Saturday, 01 July 2023 00:00

የውስጥ ደዌ የጤና ችግርና የወሊድ መከላከያ…

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

ባልተፈለገ ጊዜ ልጅ እንዳይወለድ ለማድረግ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም የሚወሰዱ የተለያዩ መከላከያ መድሀኒቶች እና የምክር አገልግሎቶች አሉ፡፡ ታድያ ሁሉም አይነት የመከላከያ ዘዴዎች ለሁሉም ሰዎች በታቀደ ላቸው መንገድ አገልግሎት ይሰጣሉን? ሲባል መልሱ አይሰጡም የሚል ይሆናል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በዚህ እትም በእንግድነት የጋበዝቸው ዶ/ር ተስፋዬ ድረስ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ በአሁኑ ሰአት በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ በእናቶች ጤና ዙሪያ ማለትም በህክምናው ዙሪያ ሲፈ ተሸ ተያያዥ የጤና ችግር ያለባቸው እናቶች በተለይም በእርግዝና ጊዜ ከፍተኛ ክትትል ያስፈልጋቸዋል የተባሉትን እንዲሁም ጽንስ በማህጸን ውስጥ እያለ ለተለያዩ ችግሮች ማለትም ለእድገት ወይንም ለተፈጥሮ ችግር የመጋለጥ እድል ሊገጥመው ስለሚችል በእነዚህ አስቸጋሪ የጤና ሁኔታዎች ዙሪያ ጥልቅ የሆነ ምርመራ ማድረግን እንዲሁም የህክምና አገልግሎትን መስጠትን በማጥናት ላይ ናቸው፡፡ ስለዚህም እናትየውንና ጽንስዋን በአንድ ላይ በማጥናት መፍትሔ ለመስጠት በዝግጅት ላይ ያሉ የህክምና ባለሙያ ናቸው፡፡
ዶ/ር ተስፋዬ ድረስ በመግቢያቸው ላይ እንደገለጹት የጤና ችግር ያለባቸው እናቶች ሲባል በእድሜያቸው ከ15-49 ማለትም በመውለጃ እድሜ ክልል ያሉት እናቶች የደም ግፊት፤ የስ ኩዋር ወይንም ሌሎች የውስጥ ደዌ ህመሞች ያሉባቸው ሲሆን ነው፡፡ በእርግጥ ብዙ ጊዜ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰቱ የደም ግፊትና ስኩዋር ሕመሞች ሊከሰቱ የሚችሉበት እድል እንደሚኖር እሙን ነው፡፡ ሆኖም ግን ህመሙ በእርግዝናም ጊዜ ይሁን ከእርግዝና ውጨ በነበረው ሕይወታቸው የሚታይ ከሆነ ጥንቃቄ የሚያስ ፈልገው ጉዳይ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የስነ አእምሮ ሕመሞች፤የሚጥል በሽታ፤የልብ ሕመም ፤የደም መርጋት ችግር ያለባቸው (በተለይም በእርግዝናም ይሁን ከወለዱ በሁዋላ በብዛት የሚያጋጥም) እና የመሳሰሉት ሕመሞች የጤና ችግር ያለባቸው እናቶች በሚለው ይገለጻሉ፡፡ በተጨማሪም በዘር የሚተላለፍ የደም መርጋት ሕመም ካጋጠመ በተከታታይ ጽንስ እንዲቋረጥ ያደር ጋል፡፡ እንዲሁም አንዳንድ እናቶች የካንሰር ሕመም ሊገጥማቸው ስለሚችል የካንሰር ሕመሙ በህክምና እገዛ ሊድን ቢችል እንኩዋን ከእርግዝና ጋር በተያያዘ ግን መቼ ነው መረገዝ ያለበት የሚለው ምክክርና ውሳኔ የሚፈልግ ነገር ይሆናል፡፡ ስለሆ ነም እንደዚህ ያሉ ህመሞች ያለባቸው እናቶች የወሊድ መከላከያ መውሰድ ግድ ይሆንባ ቸዋል፡፡ ምክንያቱም ያልተፈለገ እርግዝና ከመጣ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ስለሚያ መዝን ነው፡፡ ይህንን በወደፊት ሕይወታቸው ላይ ሊገጥማቸው የሚችለውን አስከፊ ገጽታ ለማስወገድ እናቶች እና ቤተሰቦቻቸው ከውስጥ ደዌ ህመም ሐኪማቸው፤ከማህጸንና ጽንስ ሐኪማቸው ጋር በመሆን በመመካከር ያልተፈለገ እርግዝና እንዳይከሰት ምን ማድረግ እንደሚገባ ለውሳኔ መድረስ ይገባቸዋል፡፡
ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያዎችን በሚመለከት የአለም የጤና ድርጅትና CDC የአሜሪካ በሽታዎች መቆጣጠሪያ ያወጡት ደረጃ አለ፡፡ አመዳደቡ በአራት ደረጃዎች የተከፈለ ነው፡፡
አንደኛ ደረጃ ላይ ያለው ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት አያመጣም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ያለው የተወሰነ የጎንዮሽ ጉዳት አለው፡፡ ግን ጥቅሙ ከጎንዮሽ ጉዳቱ ይበልጣል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የጎንዮሽ ጉዳቱ እና ጥቅሙ እኩል ለእኩል የሆነ ነው፡፡
በአራተኛ ደረጃ ላይ ያለው የጎንዮሽ ጉዳቱ ከጥቅሙ በጣም የበለጠ ነው፡፡
እያንዳንዱ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ ከሆርሞን እና መከላከያ መንገድ ከሚባሉት ውጪ የወር አበባ ኡደትን በመከተል እርግዝና እንዳይከሰት ለማድረግ ያስችላሉ፡፡ መከላከያዎቹ ኢስትሮጂን፤ፕሮጀስትሮን የተባሉ ሆርሞኖችን ወይንም ሁለቱንም ማለትም ኢስትሮጂንና ፕሮጀስትሮን የተባሉትን ሆርሞኖች የያዙ ሲሆኑ እርግዝናውን በመከላከል ረገድ አስተ ማማኝ የሆኑ ናቸው፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ በቀን መቁጠሪያ በመመራት እርግዝናን ለመከላከል የሚሞ ክሩ እናቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ይህ አካሄድ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ ነው ስለማይባል በተለይም የጤና ችግር ላለባቸው እናቶች አይመከርም፡፡ ሌላው በማህጸን በኩል የሚገባው ሉፕ በመባል የሚታወቅ የእርግዝና መከላከያ ነው፡፡ ሉፕ ሁለት አይነት ሲሆን አንዱ ፕሮጀስትሮን ያለው ሲሆን ሌላው ደግሞ ሆርሞን የሌለው ኮፐር የሚባል ማእድን የያዘ ነው፡፡ ይህ ሆርሞን የሌለው ኮፐር ብቻ ያለው ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ በአብዛኛው ተመራጭ የሚባለው ነው፡፡
በእንክብል መልክ የሚወሰዱት መከላከያዎች በአብዛኛው ፕሮጀስትሮንም ኢስትሮጂንም የያዙ ሲሆን 30 ማይክሮግራም ወይም 50 ማይክሮግራም ኢስትሮጂን የያዙ ናቸው፡፡ የጤና ሁኔታቸው የልብ ወይንም ሌላ ችግር ላለባቸው እናቶች በተለይም 50 ማይክሮግራም ኢስት ሮጂን ያለበት መከላከያ አይመከርም፡፡ ባጠቃላይም እናቶች የሚወስዱአቸው መድሀ ኒቶች እንደህመሙ ሁኔታ ደረጃው ከፍና ዝቅ ሊሊ ይችላል ብለዋል ዶ/ር ተስፋዬ፡፡  
የተለያዩ የጤና እውክታዎች ላሉአቸው እናቶች የወሊድ መከላከያ ያስፈልጋል ሲባል ምክንያቶቹ ግልጽ ናቸው፡፡
1/    ሳይታወቅ ያልተፈለገ እርግዝና ቢከሰት በእናትየው የጤና ሁኔታ ላይ አስቸጋሪ ነገር ሊፈጠር ስለሚችል ያንን መከላከል፤
2/     አንዲት እናት ያላት ህመም መስተካከሉ ሳይታይ እና ሳይታቀድ እርግዝናው የሚከሰት ከሆነ ጽንሱም ላይ የአፈጣጠር ችግር ሊያመጣ ስለሚችል፤
በሁለቱም ማለትም በእናትየውም በልጁም ላይ ችግር እንዳያስከትል ከሚል ነው፡፡ ስለዚህ
የጤና ሁኔታቸው ሳይስተካከል ያልተፈለገ እርግዝና እንዳይከሰት እና በልጁም ላይ ሆነ በእናትየው ላየ ችግር እንዳያስከትል ለማድረግ አስቀድሞውኑ የውስጥ ደዌ ሕመም ሐኪምና የጽንስና ማህጸን ሐኪሙ ከእናትየው ፤ከቤተሰብ ጋር በመመካከር የሚወስዱትን እርምጃ አስቀድሞ መወሰን አለባቸው፡፡
የሚወሰዱ መድሀኒቶችን በሚመለከት ከብዛታቸው የተነሳ መዘርዘር ባይቻልም ግን ለእናትየው ሕመም መፍትሔ ሆነዋልን? ህመሙ በእርግጥ በቁጥጥር ስር ወሎአልን የሚለውን ካለ ምንም ማመንታት ማረጋገጥ ይገባል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያለው ህመም መድ ሀኒት መውሰድ በግድ ሊያስፈልገው ይችላል፡፡ በዚህ ሁኔታ የወሊድ መከላከያን መውሰዱ ደግሞ ሌላ የጤና ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ ስለዚህ አገልግሎቱን የሚፈልጉ እናቶች በቅርበት ከሐኪሞቻቸው ጋር መመካከራቸው አስፈላጊ መሆኑን እንዲያምኑ ግድ ይላል፡፡ እንደ ዶ/ር ተስፋዬ ድረስ ማብራሪያ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ አንድ የተቋቋመ ክሊኒክ አለ፡፡ ክሊነኩ ከሳምንቱ ቀናት በአንደኛው ማለትም ማክሰኞ እለት ከ ሰባት ሰአት ጀምሮ ለግማሽ ቀን የሚሰራ ሲሆን ተዛማጅ የሆነ የጤና ችግር ያለባቸው እናቶች ወደ ሐኪሞች ይቀርባሉ፡፡ እናቶቹ ያለባቸውን የጤና ችግር በመመልከት ያሉበትን ሁኔታ በመመርመር እርግዝና ሊኖራቸው ይችላል አይችልም የሚለውን ሁሉ ለመወሰን የሚያስችል ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡ ለእርግዝና ምቹ የሚሆኑ ነገሮችን ሁሉ መድሀ ኒቶችን ከማሻሻል ጀምሮ እስከመቀየር፤እንዲሁም በእነዚያ መድሀኒቶች ሕመሙን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ይቻላል ወይ የሚለውን እርግጠኛ ሲኮን እርግዝና ይፈቀድላቸዋል፡፡ ይህ ሲደረግ ጥቅሞች አሉት፡፡
1/ እርግዝና ሲኖር እናትየው ላይ ችግር አያመጣም፡፡
2/ የሚጥል በሽታ፤የስኩዋር ሕመም…ወዘተ የመሳሰሉት በሽታዎች ላሉባቸው ከእርግዝናው
አስቀድሞ ከአንድ ወር እስከ ሶስት ወር ድረሰ ፎሊክ አሲድ ቢሰጣቸው ብዙ ጊዜ ከነርቭ    ጋር የተያያዙ የአፈጣጠር ችግሮችን ለጽንሱ እንዳይከሰት ያደርጋል ፡፡
እናትየው ያለችበት የህመም ሁኔታ ጥሩ ስላልሆነ እርግዝናው መከሰት የለበትም ከተባለ ግን የወሊድ መከላከያ መውሰድ እንዳለባት ስለሚወሰን ከወሊድ መከላከያዎች ጋር በተያያዘ ሌላ ውይይት ያስፈልጋል ማለት ነው ብለዋል ዶ/ር ተስፋዬ ድረስ፡፡
ባጠቃላይም የውስጥ ደዌ ሕመም ያለባቸው እናቶች እርግዝና እንዲከሰት ወይንም ያልተ ፈለገ እርግዝናን ለመከላከል አስቀድመው ከውስጥ ደዌ የህክምና ባለሙያዎች እና ከጽንስና ማህጸን ሐኪሞቻቸው ጋር ቢወያዩ ለጽንሱም ሆነ ለእራሳቸው ሕይወት ጠቃሚ መሆኑን ዶ/ር ተስፋዬ ድረስ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት አብራርተውልናል፡፡

Read 727 times