Saturday, 25 March 2023 18:35

እድሜአቸው ሳያልፍ ወደህክምናው ቢቀርቡ…

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

ባለፈው ሳምንት የመካንነት ሕክምና ክሊኒኮችን መስፋፋት በተመለከተ ከNew Leaf የስነ ተዋልዶ ጤናና የመካንነት ህክምና ክሊኒክ ቆይታ በማድረግ አንድ ሐኪም ማነጋገራችን ይታወሳል፡፡ እሳቸውም ዶ/ር ወለላ አለሙ በኒውሊፍ የመካንነትና የስነተዋልዶ ሕክምና ማእከል ውስጥ የጽንስና ማህጸን እና የመካንነት ህክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ በቅድሚያ የምታነቡት ግን አንድ ምስክርነትን ነው፡፡
‹‹…እኔ በልጅነቴ ነው እናቴ የሞተችው፡፡ አባቴ ደግሞ እናቴን ቀድሞ ነበር ያረፈው፡፡ እኔ እንዲያውም አላውቀውም፡፡ እናቴን እንኩዋን አውቃታለሁ፡፡ እስዋ ስታርፍ የሰባት አመት ልጅ ነበርኩ፡፡ እናቴ በምታሳድገኝ ወቅት ሁሉን ነገር ተንከባክባ ነበር፤ ልጄ እንዳይበርዳት፤ ልጄ እንዳይርባት፤ ልጄን እንዳትመትዋት….ብቻ ብዙ ነገር ነበር፡፡ ታላላቆቼ በእኔ የተነሳ ቁም ስቅላቸውን ነበር የሚያዩት፡፡ ከዚያም እናቴ ታመመች፡፡ እናቴ ስትታመም እኔን ከአጠገብዋ እንዳይለዩኝ ታዛቸዋለች፡፡ ከእኔ ከራቀች አይታወቅም ትመቷታላችሁ፤ እንዳትቆሸሸ አጣጥቡአት ትል ነበር፡፡ እኔም የአለችበት ሁኔታ ማለትም መታመምዋ አልገባኝም ነበር፡፡ በሁዋላ ግን አረፈች፡፡ እኔም እናቴ የምትመጣ መስሎኝ ደጅ ደጁን ባይ ምንም የሚታይ ነገር የለም፡፡ ታላላቆቼ የሁዋላ ሁዋላ ነገሩኝ። እናታችን አትመጣም፡፡ ወደ እግዚአብሔር ሔዳለች፡፡ አትመለስም ብለው ነገሩኝ፡፡ በቃ እኔም ተስፋ ቆርጬ ዝም ብዬ እንዳልሆነ ሆኜ ማደጌን ጀመርኩ፡፡ የሰው ነገር አይጥመኝ፡፡ ትህትና፤ መታዘዝ፤ የሚባል ነገር የለም፡፡ በቃ ወደ አስራ አራት አመት ሲሆነኝ ቤተሰቦቼ ስለእኔ ማሰብ ጀመሩ፡፡
እድሜዬ ወደ አስራ ስድስት አመት ሲሆነኝ ወደ አረብ አገር ሔዳ የቻለችውን ነገር ትስራ ተብሎ ተወሰነ፡፡ ቤተሰብ የሆኑ ሰዎች ጋ እንድቀጠር ተደረገ፡፡ የገባሁበት ቤት ህጻናትም ሽማግሌም አሮጊትም አዋቂም ወጣትም ሁሉም አይነት ሰው ያለበት ቤተሰብ ያለበት ወደገጠር አካባቢ ነበር፡፡ ለእኔ የታየልኝ እንዳልደፈር የሚለው ብቻ ነበር፡፡ በተረፈ ቤተሰብ የሆኑ ሰዎች ጋ ተቀጥሬ ጉልበቴን በምን መንገድ እንደምጨርስ ምን ያህል እንደምጎዳ ማንም ያሰበው የለም፡፡ ከጠዋት የጀመርኩ ምሽት ወደ መኝታዬ እስክሔድ ድረስ እጅግ በጣም እለፋለሁ፡፡ እቃ ማጠብ ብቻውን ግማሽ ቀን አይበቃምው፡፡ ቤት ማጽዳት ብቻ ግማሽ ቀን አይበቃውም፡፡ ምግባቸውን እራሳቸው ቢያበስሉም ለማብሰል የተጠቀሙባቸው እቃዎች የተመገቡባቸው እቃዎች ወገቤ እስከሚቆረጥ ድረስ ነበር የሚያለፋኝ። በልጅነቴ የገባሁበት ይህ ልፋት ወደ ሀያ አመት ሲሞላኝ ብላቀቀውም ከዚያ የባሰ ቤት ውስጥ ገባሁ። ጣሪያና ግድግዳ ሲያጥቡ መዋል፤ ምንጣፍ እያገላበጡ ማጠብ፤ ማድረቅ ማውጣት፤ ማስገባት፤ ልብስ መተኮስ፤ አረ ስንቱ …ብቻ በጣም ለፋሁ፡፡ የቤቱ ስራ ሲያልቅ በየዘመዱ ቤት እየተወሰድኩ እሰራለሁ፡፡ ማረፍ የሚባል ነገር የለም፡፡ ይህን ልፋቴን እና ድካሜን ተከትሎ የሚሰማኝ የማልቋቋመው ሕመም መጣብኝ። የወር አበባዬ በወር ውስጥ ሁለት ጊዜ ይመጣ ነበር፡፡ በዚያ ላይ የማላውቀው ሕመም ይሰማኛል፡፡ ሽታ ያለው ፈሳሽም ይፈሰኝ ነበር። ብቻ ገንዘብ ማግኘት የሚሉት ነገር በእኔ አስተሳሰብ ምንም ቁምነገር አጣ፡፡
ወደ ሀያ ስምንት አመት ሲሆነኝ ይበቃኛል፤ ደከመኝ ብዬ ወደሐገሬ መጣሁ፡፡ የለፋሁበትን ገንዘብ ይዤ በቅድሚያ ግን የሄድኩት ወደ ሕክምናው ነበር፡፡ ለማንኛውም አንድ ልጅ እንኩዋን ብወልድ ብዬ እንደምንም ብዬ ባልም አገባሁ፡፡ ልጅ መውለድ ስላልቻልኩ እና ከጤናዬም ጋር አንዳንድ የማይመች ነገር ስለነበረኝ ተፋታሁ፡፡ አሁንም በድጋሚ አገባሁ። አሁንም ተፋታሁ፡፡ እድሜዬ ወደ ሰላሳ አምስት አመት ሲሆን ሕመሙ እንደገና እያገረሽ ፈሳሹም የወር አበባውም ሲያስቸግረኝ ተመልሼ ወደ ሐኪም ቤት ሔድኩ፡፡ ግን ከምርመራው በሁዋላ የሰማሁት ምላሽ ያሳዝን ነበር፡፡ ልጅ መውለድ እንደማልችልና ጠንከር ያለ የህክምና ክትትል ካላደረግሁ አስጊ መሆኑ ተነገረኝ፡፡ ማህጸኔ በጣም መጎዳቱ ተነገረኝ፡፡ ዘር ባገኝ ልጅ ብወልድ ምንኛ በተደሰትኩ፡፡ ግን አልሆ ነልኝም። ባጠቃላይም በልጅነቴ ጀምሮ በደረሰብኝ ከባድ ስራና እንግልት መጎዳቴ ነው የተነገረኝ ብላለች ባለታሪኩዋ፡፡
ወደ ኒው ሊፍ የስነተዋልዶ እና የመካንነት ክሊኒክ ጎራ ስንል ዶ/ር ወለላ አለሙ እንደገለጹልን ጥንዶች በመጀመሪያ ወደክሊኒኩ ሲቀርቡ ካሌላ እርዳታ ውጭ በራሳቸው፤ በተፈጥሮአዊው መንገዳቸው የሚወልዱበት አጋጣሚ ካለ ምርመራው ይደረጋል፡፡ በራሳቸው ለመውለድ ደግመሞ ጥሩ እንቁላል ያስፈልጋል፡፡ የዘር ፈሳሽ በጥሩ ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ ሌሎችም እንደማህጸን ያሉት አካላት ጉዳት ያልደረሰባቸው እና የእርግዝናውን ጊዜ ጨርሰው ለመውለድ የሚችል አቅም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ እነዚህ ነገሮች ካሉ በህክምና እገዛ ብቻ እንዲወልዱ የሚደረግበት አጋጣሚ አለ፡፡ ነገር ግን ለምሳሌ የቱቦ ችግር ከሆነ የወንድ ዘርንና የሴት እንቁላልን በማገናኘት በአይቪኤፍ ማለትም በላቦራቶሪ በማገናኘት እና መልሶ ወደ ሴትዋ ማህጸን በማስገባት እርግዝና እንዲፈጠር ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በሴትዋ በኩል እንቁላል ከሌለ ወይንም በወንዱ በኩል ደግሞ የዘር ፍሬ ከሌለ ዘር ማዳቀል አይቻልም፡፡ ህክምናው እንቁላልን መፍጠር አይችልም፡፡ እንቁላሉ ኖሮ ነገር ግን በተለያየ ምክንያት ከወንድ ዘር ጋር መገናኘት ካልቻለ ያንን በላቦራቶሪ እገዛ በማድረግ ከዘር ጋር የተገናኘው እንቁላል ልጅ እንዲሆን ማድረግ ነው የህክምናው እገዛ፡፡ ስለዚህ እንደዚህ አይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች በተፈጥሮአዊው መንገድ መውለድ አይችሉም ማለት ነው፡፡
በወንድ በኩል የዘር ፍሬው መመረት ካልቻለ በሴት በኩልም እንቁላል የማይኖር ከሆነ ከሌላ ሰው የዘር ፍሬና እንቁላል በልገሳ መገኘት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሴትዋ በኩል ደግሞ የማህጸን ችግር ካለ ጽንሱ በላቦራቶሪ ቢፈጠርም የሚቀመጥበትና የሚያድግበት ማህጸን ስለሌለ ወደ ማህጸን ማስገባት ስለማይቻል ሌላ እገዛ ይጠይቃል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ላሉባቸው ሰዎች በሌሎች አገሮች የእንቁላልና የዘር ፍሬ በልገሳ የማግኘት እና ማህጸንን ደግሞ በኪራይ የማግኘት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ከባልና ሚስቱ የሚገኘው የዘር ፍሬና እንቁላል በላቦራቶሪ ተገናኝቶ በሌላ ሴት ማህጸን ውስጥ እርግዝናው እንዲቀጥል ከተደረገ በሁዋላ ልጁ ሲወለድ እንቁላልና የዘር ፍሬ የሰጡት ባልና ሚስት አስፈላጊውን ህጋዊ አሰራር አጠናቀው ልጃቸውን በቀጥታ ከሆስፒታል ይረከባሉ፡፡ ይህ አሰራር ግን በእኛ ሀገር የሌለ በመሆኑ አስቸጋሪ ነው፡፡
በስተመጨረም ዶ/ር ወለላ ባስተላለፉት መልእክት እንደዚህ ያለ ችግር ያለባቸው ቤተሰቦች ጊዜ ሳያጠፉ የመካንት ሕክምና ወደሚሰጥበት ክሊኒክ ቢሄዱ ለመፍትሔው ቅርብ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የማይሆን ሕክምና ላይ ጊዜ ማጥፋትን እናስተውላለን። ችግሩን ለሁለት ብንከፍለው የወንድና የሴት ችግር እኩል በኩል ነው፡፡ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ወደህክምና የሚመጡት ሴቶቹ ናቸው፡፡ ነገር ግን መሆን ያለበት ችግሩ እማን ጋ መሆኑን ለመለየት ጥንዶች አብረው ለህክምናው መቅረብ እንዳለባቸው ነው፡፡ ከዘህም በተጨማሪ እድሜ ሲጨምር እንቁላልም ስለሚቀንስ እድሜአቸው ሳያልፍ ወደህክምናው ቢቀርቡ ጠቃሚ ነው እላለሁ ብለዋል፡፡


Read 665 times