Saturday, 25 March 2023 17:46

ፖለቲከኞቻን የሳይካትሪስት እርዳታ ያስፈልጋቸዋል

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(3 votes)

- ከመቶ ሺ በላይ ዜጎችን ከፈጀው ጦርነት አልተማርንም
         - ለአገራችን የዝምታ ቀን ያስፈ ልገናል
             
       ኢትዮጵያችን ሁሌም የምትገርም አገር ናት። የምትደንቅ ምድር ናት። ኢትዮጵያ የዚያኑ ያህል  ደግሞ እንቆቅልሽ ናት። የሚገርመው ኢትዮጵያን ሁሉም ያማርሯታል- ከተራ ዜጋ እስከ ቱባ ባለስልጣ ናት ድረስ።  ለስልጣን ያልበቁ ፖለቲከኞች እንደ ጉድ ይረግሟታል። ይወቅሷታል። ፍትሃዊ አይደለችም ብለው ይነቅፏታል። ከልጅነት እስከ ዕውቀት ኖረውባት፣ ተምረውባት፣ ወግ ማዕረግ አይተውባትም አያመሰግኗትም። አያደንቋትም። ውበቷንና ሞገሷን ማየትም መስማትም አይፈልጉም። ታላቅነቷ ሲነሳ የሚያንገሸግሻቸው ጥቂት አይደሉም።  እነዚህ ሁነኛ ሳይካትሪስት ያስፈልጋቸዋል። እንደ ህውሃት የለየላቸው ደግሞ “እናፈርሳታለን!” ብለው ጦር ሰብቀው ይነሱባታል። ኢትዮጵያ ግን ከተፈጠረች ጀምሮ ያለውን ታሪኳን ጠንቅቃ ታውቃለች። “እናፈርሳታለን” ያሉ ሁሉ ራሳቸው ሲፈርሱ ነው ደጋግማ ያየችው- በዝምታና በትዕግስት!!
“እናፈርሳታለን” ብለው የዘመቱባት የውጭ ጠላቶች አይደሉም። ለሶስት አስርት ዓመታት ስልጣን ይዘው (ባንኩንም ታንኩንም እንዲሉ!) እንዳሻቸው የተንደላቀቁ ከፍተኛ ባለስልጣናት ናቸው። በ30 ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው አተረፉ እንጂ አልከሰሩም። ተመቻቸው እንጂ አልቆረቆራቸውም። ባዶ እጃቸውን መጥተው ሚለዬነር ሆነው ነው የተመለሱት ከስልጣን ሲባረሩ!! ምን ለማለት ነው? ኢትዮጵያ አልበደለቻቸውም። ኢትዮጵያ ከስልጣን አላባረረቻቸውም። ከሥልጣን ለመባረራቸውም ቢሆን ተጠያቂው ራሳቸው ናቸው። ግፋቸውን  ባያበዙት ኖሮ፣ በንቀት ህዝቡን ባያማርሩት ኖሮ… ዛሬም ድረስ ታንኩንም ባንኩንም ማንም የሚነካባቸው አልነበረም። እነሱ ግን አበዙት። ህዝቡን አስመረሩት። እረፍት አሳጡት። ጭራሽ በገዛ አገሩ ባሪያ አደረጉት። ተቃውሞውና አመጹ ተቀጣጠለ። እንደተለመደው በጥይትና በታንክ (በኮማንድ ፖስትም ጭምር) አመፃውን ለማፈን ሞከሩ። የቻሉትን ያህል  አደረጉ። አሰሩ። አስፈራሩ። ብዙዎችንም ገደሉም- በተለይ በአማራና በኦሮሞ ክልል ግን የግፍ ጥዋው እስከ አፍ ገደቡ ሞልቶ ስለነበር (Dawn Dawn Woyane!) ተቀጣጠለ። የማታ የማታ በህዝብ ግፊትና ጫና፣ ራሱ ኦህአዴግ መክሮና ዘክሮ፣ (በፖለቲካ ቁማርም ጭምር!)  ህወሃትን ከጨዋታው አገለሉት። የሥልጣኑ መሪና ዘዋሪ ከመሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተሰናበተ መሰለ- የህወሃት ቡድን።
ከዚያ በኋላ ነው የህወሃት አመራሮች ተሰባስበው ለ30 ዓመት አይተውት የማያውቁት የትግራይ ህዝብ ዘንድ የሄዱት- መቀሌ ገብተው የተመሸጉት።
እርግጥ ነው… ህዝቡ በእልልታና ፈንዲሻ እየበተነ አልቀበላቸውም። “አሁን ምን ልትሰሩ መጣችሁ?” ሲል ነው የተቃወማቸው። ምለውና ተገዝተው ይመስለኛል ህዝቡን ያሳመኑት። አሁን ሳስበው… ምነው በተቃውሟቸው በፀኑ ነበር እላለሁ። ለምን ቢሉ? ህዝቡ ይቅርታ አድርጎ ባይቀበላቸው ኖሮ፣ በጥላቻ ገፋፍተው ለጦርነት አይማገዱትም ነበር። ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ አያልቅም ነበር። እንዲያም ሆኖ ጦርነቱ በአንድ ጀንበር አልተቀሰቀሰም። ለሁለት ዓመት የክፋትና የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ተነዝቷል። ህወሃት ለ30 ዓመት መንግስት ሆኖ የገዛትን አገር “ኢትዮጵያን” በአንድ ጀንበር አፈርሳታለሁ ሲል የትግራይም ህዝብ ቢሆን አይቀበለውም ነበር። ስለዚህ በሩን ዘግቶ ህዝቡን መጠዝጠዝ ነበረበት። ለ2 ዓመት። ህዝቡን በፍርሃት አርዶ፣ በስጋት አስጨንቆ በጥላቻ ትርክት ሞልቶ  ለእልቂት ለማዘጋጀት። የትግራይ ህዝብ በአቢይ መንግሥት፣ በአማራ ልዩ ሃይል በኤርትራ መንግስት  በመከላከያ ሃይል መከበቡን… እኒህ ሃይሎች ተባብረው የትግራይን ህዝብ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ማሴራቸውን… ደግመው፣ ደጋግመው መስበክ… መለፈፍ ነበረባቸው- ትግራዋይን በአንድ ዓላማ ለጦርነቱ ለማነሳሳት።
ከሁለት ዓመት በፊት ህወሃት መቀሌ መሽጎ ክፋትና ሴራ ሲጎነጉን፣ የጦርነት… ከበሮ ሲደልቅ፣ ለህገመንግስቱና ለፌደራል መንግስቱ አልገዛም ሲል፣ የፌደራሉን መንግስት ለጦርነት ሲተነኩስ… እናንተ አልነበራችሁም ብዬ አይደለም እንደ አዲስ የምነግራችሁ። የዚህ ጽሁፍ ዓላማም ህወሃት የዛሬ ሁለት ዓመት የለኮሰውንና በመቶ ሺዎች ኢትዮጵያውያንን  የፈጀውን አሰቃቂ ጦርነት ለማስታወስ አይደለም። ይልቁንም ጦርነቱ ከመለኮሱ በፊት የተደረገውን የስነልቦና ዝግጅትና ቅስቀሳ ለማሳየት ነው። 2 ዓመት ሙሉ በፕሮፓጋዳን ተደጋግሞ ሲነዛ የነበረውን። ደግሞ የህወሃት አመራሮች ብቻ አይደሉም። ትግራዋይ አክቲቪስቶች፣ ምሁራን፣ ዳያስፖራ ትግራዋይ… ወዘተ… ለደም አፋሳሹ ጦርነት በትጋት ቀስቅሰዋል። የመከላከያም ሆነ የአማራ ሰራዊትን ጭራቅ አድርገው ስለዋል። ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የባሱ አምባገነን መሆናቸው በትግራይ ቲቪ ተደጋግሞ ተደስኩሯል - በህወሃት ከፍተኛ መሪዎች። የትግራይ ህዝበ ለሁለት ዓመት ከግራ ከቀኝ በየቀኑ የሚተገትጉትን ከመስማትና ከመቀበል ውጭ አማራጭ አልነበረም። ከህወሃት ፕሮፓጋዳ ውጭ ሌላ ሃሳብ የሚሰማበትና የሚገኝበት ዕድል አልነበራቸውም። “ስለዚህ ምስኪኑ የትግራይ ህዝብ ሊጨፈልቀው፣ ሊያጠፋው፣ ነፃነቱን ሊቀማው ካሰፈሰፈው ሃይል (ሃይሎች) ራሱን ለመከላከል (ከተቻለም ለማሸነፍ)  በቁርጠኝነት መዘጋጀት ነበረበት።
(ሌላ ምርጫ አልነበረውማ!) በመጨረሻም ውጤቱን ከሁለት ዓመት ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ አይተነዋል። ወንድማማች ህዝቦች እርስ በርስ ተዋግተው አሸናፊ እንደሌለ እሙን ነው። እልቂት፣ ረሃብ፣ ውድመት፣ ሃዘን፣ ሰቆቃ፣ ጥላቻ፣ ኪሳራ ብቻ ነው።
ከጦርነት ትርፍና ብልጽግና ተገኝቶ አያውቅም። ሁሌም ኪሳራ ነው። ውድመትና እልቂት ነው። ግን በቅጡ ማስተዋል የሚገባን ከወታደሩም- ከመሳሪያውም፣ ከስልጠናውም… ከሁሉም በፊት… ጦርነቱን የለኮሰውና ያቀጣጠለው ነዳጅ የፖለቲከኞች ክፉ ቃል ነው። የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ጋዜጠኞችም አክቲቪስቶችም (በሁሉም ወገን) የድርሻቸውን አዋጥተዋል። በቂየጥላቻ መርዝ ( Negative energy በሉት) ህዝቡ ላይ በመርጨት- ከጦርነቱ በፊት። ዛሬስ ከሁለት ዓመቱ አሰቃቂ ጦርነት ምን ተምረናል? እስካሁን ምንምየተማርን አይመስልም። ይኼ ነው የሚያስደነግጠው እውነታ!! ዛሬም ከፖለቲካ ሴራ አልወጣንም- ዛሬም በጥላቻ አስተሳሰብ እያቀነቀንን ነው።
መቼ ነው ግን ይቺ አገር ከጦርነትና ግጭት ቀውስ ወጥታ እፎይ የምትለው?! መቼ ነው ህዝባችን ከሞት፤ ከመፈናቀል ወጥቶ የሰላም አየር የሚተነፍሰው? መቼ ነው ከግጭትነ  እልቂት ስጋትና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገላግለን እፎይ የምንለው? መቼ ነው ህዝባችን ስለኑሮው መሻሻል፣ ሰለ ልማትና ብልጽግና ማሰብ የሚጀምረው? የብልጽግና መሪዎችና ካድሬዎች ደጋግመው ስለ ልማትና ብልጽግናን ቢሰብኩም ቅሉ ለህዝባችን ግን ለጊዜው ቅንጦት ነው። ልብ አድርጉ! ከድህነት መውጣት፤ መልማትና መበልፀግ እኮ ለህዝባችንም ሆነ ለአገራችን ወሳኝ ነው፤ ያስፈልገናል። ግን በዚህ ወቅት ተራ ተርታው ህዝብ ቁጭ ብሎ ስለ ብልጽግና ያስባል ማለት የማይመስል ነው ለምን ብትሉ… ህልውናው ስጋት ላይ ነው።
ከጦርነት፣ ግጭት፣ መፈናቀል ስጋት ገና አልወጣም። የፍርሃት ድባብ ውስጥ ነው። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሰማይ ላይ፣ አሁንም የጦርነት ደመና አልገፈፈም። በዜጎች ንግግር፣ ገጽታ፣ ስሜት ወዘተ ውስጥ ተስፋና ደስታ  ወይም መነቃቃት አይደለም የሚንጸባረቀው። ይልቁንም፤ ጥርጣሬ፣ ጨለምተኝነት፣ አሉታዊነትና መደንዘዝ ነው የሚታየው።
ችግሩ ግን ያለው ከህዝቡ አይደለም፤ ፈጽሞ!! የአገሪቱና ህዝባችን ጭንቀትና መከራ ዋነኛ ምንጩ ፖለቲከኞቻችን ናቸው። በዕቅዳቸው፣ በፕሮጀክታቸው፣ በንግግራቸው፣ በመፈክራቸው በተግባራቸው፣ በሁለመናቸው የሚያንጸባርቁት ጥላቻ ነው ክፋት ነው፤ ቂምና ቁርሾ ነው። ግጭትና ጦርነት ነው። በዚህ መሃል ህዝቡ እንዴት ብሎ ተስፋ ያድርግ? እንዴት ይረጋጋ? እንዴት ሰላም ያግኝ?
ይቺ አገር ሥር- ነቀል ለውጥ ትፈልጋለች። አብዮት አልወጣኝም። አመጽም አያዋጣም። መገፋፋቱም እንጦሮጦስ ነው የሚከተን። ከዚህ ቀደም ተሞክሮ የማያውቅ አዲስ ለውጥ ነው የሚያስፈልገው።  
አገሪቱ… ህዝቡ… የመንግሥት ባለሥልጣናቱ… ተቃዋሚዎቹ አክቲቪስቶቹ… ዳያስፖራው … ልሂቃኑ… ሃይማኖተኞቹ… ነቢያት ነን ባዮቹ… ሁሉም። ትንሽ ሰከን…ረጋ ይበሉ። ብዙ ከመናገር ይቆጠቡ። (የዝምታ ቀን ሁሉ ያስፈልገናል)
ስለ ሰላም ሊሰብኩን የሚዳዳቸው ሁሉ መጀመሪያ ራሳው ከራሳቸው ጋር ሰላም ይፍጠሩ! የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች በተለይ ከሁሉም በፊት ከራሳቸው ጋር መታረቅ አለባቸው። ከውስጣቸው ጥላቻን ማስወገድ ይገባቸዋል። በዘርና በጎጥ መከፋፈልን እርም ማለት ይገባቸዋል። ፖለቲከኞች እርስ በርስ መጠላለፍን መጠፋፋትን፤ መዋዋጥን ይተው። ከእኩልነት ይልቅ የበላይነትን ወይም ጨቋኝነትን ለህዝቡና ለአገሪቱ ሰላም ሲሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በጦርነት አስፈጅተው ድንገት ፕሬዚዳንት ሆነው ማየት ያስደነግጣል። ምንም ሳይመስላቸው ወደ ስልጣን፤ መምጣታቸው የጤና አይደለም። የሳይካትሪስት እርዳታና ድጋፍ ሊሰጣቸው ይገባል። መታከም፤ መፈወስ ያስፈልጋቸዋል። ለህዝቡ ደህንነትም ሲባል።


Read 1024 times