Saturday, 18 March 2023 20:25

ብልጽግና “ጭር ሲል አልወድም” እያለ ነው!?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(3 votes)

ብልፅግናዎች በ2010 የተረከባችኋትን ኢትዮጵያ መልሱልን ቢባሉ ከየት ያመጧታል?!
                        ኤልያስ        የዛሬ የፖለቲካ ወጋችንን ከደግ ደጉ  እንጀምር (መቼም እዚህ አገር ደግ ወሬ ብርቅ ሆኗል!)እናላችሁ… የአዲስ አበባ አስተዳደር 100ሺ ቤቶችን ሊገነባ መሆኑን ከሰሞኑ ሰምተናል። (እኔ ግን ጥሎብኝ ቁጥር ሲበዛ አልወድም!) የሚሳካ ሁሉ አይመስለኝም። ከየትም አምጥቼው እኮ አይደለም። ከዚህ ቀደም ትላልቅ ቁጥሮች ተጠርተው ያልተሳኩበት አጋጣሚ ብዙ በመሆኑ ነው በራሱ በመንግስት!! ለማንኛውም  ወደ ዜናው።
መካከለኛ ገቢ ያላቸው የከተማዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለው የ100 ሺህ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ ይጀምራል ተብሏል። (እሰየው ነው!) መቼም ልማት የሚቃወም፤ የቤቶች ግንባታ የሚጠላ ማንም የለም። (የቱንም ያህል መንግስትን ቢጠላም!) በሌላ በኩል ግን በከተማዋና በዙሪያዋ በርካታ ቤቶች  “ህገ-ወጥ በሚል እየፈረሱ ዜጎች ሲፈናቀሉ መሰንበታቸው ያሳዝናል። ህገ-ወጥ ግንባታ ቢሆንም እኮ ቀና ልብ ካለ ህጋዊ ማድረግ ይቻላል። (በመለስተኛ የገንዘብ ቅጣትና በይቅርታ ማለፍም  አንድ አማራጭ ነው።) ኢትዮጵያውን ያላቸውን ጥሪት አሟጠው በገዙት መሬት ላይ የቀለሱትን ጎጆ በግሬደር አፍርሶ፣ “ህገ ወጥ” ስለሆኑ ነው ማለት፣ በተለይ ለድሃ ቆሜአለሁ ከሚል መንግስት አይጠበቅም። ይህ ደግሞ የሚሆነው ኢትዮጵያውያን በግጭት፣ ጦርነትና ድርቅ ሳቢያ ከአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች እንደጉድ እየተፈናቀሉ ባሉበት ጊዜ ላይ ነው። እንዴት ይህን የሚያውቅ የክልል መንግስትም ሆነ የከተማ አስተዳደር የዜጎችን ቤት ያለ ሃሳብ ዝም ብሎ ያፈርሳል? (ቢያድለው እኮ  ሰርቶ መሰጠት ነበረበት!) ሰርቶ መስጠቱም ይቅር። ለትንሽ ጊዜ መታገስ ማንን ገደለ? (በመላው አገሪቱ  የተፈናቀሉት ቦታ እስኪያገኙ!) ደሞስ ዜጎችን አፈናቅሎ ሜዳ ላይ ለመበተን የምን ጥድፊያ ነው?
ጥድፊያ የሚያምረው በ100ሺ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ላይ ነው እንጂ ማፈናቀል ላይ አይደለም። በነገራችን ላይ በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት እኮ ኢትዮጵያ ከዓለም ቀዳሚዋ ተብላ ተመዝግባለች።
ወዳጆቼ፤ ሳዑዲ አረቢያ ወደ አገሬ በህገ-ወጥ መንገድ ገብተዋል ያለቻቸውን በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ሴት እህቶቻችንን ድንገት ወደ አገራቸው ስትመልሳቸው እኮ ከልባችን ረግመናታል። “ከግብፅ ጋር አብራ ኢትዮጵያን ለመጉዳት ያደረገችው ነው” በሚል ሁሉ ወንጅለናታል። (ያለ መረጃ!) ይታይችሁ… የሳኡዲ መንግስት ህገ-ወጥ ስደተኞችን በፈለገ ጊዜ ከአገሩ ማስወጣት ወይም ማባረር መብቱ ነው።ለነገሩ የመኖሪያ ፈቃድ ያላቸውንም ቢሆን ማባረር ይችላል። እኛ ግን ከማባረር በመለስ አማራጭ ቢኖር ነበር የምንመርጠው። ለምን ቢሉ? እህቶቻችን ከአገራቸው ወጥተው ሳኡዲ እስኪደርሱ የሚከፍሉትን የህይወት መስዋዕትነት እናውቃለንና! ከዚህ አንጻር ታዲያ ዜጎች በገዛ አገራቸው “ህገ-ወጥ” ተብለው ሲፈናቀሉ መንግስት (ያውም ህዝቡ የመረጠው) የተሻለ አማራጭ እንዴት ማፍለቅ ተሳነው? ብለን ብንጠይቅ ሊፈረድብን  አይችልም። ሰብአዊም ሆኖ እኮ ህግን ማስከበር ይቻላል። አገር የምትተዳደረው በህግ ብቻ ሳይሆን በጥበብም ነው።
ክፋቱ ደግሞ የብልፅግና አመራሮች (ሁሉም ባይባሉም!) የሌላቸው ነገር ቢኖር ጥበብ ነው። ጥበብና ብስለት በእጅጉ ይጎድላቸዋል። በነገራችን ላይ የፌደራል መንግስትና የህወሃት ሃይሎች የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙና ጦርነቱ ከቆመ በኋላ፤ አገሪቱ ላይ አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ይሰፍንባታል ተብሎ ቢጠበቅም፤ ተቃራኒው ነው የሆነው። በትንሹ በወር አንድ የንትርክ አጀንዳ እየተፈጠረ፣ ውዝግቡ ሲጧቷፍ ነው የሚስተዋለው። ለዚህ ደግሞ ቁጥር አንድ ተጠያቂው ሙሉ በሙሉ መንግስት ነው ባይባልም፣ የመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ጽንፈኛ ብሄርተኞችና የብልጽግና ካድሬዎች መሆናቸውን መካድ አይቻልም (ራሱም ብልፅግና አይክደውም!) በአዲስ አበባ ት/ቤቶች ከኦሮሚያ ክልል አርማና መዝሙር ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ሁከትና ረብሻ መጥቀስ ይቻላል። (የኦሮሚያ ብልጽግና ካድሬዎች የሉበትም ማለት ማበል ነው የሚሆነው!)
በአንጻሩ የኢትዮጵያ ህዝብ የብልጽግና ፓርቲን  ወዶና ፈቅዶ የመረጠው ፓርቲው ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ በእኩል ዓይን እያየ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲያስተዳድር እንጂ በየብሄሩና በየጎሳው አጥር ተጠግቶ የፖለቲካ ሴራ እንዲሸርብ አልነበረም። ሙሉ አገር የተሰጠው ፓርቲ፤ እንዴት ወደ ክልልና መንድር ወርዶ የዘውግ ፖለቲካ ያራግባል?!
እርግጥ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ድጋፉንና እምነቱን የሰጠው ለብልጽግና ፓርቲ ሳይሆን ለፓርቲው መሪና ለጠ/ሚኒስትሩ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ነበር። ከኢህአዴግ ተወርሶና ፈርሶ እንደ አዲስ በተሰራው የብልጽግና ፓርቲ ላይ ብዙሃኑ እምነት አልነበረውም- ከአገር ቤት እስከ ዳያስፖራ። ለዚህም ነው አሁን በተፈጠረው ምስቅልቅልና ሁሉን አቀፍ ቀውስ፤ መንግስትን ወይም ብልጽግናን ተወቃሽ ከማድረግ ይልቅ ሁሉም ጣቱን አንድ ግለሰብ ላይ የሚቀስረው- ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ!!
 እንግዲህ የዚህ የፖለቲካ ወግ ዓላማና ባህርይ  መሸፋፈንና ማሽሞንሞን አይደለም- ሃቅ ሃቁን በድፍረት ለማውራት ነው። (ሃቁ ነው ነፃ የሚያወጣንና!) የብልፅግና ብርቱ ደጋፊዎችና አመራሮችም ቢሆኑ በዚህ ስሜት ቢያነቡት ይመረጣል። (ጽሁፉ ከጀርባው ድብቅ ዓላማ የለውምና!) እንቀጥል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገርን የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ “ጭር ሲል አልወድም” በሚል ቅኝት እየተንቀሳቀሰ ነው የሚመስለው- ሁሉም ሳይሆኑ ጥቂቱ። ጥቂት መሆናቸውን ግን አገር ላይ የሚደቅኑትን አደጋ አያሳንሰውም። የመንግስት ስልጣኑ ዋነኛ ዘዋሪዎች በመሆናቸው የሚፈጥሩት ቀውስና ምስቅልቅል የከፋ ነው።
ነገርዬውን በእጅጉ የከፋ የሚያደርገው ደግሞ እኒህ የብልጽግና ክንፍ “ጽንፈኛ ብሄርተኞች”፣  እያንዳንዱ ውሳኔያቸውና እርምጃቸው ከፖለቲካ ትርፍ አንጻር ብቻ መቃኘቱ ነው- ሃገርን ሳይሆን ክልልን ወይም ብሄርን አሊያም ጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅምን የሚያስቀድም!!
ባለፈው ሳምንት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ግልጽ ደብዳቤ የጻፉት 15 በአሜሪካ የሚገኙ  ዳያስፖራ የሲቪክ ድርጅቶች፤ በአገሪቱ ላይ ለሚታየው ቀውስና ምስቅልቅል በቀጥታ ተጠያቂ ያደረጉት አንድ ግለሰብን ነው- “አምነነው ክዶናል”፤ “የገባውን ቃል አጥፏል” ያሉትን ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን።
እውነት ለመናገር… የአገሪቱ ፖለቲካ ቅጥ አምባሩ የጠፋው በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት ይመስለኛል- ከፕሪቶሪያው  የሰላም ስምምነት በኋላ ማለት ነው። እስከዚያ ድረስ ካድሬውም ብሄርተኛውም እጁ ላይ ያለው አጓጊ ስልጣንና ምቾት ይዘለቅ አይዘለቅ እንደሆነ ለማወቅ፣ የህወሃትን ውድቀት ማረጋገጥ ነበረበት። ህውሃት ዘወትር እንደሚለው፣ “አፈር ልሶ ነፍስ ቢዘራ” የብልፅግና ህልውና አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ማሰባቸው መባነናቸው አይቀርም። ህወሃት እጅ ሰጥቶ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ግን እፎይ አሉ። ከዚያ እነሱ በተራው እኛን እፎይታ አሳጡን።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁለት ዓመት በጦርነትም ውስጥ ሆነው እንኳን ሁሉም ነገር በቁጥጥራቸው ሥር ነበር ማለት ይቻላል- ከሞላ ጎደል። በሰላም ስምምነቱ ማግስት ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ሁኔታዎች እየከፉና እየተባባሱ መጡ- ዓይናችን እያየ።
አንድ ነገር ልንገራችሁ… ጠ/ሚኒስትሩን ወይም ፓርቲያቸውን “በ2010 የተረከባችኋትን ኢትዮጵያን (ከነችግሯ!) መልሱልን” የሚል ድንገተኛ ጥያቄ ብናቀርብላቸው፣ (እኛ ምስኪን ህዝቦች ማለቴ ነው!) ከየት አምጥተው ሊመልሱልን ነው? (በ2010 የነበረችውን ኢትዮጵያ አሁን የለችማ!) እንግዲህ በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመራው አስተዳደር፤ ኢትዮጵያን የበለጸገች፣ የህግ የበላይነት የሚከበርባት፣ዲሞክራሲ የሚያብብባት ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሁሉም  ብሔር ብሔረሰቦች እኩል የምትመች አገር ያደርጓታል የሚል ጽኑ እምነት  የነበረው- ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ። አሁን ግን ሁሉም ቀርቶብን ስልጣን ሲይዙ የተረከቧትን ኢትዮጵያን  መልሱልን ቢባሉ በእጅጉ ይቸገራሉ- ጠ/ሚኒስትሩ። ለ2 ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት ያልተደረገባት፣ በኦሮሚያ ዜጎች በማንነታቸው በጅምላ ያልተፈጁባትና ያልተፈናቀሉባት፣ ዜጎች በብሄራዊ በዓላት በአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሰንደቅና አልባሳት ደምቀውና ተውበው ጎዳና በመውጣታቸው የማይዋከቡባት፣ በአድዋ በዓል የአፄ ምኒልክና የእቴጌ ጣይቱ ምስል ያለባቸው ቲ-ሸርት በመልበሳቸው የማይፈሩባትና የማይሳደዱባት… ጤፍ ኩንታሉ 10ሺ እና 11ሺ ብር ያልገባባት… ኢትዮጵያን ከየት አምጥተው ነው የሚያስረክቡን።  (የለችማ!)
በነገራችን ላይ ዓለምን ሁሉ አጀብ ያሰኘው የጠ/ሚኒስትሩ የፖለቲካ ሪፎርም ሳይቀር ወደኋላ ተመልሷል (“Back to square one” እንዲል ፈረንጅ!) ከሰሞኑ እንኳን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዳያካሂዱ በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች መከልከላቸው እንዲሁም ወከባና አፈና እንደ የተፈጸመባቸው ተሰምቷል። በህወሃት ኢህአዴግ ዘመን እኮ መሰል አፈናዎችና  ወከባዎች የሚፈጸሙት የምርጫ ሰሞን እንጂ እንዲህ በአዘቦት ቀን አልነበረም። በተቃዋሚዎች ላይ መቼም ቢሆን ወከባና አፈና መፈጸም ኢ-ህገመንግስታዊና ህገ-ወጥ ቢሆንም፣ ምንም የህልውና ስጋት በሌለበት ሲሆን ደግሞ ነገርዬውን እንቆቅልሽ ያደርገዋል። በነገራችን ላይ አዲስ የተመሰረተው “ጎጎት” የተሰኘ የጉራጌ ፓርቲ ገና የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ሲደርጉ የአፈና ሰለባ መሆኑ ያሳዝናል። ጠ/ሚኒስትሩ እኮ ወደ ስልጣን ሲመጡ በወህኒ ቤት የነበሩ ፖለቲከኞችን በሙሉ መፍታታቸው ሳያንስ፤ ተቃዋሚዎችን ከእንግዲህ “ተፎካካሪዎች” እያልን ነው የምንጠራቸው እስከማለት የደረሰ ፖለቲካዊ ትህትና አሳይተውን እንደነበር አይረሳም። (መቼም እያታለሉን ነበር ብዬ አላምንም!)
 እንደው “ጭር ሲል አልወድም” በሚል አባዜ እንጂ እናት ፓርቲና ባልደራስ ጠ/ጉባኤያቸውን ቢያደርጉ ለመንግስት ወይም ለገዢው ፓርቲ ምን አይነት ስጋትና አደጋ ሊደቅኑ ይችላሉና ነው ይሄ ሁሉ ወከባና ክልከላ ያስፈለገው- በሰላም አገር!! የለውጡ መንግስት እንደመጣ ሰሞን እኮ ለተቃዋሚ ፓርዎች ቢሮ የመስጠትና፤ የመንግስት አዳራሾችን በነጻ የሚጠቀሙበት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ሁሉ ቃል ተገብቶ ነበር- በጠ/ሚኒስትሩ። ከሰሞኑ ግን በገዛ ገንዘባቸው ሚሊዮን ብሮች ወጪ አድርገው፤ አዳራሽ ከተከራዩ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ እንዳይችሉ ተከልክለዋል። የብልጽግና ፓርቲ አንዳንድ እርምጃዎችና ውሳኔዎች እንግዲህ ዱብዕዳና ኢ-ተገማች- መሆናቸው ነው ችግራቸው። ከዚህ የሚገኘውን የፖለቲካ ትርፍ የሚያውቀው ትዕዛዙን ያስተላፈው ወገን ብቻ ነው።
ይህን ተከትሎ ድርጊቱን ያወገዘው በወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፤ በመንግስት ላይ ክስ እንደሚመሰርት ነው ያስታወቀው። ወ/ሪት ብርቱካን ለጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤትም በደብዳቤ መጻፋቸው ታውቋል- ክስ ሊመሰርቱ መሆናቸውን የሚገልጽ። በራሳቸው በጠ/ሚኒስትሩ ተሹመው ራሱን መንግስትን (ካጠፋ) ከመክሰስ ወደ ኋላ የማይል ተቋም መመስረቱ፣ የጠ/ሚኒስትሩና አስተዳደራቸው የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የሪፎርም ውጤት ነውና ሊደነቅ ይገባል። ዛሬ ይህን ብንመሰክርም ቅሉ ነገ ምን እንደሚፈጠር ግን አናውቅም። እንደተነጋገርነው በአሁኑ ወቅት የብልጽግና ውሳኔዎችና እርምጃዎች ድንገተኛና ዱብዕዳ እየሆኑ መጥተዋልና…በራሱ በምርጫ ቦርድ ወይም በሰብሳቢዋ በወ/ሪት ብርቱካን ላይ ነገ ተነገ ወዲያ  የሚሆነውን ለመገመት ያዳግታል። ብልጽግና እንደሆነ ኢ-ተገማች (unpredictable) ፓርቲ ሆኖ አርፎታል- ቀንዱና ጭራው የማይለይ!
ወደ ሰሞነኛው አወዛጋቢ መረጃ ደግሞ እንለፍ። ከብልጽግና ከፍተኛ አመራሮች አንዷ የሆኑትና በንግግራቸው አወዛጋቢነት የሚታወቁት የከተማዋ ከንቲባ የተከበሩአዳነች አቤቤ ከሰሞኑ ለም/ቤታቸው ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ተናገሩ የተባለው ነገር ከፍተኛ የፖለቲካ ትኩሳት ቀስቅሷል። እርግጥ ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከንቲባዋ የተነፈሱት ነገር ሁሉ ለውዝግብና ለነቀፋ የሚዳርጋቸው እየሆነ መጥቷል- በተደጋጋሚና በተከታታይ! (“ጭር ሲል አልወድም” ዓይነት ይሆን እንዴ?!) የአሁኑን ግን ልዩ የሚያደርገው አንጋፋዎቹም እምብዛም የማይታወቁትም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድ ላይ መረባረባቸው ነው- በከንቲባዋ ንግግር ላይ። እንደውም አብን “ከንቲባዋ ለፍርድ ይቅረቡ” እስከ ማለት አምርሯል- ባወጣው መግለጫ።
ለመሆኑ ከንቲባዋ ምን ተናግረው ነው? በጥቂቱ እንየው። “በከተማዋ ውስጥ ባላቸው ኔትወርክ፣ በሚዲያ፣ በአክቲቪስት፣ በጥቅምና በፖለቲካ ትርፍ ተጠርተው የገቡ ሃይሎች ናቸው። የመንግስት ሥልጣንን በህጋዊ መንገድ ያላገኙ ሃይሎች፣ እነዚህን አካላት ከክልል ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ አድርገዋል። “ሆ” ብለህ አራት ኪሎ ግባ ተብለው ነው የመጡት። የታቀደው ትልቅ ነበር። የተያዘው ስትራቴጂ ከባድ ነበር። የጸጥታ አካላት ባያቆሙት ኖሮ ዛሬ እዚህ ቁጭ ብለን አናወራም ነበር።” ሲሉ ነው ከንቲባዋ ለም/ቤቱ ያብራሩት!
መንግስትን በመጣል በሃይል ስልጣን ለመያዝ ተደራጅተው ተልከዋል የተባሉትን ወገኖች በክልል ወይም ብሄርን በሚጠቁም መልኩ ያውም በመቶኛ ስሌት መቅረቡ ዓላማው ግልጽ ባይሆንም እንዲህ ነበር የተባለው፡- “ከሁለት ሳምንት በፊት በተከበረው አድዋ በዓል ላይ ለዚሁ ተግባር ቀደም ብለው ወደ ከተማዋ ከገቡት ውስጥ፣ 64 በመቶው ከአማራ ክልል፣ እንዲሁም 21 ከመቶው ከደቡብና 14 ከመቶዎቹ ከኦሮሚያ ይገኙበታል” ተብለዋል።
የሚገርመው ግን ምን መሰላችሁ? መንግስትን በመጣል በሃይል ስልጣን ለመያዝ ያሴሩ ወይም የተላኩ ቡድኖች (ተጠርጣሪዎች) ጉዳይ በአዲስ አበባ ም/ቤት ሪፖርት ላይ መቅረቡ ነው- እንደ ቀላልና ተራ ጉዳይ! “እነዚህ ሃይሎች የሚያቀርቡት የሚመስሉም የማይመስሉም ጥያቄዎች አሉ” ያሉት ከንቲባዋ፤ ግን በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን መፈታት መቻል አለባቸው” ብለዋል።
በቃ! ይኸው ነው የሚወሰደው እርምጃ። መንግስት ለመጣልና ሥልጣን በሃይል ለመቀማት ያሴሩ ቡድኖች ጉዳይ ከመቼ ወዲህ ነው በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን መፍትሄ የሚያገኘው? (በፍ/ቤት እንጂ!)
እስካሁን ግን እኒህ “ተጠርጣሪዎች” የፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው ይሁኑ ክስ ይመስረትባቸው የተሰማ ነገር የለም። በሌላ በኩል፤ የከንቲባዋን ንግግር ክፉኛ ያወገዘውና የነቀፈው አብን፤ “ንግግሩ ከፋፋይና አደገኛ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቅስቀሳ ነው፤ ከንቲባዋ ከሥልጣናቸው ተነስተው ለፍርድ ይቅረቡ” ሲል ጠይቋል።
“ንግግራቸው በማናቸውም ሁኔታ ተቀባይነት የሌለውና ዓለማቀፍ የወንጀል ጥሪና ኢትዮጵያ ፊርማ የተቀበለቻቸውን ዓለማቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች፣  ድንጋጌዎችና  በስራ ላይ ያለውን ህገመንግስት የሚጥስ ጭምር መሆኑን” አብን አስታውቋል። ወጋችን ባያልቅም የቦታ ጥበት በዚሁ እንድንገደብ አስገድዶናል።

Read 1251 times