Sunday, 12 March 2023 11:52

“የሽፋን ምስል የጋረዳቸው”

Written by  አብዲ መሐመድ
Rate this item
(0 votes)

 “በአራጣ የተያዘ ጭን” ይሰኛል፡፡ እንደ ርዕሱ ቢሆንም እንደ ምስሉ ግን አይደለም፡፡ የጭን ጉዳዮች አይዳሰሱበትም፣ አይወሱበትም፡፡ ሊነበብ የሚገባው ግሩም ሥራ ነው፡፡ አንጡራና እምቅ አቅም የፈሰሰበት ስለመሆኑ እማኝ እቆምለታሁ፡፡ ለማንም በግልጽ የሚታይ ውበት አለው፡፡ ልቤ የደነገጠበትም፣ የተደመመበትም ገና መጽሐፉን ጀምሬ ማጋመስ ሳልጀምር ነበር፡፡ ስለዚህ የተዋጣለት ስራ አለመመስከር አይቻለኝም፡፡ የኮፒውን ቁጥር እንጃ እንጂ በስፋት ሳይነበብ የቀረም አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ሦስት ጊዜ ለመታተም በቅቷልና! የኔ ጥያቄ ምስሉ ላይ ነው’ንጂ (ለተሳሳተ ግምት ይዳርጋል በሚል ተጠየቅ)፣ ደራሲው ለታሪኩ የሚመጥን ሁነኛ ርዕስ መርጧል፡፡
ዮፍታሄ ካሳ ታሪኩን ለመጻፍ መነሻው ርዕሰ-ጉዳዩ ሳይሆን ርዕሱ ስለመሆኑ ለመገመት ቢያዳግትም ቅሉ፤ ርዕሱ ብቻውን ሳይስበውና ሳያረካው እንዳልቀረ ግን ለማወቅ አያሻማም። በርግጥ ለአንድ ፀሐፊ ተስማሚ ርዕሰ ጉዳይ መምረጥ ብቻውን ፍላጎትን የሚቀሰቅስና የሚያነሳሳ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሁፍ ክፍል መምህር የሆኑት ደረጀ ገብሬ፣ “ተግባራዊ የጽሕፈት መማሪያ” በተሰኘ መጽሐፋቸው፤ “የሚፃፍበት ርዕሰ ጉዳይ ወይም ርዕሰ ነገር መጀመሪያ ራሱን ጸሐፊውን ሊያረካው፣ ሊስበው፣ ሊያደንቀው ይገባል። ለፀሐፊው ያላረካ፣ ለአንባቢው አያረካም። ፀሐፊውን ያልሳበ፣ አንባቢውን አይስብም- ይገፈትራል፡፡ ይሁንና የምንጽፍበትን ርዕሰ ጉዳይ ሁሉ፣ ሁልጊዜ ከግል ጉጉት፣ ፍላጎትና እርካታ ብቻ እየተነሳን እንጽፋለን ማለታችን እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ብዙም በማንፈልገው ጉዳይ ላይ እንጽፍ ዘንድ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ተገድደን እንኳን የምንጽፍ ቢሆን የምንጽፍበትን ርዕሰ ጉዳይ ሊስበን በሚችል መልኩ ማደራጀት እንደሚቻል መጠቆሙ ተገቢ ነው፡፡” (ገጽ 90) ይላሉ፡፡
መጽሐፉ በቴክኒክ፣ በቃላትና በውብ ገለፃዎች የበለፀገ ሆኖ ሚዛን የሚደፉ (እጅግ አጓጊ) ድንቃ ድንቅ አሥራ ሰባት አጫጭር ታሪኮችን በውስጡ ይዟል፡፡ “ወንድ አይበረክትልኝም”፣ “ሴትን ተከትዬ”፣ “ተራ ሰው የመሆን ምኞት”፣ “ላለማግባት” ወ.ዘ.ተ.…፡፡ ለመጽሐፉ ርዕስነት የታጨው ነጠላ ታሪክ እሚያወሳው፤ ከአንድ አራጣ አበዳሪ የተበደረውን ገንዘብ መክፈል ስላቃተው አንድ ሰው ነው፡፡ በወቅቱ መክፈል ላልቻለው ብድር ምትክ እንዲሆን፣ ወይም ለጊዜ ማራዘሚያነት ሚስቱን ለአራት ወር በመያዣነት ለመስጠት ስለተገደደ፣ የሁለት ልጆች አባት ውጣ ውረድ የሚዳስስ ጭብጥ አለው፡፡ ያስያዘው ወይም እንደተያዘበት እሚያምነው (ርዕሱ እንደሚጠቁመን) ጭኗን ብቻ አይደለም። ከጭን ከፍ ሲል ይወዳታል፡፡ ፍቅሩን አሳልፎ መስጠት ሞት ሆኖበታል፡፡ ለሁለት ልጆቹ እናት የተለየ አክብሮትና ውዴታ አለው፡፡ በዚህ ምክንያት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ ይህን ካላደረገ አንድም የለፋበት ቤትና ንብረት ለነፋስ መበተኑ ነው? አንድም ልጆቹ ዓይኑ እያየ መሞታቸው ነው፡፡ መጨረሻውና እጣ ፈንታው ምን ይሆን? አንብባችሁ ፍረዱኝ፡፡…ብቻ ሁሉም ታሪኮች የራሳቸው ለዛና አጫዋች ውብ ፍሰት አላቸው፡፡ በዚህ ረገድ ደራሲው የሚያነሳው ርዕሰ ጉዳይ መልክ፣ ጠባይ፣ ተደራሲ ልብ ይል ዘንድ…የሚያስችል የአገላለጽ ስልት አለው፡፡
ቀጥሎ በዝርዝር ባይሆንም ለማየትና አስደምሞኝ እንድታዩት የመረጥኩት መጽሐፍ የግሩም ተ/ሀይማኖት ሥራ የሆነው “የባከኑ ጭኖች”ን ነው፡፡ ከርዕሱና ከፊት ሽፋኑ ጀምሮ አንባቢ ያሳስታል፡፡ በወሲባዊ ስንክሳሮች ዙሪያ የተፃፈም ይመስላል፡፡ ምስሉ ራቁታቸውን የቀሩና የተኮራመቱ ነፍሶችን ለማሳየት ታስቦበት የተቀናበረ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ገልጦ ማንበብ ያልጀመረ ተደራሲ ምስሉን ከርዕሱ ጋር አያይዞ ወሲባዊ ጉዳይ ላይ ትኩረቱን ያደረገ መጽሐፍ ሊመስለው ከቻለ ስህተት ነው፡፡ ደራሲው በሙያው ጋዜጠኛ ነው፡፡ ከዚህ ሥራው ቀደም ሲል “የሞት ጉዞ” የተሰኘ የስደት ጉዞ ታሪኩን አስነብቦናል፡፡ ግሩም በባከኑ ጭኖች ውስጥ የቀነበበልን ኢ-ልቦለድ ታሪኮችን፣ ወጎችን፣ እውነተኛ ገጠመኞችን፣ በሁሉን አወቅ የአተራረክ ዘይቤ አዋዝቶ የሚያቀርብበት አጫዋች ተረኮችም ጭምር ናቸው፡፡ ርዕሱ ሲፋቅ እሚጠቁመን ዝም ብሎ ብክነትን አይደለም። ሴቶች ኑሮን ለማሸነፍ በሚያደርጉት ትግል፣ በስራና በሕይወት መስመር ላይ እያሉ እድሜያቸውን ልብ ሳይሉት ገፍቶ ሳያገቡ፣ ሳይወልዱ… እንዲሁ ባክነው ስለሚቀሩ እንስቶችን ሕይወት እንዲወክልለት የሰየመው እንደሆነ ከንባቤ ለመረዳት ችዬአለሁ፡፡ ሁሉም የራሳቸው የሆነ ልቀትና ከፍታ ያላቸው ናቸው፡፡
በመሠረቱ ማንኛውም ፀሐፊ ሥራዎቹ በሁሉም አንባቢያን ዘንድ ተቀባይ እንዲሆኑ የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ከአፃፃፍ ስልት ባሻገር የርዕስም ሆነ የምስል ጉዳይን ቦታ ሰጥቶ ከግምት መክተት አለበት፡፡ እኚህ ሁለት ሥራዎች የአንባቢን ሥነ-ጽሁፋዊ የግንዛቤ ደረጃና ተጠየቃዊ አስተሳሰብ ከፍ የሚያደርጉ መሆናቸውን መመስከር ይቻላል፡፡ የምስል ሽፋናቸው፣ የርዕስ መረጣቸው ታሳቢ ተደርጎ (ከበቂ ማስተካከያ ጋር) በተገቢው መንገድ ዳግመኛ ታትመው የሚዳረሱበት እድል ቢኖር  ሸጋ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይሄን ከተገበሩ ተደራሲን በራሳቸው አቅጣጫ መሳብና ማምጣት የሚችሉ መሆናቸው አያጠራጥርም። እነዚህ ፈጠራዎች በራሳቸው ቀለም ልዩ-ልዩ ጭብጦችን ፈልቅቀው…የራሳቸውን ሚዛን የሚያነሱ ናቸው፡፡ ዮፍታሄና ግሩም የፈጠራ አቅማቸው እጅግ የጎለበተ ስለመሆኑ በጉልህ የሚታይ ነውና መመስከር አይገድም፡፡ በእንግዳ እሳቤዎች፣ በአዳዲስ ገለፃዎች… የበለፀጉ ድንቅ ስራዎችን አስነብበውናል፡፡ የሚቀሰቅሱም ሲላቸው ስሜትን የሚንዱም ናቸው፡፡ የተለየ ጣዕም ሰጥተው ሁለመናዬን ገዝተውታል። በቀዳሚ ንባቤዎ ሆነ በዳግመኛው…አጥጋቢ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ምንም እንኳን ለስሜታዊም፣ ለሚዛናዊም ምላሽ እንደዘገየሁ ቢሰማኝም፣ ግና በዋነኝነት ሥራዎቹ ውስጣቸው ሌላ እንደሆነ በመንገር ከሞላ ጎደል ተደራሲን ከተሳሳተ ግምት ለማዳን ያሰናዳሁት ጥቆማዬም ጭምር ነው፡፡Read 970 times