገጣሚው ግጥም ለመጻፍ ምጡ ከውስጥ ወደ ውጭ እንደሚሆን እናውቃለን ። ዳሩ ግን ወረቀት ላይ የተለቀሱ ስንኞች፣ ጣት ቀሳሪ ከሆኑ ሦሥቱ ቀሪ ጣቶች ወደ እራስ ይሆናሉ። ግጥም ከራስ ጋር ትንሽ ጊዜ ታሳልፍ የሚል እምነት አለኝ። ያደርጋል፣ ይሆናል፣ ናቸው፣ ያረጋት፣ የሆነች...ብዙዎቹ ትዝብትንና መልዕክትን ሲታከኩ ባይ ጊዜ ይኼን አልኩ።
«ኖር»
ገጣሚ ዮናስ መስፍን፤ የቃል እና የሐሳብ ሐብታም ነው። ቃላቱን አላግባብ ሲደርታቸው ሳይ (ይኼ ባይሆን ስል)፣ ገለጻው ልብ-ወለድን ሲያስንቅም እንዲሁ እያነበብኩ ጨረስኩ። «ደመናማ ዕለትን»፣ «ዝናብ ዘመን ነው...»፣ «ልባም ገጽ»፣ «ዘበት»ን የመሰለ ግጥም ቢደጋገም እያልኩ፤ እንደ አገው ፈረስ ሽምጥ እየጋለብኩ ደግሞም ልጓሜን ያዝ እያደረግኩ ነው የጨረስኩ። አንዳንዱ ግጥም በ«በአንዲት ዝንጀሮ ናት የምታስደንቀን» ፍሰት ፈሷል፤ አንዳንዱም የሎሬቱን ጓዳ ዳብሷል፣ አንዳንዱም ከስሜቱ ተቆርሷል።
«ህሊናዬን በጥቅም ልሸጠው ያልኩ ዕለት
ከሚገዛኝ ይልቅ ዋጋ አጣሁለት»
የገጣሚውን ተቆርቋሪነት፣ አስተዋይነት፣ አርቆ አሳቢነት መጽሐፏ ትጠቁማለች። የግጥሙ መልዕክት ከግርጌ ኼዶ የመሸገ ይበዛዋል። በክብ አጨራረስ የተጠቃም ብዙ ግጥም አይቻለሁ።
3. የቃላት ድረታ
ግጥም ውስጥ ቃላት ሲደጋገሙ ሁለት መጠሪያ አላቸው - Repetition & anaphora. መደጋገም ቢያመሳስላቸውም ቦታ ይለያያቸዋል።
(...በዚህች መጽሐፍ «አቅም» በተሰኘ ግጥም ውስጥ አቅም የሚለው ቃል 4 ጊዜ፤ «ምክር» በተሰኘ ግጥም ውስጥ  ‘ልብ’ የሚለው ቃል ከ 5 ጊዜ በላይ፣ «እንቆቅልሽ» በሚለው ግጥም ውስጥ በድን የሚለው ቃል 7 ጊዜ መደረቱ ጥቅም አልባ ነው እላለኹ። ቃል ተደርቶ ግጥሙ መቺ ከሆነ እሰየው ይበል ያስብላል።
«ሣቄን ሣቅ አስቆት
ሣቄ ሲስቅ በሣቅ
ሣያስቅ ያስቃል
ሣቅ ተስቆ ሲሳቅ»
ይኼ ቆንጆ ነው ማለቴ ሳይሆን ቢያንስ’ኳ ግጥሞች እንዲህ ተደጋግመው ልብ ላይ ሳይጎረብጡ የሚደርሱ ከሆነ ብቻ ቢደጋገሙ ይመረጣል። እንደ ሐሳብ ግን ከበድኖች መሐል የወጣ በድን፣ አንዲት ነፍስ ያድን ያስገርማል። አልያም «ላዩ በድን ታቹ በድን መሐሉ ነፍስ ያድን» የሚለውን የተለመደ እንቆቅልሽና የፍካሬ ፍቺውን ያስታውሳል። «ሦሥት ጉልቻ» በተሰኘ ግጥሙ ውስጥ 5 ግዜ የሚደጋገመው “ኩል” በአንጻራዊ  ከሌሎቹ የተሻለ  እንደሆነ ተሰምቶኛል።
«ኖር»
መጽሐፉ በ«ፍቱልኝ አልልም» በምድር ላይ የሚባዝን የለም፤ ምንጊዜም እንደሰው፣በ «የሚናገርለት» ለተበዳዩ ሰው፣ በ«ልዩነት» በመንጋው ለሚገለል ንጡል፤ መንጋውንም ስለሚማርከው ንጡል፣ ከራስ አስታራቂ እንደሚሻን፣ ራስን እንደ አዋቂ የመኮፈስ አባዜአችንን፣ የ«ለየቅል» ኹናቴኣችንን፣ ጎንም መከራን እንደሚለምድ በ«መከራና ምክር» ያቀረቡት ሰው፣ ተአማኒነት እምብዛም መሆኑን («ብቻውን የበላ»)፣ Every end is a new begining  ይሉትንም ...
«ለሰው ልጅ ያልገባው
አንዳች ስውር ነገር
ከህልሙ መፈታት ምኞቱ ባሻገር
የአንደኛው ፍፃሜ
አዲስ ጅምር ውጥን ማለት እንደነበር»
በማለት ሌሎች ውብ ነገሮችንም ሰንቋል። ብዙዎቹ ግጥሞች ከተጻፉ የቆዩ ናቸው። ሊደነቅ ይገባዋል። ከትናንት ሌማት ሰበዝ ተመዝዞ፣ ከዛሬ ስሜቱ ተቀንፎ፣ ከነገ ህልምም ምስል ተውሶ ሊቀርብ ይገባዋል ግጥም። «አፍላ ገጾች» የምክር መጽሐፍ ወደ መምሰል የሚመወስዷት ብዙ ግጥሞችን ይዛለች። ግጥም አይመክርም አይደለም ...ግጥም አመካከሩ ይለያል ነው።
«እኔስ ኖሬዋለሁ ሲከፋኝ ሲደላኝ
ከእንግዲህ ተወልዶ ሰው ለሚሆን ይብላኝ»
ለወላጅ እና ተወላጅ የተገጠመ ምክር እና እዝነት ነው። ግን የመጣበት መንገድ ግጥም ተብሎ ከአእምሮ እንዳይፋቅ ሆኗል። በዚህ መልኩ ከገጣሚ ዮናስም የማይረሱ ያገኘኋቸው አሉ።
4..ግጥም እና ሥነ-ቃል
በሥነ-ቃል በኩል የሚገኙ ግጥሞች ወደር የላቸውም። አንድ...
«ተው በሬ ተው በሬ ሲል እየሰማሁት
የጠመደበትን ቦታውን አጣሁት»  የሚል ሥነ-ቃል ብዙውን ጽሑፋዊ ግጥም የሚያስከነዳ ርቀት ተጉዟል ቢሉ አያስተችም። ጉምቱ ገጣሚያንም ይኼን ይመሰክራሉ።
ሥነ-ቃል ከትወልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ  የማይዳሰስ ንብረት ነው። በሀገራችን ካሉት ገጣሚያን መካከል ሥራቸው ተቀንጭቦም ቢሆን በቃል የሚታወስላቸውን እንጥቀስ። የኤፍሬም ስዩም «ፍቅሬ ሶሊያና»፣ የሰለሞን ሳህለ «ያማል»፣ የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኀን «ምነው እመ-ብርኀን የምትለዋ ስንኝ»፣ የበረከት በላይነህ ግብረ-ሞረድ፣ የገብረክርስቶስ «ከሞተች ቆይቷል»፣ የደበበ ሰይፉ «ልጅቱ የዘመነችቱ»፣ የመንግስቱ ለማ «በጠራ ጨረቃ»፣ እና ሌሎቹም። ሊረሳ የማይገባው ነገር ሥነ-ቃል እገሌ የሚባል ባለቤት የለውም። ከላይ የጠቀስኳቸው ገጣሚያን ሥራዎች በቃል ከመያዝ አንጻር እንጅ ሥነ-ቃል ለመሆን ደርሰዋል ለማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል። የሥነ-ቃል ክዋኔ እና ተለዋዋጭነት ባህርያቱ፤ የመግለጽ፣ የማጠናከር፣ የማስመለጥ፣ የመግታት ተግባራቱም አይዘነጋም።
በአፍላ ገጾች  የግጥም መድበል በኩል የመጡት አንዳንድ ግጥሞች መደላድላቸውን ሥነ-ቃል ሲያደርጉ እናያለን። «ጉርስ» [የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል በሚል ሐሳብ ላይ]፣ «ፍጻሜ አልባ ጅምር» [Every end is a new begining በሚል ሐሳብ ላይ]፣ «ብቻውን የበላ» [ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል በሚል ሐሳብ ላይ]፣ «እንቆቅልሽ» [ላዩ በድን ታቹ በድን መሐሉ ነፍስ ያድን በሚል ሐሳብ ላይ]፣ «የታሪክ ምናብ» [ልብ ግዙ በሚል ፈሊጥ ላይ]፣ «ዕድሜ ማራዘሚያ» [ሳነሳህ መጣህ ዕድሜህ ረጅም ነው በሚል ሐሳብ ላይ]፣ «መከራና ምክር» [ምከረው ምከረው እምቢ ካለ መከራው ይምከረው በሚል ሐሳብ ላይ]፣ «ሰው መሆን» [ሰው ኹን በሚል ፈሊጥ ላይ] እና ሌሎችም በነባር ሐሳብ ላይ ተንደርድረው ግጥም ሲገነቡ እናያለን። በዚህ ረገድ ገጣሚ መስፍን ወንደሰን በ«የኔ ቢጤ ሰማይ» መጽሐፉ ነባር አባባሎችን Deconstruct ሲያደርግ ለማየት ችያለሁ። ከምናውቃቸው የዘፈን አዝማቾች፣ ሥነ-ቃሎች እየተነሳ ገራሚ ሐሳብ አስነብቦናል።
5.የተንዛዛ ገለጻ እና ውክልና
ውክልና ግጥምን ውበት ያላብሳል ፤ራሱም ሐሳብን ይለብሳል። የcss ዓይነትም ጸባይ አለው። ነገሮችን በውክልና መግለጽ ትኩረት ይስባል። ግጥም እንደ ነፍሳት የሕይወት ዑደት (metamorphosis) አላት። (Egg-larva-pupa-adult) እንደሚባለው (ideation-contemplation-evocation-presentation) የሚባሉ ሒደቶችን ታልፋች የሚል እምነት አለኝ። የተጸነሰ ሐሳብ፣ ብስልስሎሽ ኖሮት፣ ለመውጣትም መቃተትን አካቶ በስንኝ መልኩ ይወለዳል እሱም ረጅም  ግጥም ነው። ይኼን ኺደት ተቃርኖ (አሳጥሮ) ግጥም ለመሆን ቢበቃ (incomplete metamorphosis) ነው ይኼውም አጭር ግጥም ነው።
አጭር ግጥም የተቀባበለ ጥይት ነው። የሚታደነው አካል በታየ ቅጽበት የሚተኩሱት። ፍጡን ስሜትን፣ ቅጽበታዊ መቃተትን የያዘ ነው። በአንጻሩ ረጅም ግጥም ጥይት አቀባብሎ የመተኮሱን ኺደት ያካትታል። ይኼ ግጥም ለቅርጽ ፋታ ይሰጣል። ውበት ያለብሱኝ ይሆን ?ብሎ ይጠብቃል።
አፍላ ገጾች ከአጭሩም ከረጅሙም ግጥም ተነካክታለች። አጭሮቹ ከቀረቡበት ለዛ አንጻር ሐሳብ ብቻ ናቸው የሚባሉ አሉ፤ የሚያስጨበጭቡም አሉት። ከረጅም ግጥሞቹ  መካከል አንዳንዶቹ «መንዛዛት» በተባለ ዋግ ተነድፈዋል። ግጥሙ ማለቅ ከሚጠበቅበት ቦታ አልፎ የማብራራት አባዜ። «ባለጠግነት» የተሰኘ ግጥሙን ለምሣሌነት ማቅረብ እንችላለን። ግጥም የሰራችውን ምግብ እስከ ማጉረስ አትጓዝም፡፡ ምናልባት ምግቡን እስከ ምግብ ማቅረብ ድረስ ብትኼድ ነው። ሰርታ፣ ፈትፍታ ካጎረሰች ምኑን ቁጥብ፣ ምኑን ምሥጢር ሆነች? በምንስ በስንኝ ከተዋቀረ የአጭር አጭር ተረክ ተለየች?
«አጠቃሎ»
እንጨት ተሰብሮ፣ ተሰብስቦ ማሰሪያ ልጥ ይሻል። «አንድ ዓይና እና አንድ አይና ተጋብተው ኹለት ዓይን ያለው ልጅ ወለዱ» ይሉም ዘንድ ገጣሚው ገጠመ፣ እኔ አንብቤ ጻፍኩበት፤ ከኹለታችን የተውጣጣ ጠቃሚ ነገር ይኖራል። ደግሞስ «አልጋ ላይ ከምትውል ሴት ገጣባ አህያ ይሻላል፤ ለምን ቢሉ ተሸክሞ ያበላል» ይሉ የለ፤ እንደ አዋቂዎች አንብቦ ዝም ከማለት ለማወቅ ስሜትን መሰንዘር መልካም ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
«አፍላ ገጾች» የተጻፈችበት ዘመን ከመራቁ የተነሳ ግጥሙ የተዋቀረበት ቅርጽ ብዙም አልሳበኝም (ውበቱ ደብዝዞብኛል)። የረጅም ግጥም ሐሳቦቹ ጠንካራ ሆነው፣ ቃላቶቹ ለጉድ ዘንበው  ሳለ ጥሩ ቅርጽ ያጡ ይመስለኛል። የግጥም ጭብጥ መገኛው ግዴታ ከግርጌ እንዲቀመጥ ማን አዘዘን? ጭብጥ መጀመሪያ ላይ፣ መሐል ላይ፣ መጨረሻ ላይ አልያም ደግሞ ከኹሉም ውጭ ሊገኝ ይችላል። ግጥሙ አመራማሪ (ቅኔ) ከሆነ መጀመሪያ፣ መሐል ወይም ከግርጌ  ስንኙ ልናገኝ የምንችለው፣ ለጭብጡ መንደርደሪያውን እንጅ ጭብጡን አይሆንም።
ግጥም ውስጥ ከተቀመጠልን ቋንቋ ዘለን የማናውቀው ስሜት ሊዋረሰን ይገባል። ልክ ሌላ «diction» ያለው ግጥም ሲነበብ፣ ያን ቋንቋ (ዘዬ) የማይችል ሰው በስሜት የመናጥ ኺደት። ቀለም፣ ዜማ፣ ምቱን ሳይቀር እየጨመሩብን ሲሉ፣ ግርምትን ሲጭሩ መታየት መቻል አለብን።
ስሜት በብዙ ነገር ይወከላል። ሚዛን ለፍትሕ፤ ሻንጣ ለጉዞ፣ ሰንሰለት ለእስራት፣ ቀይ አበባ ለፍቅር... ወዘተ።  ወደ ውጭ ግጥሞች ጎራ ያልን እንደሆነ የwilliam wordsworth ን «my heart leaps up when I behold»ን አንብበን በሰማይ ላይ ያለ ቀስተ ደመናን ለሐሳቡ ወክሎ እናገኛለን።  የpercy Bysshe shelleyን «To the moon»ን ያነበብን እንደሆነ ብቸኝነቱን በጨረቃ ወክሎ እናገኛለን። ሌሎችም ይኼንኑ ሲያደርጉ መታየት የተለመደ ነው።
˝Is there an objective measure for as asthetic beauty in poetry?˝ ቢሉ...
˝Beauty is in the Eye  of the Beholder! Poetry is very Personal and no two Poets are alike in this respect.˝ከማለት የዘለለ መልስ የለኝም። ለዚህም ነው  የዚህች ግጥም ስብስብ ውበት በእኔ እይታ የደበዘዘ ቢመስለኝም፣ ደፍሬ ሌላው ያነበባት ሰው እንደኔ ያስባል የማልለው።
ገጣሚ ዮናስ መስፍን ስንኝ ውስጥ ብዙ ሀገራዊ ጉዳዮች አሉ። ትውልድ እንዳይዘናጋቸው የሚፈልጋቸው፣ የሚጸጽተው፣ የሚሞግተው ።«ልብ ያለው ልብ ይበል»ነውና ሐሳቦቹን ለቃቅሞ መያዝ አይከፋም። አንብቧት።Read 868 times