Saturday, 17 June 2023 00:00

በአንድ ጀንበር የተሳካለት የለም !!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 በህይወት ዘመኑ ከ1ሺ በላይ የፈጠራ ፓተንት ባለቤት ለመሆን እንደቻለ የሚነገርለት ቶማስ ኤዲሰን፣ በልጅነቱ “ትምህርት የማይገባው ደደብ ነው“ ተብሎ ነበር - በሁሉም መምህራኑ፡፡ የሚማርበት ት/ቤት አጥቶም  ቤቱ ለመቀመጥ  ተገድዶ ነበር፡፡ በኋላስ?
በኋላማ ትምህርት የማይገባቸው “ደደቦቹ“፣ ራሳቸው መምህራኑ እንደነበሩ አረጋግጧል፡፡ የሸክላ ሙዚቃ ማጫወቻና የመብራት አምፖልን ጨምሮ፣ ከ1ሺ በላይ የፈጠራ  ፓተንት ባለቤት ለመሆን በቅቷል - ኤዲሰን፡፡
ዛሬ ታዲያ ቶማስ ኤዲሰን፣ በዚህች ዓለም ላይ ከኖሩ ስኬታማ ፈልሳፊዎች አንዱ በመሆን ዘወትር ስሙ ይጠቀሳል፡፡ ከዚያም ባለፈ ግን የእርሱ ግኝቶች፣ የቢሊዮኖችን ህይወት መለወጥና ማሻሻል ችለዋል፡፡
የዓለማችን እጅግ ስኬታማ የፊልም ዳይሬክተር የሆነው ስቲቨን ስፒልበርግ፣ ታዋቂ ከመሆኑ በፊት በሳውዘርን ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ፣ የሲኒማ ጥበብ ት/ቤት ውስጥ ገብቶ ለመማር ቢጠይቅም ተቀባይነት አላገኘም ነበር - “ለትምህርቱ ብቁ አይደለህም“ በሚል፡፡ ስፒልበርግ በልጅነቱ የገጠመው የመማር ተፈጥሮአዊ እክልም፣ የት/ቤት ቆይታውን ፈታኝ አድርጎበት እንደነበር ይነገራል፡፡ እኒህ ሁሉ ግን የዓለማችን ስኬታማ የፊልም ዳይሬክተር ከመሆን አላገዱትም፡፡
ስቲቨን ስፒልበርግ በሰራቸው የሆሊውድ ፊልሞች ፣ ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ  ገቢ አግኝቷል፡፡ ከብሯል - በልጽጓል ቢባል ይሻላል፡፡  ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ለኦስካር መታጨት በራሱ እንደ ትልቅ ክብር በሚቆጠርባት ሆሊውድ፣ 3 የኦስካር ሽልማቶችን አሸንፏል፡፡ በተጨማሪም  7 የጎልደን ግሎብስ እና 11 የኤሚ ሽልማቶችንም ማሸነፍ ችሏል፡፡
የማታ ማታም፣  ሲኒማ ለማጥናት “ብቁ አይደለህም“ ብሎ ዕድል የነፈገው ዩኒቨርሲቲ፣ በግቢው ውስጥ በስሙ ህንጻ ገንብቶለታል፤ለክብሩ፡፡    
እጅግ ተወዳጁና ዶ/ር ሲዩስ በሚል ስሙ  ዓለም የሚያውቀው  የህጻናት መጻሕፍት ደራሲው፣  በአንድ ጀምበር የስኬት ማማ ላይ አልወጣም፡፡ የመጀመሪያ የህጻናት መጽሐፉ፣ በ27 የተለያዩ አሳታሚዎች ውድቅ ተደርጎበት ነበር - አይረባም በሚል፡፡ በዚህም ሳቢያ ተስፋ ቆርጦ የመጽሐፉን ረቂቅ ለማቃጠል ወደ ቤቱ ሲያመራ፣ የክፍል ጓደኛውን መንገድ ላይ አግኝቶ ነው፣ ሥራውን ያተረፈለት፡፡ በኋላም ይሄው ጓደኛው  አሳታሚ እንዲያገኝ አግዞታል፡፡
ዛሬ ዶ/ር ሲዩስ በህይወት ባይኖርም፣ በስኬታማነት ከሚጠቀሱ  የህጻናት መጻሕፍት ደራሲያን አንዱ ሆኗል፡፡ እነዚያ በበርካታ  አሳታሚዎች “ለአቅመ ህትመት አልደረሱም፤ አይረቡም“ የተባሉት መጻሕፍቱም፣ በመላው ዓለም ከ600 ሚሊዮን በላይ ቅጂዎች ተቸብችቦለታል፡፡
የአብዛኞቹ የዓለማችን ስኬታማ ሰዎች ታሪክ ከሞላጎደል ተመሳሳይ ነው፡፡ የሚበዙቱ ተደጋጋሚ ውድቀትና ተቀባይነት ማጣት ከቀመሱ በኋላ ነው ለስኬት የበቁት፡፡ እኛ ግን በአብዛኛው ስኬታቸው  እንጂ ውድቀታቸው ስለማይነገረን፣ በአንድ ጀምበር የስኬት ማማ ላይ የወጡ ቢመስለን አይፈረድብንም፡፡ እውነቱ ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ስለዚህ ውድቀትን ፈጽሞ አትፍሩት፤ ለስኬት ጠንካራ መሰረት ነው፡፡

Read 1898 times