Saturday, 29 April 2023 18:00

አስገዳጁ የነዳጅ ግብይት በተጠቃሚዎች ላይ ከፍተኛ ጫናን መፍጠሩ ተጠቆመ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 “የዲጂታል ግብይቱ አማራጭ የግብይት መንገድ እንጂ ብቸኛው መንገድ ሊሆን አይገባም” ተጠቃሚዎች
        “የነዳጅ ዓይነት ስርዓቱ በሂደት ተግባራዊ መደረግ ነበረበት፡፡” የነዳጅ ማደያ ሰራተኞች
        “አዲስ ነገር ከሚፈጥረው ግርታ ውጪ ምንም የታየ ነገር የለም፡፡” ኢትዮ ቴሌኮም
              
         ከሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የነዳጅ ግብይቱ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓት ብቻ እንዲከናወን የወጣው መመሪያ መተግበር መጀመሩ በከተማዋ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅን ፈጥሯል፡፡
በኢንተርኔት መንቀርፈፍና በሲስተም መጓተት ሳቢያ አሽከርካሪዎች ለከፍተኛ እንግልትና ለረዥም ሰልፍ ጥበቃ የተዳረጉ ሲሆን ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ፣ አዲስ ነገር ከሚፈጥረው ግርታ በስተቀር ምንም የታየ ነገር የለም ብሏል፡፡
የዲጂታል የክፍያ ስርዓቱ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ካለፈው ሰኞ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ጀምሮ በከተማዋ በሚገኙ በርካታ የነዳጅ ማደያዎች ረዥም ሰልፎችና የትራፊክ መጨናነቅ የታየ ሲሆን በርካታ አሽከርካሪዎችም ለከፍተኛ መጉላላትና ለስራ መፍታት ተዳርገናል ብለዋል፡፡በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ 18 ማዞሪያ አካባቢ በሚገኘው ኖክ ነዳጅ ማደያ ውስጥ ነዳጅ ለመቅዳት ለረዥም ሰዓት ተሰልፈው ያገኘናቸው አንድ አሽከርካሪ እንደሚናገሩት፤ የነዳጅ ግብይቱ በዲጂታል የክፍያ ስርዓት መሆኑ አንድ አማራጭ እንጂ ብቸኛ አማራጭ ሊሆን አይገባም ብለዋል፡፡ ‹‹በህጋዊ የመገበያያ ገንዘባችን ላይ በግልፅ ተፅፎ የተቀመጠው “ለአምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል” የሚለውን ህግ መጣስ ህገወጥ መሆን ነው፡፡ እኔ በኪሴ ውስጥ የአገሪቱን የመገበያያ ገንዘብ ይዤ የምፈልገውን ነገር የመግዛት መብት አለኝ፡፡
ሻጩም የመሸጥ ግዴታ አለበት፡፡ ላምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል የተባለውም ለዚሁ ነው፡፡ ካሽ ገንዘብ ስለያዝክ አልሸጥልህም ብሎ መመለስ የሚቻልበት በምንም አይነት አሰራር ሊኖር አይገባም›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡
አክለውም፤‹‹መንግስት የሚያወጣቸው ህጎችና መመሪያዎች ቀደም ያሉ አገሪቱ ያወጣቻቸውን ህጎች የሚፃረር ሊሆን አይገባም›› ብለዋል፡፡
በዚሁ ማደያ በነዳጅ ቀጅነት ስራ ላይ የተሰማሩ ሌላው አስተያየት ሰጪ አዲሱ የዲጂታል ግብይት አሰራር በድንገትና በአንድ ጊዜ ተግባራዊ እንዲሆን መደረጉ በተጠቃሚዎች ላይ ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል፡፡ ለተወሰነ ጊዜ የዲጂታል ክፍያ ስርዓቱ ከቀደመው የእጅ በእጅ ክፍያ ስርአት ጋር ጎን ለጎን በማስኬድ በሂደት ወደ ዲጂታል የክፍያ ስርዓቱ መግባት የሚያስችል አሰራር መኖር ነበረበት›› ብሏል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በበኩሉ፤ በዲጂታል የክፍያ ስርዓት ነዳጅ ለመቅዳት የሚስችለውን አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ ለወራት ሲሰራ መቆየቱንና በቂ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ስራ ላይ ማሰማራቱን ገልፆ፤ ሰሞኑን የተከሰተው ችግር አዲስ ነገር የሚፈጥረው ግርታ ነው ብሏል፡፡ በሂደት ተጠቃሚዎ ከሲስተሙ ጋር በመግባባት ወደ ዲጂታል የክፍያ ስርዓቱ የሚገቡ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

Read 1429 times