Saturday, 24 June 2023 20:47

የወንድ ልጅ ጥቃት ይቁም!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ከማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በጨረፍታ

 

(የቀለበት ጣቴ አሻራ)


       ባለፈው ሰሞን ወደ አንድ ቦታ ጎራ አልኩ (ቦታው ለጊዜው ይቆይ)። አሻራ ስጥ ተብዬ ገባሁ። የአሻራ ቴክኒሻኗ ከመስኮት ባሻገር ተቀምጣ ጣቶቼ አሻራ ጨርሰው፣ የደም ስሬ እስከሚታይ ድረስ በማሽኑ መጠመጠቻቸው።
“ቀኝ ግራ፣ ቀኝ ግራ” እያለች እንደ ወታደራዊ ትርኢት ታዝገኝ ያዘች። እግሬ መቀፍደዱ እንጂ ወታደራዊ ትርኢት ያስንቃል።
“ይቅርታ የቀለበት ጣት አሻራዎ አልመጣልኝም”
ዞር ብዬ “እንዴት? ለምን እንዴት?” አልኳት።
ፈገግ እያለች፤ “እኔ እንጃ” አለችኝ።
የቀለበት ጣቴን አድፈጠፈጥሁት፣ ፍጭጭ የሚል አሻራ የለውም።
ከዚያ ዘውዲቱ የተባለች ሴኪዩሪቲ ጋርድ ተጠራች። ብረት በጨበጠ እጇ የቀለበት ጣቴን አድፈጠፈጠችኝ።“ኧረ በማርያም፣ ኧረ ስለ ወንድ ልጅ አምላክ” ብላት ልትለቀኝ ነው! (የወንድ ልጅ አምላክ ግን የተለየ ነወይ? ሰው ሲቸግረው የማይጠራው የለ!)
ዞር ብዬ ሳያት አሻራ ማንሳቷን ትታ ትስቃለች። “ጥርስሽ አይርገፍ” አልሁ በውስጤ። ጥርሷ ሀጫ በረዶ ይመስላል።
በቃ ደግማ ታድፈጥፍጠኝና ትሳቅ ብዬ፣ ዘውዲቱን እስኪ ተጫኝው ስላት፣ “በቃ” አለች ቴክኒሻኗ። በመጨረሻም ከጣት አሻራዬ ሳይሆን ከደም ስሮቼ አሻራ አገኙ።
“በቂ አገኘሽ” አልኳት ደም የነሰረውን ጣቴን እየተመለከትኩ። “ለጊዜው “Sufficient” ነው አለችኝ።
“X-ray ነው ወይስ አሻራ ያነሳችሁኝ?”
ሳቀች። “የቀለበት ጣትህን ነገር አስብበት?”
“አልገባኝም። ከአስር ጣቶቼ ተለይቶ እንዴት የቀለበት ጣቴ አሻራ ጠፋ? ማን ወሰደው?“ ጠየቅኋት።
“እኔ እንጃ” አለች እየተሽኮረመመች።
“በቃ ቀለበት ፈግፍጎት ሊሆን ይችላል” ብዬ ዞሬ ሳላያት ወጣሁ።
ከኋላዬ የሆነ ድምፅ ሰማሁ (ለጊዜው ይቅር)። በአሻራ የመለየት ደረጃ ደርሰዋል ማለት ነው?
ገና ወደ ክፍሉ ስገባ ያሳየችኝን ፈገግታና እይታ አይቼ መጠርጠር ነበረብኝ!
በመጨረሻም፣ የቀለበት ጣቴ ለአንድ ሳምንት ማሳጅ ተደርጎለት ወደ ስራ ተመልሷል።
ወገን፣ ኧረ የወንድ ልጅ ጥቃት ይቁም!
(ዘላለም ጥላሁን)



Read 1595 times