Saturday, 18 March 2023 17:45

“አዲስ እረኛ፣ ከብት አያስተኛ”

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ህንዶች እንዲህ የሚል ተረት አላቸው።
አንድ ጊዜ አሞራዎችና ቁራዎች ስምምነት ላይ ደረሱ አሉ። ስምምነታቸውም ከጫካ የሚያገኙትን ማንኛውንም ነገር እኩል ሊካፈሉ ነው።
አንድ ቀን በአዳኞች ተመትቶ ቆስሎ መነቃነቅ የማይችል አንድ ቀበሮ ዛፍ ሥር ተኝቶ ያገኛሉ። በዙሪያው ተሰበሰቡ።
ቁራዎቹ፡- “ከወገቡ በላይ ያለው የቀበሮ ገላ ክፍል ሊደርሰን ይገባል” አሉ።
አሞራዎቹ፡- “እሺ እኛ የገላውን የታችኛውን ግማሽ እንወስዳለን” አሉ።
ይሄኔ ቀበሮ እየሳቀ፡-
“እኔ ሁልጊዜ አምን የነበረው አሞራዎች ከቁራዎች የበለጡ ፍጡሮች ናቸው የሚለውን ነበር። ስለሆነም መውሰድ ያለባቸው የአካሌን የላይኛውን ክፍል ነው ብዬ ነበር የማምነው። የላይኛው የአካላቴ ክፍል ራሴና አንጎሌ አለ። በጣም ጣፋጭና ስባት ያለው ክፍል ነው” አለ።
አሞራዎቹም ሀሳባቸውን ይለውጡና፡-
“ቀበሮ ያለው ትክክል ነው። እኛ መውሰድና መብላት ያለብን ከወገቡ በላይ ያለውን ክፍል ነው” አሉ።
ቁራዎቹ፡- “አይደለም፤ እኛ መውሰድ ያለብን እስካሁን በተስማማነው መሰረት መሆን አለበት። የላይኛው ክፍል የእኛ ቅርጫ ነው” አሉ።
ጠብ ተነሳ። ጠቡ ወደ ጦርነት ተሸጋገረ። ተተካተኩ። ከሁለቱም ጎራ ነብስ ጠፋ። ብዙ ሬሳ ተዘረረ።
የተረፉት ከሁለቱም ወገን እየሸሹ በመከራ ከጦር ሜዳው አምልጠው ወጡ።
አያ ቀበሮም አጠገቡ የተዘረሩትን አሞሮችና ቁራዎች ያለሀሳብ እያማረጠ እየበላ ከቁስሉ አገግሞ ዘና ብሎ እየተጎማለለ፣
“ኃያላን ሲናቆሩ ደካሞች ይጠቀማሉ” እያለ ሰፈሩን ለቆ ሄደ።
***
“ሁለት ፓርቲዎች ሲጣሉ፡-  ተቦጫጭቀው እስኪዳከሙ ጠብቅ። ቀስ ብለህ ትጠቀምባቸዋለህ። በጣም ቀስ ብለህም አስታራቂያቸው ልትሆን ትችላለህ” የሚል እሳቤ ያላቸው አያሌ ናቸው። የሀገራችን ፖለቲካና ፖለቲከኞች የቅርጫ ስርዓት እስከዛሬ እንዳስቸገረ አለ።
ሚቼላ ሮንግ የተባለችው ፀሐፊ፡ “አሁን መብላት የኛ ተራ ነው”፤ (የኬንያው ፊሽካ- ነፊ (ጋዜጠኛ) ታሪክ (The story of a Kenyan whistle-blower) በሚለው መፅሐፏ የምትነቁጣቸው ነጥቦች አይናችንን እንድንከፍት ይረዱናል።
“እነዚያን አንፀባራቂ ባለተስጥኦ አፍሪካውያን አስታወስኩ። አንዴ ይፋለሙት የነበረውን ሥርዓት አወድሰው፣ እስከነጭራሹም ጦርነት ፈጥረው ይዋሃዱታል። አሁን ነው የለውጥ ሰዓት። አሁን ጊዜው በስሏል ይላሉ። የማታ ማታ ግን ያው እየፈወስነው ነው የሚሉት ሥርዓት አንቅሮ ይተፋቸዋል። አዋርዶ ያባርራቸዋል”
“ኢትዮጵያና ኬንያ ምንና ምን ናቸው?...” እያሉ መግጠም የተለመደ ነገር ነው።
የፖለቲካ ተንታኙን ዤራር ፕሩኒያን ማዳመጡም አይከፋም።
“ኬንያ ከነፃነት በኋላ የፈጠረችው የአገዛዝ ስልት የጎሳዊ-ምሁርነት (ethno-elitism)፤ በየዘመኑ የሚሽከረከሩ ተፎካካሪ ምሁራን የሚቀመጡበት ለሁሉ እኩል እድል ይሰጣል የተባለውን ነገር መሳለቂያ የሚያደርግ ሥርዓት ነው። የአንድ ቡድን ጥቅም የሚጠበቅበትና ሌሎቹ ሁሉ ሙልጭ የሚወጡበት ድምሩ ዜሮ የሆነ ግጥሚያ ነው። አንዱ “ይሮ!” ሲል ሌላው “ኩም አልን!” የሚልበት ሥርዓት ነው።”
በፈረንሣይ ተናጋሪ የአፍሪካ አገሮች ይህ ሥርዓት፤ Ote-toi de la,que je m’y mette- “አንተ ዞር በል፤ እኔ ልቀመጥ” የሚሉት ዘዴን የያዘ ነው። በእንግሊዝኛ ተናጋሪ የአፍሪካ አገሮች ደግሞ አገላለጹ የበለጠ “ፈጣጣ” ነው -  It’s our turn to eat (“አሁን መብላት የእኛ ተራ ነው” እንደማለት ነው) በፓርላማ መቀመጫ፣ በሚኒስትሮች ሹመት፣ በቢሮክራሲ ድልድል ሁሉ እያንዳንዱ መንግሥት ከራሱ ባኮ እያወጣ የራሱን ሰው ብቻ ማከማቸቱን ይያያዘዋል።
ዳሩ “የዲሞክራሲ ፅጌረዳ በኬንያ ሥር የለውም” ብለዋል ኦራፕ ሞይም´ኮ።
ሙስናም ከአንዱ ደጅ አንዱ ደጅ እየተዟዟረ፣ ከአንዱ እጅ አንዱ እጅ እየተሸጋገረ፣ መቼም አፍሪካ “ቀልቀሎ ስልቻ፣ ስልቻ ቀልቀሎ…” መሆኑ አይታበልም። በር ሲዘጉበት በመስኮት፣ በመስኮት ሲሉት በጣራ እየሾለከ መከራ እንዳሳየን ነው።
እዚህ ላይ ስለ ኬንያ ይሁን እንጂ (እሳት ካየው ምን ለየው) የጠበቃ ቺራ ማይና ሃሳብ ቁምነገር አለው።
“ኬንያ ውስጥ ሙስና ከክልል ክልል ይሰደዳል እንጂ በመዋቅር መለዋወጥ (reform) አይወገድም።”
አንድ ሥርዓት ተለውጦ ሌላ  ሥርዓት ሲመጣ፣ አንድ ምርጫ ተካሂዶ ሌላ የአመራር አካል ሲለወጥ፣ ወይም አዲስነቱን “ለማረጋገጥ” ያለፈውን ሲያወግዝ፡ ያለውን ሱሪ በአንገት እስከማለት ድረስ “ይሄን አርግ”፣ “ይሄን ፍጠር” ሲል፣ ዘመን በተለወጠ ቁጥር ህዝብ ወከባና ግራ-መጋባት ውስጥ ሊገባ ይችላል።
በአገራችን ለውጡ ይዞት በመጣው ነውጥ፣ ህዝቡ ኑሮው ሲመሳቀልና ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ሲገባ እያስተዋልን ነው፡፡ “አዲስ እረኛ፣ ከብት አያስተኛ” የሚባለው ይሄኔ ነው።  Read 3272 times