Saturday, 17 June 2023 00:00

የሚታዘቡትን ፈረስ ጉቶ ላይ ይጋልቡበታል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አንድ ብልህ ንጉስ በከተማው ውስጥ ሶስት አዋቂዎች ነን እያሉ ህዝቡን ይመክራሉ፤ ያወናብዳሉ የሚባሉ ሰዎችን በተራ በተራ ጠርቶ ጥያቄዎችን ይጠይቃቸዋል፡፡
የመጀመሪያው አዋቂ እንደገባ እንዲህ ሲል ይጠይቀዋል፡-
“ህዝቡ ይውረድ ይውረድ እያለ እያስቸገረኝ ነው፡፡ እኔ ግን በስልጣን ላይ ለመቆየት እፈልጋለሁ፡፡ ምን ባደርግ ይሻላል?”
አንደኛው አዋቂ፡-
“ንጉስ ሆይ፤ እርሶን የመሰለ ደግ ንጉስ ይውረድ ያለው ህዝብ ከእንግዲህ ሊታመን አይገባውም፡፡ ይልቁንም ሊቀጣ ይገባዋል፡፡ ስለዚህ ለመቀጣጫ ከህዝቡ መካከል ቀንደኛ የሚባሉትን አንድ ሶስቱን በአደባባይ ይቅጧቸው። ያኔ ለጥ ሰጥ ብሎ ይገዛል” ሲል መለሰ፡፡
ሁለተኛውን አዋቂ አስጠርቶ፡-
“ህዝቡ ያለ አንተ መኖር አንችልም፡፡ ለዘላለም፤ ይቆይልኝ እያለ አስቸገረኝ፡፡ እኔ ግን ስልጣኔን ማስረከብ እፈልጋለሁ፡፡ ህዝቡ ኑርልን የሚለኝ እውነቱን ይሁን ውሸቱን ለማወቅ ተቸግሬያለሁ። ምን ትመክረኛለህ?”
ሁለተኛው አዋቂም፡-
“ንጉስ ሆይ፤ ይህን ህዝብ አይመኑት፡፡ ይኑሩልን ሲል ይሙቱ ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማወቅ ቀንደኛ የሚባሉት አንድ ሶስቱን አስጠርተው በአደባባይ ቢቀጡ ማታለሉን ትቶ ለጥ ሰጥ ብሎ ይገዛል” አለ፡፡
በመጨረሻ ሦስተኛውን አዋቂ አስጠራና፡-
“ህዝቤ ይውረድ አይለኝም፡፡ ይኑርም አይለኝም፡፡ ዝም ብሎ እየተገዛ ነው፡፡ የልቡን ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ ምን ባደርግ ይሻለኛል?” ሲል ጠየቀው፡፡
ሦስተኛው አዋቂም፡-
“ይህንን ህዝብ አይመኑት። ይሄኔ ሴራ እየጎነጎነ ነው፡፡ ስለዚህ የህዝብ መሪ ናቸው የሚባሉትን ሽማግሌዎች አስጠርተው ሸንጎ ፊት ቢያስገርፏቸው የተዶለተችው በሙሉ ትጋለጣለች፡፡”
ከዚህ በኋላ ንጉሱ ህዝቡ እንዲጠራ አዋጅ አስነገረና፣ ህዝቡ ሲሰበሰብ እንዲህ አለ፡-
“እነዚህ ሶስት አዋቂዎችን አስጠርቼ ´ህዝብ ይጠላኛል ወይ?´ ብል አትመነው! አሉኝ፡፡ ‘ህዝቡ ይወደኛል ወይ?’ ብል አትመነው አሉኝ፡፡ ‘ህዝቡ መውደዱንም መጥላቱንም አልነግር አለኝ‘ ብል አትመነው አሉኝ፡፡ ምን ታስባላችሁ?” ሲል ጠየቀ፡፡
ህዝቡም መክሮ ሲያበቃ በተወካዩ በኩል መልስ ሰጠ፡፡ ተወካዩ የሀገር ሽማግሌም፡-
“ንጉስ ሆይ፤ ከህዝቡ ጋር ስንመክር አንድ እልባት ላይ ደረስን፡፡ እነዚህ ሦስት አዋቂዎች በተለያየ ጊዜ ስለ እርሶ ጠይቀናቸው የመለሱልን መልስ ‘ንጉሱን አትመኗቸው’ የሚል ነበር፡፡ ስለዚህ በወዲህም ወገን በወዲያም ወገን፣ መተማመን እንዲጠፋ አድርገዋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ሊቀጡልን ይገባል” አሉ፡፡
ንጉሱም፡-
“እናንተ ባላችሁት እስማማለሁ። ስለሆነም ቅጣታቸውን ይቀበላሉ። ያም ሆኖ ለናንተም አንድ ምክር ልምከራችሁ። ሁልጊዜ ተነጋገሩ፡፡ ተመካከሩ፡፡ ግልጽ  ሁኑ፡፡ ጥፋት ስታገኙ ጥፋተኛውን ቅጡ፡፡ ንጉስ ያልፋል፡፡ መንግሥት ይለወጣል፡፡ ሁሌም ነዋሪው ህዝብ ነው።” ሲል ነገራቸው፡፡
***
ብልህ ንጉስ ማግኘት መታደል ነው፡፡ የአገር አዋቂዎች ማጣት መረገም ነው፡፡ የሚመካከር ህዝብ መላ ያገኛል፡፡ ችግሩን የማይፈታ ህዝብ በሽታውን እንደደበቀ ህመምተኛ ነው፡፡ ግልጽነት ሲኖር እውነት ወደ አደባባይ ትወጣለች፡፡ ግልፅነት ከመሪዎችም፣ ከምሁራንም፣ ከህዝብም የሚጠበቅ ፍቱን ወርቅ ነው፡፡ ግልጽነት ከአንድ ወገን ብቻ የሚጠበቅ ከሆነ ሌላውን ወገን መሸፈኛ፣ የተንኮል ጭምብል ይሆናልና ጥንቃቄን ይፈልጋል፡፡ ግልፅነት አለቃ ምንዝሩን የሚፈትሽበት መሳሪያ ብቻ ተደርጎ አንዱን ንፁህ፣ አንዱን አዳፋ፣ አንዱን ቀና፣ ሌላውን ጎልዳፋ  ብሎ ለመፈረጅ፣ መጠቀሚያ መሆን የለበትም፡፡ ግልፅነት ሁሉም ላይ የሚሰራ፣ ለሁሉም የሚያገለግል መርህ ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡
ግልፅነት ከብልጥነት መለየት አለበት፡፡ ግልፅ ነኝ ማለት ድብቅነትን መሸፋፈኛ እንዳይሆን ብርቱ ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ አዋቂ ሳይሆኑ የወቅቱን መፈክር ለማንገብ ብቻ አዋቂ ለመምሰል መሞከር ግልፅነት አይደለም፡፡ ከስህተት ሳይማሩ ከስህተት የተማሩ ለመምሰል መሞከር ግልፅነት ከቶ አይደለም፡፡ በአፍ ቂቤ፣ በልብ ጩቤ ይዞ መቅረብ ግልፅነት አይደለም፡፡
“ብቅል ለመበደር የምትሄድ ብቅል ያላስቀመጠችውን ‘ምን ሴት ትባላለች!‘ ትላለች” እንዲሉ፣ አንዱ ካንዱ ላይሻል ነገር ጥፋተኛው እራሱን እንከን የለሽ አድርጎ ሌላውን ጥፋተኛ ቢወቅስ፣ ያኛውን አጋልጦ እራሱን ሸሽጓልና ግልጽነት እሱ ዘንድ ከቶ የለም፡፡ የግልፅነት ስርአት ሁሉን አቀፍ ሊሆን ይገባል፡፡ ከእሙናዊው ተግባር የፈለቀ መሆን አለበት፡፡ ግልፅነት ከሁሉ አስቀድሞ እውነተኝነትን መጠየቁ ለዚህ ነው፡፡
የአስተዳደግ ጉድለት፣ የአስተዳደር ጉድለትን ያስከትላል፡፡ ራሱ በወጉ ሃላፊነቱን ያልተረከበ፣ ራሱ እድገቱን ያላግባብ የወሰደ፤ እራሱ ሹመቱን በኢ-ርቱእ መንገድ የነጠቀ ሰው፤ ስርአት ያለው አስተዳደር ለማስፈን ይቸግረዋል፡፡ ይልቁኑም “ብልጥ ሌባ የቆጮ መቁረጫ ትሰርቃለች” እንደሚባለው ከቆጮውም ይልቅ መቁረጫውን ይዟልና ህግ አውጭም፣ ፈራጅም፤ ገምጋሚም አስገምጋሚም፤ ሰብሳቢም፣ መራጭም፣ ሆኖ ሁሉን ከእፍታው ይጨልፋል፡፡ ጠያቂ የለበትምና ልቡም እጁም አያርፍም፡፡ ሙስናን ለማስፋፋት ቅርብ ሆነ ማለት ነው፡፡ የአገርና የግለሰብን ጥቅም ያደበላልቃል፡፡ የተማረረን ከተማረ በላይ ያደንቃል፡፡ ባለሙያነትንና ባለእውቀትነትን ከአፋዊ ችሎታ በታች ያያል፡፡ ይህን መሳይ ድርጊት ሁሉ የመልካም አስተዳደር አለመምጣት መርዶ ነው፡፡ ያው በፈንታው የዲሞክራሲን በር ይዘጋል፡፡ የሰላምን ወጋገን ይጋርዳል፡፡ የፍትህን ሚዛን ይነጥቃል፡፡
በተለይ እጅግ ወቅታዊ የሆኑትን፣ የአገርም ሆነ የአገርና አገር ጥያቄዎችና ችግሮች በዲሞክራሲያዊና በዲፕሎማሲያዊ  መንገድ መፍታት፣ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አፍጦ የመጣበት ሰአት ነው፡፡ የችግር ቅደም-ተከተልን ጥያቄ (Prioritization ) ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ሁኔታና ከተጎራባች አገሮቿ፣ እንዲሁም ከሉላዊ እንቅስቃሴና መስተጋብር (Global action and Interaction ) ጋር አጣጥሞ ለመጓዝ ይቻል ዘንድ ለአቻ ቦታ አቻ ሰው መድቦ መራመድ፣ ከወደቁ ወዲያ ከመንፈራገጥ ማዳኑ ብቻ ሳይሆን እስከ ፍልሚያው ሄደው ያለውን ጎርበጥባጣና ኩርንችታማ ጎዳና ለመጥረግ በቅጡ ያግዛል፡፡ ጦርነት የሰላማዊ መንገድ መሟጠጫ እንጂ መነሻ መሆን በጭራሽ የለበትም፡፡ አለመዘናጋት ግን አሁንም ወሳኝ ነው፡፡
የጥንቱ የጠዋቱ ሼክስፒር በ‘ሃምሌት’ ውስጥ “ፈጥነህ ጠብ ውስጥ አትስጠም፣ አንዴ ከገባህበት ግን፣ እጅህ ከባላንጣህ ይቅደም!” (ፀጋዬ ገ/መድህን እንደተረጎመው) ያለውን አለመርሳት ደግ ነው፡፡
ረጅም መንገድ አለብኝ ብሎ በርካታ ስንቅ የጫነ ሰው ስንቁን ቅርብ ቦታ መጨረስ የለበትም፡፡ በትንሽ እንቅፋትም መውደቅ የለበትም፡፡ ነገ ሰፊ የምርጫ ትግል ያለበት፣ የዛሬ አዘገጃጀቱ “የሚወጋ ጦር ከእጅ ሲወጣ ያስታውቃል” አይነት መሆን አለበት፡፡ የብዙዎችን ተሳትፎና ድጋፍ በጠዋት ለማግኘት መጣር አለበት፡፡ መፎካከር ለማሸነፍ ብቻ እንዳልነበረ ሁሉ፣ ነገም እንደዚያው መሆኑን አውቆ መጓዝ ያሻል፡፡ መጋቢ ጅረቶች ሁሉ ወደ ወንዝ ለመቀላቀልና የአገር ሃይል ለመሆን እንደሚችሉ አጢኖ፣ ጊዜ መውሰድ አቅጣጫን ማግኘት ያሻዋል፡፡ ጊዜያዊ የአገር ጉዳዮችን ከዘላቂ ፍሬ ነገሮች አነፃፅሮ፣ አንዱ በሌላው እንዳይጋረድ ደህና አድርጎ ማስተዋል የሁሉም ድርጅቶች አጓጓዝ መሆን አለበት፡፡
ዳምኖም አጉረምርሞም ላይዘንብ እንደሚችል ሁሉ፣ ዘንቦም ሙሉ ጥጋብ ላይሆን እንደሚችል፣ ማስተዋል ይገባል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ከህዝብ ያልመከሩበት፣ ህዝብን ያላሳተፉበት አካሄድ መሰረት-የለሽ ፒራሚድ ነው፡፡ ብዙ እድሜ የለውም፡፡ በአጭር ጊዜ ፈተና ይዳከማል፡፡ አዋቂዎቹን እንደፈተሸው ብልህ ንጉስ፣ ጠያቂ የመጣ ዕለት በአደባባይ መጋለጥ ይከተላል፡፡ ብዙም ሳይቆይ በቅንጣት ጥያቄ ግዙፍ ሀጥያት ይታያል፡፡ የሚታዘቡትን ፈረስ ጉቶ ላይ ይጋልቡበታል የሚባለው እንግዲህ ያኔ ነው!   


Read 1614 times