Saturday, 01 April 2023 20:17

ካንሰር በጊዜው ካልታከመ ውጤቱ ህልፈት ነው

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

ይህ የላንቺና ላንተ አምድ አላማዎች አሉት፡፡
. ሰዎች በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ሕመም እንዳይገጥማቸው አስቀድሞውኑ እንዲጠነቀቁ ለማድረግ የተለያዩ መረጃዎችን መስጠት፤
. የጤና መታወክ ከገጠመ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ የደረሰባቸውን እክል በተገቢው አስረድተው አገልግሎቱን ለማግኘት መሞከር እንዳለባቸው    ማሳየት፤
. ባጠቃላይም የጤና ተቋማትም የት እንደሚገኙ መጠቆምና ምናልባትም በቅርብ የማይገኙ ቢሆን እንኩዋን አስቀድሞውኑ እራስን በኢኮኖሚ፤ማህበራዊ፤እና ቁሳዊ መንገድ ማዘጋጀት እንደሚገባ የሚጠቁም ነው፡፡


        በተለይም በሶስተኛው ደረጃ የተጠቆመው የሚያሳየው ብዙ ጊዜ እናቶች የጤና እክል ቢገጥ ማቸው በቅርባቸው ሕክምናው ከሌለ ራቅ ወዳለ ቦታ ሄዶ መታከም የማይታሰብ እየሆነ ስለሚጎዱ መደረግ ያለበትን መጠቆም ነው፡፡ በሌላም በኩል ወላድ እናቶች በተመሳሳይ መንገድ በቅርብ ሕክምና ከሌለ በተራዘመ ምጥ ስለሚሰቃዩና ውጤቱም አስከፊ ስለሚሆን ይህንን መሰል ችግር እንዳይከሰት አስቀድሞውኑም ጥቆማ ማድረግ የመገናኛ ብዙሀን የስራ ድርሻ እንደመሆኑ የላንቺና ላንተ አምድም የሚያተኩርበት ነው፡፡  
በዚህ አምድ ለንባብ ያልነው የአንድ መካከለኛ ክሊኒክን እንቅስቃሴ በሚመለከት ነው፡፡ ክሊኒኩ Purple በመባል ይታወቃል፡፡ትርጉሙም ወይንጠጅ ማት ነው፡፡ የዚህን ክሊኒክ ምንነት የሚያስረዱን መስራቹ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ ናቸው፡፡ ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የጽንስና ማህጸን ሕክምና Specialist (እስፔሻሊስት)ና የማህጸን ካንሰር Sub Specialist (ሰብ እስፔሻሊስት) ናቸው፡፡
ፐርፕል የተሰኘው ክሊኒክ መስራች እና እንደኮንሰል ታንት በመሆን የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ በክሊኒኩ ሌሎች የስራ ድርሻዎችን የያዙ ባለሙያዎችም ቤደረጃው ይገኛሉ፡፡
ዶ/ር ታደሰ ከአሁን ቀደም በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ቀዳሚ ከሆኑት የመራቢያ አካላት የካንሰር ሕክምና ባለሙያዎች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ አሁን የግል ክሊኒክን ከመክፈት ጋር ስራው እንዴት ይታረቃል? በሆስፒታሉ ያሉ ታካሚዎችን የማገልገል ሁኔታ በምን መልኩ ይካሄዳል የሚለው የመጀመሪያ ጥያቄ ነበር፡፡
ዶ/ር ታደሰ ሲመልሱ በእርግጥ የመራቢያ አካላት ካንሰር ሕክምና በኢትዮጵያ ገና በጅምር ላይ ያለ ህክምና ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ስልጠናው ሲጀመር የመጀመሪያ ከነበሩት ሰዎች መካከል የነበርኩ ሲሆን ሕክምናውም እንዲስፋፋ ካደረጉት መካከል ነኝ፡፡ ሕክምናውን ስንመለከት ብዙ ታካሚና በጣም ውስን የሆነ የህክምና ባለሙያ እንዲሁም የህክምና አገልግሎቱን ለማዳረስ የማያስችሉ የህክምና እቃዎች ባሉበት ሁኔታ እንገኛለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በግላቸው በስራሂደት፤በቤተሰብ፤ ከባለሙያዎ ችም ጭምር በተለያዩ መንገዶች ህክምናውን ለማግኘት ሲሉ የሚመጡ ታካሚዎች ያሉ ሲሆን ካለው የአገልግሎት ብቃት ማነስ የተነሳ መርዳት የማይቻልበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በሌላም በኩል ለህክምናው የሚቀርቡ ሰዎች በትክክለኛው መንገድ በቀላሉ ከትክክለኛው ባለሙያው ጋ ደርሰው ሕክምና ወይንም ውሳኔ  የማግኘት (የካንሰር ሕክምና አንድ አይነት ብቻ ሳይሆን ብዙ ጊዜ Multi-Modality መልቲ ሞዳሊቲ ስለሚባል) ችግር ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ይህ ከትክክለኛው ሐኪም ጋ በጊዜው ደርሶ ትክክለኛውን ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል፡፡ የካንሰር ሕክምና ደግሞ በጊዜው ካልተሰጠ ችግር እንደሚያስከትል እሙን ነው፡፡
ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ እንዳሉት ህክምናው ገና ብዙ ነገሮችን ማስተካከልን የሚሻ በመሆኑ እኔም በአቅሜ በሙያዬ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ትንሽ አስተዋጽኦ ባደርግ የሚል አቋም ይዤ ፐርፕል የተሰኘችውን ክሊኒክ ከፍቻለሁ ብለዋል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ ታካሚዎች በቀጥታ ከትክክለኛው ሐኪም ማለትም እስፔሻሊስቱን በቀጥታ አግኝተው በአገር ውስጥ በምን ደረጃ መታከም እንዳለባቸው ካልሆነም በውጭ ሀገር መታከም ካስፈለጋቸውም ያለውን ሁኔታ ለማፋጠን እንዲያስችል ክሊኒኩ ይረዳል፡፡
የመራቢያ አካላት ካንሰር በተለይም የማህጸን ካንሰር ሕመሙ እስኪታወቅ ድረስ በራሱ ጊዜ መፍጀቱ እሙን ነው፡፡ ሕመሙ እስኪታወቅ ድረስ የፈጀው ጊዜ ሳያንስ ከታወቀ በሁዋላ ደግሞ አፋጣኝ መፍትሔ የማያገኝ ሲሆን ብዙዎችን እንደሚጎዳ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ ሴቶች በዚህ ሕመም ሲጀምር እንዳይጋለጡ ካልሆነም ደግሞ ሕመሙን በቶሎ ሕክምና ሰጥቶ ለማዳን እንዲቻል ባለሙያው ሁሉ በሚችለው መንገድ ቢረባረብ እናቶችን ማዳን ይቻላል የሚል እምነት ስላለኝ የድርሻዬን ልወጣ ከሚል ይህንን ፐርፕል ክሊኒክ ከፍቻለሁ ብለዋል፡፡
አንዳድ ጊዜ ሰዎች መታመማቸውን የመደበቅ እንዲሁም ለህክምና ሲሄዱ ብዙ ሰው ካለበት የህክምና ተቋም የአለመሄድ ባህርይ አላቸው፡፡ በተለይም የማህጸን ካንሰር አስቀድሞ የማይ ታወቅ መሆኑ እና ሲታወቅ ደግሞ በቅርብ ካሉ ሰዎች ጋር ተመካክሮ ቶሎ ወደ መፍት ሔው ወይንም ወደህክምናው ከመሄድ ይልቅ ድብቅ ሆኖ የመቆየት ነገር ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን ምንም እንኩዋን ለመደበቅ ወይንም ወደ ሕክምናው ከመቅረብ ቢሸሹ የሁዋላ ሁዋላ ግን ሕመሙ ሲበዛ ወደ ህክምናው መቅረባቸው የማይቀር ሲሆን መፍትሔው ግን የራቀ ነው፡፡ የካንሰር ሕክምና በጊዜው ካልታከመ ውጤቱ ህልፈት መሆኑን ሁሉም ልብ ሊለው ይገባል፡፡ እንደ ዚህ ያለውን ችግር ከመፍታት አኩዋያ በአንድ ወቅት የመንግስት ሆስፒታሎች በት ርፍ ሰአታቸው ማለትም ምሽት ላይ ከፍለው መታከም ለሚችሉ ካለወረፋ በቀጥታ ባለሙያ ዎችን እንዲያገኙ እድሉን ፈጥረው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ምክንያቱ ለጊዜው ባይታወቅም አገልግሎቱ ግን መቋረጡ እሙን ነው፡፡ እንደ ዶ/ር ታደሰ እማኝነት በዚህ መልክ የሚከፈቱ ክሊኒኮች ምናልባትም ሁሉም ሰው ወደ ተወሰነ ቦታ ሄዶ የህክምናው አሰጣጥ ከሚጨናነቅ እንደ አንድ መፍትሔ የሚታይበት አጋጣሚም እንደዚህ ያሉ ክሊኒኮች መከፈታቸው ነው እንደ ዶ/ር ታደሰ ማብራሪያ፡፡
ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ እንደሚሉት ክሊኒክ እንድከፍትና ይህንን አገልግሎት ለመስጠት በር መክፈት አለብኝ ያሰኙኝ ምክንያቶች ብዙ ናቸው፡፡ በካንሰር ሕመም እና ታማሚዎች ዙሪያ ብዙ ገጠመኞች አሉ፡፡
ህመምተኞች በተለያየ ማለትም ተገቢ ባልሆነ ቦታ ማለትም በባህል፤በእምነት፤ወይንም ሊረዳቸው በማይችል የህክምና ተቋም ጊዜያቸውን ፈጅተው ወደ ሕክምናው መምጣት አንዱ እንደ ችግር የሚታይ ነው፡፡
የካንሰር ሕክምና ውጤቱ በዋናነት የሚለካው በካንሰሩ ደረጃ ላይ ነው ፡፡ ይህም  ማለት አንደኛ፤ሁለተኛ፤ሶስተኛ ወይንም አራተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ ለህክምናው አሰራር ወሳኝነት አለው፡፡  
ሌላው ነገር የካንሰር ሕመሙ ከተነሳበት ቦታ ወደ ሌላው አካባቢ ምን ያህል ተሰራጭቶአል የሚለው ሌላው ወሳኝ ነገር ነው፡፡  
በትክክለኛው መንገድ ሕክምናውን የማይከታተሉ ከሆነ በሁለት በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ደረጃ አንድ ነው የተባለ የካንሰር ሕመም ወደሕክምናው በድጋሚ ሲመጣ ደረጃውን ለውጦ ሊመጣ ይችላል፡፡ የካንሰር አይነቱ በእድገቱ ላይ ለውጥ ይኖረዋል፡፡ አንዳንዱ በተፈጠረበት ጥቂት ጊዜ ውስጥ ደረጃውን የሚለዋውጥ ሲሆን አንዳንዱ የካንሰር አይነት ደግሞ ከተፈ ጠረበት ወቅት በቀስታ ፤ረዘም ባለ ጊዜ ውስጥ ደረጃውን የሚለውጥ ስላለ እንዲህ ነው በሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ስለዚህ ጊዜ በጣም ወሳኝነት አለው፡፡ ህመሙ ያጋጠማቸው ሰዎች በጊዜ ወደትክክለኛው ሐኪም ደርሰው ሁኔታው ካልታወቀና መፍትሔ ካልተሰጠው ህይወት ወደማብቃቱ ጎዳና ማዘመምዋ አይቀርም፡፡ ጊዜውን ፈጅተው ወደማብቂያው ላይ የሚመጡ ታካሚዎችን በሚመለከት ምንም ነገር መለወጥ አይቻልም ከማለት ሌላ ምንም ማለት አይቻልም፡፡
ከህመምተኞች አንጻር አንዳንድ መታረም ያለባቸው ነገሮች መኖራቸውንም ማንሳት ይቻላል ብለዋል ዶ/ር ታደሰ ኡርጌ የጽንስና ማህጸን ህክምና እስፔሻሊስትና የመራቢያ አካላት ካንሰር ህክምና ሰብ እስፔሻሊስት ገጠመኛቸውን በማስታወስ፡፡
‹‹አንዳንድ ታካሚዎች ህመሙ አንዳለባቸው ከተረዱ በሁዋላ ለህክምናው ወደተለያዩ ቦታዎች በመሄድ መታየታቸውንና የተቻለውን ያህል ህክምና ማድረጋቸውን ይገልጻሉ፡፡ በስተመጨረሻም በቀዶ ህክምና መታከም አለብሽ ተብያለሁ ይላሉ፡፡ በምርመራ ሁኔታቸው ሲታይ ህመሙ መጨረሻ ደረጃ ላይ በመድረሱ ምክንያት የቀዶ ህክምናው አስፈላጊነት የማይታይበት ደረጃ መድረሱ ይነገራቸዋል፡፡ እነሱም አ.አ.አ.ይ ኦፕራሲዮን መደረግ አለብኝ በማለት ይሟገታሉ፡፡ ታማሚዎቹ ብቻም አይደሉም ሙግት የሚገጥሙት፡፡ ቤተሰባቸውም ጭምር ነው፡፡ እንግዲህ እኛም የሰውን ህይወት የማዳን ተልእኮአችንን በተገቢው መንገድ እንድንወጣ ታማሚዎች እንዲረዱን እንፈልጋለን፡፡ ይኼውም ቢቻል ቢቻ ከመታመም በፊት የጤና ምርመራን አስቀድሞ ማድረግ ካልሆነ ደግሞ በጊዜ ህክምናውን በስነስርአቱ መጀመር ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡            

Read 968 times