Saturday, 06 May 2023 18:41

እሽሩሩ መዉደድ--- እሽሩሩ ፍቅር

Written by  መኮንን ደፍሮ-
Rate this item
(2 votes)

ሳባ እባላለሁ፡፡ ቅፅል ስሜ ጁሊ፡፡ እነሆ ዕጣ ፈንታ ካዛንቺስ የተባለ ሲኦል መንደር ወርዉሮኝ አበሳ የበዛበት የቡና ቤት ኑሮን መግፋት ከጀመርኩ ዓመታት አለፉ፡፡ የመከኑ ግን ታሪኬ ሲተረተር አብረዉ የሚወሱ (እኔ ለሌሎች ስተርክ ሳንሱር አድርጌ የምዘላቸዉ) ድፍን ሦስት ዓመታት፡፡ እዚህ ሮማን ቡና ቤት አብረዉኝ ከሚሠሩት ሴቶች ተገንጥዬ ጥጌን ይዤ ቢራ እየጨለጥኩ ተጎልቻለሁ፣ ግንባሬ ጎትቶ የሚያመጣልኝን ወንድ በቋፍ እየጠበቅኩ፡፡ እንደ ሁልጊዜዉ ጥቁር አጭር ቀሚስ ነዉ የለበስኩት፡፡ አብዛኛዉ ልብሴ ጥቁር ነዉ፡፡ ጥቁር ጨርቅ የጠይም ገላዬን ዉበት እንደሚያጎላዉ አዉቃለሁ፡፡ ከሁለት ቀን በፊት ብቅ ብሎ የነበረዉ ረጅም ሪዛም ሸበላ (ቀልቤን ሰርቆ የሄደዉ ሸበላ) ዐይኑን እንዲሁ ገላዬ ላይ ሲያንከራት አመሸ፣ ቤቱን ያ ሁሉ ቆንጆ ሴት ሞልቶት ሳለ፡፡ በእዛ ቀን የለበስኩት ጥቁር ነበር፡፡ ሸበላዉ ምናልባት ዛሬ ይመጣ ይሆናል፡፡
ጥቂት ተስተናጋጆች ናቸዉ ቡና ቤቱ ውስጥ ያሉት፡፡ አዜብ (ቅፅል ስሟ ሩት፡፡ ሁላችንም የሥራ ቦታ ቅፅል ስም አለን) ከእኔ ተቃራኒ ካለዉ ወንበር ላይ ተቀምጣ ቦርሳ ዉስጥ በምትያዝ ትንሽዬ የፊት መስታወት ላይ አተኩራ ፊቷን በማስዋብ ተግባር ላይ ተጠምዳለች፡፡ የምሸሸዉን ትዝታ የሚጎትት የኩኩ ሰብስቤ ዘፈን ግድግዳው ላይ በተሰቀሉት ስፒከሮች በኩል ጐላ ብሎ ይንቆረቆራል፡
 የሰማዩ ዝናብ ከዳመናዉ መጣ
 ከዐይኔ የሚመነጨዉ ኧረ ከየት መጣ?
ተመራምሬያለሁ እኔ ግን በሐሳቤ
ዕንባዬ የመጣዉ ነዉ እኮ ከልቤ
ክረምት አልፎ በጋ ሁሌ አይቀርም ሲባል
የእኔ ዕንባ አላባራም ገና ነዉ ይዘንባል
ከአንጀቴ ከሆነ ዕንባዬ የሚፈሰዉ
ምክንያቱ አንተ ነህ አላዉቅም ሌላ ሰዉ
እኔ እወድሃለሁ ፍቅሬ አስብሃለሁ
ይወቴ በሙሉ ያንተ ነዉ ብያለሁ
ሲጋራዬን እያቦነንኩ ዘፈኑን ተከትዬ በትዝታ እየተብሰከሰኩ ሳለ ከእኔ እኩል እዚህ ቡና ቤት ግልሙትና የጀመረችዉ መክሊት (ቅፅል ስሟ ሮዛ) በቡና ቤቱ የጀርባ በር በኩል ዘልቃ እየተጣደፈች መጥታ ጉንጬን ሳመችና ባልኮኒዉ አጠገብ ተሰብስበዉ ለሚያወጉት ሴቶች ለስንብት እጇን አዉለብልባ ቤቱን ለቃ ተሰወረች፡፡ አጠገቤ መጥታ ሳለ ነስንሳዉ የሄደችዉ ስርንን የሚበጥሰዉ ርካሽ ሽቶዋ ጠረን ገና በአየር ተጠርጎ ስላልተወሰደ ምቾቴን አጓድሎታል፡፡ መክሊት እዚህ ቡና ቤት ሥራ የጀመረችዉ ከእኔ ቀድማ ነዉ፡፡ በቀለም ትምህርት እስከ ኮሌጅ ገፍታለች እየተባለ ስለሚወራ ‘ምሁሯ’ የሚል የአግቦ ስም ሰጥተናታል፡፡ ከእሷ በቀር እዚህ ቡና ቤት የምንሠራ ብዙዎቻችን ከሃይስኩል አልዘለቅንም፡፡ ደግሞስ ቀለም ለሴት ልጅ ምን ይፈይዳል? ሴት ልጅ ቁንጅና ይኑራት ብቻ፡፡ መልክ ካለ ሁሉ አለ፡፡
ይህን ብሽቅ ሥራ እየሠራሁ ረብጣ ገንዘብ አፍሳለሁ፤ ግን ይህ ነዉ የሚባል የአፈራሁት ጥሪት የለም፡፡ የዘወትር ጥረቴ የዕለት ቀዳዳዬን ከመሙላት ዘሎ አያዉቅም፡፡ ማለቴ የወደፊት ዕጣዬን በቀቢፀ ተስፋ የምጠብቅ ሰዉ ነኝ፡፡ ደግሞስ የወደፊቱን ጊዜ አስረግጦ መተንበይ የሚችል ማን ነዉ? ሰዉ በዕጣ ፈንታዉ እግረ ሙቅ የተጠፈረ ፍጡር ነዉ፡፡ ማለቴ ሕይወት ከሰዉ ልጅ ትልም አፈንግጦ በዘፈቀደ በራሱ ቅያስ የሚነጉድ ነዉ፡፡ እናም የሰዉ ድካም ከንቱ ነዉ፡፡ እነሆ ለምሳሌ፣ ከቀናት በፊት የምሠራበት ቡና ቤት ባለቤት ወይዘሮ ሮማን ብቸኛ ልጅ በሠርጓ ዋዜማ እንደ ሸክላ ተሰበረች፣ ገና በለጋ ዕድሜዋ፡፡ ያ ሁሉ ልፋቷ  በሞት ተደመደመ፡፡ አሁን እንደዉ ያን ዉብ ገላ ምስጥ ይበላዋል? የሰዉነት ፋይዳ ምንድን ነዉ? ሰዉ ከትቢያ የሚልቅ ዋጋ አለዉን? ሰዉ ከጉንዳን፣ ከድንጋይ፣ ከአሸዋ፣ ከአፈር በምን ሚዛን ይልቃል? ሕይወት ፋይዳ ቢስ አይደለምን? በየትኛዉም ቅፅበት እንዳልነበር የሚሆን ወረት፡፡   
 የእኔ የኑሮ ርዕዮተ ዓለም የአሳማ ነዉ፡፡ ሀፍተ ሥጋ ወዳድ ነኝ፡፡ ለነገሩ የእኔ ኑሮ ሥጋ ለሥጋ አይነት ነዉ፡፡ እናም በልቼ እንዳድር ያበቃኝን ሥጋዬን ማዋደዴ የሚያስደንቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ ዉበቴ እስካልረገፈ ድረስ በልቼ ማደር እችላለሁ፡፡ የሕይወት ርዕዮተ ዓለሜን ሌሎች አያዉቁትም፡፡ ቢያዉቁት ምናልባት ይሳለቁብኝ ይሆናል፡፡ እኔ ግን ለለግጣቸዉ ቁብም የለኝ፡፡ ስለ ነገ ለምን ልጨነቅ? ደግሞስ በሰቀቀን የተቀበልነዉ ትናንት እንደ ጥላ እንደዘበት ሲያልፍ አልታዘብንም? ታዲያ ነገ ምኑ ያጓጓል? ከድካም በቀር ከትናንት ኑረት ምን አተረፍኩ? መጪዉ ጊዜ ከኖርኩት ትናንት የተለዬ ሊሆን ይችላል?  
ባልኮኒዉን ከበዉ ቢራ የሚጨልጡት ጋለሞታ የሥራ ባልደረቦቼ ሳቅና ንትርክ አለሁበት ድረስ ይሰማል፡፡ ያዉ እንደ ለመዱት ሰዉ እያሙ ይሆናል፡፡ የቡና ቤት ሴት እንደ ሀሜት ከልቧ የምትወደዉ ነገር የለም፡፡ አብዛኛዉ የቡና ቤት ወሬ በግለሰቦች ታሪክ ላይ የሚሽከረከር ነዉ፡፡ መነሻዉም መድረሻዉም የሌሎች የተሸሸገ ጀርባ ነዉ፡፡ የሌሎችን የተሸሸገ የጀርባ ታሪክ የመቅደዱ ሂደት ተወዳጅ የሆነዉ ሁሉም የወሬ ኤክስፐርት፣ የወሬ ፕሮፌሰር የገዛ ሕይወቱን በከፊልም ቢሆን ተፅፎ ስለሚያገኝበት ነዉ፤ ስለሌሎች ማዉራት ስለራስ መስማትም ጭምር በመሆኑ ነዉ፡፡
ማኅበራዊ መስተጋብሬ ሰፊ ቢሆንም አንደበተ ቁጥብ ነኝ፡፡ በእዚህም ምክንያት አንዳንዶች ጋግርታም ናት ይሉኛል፡፡ ዝምታዬ ማንነቴን የጋረድኩበት ጭንብል ነዉ፡፡ ምስጢሬን በልቤ እቀብራለሁ እንጂ ለሌሎች አልነዛም፣ ወዳጆቼ እንኳ ልቤን አያዉቁትም፡፡ ጭንብሌ ቢገፈፍ የሚገለጠዉ ግብዝነቴ፣ ቂመኛነቴ፣ ከሀዲነቴ፣ ራስ ወዳድነቴ፣ ቅናቴ፣ ሀኬተኛነቴ፣ ጨካኝነቴ እና ሴሰኛነቴ ነዉ፡፡ አንደበተ ቁጥብነቴ ስሜ በሌሎች እንዳይጠለሽ የጋረደ ግምጃዬ ነዉ፣ በሐሜት ከመብጠልጠል የሚተርፍ ሰዉ ባይኖርም፡፡ ክፉም ሆንክ ደግ በሌለህበት እንደ ሙዳ ሥጋ ትቦጨቃለህ፣ እንደ ቋንጣ ትዘለዘላለህ፡፡ ቢሆንም ግን ቁጥብነትን የመሰለ ነገር የለም፡፡ ወዳጅ አገኘሁ ብሎ ለባዕድ ገመናን ገልጦ መንዛት አይገባም፡፡ ቀንደኛ ጠላቶቻችን ትናንት አብረዉን የበሉ አይደሉምን? መቃብራችንን ለመማስ የሚማስኑት የአሟሟታችንን መንገድ ስለሚያዉቁት አይደለምን? የዉድቀታችንን ፈለግ? የዛሬ ወዳጆቻችን ነገ ሲክዱን ጠልፈዉ የሚጥሉን በሽንቁራችን ገብተዉ ነዉ፡፡        
ቡና ቤቱ ዉስጥ ከሚሠሩ ሴቶች በንፅፅር ያልጠለሸ ስም ያለኝ እኔ ነኝ፣ ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ቢሆንም፡፡ ላይ ላዩን ሐሜትን የምፀየፍ ልምሰል እንጂ የሰዎችን ጀርባ መበርበር እወዳለሁ፡፡ አንዱ የሌላዉን ምስጢር እንዲዘከዝክልኝ ማድረጉም ለእኔ ተራ ተክህኖ ነዉ፡፡ የሌሎችን ጀርባ የማወቅ ጉጉት የሌለኝ ዳተኛ መስዬ ብታይም፣ ማን ምን እንደሆነ፣ ምን እንዳደረገ፣ ምን እንደሚፈልግ ልቅም አድርጌ አዉቃለሁ፡፡ ለምሳሌ፣ አዜብ ለጋስ ብትሆንም ከእኔ የባሰች በካና ናት፡፡ ቂልነቷ የበዛ ነዉ፣ ወርቅ ላበደረ ወርቅ የምትል ናት፡፡ ማሕሌት (ቅፅል ስሟ ቲና) የታወቀች ሐሜተኛ ናት፡፡ መክሊት የረባ ያልረባዉ ነገር ቶሎ የሚያስከፋት ሆደባሻ ናት፤ የመከዳት ታሪኳን ምሬት ጆሮ ለሰጣት ሁሉ በመዘክዘክ የምታሰለች ችኮ፡፡ ባመነዉ ያልተከዳ ማን ነዉ? ሄለን (ቅፅል ስሟ ሊሊ) አዱኛ አምላኪ ናት፣ ወዳጅነትን የምትሰፍረዉ በጥቅም ሚዛን ነዉ፡፡ ርዕዮቷ የተገነባዉ “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ” በሚለዉ ብሂል ነዉ፡፡
ማሕሌት እና ባልኮኒዉ ጋ ተቀምጦ ቢራ ሲጠጣ የነበረዉ ቋሚ ደንበኛዋ አበራ ዳንስ ወለሉ ላይ ወጥተዉ በባህር ማዶ ዘፈን ተቃቅፈዉ መደነስ  ጀምረዋል፡፡ ማሕሌት ያን ታላቅ ዳሌዋን እያዉረገረገች፡፡ የሁሉም ሰዉ ዐይን እነሱ ላይ ነዉ፡፡
     ከዉጪ ሪዛሙ ሸበላ ገብቶ ፊት ለፊቴ ከሚገኘዉ ቦታ ላይ ተቀመጠ፡፡ ረጅም ነዉ፣ መልከ መልካም፡፡ የቀይ ፊቱን ሰፊ ወሰን የሸፈነዉ ሪዙ መጀመሪያ ቀን መጥቶ ካየሁት ጥቂት በመጎፈሩ ሳይሆን አይቀርም ግርማዉን አግንኖታል፡፡ የተቀመጠዉ ከባልኮኒዉ ጥቂት ራቅ ብሎ ካለዉ ቦታ ነዉ፡፡ የሆነ ገፅታዉ ከቀድሞ ፍቅረኛዬ ጋር ይመሳሰላል፣ አፍንጫዉ፣ የትከሻዉ ስፋት፣ የከናፍሩ ስስነት ምናምን፡፡ በዐይን ቋንቋ ተነጋግሮ ትኩረት ለመሳብ የሸበላዉ ዐይኖች ወደ እኔ የሚወረወሩበትን አጋጣሚ በቋፍ እየጠበቅሁ ነዉ፡፡ በተቃራኒዉ፣ ሸበላዉ ዐይኑን ሄለን ላይ ተክሏል፡፡ ቀልቡ ሳይወዳት አልቀረም፡፡ እዚህ ቡና ቤት ከምንሠራዉ ጋለሞቶች ብዙ ደንበኛ ያላት ሄለን ናት፡፡ ሄለን ከእኔ የባሰች ጋግርታም ብትሆንም በሰዉ የመወደድ ፀጋን የታደለች የጠይም ቆንጆ ናት፡፡ ቀዝቃዛነቷ ስትፈጠር ጀምሮ የተጣባት ይሁን ዘግይቶ የተከሰተ በዉል አይታወቅም፡፡ ዉበቷ ነዉ ድብርቷን ሸፍኖ ዓለም መኖሯን እንዳይዘነጋ የረዳት፡፡ ብዙ ጊዜ እኛ ሥራ አጥተን ጦማችንን ስናድር እሷ ወንድ አማርጣ ትወጣለች፡፡ ሄለን ሐሜት ልብሷ ነዉ፤ ቡና ቤቱ ዉስጥ የእሷ ስም ሳይብጠለጠል ቀርቶ አያዉቅም፡፡
ሸበላዉ ዐይኖቹን ከሄለን ላይ ነቅሎ ወደ እኔ ሲወረዉር ዐይን ለዐይን ተጋጨን፣ ተሽኮርምሜ ዐይኖቼን ሰበርኩ፡፡ እንደገና ባልኮኒዉ ዙሪያ የጦፈዉን ሁካታ የምከታተል መስዬ በስላቺ ስሰልለዉ አሁንም ዐይኖቹን እኔ ላይ እንደሰፋ ነዉ፡፡ ሸበላዉ ሴት አዉል ይመስላል፡፡
የባልኮኒዉን ትዕይንት መታዘብ ትቼ ወደ ሸበላዉ ሳማትር አዜብ ፊቱ ተገትራለች፣ እነዛን አንደ ኮርማ በሬ ቀንድ ከርቀት የሚታዩትን ጡቶቿን ወድራ፡፡ ያለ ወትሮዋ ደርሳ አስተናጋጅ መሆኗ ደንቆኛል፡፡          
ጎኔ ካለዉ ጠረጴዛ (በግራዬ በኩል) ጥንዶች ተቀምጠዋል፡፡ ወንድየዉ ፀጉሩን ድሬድ ሎክ ተሠርቷል፡፡ ሙሉ ቀልቡን አብራዉ ካለችዉ ሴት ጋር ያደረገ ቢመስልም በአይኑ ቂጥ እኔን ሰርቆ ማየቱን አላቆመም፡፡                        
ሸበላዉን እየሰረቅሁ መመልከቴን ቀጥያለሁ፡፡ ቢራ የተሞላ ብርጭቆዉን አንስቶ ወገቡ ድረስ ተጎነጨና ሲጋራዉን ምጎ ጭሱን አየር ላይ ተፍቶ ቡሹን ሲጋራ መተርኮሻዉ ላይ ደፈጠጠ፡፡ አዜብ ቢራ ካቀረበችለት በኋላ እንኳ ከሦስቴ በላይ ወደ እሱ ተመላለሰች፡፡ ቀልቡ ሳይጠላት አልቀረም፤ እንጂማ ወንበር እንድትጋራዉ ጠይቆ ቢራ ይጋብዛት ነበር፡፡ ከስፒከሩ የፍራንክ ሴናትራ መረዋ ድምፅ መንቆርቆሩን ቀጥሏል፡፡
ሸበላዉ ዐይኖቹን ዳንስ ወለሉ ላይ ተክሏል፡፡ የእነ ማሕሌት ዳንስ የመሰጠዉ ይመስላል፡፡ ዐይኖቹን ከዳንስ ወለሉ ላይ ትዕይንት ላይ ሳይነቅል ሁለተኛ ሲጋራዉን አቀጣጠለ፡፡ ጎኔ የተቀመጡት ጥንዶች የጦፈ ወግ አለሁበት ድረስ ጎልቶ ይሰማል፣ ጆሮዬን ጥዬ የሚሰልቁትን ወግ ማዳመጥ ጀመርኩ፡    
“ኧረ እባክህ! በጣም ይገርማል! ምን አፋታቸዉ?” ሴቷ፡፡
“ምን እባክሽ፣ እሱ መች ይረባል፡፡ ያቺን የመሰለች ልጅ …” ወንዱ፡፡ ከፊል የፊቱ ገፅ ብቻ ነዉ የሚታየኝ፡፡ ትከሻ ሰፊ ነዉ፡፡   
 “እንዴት አወቅክ አንተ?”  
 “የድሮ ወዳጄ አልነበር እንዴ?”
“ዉሻ ነዉ ለካ አንተ?”
“እየነገርኩሽ! እሱ አመሉ ነዉ፣ በአንድ አይረጋም፡፡ ዛሬ ከአንዷ ጋር አይተሽዉ ከሆነ ነገ ከሌላዋ ጋር ታገኝዋለሽ፡፡ እሚገርምሽ እኮ ከበፊቷ አንድ ወልዷል፡፡”
“ይገርማል! ግን እኮ አንደዛ አይነት ሰዉ አይመስልም፡፡”  
“ቢራ ይጨመራ? ጠጪ እንጂ!” አጨብጭቦ አስተናጋጇን ጠራ፡፡
“እንዴ ይብቃን! ልታሰክረኝ ነዉ እንዴ አላማህ? በዚያ ላይ መሽቷል፡፡”
“እንጫወት እንጂ፣ ገና እኮ ነዉ?”
“ምን ማለትህ ነዉ? ባለትዳር መሆኔን ረሳኸዉ? አንተን ብዬ እንጂ …?”
“ተይ እንዲህ አትበይ፡፡ ምንም ቢሆን የመጀመሪያሽ እኮ እኔ ነኝ፡፡”
“እኔስ አንተን ብዬ መስሎኝ ኃጢያት ዉስጥ የገባሁት፡፡ ተረዳኝ እንጂ!”      
ፊት ለፊቴ የተቀመጠዉ ሪዛም ሸበላ ዐይኖቹን ከነ ማሕሌት ላይ አሽሽቶ ወደ እኔ ሲዞር ለሁለተኛ ጊዜ ዐይን ለዐይን ተጋጨን፣ ቀድሜ ዐይኖቼን ሰበርኩ፡፡ ከጎኔ ያሉት ጥንዶች የሚቀዱት ተባራሪ ወሬ አሁንም በጆሮዬ መስረጉን ቀጥሏል፡፡
“ማመን ይከብዳል! እዉነትህን ነዉ? እሷስ እንዴት እሽ አለች?” ሴቷ፡፡
“አንቺ ደግሞ፣ ሰዉየዉ እኮ ዮናስ ነዉ፡፡ ምን ነካሽ?” ወንዱ፡፡
“ኧረ እባክህ? አሳምኗት ነዉ አየህ?”
“ምላሱ ጤፍ ይቆላል ስልሽ!”
ማሕሌት እና አበራ አዲስ የተከፈተዉን ዘፈን ምት ተከትለዉ ተቃቅፈዉ መደነሱን ቀጥለዋል፡፡ የማሕሌት ቁመት ከአበራ ስላጠረ ጎበጥ ብሎ ሊያቅፋት ተገዷል፡፡
 የዳንስ ወለሉን ትእይንት መታዘቡን ትቼ ወደ ሸበላዉ ሳማትር ለሦስተኛ ጊዜ ዐይኖቻችን ተጋጩ፣ በአጸፋው ፈገግታዬን ብልጭ አድርጌለት ዐይኖቼን ሰበርኩ፡፡
 ጆሯችንን ሲያደነቁር የነበረዉ ሙዚቃ አብቅቶ ሌላ ሲቀጥል ማሕሌት እና አበራም በዳንስ ብዛት በመዳከማቸዉ እንደተቃቀፉ (እሷ የፊቷን ላብ በአይበሉባዋ እየጠረገች) ወደ መቀመጫቸዉ ተመለሱ፡፡
ባልኮኒዉ ጋ የተቀመጠችዉ ሄለን ቢራዋን ትጨልጣለች፡፡ጎኔ የነበሩት ጥንዶች ወጥተዉ እንደሄዱ ሸበላዉ ከመቀመጫዉ ተነስቶ ቢራዉን ይዞ ወደ እኔ መጣ፡፡   “መቀመጥ እችላለሁ?” አለ ፊት ለፊቴ ቁሞ በትኩረት እያስተዋለኝ፡፡ ድምፁ አስገምጋሚ ነዉ፡፡    “ይቻላል፡፡” አልኩ ፈገግ ብዬ ፊቴ ወዳለው ሶፋ እንዲቀመጥ እየጠቆምኩ፡፡  “አመሰግናለሁ፡፡” በቁሙ ከአጭር ቀሚሴ የተረፉትን ጭኖቼን በስርቆት ገርምሞ ወንበር ስቦ ፊት ለፊቴ ተቀመጠ፡፡
“ብቻዬን መቀመጡን ጠልቼ ነው አንቺ ጋ የመጣሁት፡፡”
“ጥሩ አደረክ፣ ከሰው ጋር መጫወት መልካም ነው፡፡” ሽቶዉ ከቡና ቤቱ የሲጋራና መጠጥ ጠረን በላይ ነግሶ በአፍንጫዬ መስረጉን ቀጥሏል፡፡
 “ሀኒባል እባላለሁ፡፡”
 “ጁሊ፡፡” እጅ ለእጅ ተጨባበጥን፡፡
 “ታዲያስ ጁሊ? ሕይወት እንዴት ነው?” አለ ወንበሩን ወደ ፊት ስቦ፡፡ ጥያቄዉ ብሽቅ ነዉ፡፡
 “ሁሉም መልካም ነዉ፡፡” የዉሸት ፈገግ ብዬ፡፡  
  “ካዛንቺስ እንዴት ተለዉጧል እባክሽ! ሁሉ አዲስ ሆነብኝ እኮ፡፡”
  “ካዛንቺስ ዉስጥ ምን አዲስ ነገር አየህ?”
  “ብዙ ነገር፡፡”
 “ለምሳሌ?”
“ለምሳሌ እንደ አንቺ አይነት ዉብ ሴት፡፡”
“ሴት የትም አለ፡፡”
“ባህር ማዶ ነበርህ?” ወንበሬን ወደ እሱ አስጠጋሁ፡፡
                  “ኧረ እዚሁ ነኝ፡፡ ከአገር ወጥቼ አላዉቅም፡፡ በነገርሽ ላይ ከአገሬ ወጥቼ መኖር አልሻም፡፡ ኢትዮጵያ እኮ ልዩ አገር ነች፣ ሐበሻ እኮ ድንቅ ህዝብ ነዉ፡፡” የሐበሻ ድንቅነት አልተዋጠልኝም፡፡ ሐበሻ ምድር ላይ ያለዉስ ልዩ ነገር ምንድን ነዉ? ሀኒባል ምን ሊለኝ እንደ ፈለገ በቅጡ አልገባኝም፡፡ ፈረንጂ እሴት አልቦ ነዉ ማለቱ መሰለኝ፡፡ ተሳስቷል፡፡ ወግ እና ባህል የሌለዉ ህዝብ የለም፡፡ ብቻ ሀኒባል ምን ሊለኝ እንደ ፈለገ በዉል አልገባኝም፡፡    
 “ካዛንቺስን ከረገጥህ ቆይተሃል ማለት ነዉ?”  
“አዎ፡፡ ረጅም ጊዜ ሆነኝ፡፡”  
“ለዚያ ነዋ ሁሉ አዲስ የሆነብህ?”
“በትክክል፡፡” ሲጋራ አቀጣጠለ፡፡
“ታጨሻለሽ?” ማልቦሮ ፓኮ እየዘረጋልኝ፡፡
“አዎ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡”
ሲጋራዬን ለኮሰልኝ፡፡”      
 “ሐብልሽ ያምራል፡፡”
“አመሰግናለሁ፡፡” ረጅም ዘመን አንገቴ ላይ ታስሮ የኖረዉን ሐብሌን ያደነቀ ሰዉ አልነበረም፡፡” ሐብሉ የሟቿ እናቴ ነዉ፡፡ ካደግሁ በኋላ ነዉ የአሳደገችኝ አክስቴ በአደራ አስቀምጣ ኖራ ያወረሰችኝ፡፡
“ቢራ ይጨመራ?” መልሴን ሳይቀበል በምልክት አስተናጋጅ ጠራ፡፡ ሦስተኛ ቢራዬን አዘዝኩ፡፡
ሀኒባል እጅግ ጨዋታ አዋቂ ነዉ፡፡ ወጉ ለዛ አለዉ፡፡ ስለ ሕይወት ያለዉን የካበተ ዕዉቀትም መታዘብ ችያለሁ፡፡               
አራተኛ ቢራዬን ላዝ በዐይኖቼ አስተናጋጅ ሳማትር የቡና ቤቱን በመሸተኛ መጨናነቅ አስተዋልኩ፡፡
 ከእረፍትና በአል ቀን በስተቀር የቡና ቤታችን ሥራ ቀዝቃዛ ነዉ፡፡
ካዛንቺስ የሚደምቀዉ በበአልና በእረፍት ቀናት ነዉ፡፡  
ከሀኒባል ጋር ቡና ቤቱ ዉስጥ ቢራ እየጠጣን አምሽተን እኩለ ሌሊት ላይ መኖሪያ ቤቱ ለመሄድ ተዋዉዬ ተያይዘን በመኪናዉ ጉለሌ አቀናን፡፡   
                  * * *
   ሀኒባል ቤት አልጋ ላይ ሰፍሬያለሁ፡፡ መኝታ ቤቱ ሰፊ ነዉ፣ ጎን ለጎን ተራርቀዉ የተሠሩ ሁለት መስኮቶች አሉት፡፡ ፊት ለፊቴ ግድግዳዉ ላይ ሀኒባልና አንዲት ጠይም ሴት ሐይቅ ዳርቻ የተነሱት ባለ ቀለም ፎቶግራፍ ተሰቅሏል፡፡   ሀኒባል ብዙ ብር ከፍሎኝ ነዉ ቤቱ ያመጣኝ፡፡ ሌሎች ደንበኞቼን አስከፍል ከነበረዉ እጥፍ ነዉ ያስከፈልኩት፡፡ ሸርሙጣ ብሆንም በዉድ እንደምገኝ ሀኒባል እንዲያዉቅ ብዬ ነዉ እንዲህ ማድረጌ፡፡ ተመኔ የገላዬን ዉድነት ስለሚያዉጅ፡፡
 “ቤቴ ይህን ይመስላል፡፡” አጠገቤ ወንበር ላይ ተቀምጦ ያጨሳል፡፡ ከላይ እርቃኑን ነዉ፡፡ ደረተ ሰፊ ነዉ፣ ክንዶቹ ፈርጣማ ናቸዉ፡፡
 “ያማረ ነዉ፡፡”   
“ምን እባክሽ … ሴት ከሌለበት ባዶ ቤት ምን ይረባል?”                      
 “እዉነት ነዉ፡፡ አብሮነት ቤት ያሞቃል፡፡”
“አግብተህ ነበር?”
“ኧረ በጭራሽ፡፡” ከተቀመጠበት ተነስቶ መጥቶ ጎኔ ተጋደመ፡፡
“አንቺስ ትዳር አልሞከርሽም እስካሁን?”
“አዎ የትዳሩን ዓለም ገና አላየሁትም፡፡” ቀይ የብርሃን ወጋጋን የሚረጨዉን የራስጌያችንን መብራት ካበራ በኋላ የጣሪያዉን ተቀናቃኝ ብርሃን ደረገመዉ፡፡   “እንዴት እስከ አሁን?” ተጠግቶኝ ወገቤን አቀፈ፡፡ የጠጣዉ ቢራ ጠረን ከቀዝቃዛዉ አየር ጋር ተቀላቅሎ በአፍንጫዬ ይሰርጋል፡፡  “ገና ልጅ እኮ ነኝ፡፡ አረጀዉብህ እንዴ? ሂ ሂ ሂ፡፡” ከወገቤ የሸሸዉ እጁ የዉስጥ ሱሪዬን ዘልቆ ጭኖቼ መሐል ገባ፡፡ እጁን አሸሸሁ፡፡ “እሱስ ገና ልጅ ነሽ፡፡ የማግቢያ እድሜ ላይ ነሽ ብዬ ነዉ፡፡”
 “ልቤን የረታ ወንድ ገና አላገኘሁም፡፡” መልሴን በሳቅ አጀብሁ፡፡ ይቺ መልሴ ቅጥፈት ናት፡፡ መቸስ ሸርሙጣ መሆኔ ባል አሳጣኝ አልለዉ ነገር፡፡ ሸርሙጣነቴ ነዉ በፍቅሩ የምሰፈሰፍለትን የቀድሞ ደንበኛዬን እስክንድርን አግባኝ ብዬ አፍ አዉጥቼ እንዳልጠይቀዉ የገደበኝ፤ በራስ መተማመኔ ተንኮታኩቶ፡፡ ሸርሙጣን ማን ለትዳር ያጫል? የእኔ እስክንድር የወንዶች ቁንጮ፡፡ ልቤ ለፍቅር እጁን የሰጠዉ ለእሱ ነዉ፡፡ ግን፣ እሱ እንደማመልከዉ አያዉቅም፡፡ ከምንም ነገር አብልጬ እንደምወደዉ አያዉቅም፡፡ ለእሱ እኔ ባሻዉ ጊዜ የሥጋ አምሮቱን የሚወጣባት ተራ ሴት ነኝ፡፡ በልቡ ዉስጥ ከእዚህ የሰፋ ሥፍራ የለኝም፡፡ የይሉኝታን እግር ብረት ሰብሬ ከእሱ ጋር እስከ ሕይወቴ ፍፃሜ ድረስ አብሬዉ ልኖር እንደምመኝ አልነገርኩትም፡፡ ከእሱ ጋር ስተኛ እንደዛ የምሆነዉ የፍትወት ዛር የተጣባኝ ቅንዝረኛ ስለሆንኩ እንጂ በፍቅሩ አብጄ መሆኑን አያዉቅም፡፡ ቀንደኛ ጠላቴ ይሉኝታ ነዉ፣ ያፈቀርኩትን ሰዉ የግሌ እንዳላደርግ የገደበኝ፡፡ ጠይቄዉስ ቢሆን? ጥያቄዬን ይቀበል ነበር? ምናልባትም ጥያቄዬን ይገፋዉ ይሆናል፡፡ ሁሉም ወንድ አድኖ ማግባት የሚፈልገዉ ጨዋ ሴት ነዉ፡፡ በግብሯ እንዳልተባበሩ ሁሉ ሸርሙጣን ፈላጊ የለም፡፡ ግን ሁሉም ወንድ ገላዬን ፈላጊ ነዉ፡፡ ይኸን ገላዬን፣ ሁሉም ሳይረግፍ ሊያቅፈዉ የሚራኮትበትን፡፡ ከዛስ? ከዛማ ሁሉም ይንቁኛል፣ ምን ቢያስጎመጅ የሸርሙጣ ገላ እፅበለስ ነዉ በሚል ብሂል፡፡ አቅፈዉኝ አድረዉ ሲነጋ በመንገድ ሲያዩኝ ሸሽተዉ መንገድ ይለዉጣሉ፡፡ ታዝቤ ዝም እላለሁ፡፡ ሸርሙጣን ማነጋገር ዉርደት ነዉ? በድብቅ የማትሸረሙጥ ሴት ማን ናት? ሁሉስ ጨዋ ነኝ ባይ ወንድ ዘላ ዘላ የደከማትን ሴት አይደል በጋብቻ ዉል ተብትቦ ቤቱ የሚያስገባዉ? ለብቻ የተሸለመዉ የሚመስለዉ የሚስቱ ገላስ የሌሎች ትራፊ አይደል? ሸርሙጣ የተለየች ፍጡር ናት? ገንዘብ ያለዉ ወንድ የሚተኛት ሴት ናት ሸርሙጣ፡፡ ሁሏስ ጨዋ ነኝ ባይ ግብዝ ሴት ኪዳን ሽራ ወንድ እንደ ቡታንታ፣ እንደ ቀሚስ፣ እንደ ኮት፣ እንደ ሸሚዝ እየለዋወጠች በሰበብ አስባቡ የተባእት ኪስ አታራቁትም? ሁሉስ ጨዋ መሳይ ወንድ (አንገት ደፊ አገር አጥፊ) ወንድ የመለዋወጥ ገድል ካላቸዉ ኮሌጅ በጣሽ አለሌዎች ጋር አብሮ አልተንዘላዘለም? መንገዱ ነዉ እንጅ ተግባሩ አንድ አይነት ነዉ፡፡
 “እዉነት ብለሻል፡፡ እህል ዉሃ ካልሰመረ አብሮነት ከንቱ ነዉ፡፡” ያሸሸሁት እጁ መልሶ ዉስጥ ሱሪዬን ዘልቆ ገባ፡፡ መልሼ አልተከላከልኩም፡፡ በመሐላችን ታላቅ ዝምታ ነገሰ፡፡ ዳሌዬን የሚታከከዉ አፍረቱ በሁለመናዬ እሳት ለኩሶ ሊያነደኝ ደርሷል፡፡ ገላዬ ላይ የሚርመሰመሱት ጣቶቹ መላ አካሌን እጅግ አግመዉታል፡፡
 “የዉቦች ንግስት ነሽ፡፡” ዐይኖቹ ዐኖቼ ላይ ተተክለዋል፡፡ የቅንዝር ነበልባል ዉስጣቸዉ ይንቀለቀላል፡፡ ልቤ በሀኒባል የዉዳሴ ቃል ደስ ተሰኜ፡፡ ቁንጅናን ከወንድ አንደበት ማድመጥ ያስደስት የለ፡፡ ከሀኒባል ልሳን የሚፈሱት ቃላት ነፍስን ደስ የሚያሰኙ፣ ለጆሮ የጣፈጡ ናቸዉ፡፡ ሀኒባል ልክ እንደ ታላቅ ባለቅኔ ነበር የሚናገረዉ፡፡
  “ጠረንሽ ልዩ ነዉ፡፡” ተስቦ መጥቶ የጎመራ ወይን በመሰሉ ከንፈሮቹ ከንፈሮቼን አተመና አጭር ቀሚሴን አወለቀ፡፡ ቀዩ የብርሃን ዉጋጋን የእርቃን ገላዉን ቅላት አጋኖታል፡፡ እጆቹ አንድም የሰዉነቴ ክፍል ሳይቀራቸዉ መዳሰስ ጀመሩ፡ ፀጉሬን፣ ፊቴን፣ አንገቴን፣ ጡቶቼን፣ ዳሌዬን፣ እምብርቴን፣ ጭኖቼን፣ አፍረቴን… ሰመመን ባህር ዉስጥ እስክሰምጥ ድረስ፡፡ በወሲብ ጥም ነድጄ ስሩ ተነጠፍኩ፣ እላዬ ተከመረ፡፡ አልጋዉ ላይ ድርና ማግ ሆን፡፡ ሀኒባል ቤቱ ባደርኩ በማግስቱ የራት ግብዣ ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ ሳልግደረደረ ግብዣዉን ተቀብዬ ቤቱ አቀናሁ፡፡ ሥጋዬን ሳይወድ አልቀረም፡፡        
                * * *   
 ዛሬ ሀኒባል ወርቁ የሳባ አየለ ባል ነዉ፡፡ የሀኒባልን ቀልብ ማርኬ ደጄን እንዲጠና ያደረግሁት በልዩ ኪነት ነዉ፡፡ ይህን በማድረግ የቀደመችኝ ሴት አልነበረችም፡፡ የቡና ቤታችን አዲስ ደንበኛ ሆኖ በመጣ ሰሞን በፍቅር አንበርክኮ የግሉ ለማድረግ ያልተረባረበች፣ ያልተሽቀዳደመች ሴት አልነበረችም፡፡ በተለይ አዜብ ሀኒባልን ስታይ የሚያደርጋትን ነበር የሚያሳጣት፡፡ እሱን ለመቅረብ ብዙ ጥረት ማድረጓን አዉቃለሁ፣ ፊት ነሳት እንጂ፡፡ በእዚህም ምክንያት ለእሷ ያለኝ ጥላቻ ታላቅ ነዉ፡፡ አዜብ ተወዳዳሪ የሌላት ቆንጆ ብትሆንም ጮሌነት ይጎድላት ነበር፡፡
ወንድን በግዞት ስር የማዋል ጥበቡን አልተካነችም፡፡ በዉድ ሽቶ መታጠብ፣ ፋሽን ጨርቅ መደረት ብቻዉን የወንድን ቀልብ አይስብም፣ ለትዳር አያሳጭም፡፡ እኔ ሳባ ግን ቆነጃጅቱን ተገዳድሬ አሸንፌ ሀኒባልን የግሌ አደረሁ፣ ወንድን የመሳቢያ መግነጢሱን አዉቀዉ ስለነበር፡፡ በሸርሙጣነቴ ያካበትኩት ጥበብ ይህ ነዉ፡፡                     
ሀኒባል ልቡናዉ ዉስጥ የሸሸገዉን ገመና እኔን ተጠልሎ ለመርሳት የሚጥር ምስጢራዊ የሆነ ሰዉ ነዉ፡፡ በተለያዩ ጊዜአት በህቡዕ ልበረብረዉ ብጥርም የጀርባ ታሪኩን ዝርዝር ማወቅ አልቻልኩም፡፡ በቅርቡ እንኳ ያለፈ የፍቅር ሕይወቱን ታሪክ እንዲያወጋኝ በጥበብ የቀደድኩትን የወግ አጀንዳ ጠምዝዞ ዉስኪና አሰልቺ የፖለቲካ ሐሜት ሲግተኝ አመሸ፡፡ ከዚያ በድሪያ የስሜቴን  እሳት ለኩሶ ወደ አልጋ ወሰደኝ፤ የጠየኩትን የምዘነጋ ይመስል፡፡ ይህም ሆኖ፣ ሽንቁሩን ገልቤ ጎዶሎዉን መታዘብ አልተሳነኝም፣ ፍቅር ጎሎታል፡፡ ይኸን ጉድለቱን አስልቼ ነበር በወጥመዴ ተብትቤ የጣልኩት፤ አፍቃሪ ሴት መስዬ በመቅረብ፡፡
ምሁርነቱ በወጥመዴ ከመዉደቅ አላስጣለዉም፡፡
አፍቃሪ መስሎ ሌሎች ልብ ዉስጥ መጎዝጎዝ የተለየ ተክህኖ ይጠይቃል፡፡ ወንድ ልጅ እንደ እናቱ የምታባብለዉን ሴት ያመልካል፡፡ ታዲያ ሀኒባልን ከእኔ ጋር እንደ አለቅት ምን አጣበቀዉና? ብልሀቱ ሌላ ነዉ፡፡ ወንድን በፍቅር ለመጣል ከመነሳት በፊት የልብ ትርታዉን ማወቅ ያስፈልጋል፤ ጥረታችን ከሽፎ ገሸሽ እንዳያደርገን፡፡ ሀኒባል ሊያመልከኝ የተገደደዉ በእሹሩሩዬ ነዉ፤ በፍቅሬ እጅ ሲሰጥ ሸርሙጣነቴ እንኳ ቁብ አልሰጠሙም፡፡
ወንድ ‘እሹሩሩ ፍቅሬን’ እንዲዘፍኑለት ይፈልጋል፣ ሥጋጃ ሆነዉ እንዲጎዘጎዙለት ይሻል፡፡ እሹሩሩ፡፡ ወንድን እሹሩሩ እያሉ ለመኖር ያን ሰዉ ማፍቅር አያስፈልግም ወይ ትሉ ይሆናል፡፡ ወንድን እንደ ባሪያ ገዝቶ ለመኖር ፍቅር ብቸኛዉ መንገድ አይደለም፡፡ ዋናዉ ነገር ኩሸትን መካን ነዉ፤ ቁም ነገሩ ግብዝነትን መላበስ ነዉ፡፡ ሳይወዱ የወደዱ መምሰል፡፡ ሳያዝኑ ያዘኑ መምሰል፡፡ የዉሸት ማንባት፡፡ በጥርስ መሸኘት፡፡ እባብ ሆኖ ርግብ መምሰል፡፡

Read 827 times