Saturday, 29 April 2023 18:32

ቤት ውስጥ ካለው አልማዝ፣ ደጅ ያለው ጠጠር!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ይቺን ከፈረንጅ ጽሁፍ ላይ ያገኘኋትን ነገርዬ እዩልኝማ፡፡ በአንድ ወቅት የሆነ ሰው አንድ በጣም አዋቂ የሚባሉ አዛውንት ዘንድ ይሄድና ጨነቀኝ የሚለውን ጥያቄ ይጠይቃቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ ሰውየው ባለትዳር ቢሆንም፤ በድብቅ ደግሞ ቅምጥ ነበረችው፡፡ “አንድ ነገር ጨንቆኝ እንዲያማክሩኝ ፈልጌ ነው፡፡ አንደኛውን ተሰብስቤ ከሚስቴ ጋር ብቆይ ይሻለኛል ወይስ ጠቅልዬ ወደ ቅምጤ ብሄድ ይሻለኛል?” አዛውንቱ ገና የተቀጠፈ ትኩስ ጽጌረዳና ቁልቋል ይዘው ሰውየውን ይጠይቁታል፡፡
“ከእነኚህ በእጄ ከያዝኳቸው ከሁለቱ አንዱን ምረጥ ብልህ የትኛውን ትመርጣለህ?”
ሰውየው ፈገግ ብሎ፣
“ምን ጥያቄ አለው፣ ጽጌረዳውን ነዋ!” ይላቸዋል፡፡
አዛውንቱም እንዲህ አሉት፤
“አእምሮህ ትንሽ ሳይቃወስ አይቀርም፡፡ ምን መሰለህ፣ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በውበት ላይ ብቻ ያተከሩና በጣም ውብና ትኩስ የሆነውን ነገር ይመርጣሉ፡፡ ግን  ደግሞ ሀቁ ጽጌረዳው ትንሽ ቆይቶ ይጠወልግና ይደርቃል፡፡ ቁልቋሉ ግን እሾህ ቢኖርበትም አይተህ የማታውቃቸው አይነት አበቦች ይፈነዳሉ፡፡
“ሚስትህ፤ጉድለቶችህንና ድክመቶችህን ታውቃለች፡፡ ቅምጥህ፤ ስኬትህንና ገንዘብህን ብቻ ነው የምታውቀው፡፡ ሚስትህ በችግርህ ጊዜ ሁሉ አብራህ ከጎንህ ነች፣ እንባህን ታውቃለች፣ ምንም ይሁን ምንም በክፉ ጊዜም ሆነ በደግ ጊዜም ትወድሃለች፡፡ ቅምጥህ ግን በችግርህ ጊዜ ትታህ አሁን አንተ የምታደርግላትን ሁሉ ወደሚያደርግት ሌላ ሰው ዘንድ ትሄዳለች፡፡ አእምሮው የተቃወሰ ሰው ማለት፣ ቤቱ አልማዝ አስቀምጦ ጠጠር ለመልቀም ወደ ደጅ የሚወጣ ነው፡፡”
አሪፍ አይደለች! ልክ ነዋ...በእጃችን ያለውን  ሸጋ ነገር ትተን፣ የተብለጨለጨውን ሌላ ነገር የምናስስ ስንታችን ነን፡፡ እናማ... በአንድ ወቅት እንደ ልብ ይዘፈን የነበረውን፣ “አንዳንድ ጊዜማ ይሻላል ውሽማ...” የሚልን ዘፈን እንደ መመሪያ በመውሰድ ቤታችን አልማዝ አስቀምጠን፣ ደጅ ጠጠር ፍለጋ የምንወጣ መአት ነን... በግለሰብ ደረጃ፣ በቡድን ደረጃና በሀገር ደረጃ ሳይቀር!
እኔ የምለው...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ በሆነ ባልሆነው “ከእንትን ሀገር ተሞክሮ በመውሰድ...” ምናምን እያልን በምንም በምናምንም የማይመስሉንን ፈረንጆች ስንኮርጅ፣ ወይም እንኮርጃለን ስንል የነበረው ነገር፣ አበቃለት ወይስ ማውራቱ ቀርቶ በድርጊት ብቻ ሆኖ ነው! 
ስሙኝማ እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...ኮሚክ እኮ ነው፡፡ ይቺ ሀገር ብዙ፣ እጅግ ብዙ በጎና ምርጥ ነገሮች ያሏት ነች፡፡ ቦተሊካችን እንደሆነው እየሆነብን ልብ ለልብ፣ እርስ በእርስ መነጋገርና ማውራት ትተን፣ በጎሪጥ መተያየቱ በዛና ነው እንጂ፣ ይቺ ለበርካታ ሺህ ዓመታት የኖረች ሀገር ውጪ፣ ውጪ ማየትን የማያሰኙ፣ የሌሎችን መናፈቅ የማያስመኙ በርካታ ነገሮች አሏት፡፡ “አንዲናየብል ፋክት!” አንዲል ፈረንጅ፣ በራሱ ቋንቋ! እናማ...የሚያምርብንን ነገሮች እንደማይምሩብን የሚያመስሉ ቦተሊካዊ ትርክቶች መስማት የተለመደ ሆነና ነው እንጂ፣ ደጅ ጠጠር ፍለጋ የማያስወጡ በርካታ የተሸፈኑ አልማዞች ሳይኖሩ ቀርተው አይደለም፡፡
እናላችሁ...እንደው ከትንሹ ወይም ትንሽ ከሚመስለው እንነሳና አንድ ጊዜ ስለ ንቅሳት አውርተን ነበር፡፡ (በነገራችን ላይ... ለ‘ጄኔራል ኖውሌጅ’ ያህል “ታቱ” የምትባለው ቃል በፈለገው አይነት ቄንጠኛ የፈረንጅ ፊደላት ብትጻፍም ‘ንቅሳት’ ማለት ነች... አራት ነጥብ! እኔ የምለው... ‘አራት ነጥብ’ የምትባለው አጽንኦት መስጫ የነበረችው ነገር ከቦተሊካችን መዝገበ ቃላት ‘ዲሊት’ ተደረገች እንዴ!) እናላችሁ...አለ አይደል... የምዕራብ ሀገራቱ ሙዚቀኞች፣ ስፖርተኞችና የመሳሰሉት ‘ሴሌብሪቲዎች’ (አይደል የሚባሉት!) ሰውነቶች ላይ የምናያቸው ንቅሳቶች መጀመሪያ አካባቢ ድንግርም፣ ግርምም ይሉ ነበር፡፡ አብስትራክት የሚባሉት አይነት ስዕሎች ያስሉበት፣ የጠፋ ቋንቋ ፊደላትን ከሆነ አፈር ስር አስቆፍረው ቆዳቸው ላይ ያስነቅሱበት፣ በአስገራሚ ሁኔታ  ተጣለልፎ ለመለየት የሚያስቸግር ቀለበት መንገድ ንድፍ ይሥሩበት ግራ ግብት የሚል ነበር፡፡
በኋላ ላይ ፈረንጅ በተደናጋገረ እኛም አብረን አንደነጋገርም ብለን ነው መሰሰኝ መገረሙን ትተን ነበር...ከርሞ፣ ከርሞ እነኛ የተወዛገቡ የጸሎት ይሁኑ፣ የአስማት ይሁኑ፣ ጥቁር ዶሮ የማዞር ይሁኑ፣ ግራ የሚያጋቡ ንቅሳቶች እዚሁ በሀገር ልጆች ላይ ልናይ!
እናላችሁ...ከዚህ ቀደም እንዳወራነው የንቅሳት ጥበብ እኮ አዚህ ሀገር ለበርካታ ዘመናት የኖረ ነው...ቤት ውስጥ የተቀመጠ አልማዝ መሆኑን ረስተን ጠጠር ለቀማ የወጣንበት፡፡ አዎ፣ የሀገር ልጆችን ንቅሳት “ያልተነበበ ጋዜጣ...” ምናምን እያልን ስንዘባበትና ስናሾፍበት ኖረን፣ በንቅሳት የደመቁ እህቶቻችንን መደበኛ መጠሪያ ስማቸውን ችላ እያልን “ኒቂሴ...” እያልን ልናስቅባቸው ልናሸማቅቃቸው ስንሞከር ኖረን፣ አሁን የሌሎች ሀገራት ሙዚቀኞች፣ ኳስ ተጫዋቾች፣ ተዋናዮችና ዓይን መግባት የሚፈልጉ ‘ዓለም ዘጠኞች’፣ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ሲዥጎረጎሩ እያየን, እነሱኑ ለመምሰል መከራችንን እያየን ነው፡፡
ንቅሳትን እኮ እነሱ አይደለም አስራ ሰባት ብርሌ ጠጅ ላይ አስራ ስድስት መለኪያ እንደደረገመ ሰዓሊ.፣ መላ ቅጡ የጠፋ ሥራ ከማስመሰላቸው በፊት እኮ፣ እኛ ዘንድ ረጅም ዘመናት ያስቆጠረ ባህል ነበር፡፡ ኮሚክ እኮ ነው፣ “እንጀራ  የሚባለው ነገር እንኳን እኔ ልመገበው ቀርቶ ለጠላቴም አልመኘውም፣” ስንል የነበርነው፣ የጤፍ ታላቅነት መቼ ታየን መሰላችሁ...የሆነ ፈረንጅ ናሙና ሞጭለፍ አደርጎ ወደ አውሮፓ ሄዶ፣ የጤፍ ግኝት ኮፒራይት ለእኔ ይገባል ብሎ አመለከተ የተባለ ጊዜ! አሀ... ከፈረንጅ  ጋር ተያያዛ! የእርጥብ ሳንድዊችን ኮፒራይት ማክዶናልድስ “ለእኛ ይገባል...” ሊል ስለሚችል ነቃ ማለቱ ሳይሻል አይቀርም፡፡ ቂ...ቂ...ቂ...)
አሀ... በቀድሞ ጊዜ እኮ በተለይ እናቶቻችን፣ እህቶቻችን ይነቀሱ የነበረው ለቲክ ቶክ ካሜራ ምናምን ምቹ እንዲሆን ለማድረግ ሳይሆን፣ እያዳንዷ ጭረት ጥልቅ ትርጉም ትርጉም ነበራት፡፡ ያለ ትርጉም የሚሠራ ንቅሳት እንደሌለ ነው ሲወራ የምንሰማው፡፡ እናላችሁ፣ ወጣቶቹ እንደሚሉት ‘ጭውቴዋ!’ እንዲህ ሆና ሳለች፣ ገና አሁን ከፈረንጅ ሀገር ተፈጥራ የመጣች ይመስል ስንረባረብ ማየቱ ያሳዝናል፡፡
(ቅንፍ ውስጥ ገብተን ጠቆም ለማድረግ ያህል) ብዙዎች በተለይም እህቶቻችን ንቅሳቶች እንዲነደፉባቸው የሚፈልጉባቸው የሰውነት ክፍሎቻቸው፣ “እንደው ዝም፣ እንደው ዝም ማለቱ ይሻላል...” የሚያሰኙ ናቸው ይባልል፡፡
እኔ የምለው...የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው፣ “እንደው ዝም፣ እንደው ዝም...” አይነት ነገር የሚል ዘፈን ነበር እንዴ! አይ...ምናልባት እንደዛ የሚል ዘፈን ከነበረ ሪሳይክል ሳይደረግ ይመለስልን ለማለት ነው፡፡ አሀ... ዘንድሮ “እንደው ዝም፣ እንደው ዝም፣” የሚያሰኙ ነገሮች እየበዙብን ነዋ!
ስሙኝማ... የዘፈን ነገር ካነሳን አይቀር፣ በቀደም አንድ ወዳጃችን የሆነ ሰርግ ላይ ሄዶ ነበር፡፡ እናላችሁ... ሙሽራውና ሙሽሪት ወደ አደራሹ ሲደርሱ አጃቢዎቹ... “እየሰበረ ሰጠው ለአሞራ!” እያሉ ድብልቅልቁን አወጡት አሉ፡፡ እኔ የምለው... ዘንድሮም ሰርግ ላይ “እየሰበረ ሰጠው ለአሞራ!” እና “አርመሰመሰው!” እየተባለ ይዘፋናል እንዴ! ልክ ነዋ...መጠየቅ አለብና! እዚህም እዛም በሆነ ባልሆነው፣ ጠብ ያለሽ በዳቦ ነገር ስለበዛ፣ ሰርግ ለጠብ ሳይሆን ለጨዋታና ሰርጉን ለማሟቅ የሚዘፈኑት ዘፈኖች ጠብ ፍለጋ አይደሉም ለማለት ያህል ነው፡፡ አሀ... አይደለም እንዲህ አይነት ቃላት ተንፍሰን “በሆድህ እንዲህ፣ እንዲህ ብለህ ሰድበኸኛ/ሰደብኸናል!” ለመባባል ምንም ያህል የማይቀረን ጊዜ ላይ ነን እኮ!  
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... እንበልና የሆነ ቦታ ተቀምጣችሁ እየተዝናናችሁ ነው፣ ወይም ለመዝናናት እየሞከራችሁ ነው እንበል፡፡ (ስሙኝማ...የሆነ ሰው ስለ ቀድሞ ጊዜ የመዝናኛ መንገዶችና ስለዚህኛው ዘመን የመዝናኛ መንገዶች ጥናት አድርጎ የሆነ  መጸሐፍ ምናምን የማይጽፍልንሳ! አሀ... ብዙ ነገሮች ተውጠዋላ! እነ እንትና... በፊት እንደለማዳችሁት ቁርስ ላይ “ፉሉ ውስጥ ባቄላ አስምስላችሁ የከተታችሁት አተር ነው!” ብሎ ቀውጢ ምናምን ማድረግ መቅረት አለመቅረቱን አረጋግጡማ!)
እናላችሁ... ተቀምጣችሁ ወይ ሰው ጥበቃ፣ ወይም እንዲሁ ዘወር፣ ገልመጥ እያላችሁ ታያላችሁ፡፡ እና የሆነ ሰው መጥቶ “ስማ፣ ችግር አለ? ምንድነው አሥሬ እየተገላመጥክ የምታየን?” ቢላችሁ ምን ታደርጋላችሁ! ብዙ መገለማመጥ ጥሩ ላይሆን ይችላል ለማለት ነው፡፡ እናማ...ቤት ውስጥ ያለው አልማዝ ችላ እየተባለ፣ደጅ ያለ ጠጠር ፍለጋ መውጣት አሪፍ አይደለም ለማለት ነው፡፡  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1207 times