Saturday, 17 June 2023 00:00

“ዘጭ ትላላችሁ፣” እያሉ ያሟርቱብናል እንዴ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...የፈረንጆች 2023 የጉድ ዓመት ሆነና አረፈው እኮ!
እኔ የምለው... እነኚህ ፈረንጆች ምንድነው የሚያሟርቱብን! እንኳን የእነሱ ተጨምሮበት አሁን ያለብንን ቁልል ትከሻችን አልቻለውም፡፡ አንዱ የፈረንጆቹ ዩቲዩብ ቻናል ላይ ምን የሚል አለ መሰላችሁ ...በእዳ ጫና የተነሳ በአውሮፓውያኑ 2023 ዘጭ ሊሉ ይችላሉ ከሚባሉት አሥራ ሁለት ሀገራት የማን ስም በሰባተኛ ደረጃ ላይ ቢጻፍ ጥሩ ነው...የእኛው! ማለት...እነ ቲማቲምና እነ ሽንኩርት በነጋ በጠባ መከራችንን እያበሉን ያለው ሹክ ተባለብን (መቼም የአሳባቂዎች ዘመን ነውና! ቂ...ቂ...ቂ...) ወይስ ‘የምርመራ ጋዜጠኝነት መሆኑ ነው!” 
ስሙኝማ...የእውነት ግን ብዙ ነገሮች የጉድ ዘመን ውስጥ ነን ቢያስብሉ አይገርምም፡፡ የእኛ ብቻ ሳይሆን በተቀረው ዓለም የሚሆነውንና የሚደረገውን ስትሰሙና በምስል ስታዩ ይሄ ‘ኤንድ ታይምስ’ (የዓለም መጨረሻ እንደማለት) የሚባለው ነገር የምር ነው እንዴ ትላላችሁ፡፡
ባስብ ብሠራ ብመኝ
መቼም ዘንድሮ አልሆነኝ
አዘነ ሆዴ ተናደደ
ምነው ይዞኝ በሄደ፣
የሚል ዜጋ እየበዛ ቢሄድ አይገርምም...ሁሉም ነገር  ከአቅሙ በላይ እየሆነበት እኮ  ነው፡፡
እናላችሁ... ከእኛይቱ ሀገር አሻግራችሁ ስታዩ ከደግ ይልቅ በአብዛኛው ክፉው፣ ክፉው ነገር በሚሰማባት ዓለማችን ሁሉም ነገር ...አልፈጠነባችሁም! አሀ...ለምን እንደሆን እንጃ እንጂ ክፉው፣ አስቀያሚው ነገር ሁሉ ከድምጽ ፍጥነት ምናምን መቶኛ ጨምሮ እየበረረ ነው የሚመስለው፡፡
ልክ ነዋ፣ እንደ ማምለጫ፣ እንደ መሸሸጊያ፣ እንደ መተንፈሻ፣ እንደ ትከሻ ማሳያ የምንቆጥራት ‘አማሪካን’ መላ ቅጧ ጥፍት ያላት ነው የምትመስለው፡፡ “እንትና እኮ አሜሪካ ሄደ!” በሚባልበት ወቅት እኮ የአቅም ጉዳይ እየሆነ ነው እንጂ ርችት ሊተኮስ ምንም አይቀርም ነበር፡፡ ሰዋችን በአግራሞት “አሜሪካ ለማኝ አለ ነው የምትሉኝ!” የሚባልበት የመንግሥተ ሰማያት እጩዎች መሰባሰቢያ ትመስል ነበር፡፡ አሁን አሁን ሀገራቸው እየተመሳቀለች፣ አሜሪካውያኑም እየተመሳቀሉ ነው፡፡ (እስቲ ደግሞ አንዳንዴ እንዲህ ሲሪየስ ሆነን እናውራማ!)
“በ2023 ዘጭ ትላላችሁ፣” እያሉ ያሟርቱብናል እንዴ!
እናማ...ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዛቹ በ‘አማሪካችን’ እየተፈጠሩ ያሉ ነገሮች በእርግጥም “የሰው ልጅ እዚች ዓለም ላይ ያለውን ኮንትራቱን እያገባደደ ነው እንዴ?” ለማሰኘት ምንም አይቀራቸውም እኮ!
ለምሳሌ የባዮሎጂ ቲቸር ‘ፎርዝ ግሬድ’ ያስተማሩን የወንድና የሴት ገለጻ በአፍ ጢሙ እየተደፋ ይመስላል፡፡ ታዲያላችሁ...በዛች ሀገር “አንተ፣” ወይም “አንቺ፣” የሚሉ ተውላጠ ስሞችን መጠቀም ቀስ በቀስ እየተከለከለ ነው ይባላል፡፡ እናማ...ጾታ የተፈጥሮ ጉዳይ ሳይሆን የግለሰቡ ምርጫ ነው የሚል ነገር ሀገሪቱን እያመሳት ነው፡፡ እንዴት መሰላችሁ...ለምሳሌ ፊፍቲ እስኪደፍን ድረስ  “አቶ፣” “ጋሼ፣” “አባወራ፣” ምናምን ሲባል የኖረውና ‘በወንድነቱ’ ለእነሆ በረከት ምናምን ያልሰነፈው እሱዬ ደንገት ተነስቶ “ከዛሬ ጀምሮ አንተ ሳይሆን አንቺ ነኝ...” ካለ በቃ “አንቺ...”  ተብሎ ነው የሚጠራው፡፡ ማንም ሰው “አንተ...” ብሎ ቢጠራው ህግ ፊት ሊወስደው የሚችል ነው የሚመስለው፡፡ ወይም ደግሞ እሷዬዋ ለሰባተኛ ጊዜ ሀያ ስድስተኛ ልደቷን ስታከብር “ከዛሬ ጀምሮ አንቺ ሳይሆን አንተ ነኝ...” ከዛ በኋላ በኦፊሴል “እሱ...”  ትሆናለች ማለት ነው፡፡ እናንተ ምስኪኖች ሆዬ ሳውታቁ... “አንቺ ሶፊ፣ እንዴት ነው ያማረብሽ!” ብላችሁ በሴት ተውላጠ ስም ስለጠቀሳችኋት ጉዳችሁ ፈላ ማለት ነው፡፡ “አንቺ ሶፊ...ይቅርታ፣ አንተ ሶፊ ማለቴ ነው፡፡” እናላችሁ... 2023 እውነትም የሚገርም ዘመን ነው፡፡ደግሞላችሁ... ይሄ የጾታ ቅየራ የሚባለው ነገር አለ፡፡ ማለትም በቀዶ ጥገና ወንዶች ሴት፣ ወይም ሴቶች ወንድ የሚሆኑበት፡፡ እንዳሁኑ ሳይሆን ቀደም ሲልም ይደረግ ነበር ይባላል፡፡ አሁን ነገሮችን ያጦዘው ምን መሰላችሁ...ህጻናት ካለወላጆቻቸው ፈቃድ በራሳቸው ጾታቸውን መቀየር ይችላሉ መባሉ ነው፡፡ ደግሞ ህጻናት ሲባል አሥራ ስምንት፣ አሥራ ስድስት ምናምን ያልሞላቸው ማለት ሳይሆን ከአስር ዓመት በታች ያሉ ህጻናትንም ማለት ነው፡፡ አይገርምም! እና 2023 የሚሉት ዓመት ግራ የሚገባ ዓመት አይደል! እናማ... አንዲት የስምንት ዓመት ህጻን ድንገት “በቃ ወንድ መሆን እፈልጋለሁ...” ካለች ዳዲ እና ማሚ አያገባቸውም፡፡ “ወላጆች መስማማታቸውን መፈረም አለባቸው...” ምናምን የሚል የሆስፒታል ጣጣ የለም፡፡ በአጭሩ ወላጆች በህጻናቱ ምርጫ አያገባቸውም ነው ነገሩ፡፡
“በ2023 ዘጭ ትላላችሁ፣” እያሉ ያሟርቱብናል እንዴ!
በቅርቡ አንዲት (ቀድሞ “አንቺ” ትባል የነበረች ማለት ነው) በቃ “አንተ ነኝ...” ካለች በኋላ ታረግዛለች (ወይም ያረግዛል!) እናላችሁ...ዜናው ይጠቀስ የነበረው “ነፍሰ ጡሯ...” እየተባለ ሳይሆን “ነፍሰ ጡሩ...” እየተባለ ነበር፡፡ “እሱ የምናምን ወር ነፍሰ ጡር ነው...” አይነት ነገር፡፡ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሜሪካ ውስጥ ነገርዬው ከእምነት፣ ከባህልና ከሞራል ከመሳሰሉት ነገሮች ይልቅ ፖለቲካዊ መልክ ይዞ ተናንቀውላችኋል፡፡ ድሮ መንገዶቿ ሁሉ በወርቅ የተነጠፉ ናቸው ሊባልላት ምንም አይቀራት የነበረችው ‘አማሪካን’ ውስጥ እየሆኑ ያሉ ግራ የሚገቡ ነገሮችማ መአት ናቸው፡፡
ስሙኝማ...የተነበዩዋቸው አብዛኞቹ ትንበያዎች ይሳኩላቸዋል የሚባልላቸው ሰዎች ለአውሮፓውያኑ 2023  ተንብየዋል የተባሉ አንዳንድ ነገሮች  እናውራማ፡፡ (አሀ...እኛስ ከወሬው ለምን ይቀርብናል!)
ባባ ማንጋ ቡልጋሪያዊት፣ በአውሮፓውያኑ 1996 በሰባ አምስት ዓመቷ ያረፈች፣ የዓለም ታላላቅ ክስተቶችን በመተንበይ ስሟ የሚነሳ ነው፡፡ እናላችሁ የአሜሪካውን የሽብርተኞች ጥቃት አስቀድማ ተንብያለች ይባላል፡፡ በአውሮፓውያኑ 1989 እንዲህ ብላ ነበር... “አሰቃቂ! አሰቃቂ! የአሜሪካ ወንድሞች በብረት  ወፎች ጥቃት ተፈጽሞባቸው ይወድቃሉ፣ ተኩላዎች በጫካ ውስጥ ይጮሀሉ፣ የንጹሀን ደምም ይፈሳል፡፡” ይህንን ነው ከአሜሪካ የአሸባሪዎች ጥቃት ጋር የሚያያይዙት፡፡ በተጨማሪም የኮቪድ ወረርሽኝን፣ የልዕልት ዲያናን ሞት፣ የቼርኖቢል አደጋን የመሳሰሉትንና ሌሎችን በትክክል ተንብያለች ነው የሚባለው፡፡
የእሷን ትንበያዎች የሚከታተሉ፣ በ2023 እጅግ አውዳሚ የኑክሌር አደጋ እንደሚደርስ ተንብያለች ነው የሚሉት፡፡ የሆነ የኑክሌር ሀይል ጣቢያ ላይ ፍንዳታ ተከስቶ መርዛማ ደመናዎች እስያን ያለብሷታል፡፡ እነኚሁ መርዛማ ደመናዎች ምድርን ከማልበሳቸው የተነሳ ገዳይ የሆኑ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ ይስፋፋሉ ብላለች ነው የሚባለው፡፡
አሁን በሩስያና በዩክሬይን መሀል በሚካሄደው ጦርነት የኑክሌር ጣቢያዎች የመመታታቸው አደጋ ከፍተኛ ነው ይባላል፡፡ ጦርነቱ እየተባባሰ መሄዱና በጦር ሜዳው ላይ እየዋሉ ያሉት ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች አይነትና ብዛት እንዲሁም አውዳሚነት እየናረ መሄድ የኑክሌር ጣቢያ የመመታቱን አደጋ አባብሶታል ነው የሚባለው፡፡ በተለይም ምዕራባውያኑ ግምጃ ቤታቸውን እያራቆቱ ለዩክሬይን እያቀረቧቸው ያሉ የጦር መሳሪያዎች ነገሮችን እጅግ እያወሳሰቡ ነው፡፡ እናማ... 2023 ይህ ሁሉ ጣጣ የበዛበት ለምን እንደሆነ አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡
“በ2023 ዘጭ ትላላችሁ፣” እያሉ ያሟርቱብናል እንዴ!
ደግሞላችሁ በ2023 ሶላር ስቶርም የሚባል የተፈጥሮ ክስተት የዓለምን የአየር ንብረት ያመሳቅለዋል ብላለች ይላሉ፡፡ ታዛቢዎች በዘመኑ ቋንቋ ‘የጸሀይ ሱናሚ ይከሰታል ማለቷ ነው፣’ ይላሉ፡፡ በነገራችን ላይ የጸሀይ ማዕበል ከፍተኛ የቴክኖሎጂዎች መቃወስ ያስከትላል ይባላል፡፡
ይሄ ብቻ መሰላችሁ...በ2023 በአንድ ሀያል ሀገር ባዮሎጂያዊ የጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ ውሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህይወት ይጠፋል ብላለች ነው የሚባለው፡፡ “ይህ እንኳን ሊሆን አይችልም፣” ማለት የዘንድሮዋን ዓለማችንን አለማወቅ ይሆናል፡፡ ያስፈራል፣ በጣም ያስፈራል! ደግሞላችሁ... ቡልጋሪያዊቷ በ2023 ተፈጥሯዊ እርግዝናዎች ያበቃላቸዋል ብላለች ነው የተባለው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በፊት በዓመት ሠላሳ ሺህ ልጆችን ‘የሚያመርት’ ፋብሪካ እየተቋቋመ ስለመሆኑ የተወራው ትዝ ይላችኋል! አዎ፣ ያስፈራል! ሌሎችም ብዙ ነገሮችን ተንብያለች፡፡ደግሞላችሁ.... ፈረንሳዊው ኖስትራዳመስ አለላችሁ፡፡ እሱም የአዶልፍ ሂትለርን ወደ ስልጣን መምጣትና ሌሎች በትክክል የተፈጸሙ ትንበያዎችን አስቀድሞ የተነበየ ነው ይባልለታል፡፡ ኖስትራዳመስ በ2023 ታላቅ ጦርነት ይኖራል ብሎ ተንብዩዋል ነው የሚባለው፡፡ ብዙዎች ይህን ከሩስያና ከዩክሬይን ጦርነት ጋር ያያይዙታል፡፡ “የሰባት ወራት ታላቅ ጦርነት፤ ሰዎች በክፋት የተነሳ ይሞታሉ፣” ነው ያለው፡፡ “ሰባት ወራት...” የሚለውን ሲፈቱት እሱ “ጦርነት” ያለው ሙሉ ጦር ሀይሎች የሚሳተፉበትን እንጂ እዚህም፣ እዛም ብልጭ፣ ድርግም የሚለውን አይደለም ይላሉ፡፡በጦርነቱ የተነሳ የስንዴ ዋጋ እጅግ ከመናሩ የተነሳ ሊፈጠር የሚችለውን እጅግ ዘግናኝና ለማመን የሚከብድ ሁኔታም ጠቅሷል፡፡ ሆኖም ሊፈጠር ይችላል ያለውን ሁኔታ እዚህ ላይ መጥቀሱ ከኤቲክስም፣ ከሞራልም አንጻር ተገቢ ስላልሆነ እንዝለለውማ! እናማ እስካሁን ያወራነው ለጠቅላላ እውቀት ያህል እንጂ የ“እመኑ/አትመኑ” ጉዳይ አይደለም፡፡ አራት ነጥብ! (ምነው አሁን፣ አሁን ነገራቸውን “አራት ነጥብ፣” ብለው የሚጨርሱ ብዙ ፖሊቲከኞች አንሰማምማ!)
“በ2023 ዘጭ ትላላችሁ፣” እያሉ ያሟርቱብናል እንዴ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1105 times