Saturday, 29 April 2023 18:15

በመንግስትና “በኦነግ ሸኔ” መካከል የተካሄደው ድርድር የሰላም ተስፋን ጭሯል ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(11 votes)

 ላለፉት አራት አመታት በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሲካሄድ የቆየውን ግድያ፣ አፈና፣ ዝርፊያና፣ የንብረት ውድመት ለማስቆምና ግጭቱን ለማብቃት በመንግስትና ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት እያለ በሚጠራው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከፈረጀው አማፂ ቡድን ጋር በታንዛኒያ የተካሄደው ድርድር የሰላም ተስፋን የጫረ እንደሆነ ተነገረ፡፡ ድርድሩ በአካባቢው ሰላምን ለማስፈንና ሁለቱም ወገኖች ችግሮቸውን በውይይት ለመፍታት የሚችሉበት መንገድ ለመፈለግ የሚያስችል እንደሆነ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስት ባለስልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሀፊ ቃለ አቀባይ ለሮይተርስ ገልፀዋል፡፡
ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ተለይቶ በመውጣት የትጥቅ ትግል የጀመረውና ላለፉት አራት አመታታ በደቡብ ኦሮሚያ፣ በምእራብ ሸዋ- በአራቱ የወለጋ ዞኖች ውስጥ ሲንቀሳቀስ የቆየው አማፂ ቡድን ዜጎችን ለሞት፣ ለስቃይ፣ ለስደትና ለንብረት ውድመት  አጋልጧል። ይህንኑ አማጺ ቡድኑ በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጥቃት ለማስቆምና ችግሮችን በንግግር ለመፍታት ተደጋጋሚ ሙከራ ሲደረግ መቆየቱን የሚገልጹ ምንጮች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ድርድሩ ሳይካሄድ መቆየቱን ተናግረዋል።  
ባለፈው እሁድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ “ከሸኔ” ቡድን ጋር በታንዛኒያ ድርድር ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀው ነበር፡፡ ይህንን ተከትሎም በፌደራል መንግስቱ በኩል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን የሚመሩት ቡድን በድርድሩ ላይ የተሳተፈ ሲሆን በሸኔ ቡድን በኩል ደግሞ የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር መሃመድ ሃሰን እና የጦሩ አዛዥ አማካሪ  ጂሬኛ ጉደታና አብዲ ጦሃ እንደተሳተፉና በድርድሩ የኖርዌይ፣ የኬኒያና የኢጋድ ተወካዮች መሳተፋቸውም ታውቋል፡፡
ድርድሩን አስመልክቶ አማፂው ቡድን ባወጣው መግለጫ፤ ድርድሩ በሦስተኛና ገለልተኛ ወገን አደራዳሪነት እንዲካሄድ መጠየቁን ጨምሮ ሁሉም ቅድመ ሁኔታዎቹ በመንግስት በኩል ተቀባይነትን ማግኘታቸውን አስታውቋል፡፡ አማፂ ቡድኑ በዚሁ መግለጫው፤ የቆመለትን አላማ ለማሳካት ጦርነት አማራጭ ነው ብሎ እንደማያምንና ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ለሰላም ዝግጁ መሆኑን ሲገልጽ መቆየቱን አመልክቷል፡፡“ኦነግ ሸኔ” የሚለው መጠሪያ የድርጅቱን ዓላማና ጥያቄ ለማንኳሰስ ያለመና ሆን ተብሎ የተደረገ በመሆኑ መጠሪያውን አልቀበለውም ያለው አማፂ ቡድኑ መንግስት ከዚህ አድራጎቱ እንዲታቀብም አሳስቧል። “የኦሮሞ ነፃነት ጦር” በሚል የድርጅቱ መጠሪያ ሊጠራ እንደሚገባም ገልጿል፡፡በመንግስትና በአማፂ ቡድኑ መካከል ድርድር ለማስጀመር ካለፈው ታህሳስ ወር ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግ የቆየ ሲሆን በአማፅያኑ በኩል ወጥ የሆነ አቋም ባለመታየቱና ድርጅቱ ባለው የተበታተነ መዋቅር ሳቢያ ድርድሩ ሲራዘም መቆየቱን ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

Read 2604 times