Monday, 03 July 2023 09:32

ነገረ ህትመት ወ መጻሕፍት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንድ መጽሐፍ በሽያጭ ረገድ ብዙ ሺ ኮፒ ታትሞ በአንድ ሳምንት ተሽጦ ስላለቀ ብቻ  በይዘቱ ምርጥ ነው ማለት አይደለም፡፡ በብዙ ሺ ኮፒ መታተሙ፣ ለመነበብ ተደራሽ  ያደርገዋል እንጂ በሁለንተናው ሚዛን የሚያነሳ ብቁ ስራ ነው የሚያስብል ማረጋገጫ አይሆንም፤ ወይም ሊሆን አይችልም፡፡ (አልባሌ ሆኖ ሰፊ ተነባቢነት ያገኘ ስራ ብዙ መጥቀስ ይቻላልና) በዋናነት የመጽሐፉ ሀሳብ ለአእምሮ ብርሃን በመስጠቱ፣ ልብን በመለወጥ ብቃቱ፣ አማራጭ የኑሮ ቀዳዳዎችን አጮልቆ በማመላከቱና በሌሎችም አበይት መመዘኛዎች ሊለካ ይችላል፡፡
(ከሀገር በቀል የህትመት ቀለም ጎርፍ ውስጥ በብዛትም ሆነ በተነባቢነት ስፋት የትላንቱ ፍቅር እስከ መቃብር እና የዚህ ዘመኑ ዴርቶጋዳን እሚስተካከል ይኖር ይሆን?)
 በውጭው አለም ከ1500 ዓመታት በፊት የታተሙ መጻሕፍት ዛሬ-ዛሬ አስገራሚ ዋጋን ሰቅለዋል፡፡ ለአንድ ቀደምትና ነባር መጽሐፍ ብዙ ሺህ ዶላር ማውጣት  እንግዳ መሆኑ አብቅቷል፡፡ ዘመን አይሽሬ የጠፉ ቅጂ ስራዎች ከሚገመተው በላይ ብዙ እጥፍ በሆነ ገንዘብ ሊሸመቱ ያልቻሉበት ደረጃ ላይ ናቸው፡፡ በአለማችን ውስጥ ገናና ክብር ያገኙ መጻሕፍት ሆነው ነገር ግን ህትመታቸው በመጥፋቱ ብቻ ቀዳሚነቱን የወሰዱም እንዲሁ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ጆን ስናይደር “A Guid through Book land ” በተሰኘ ተወዳጅ መጽሐፉ ለአንድ ነጠላ ህትመት ከተከፈሉ ዋጋዎች ሁሉ የላቀው ክፍያ ብሎ በጥናቱ ካካተታቸው መካከል ይሄ ይገኝበታል፡፡…በ1930 በተለምዶ የቮልቤከር ስብስቦች ተብለው የሚጠሩ መጻሕፍት በኮንግረስ ላይብረሪ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የአሜሪካን ኮንግረስ እኚህን የተበታተኑ ቅጂዎች ከመላው አለም ሰብስቦ ለማኖር ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት 600,000 ዶላሮችን አውጥተውበታል፡፡ በጊዜው ለጥቂት ህትመት ከተከፈሉ ዋጋዎች ውዱ ክፍያ ነበር፡፡ ሌላው በ1485 በዌስት ሚኒስቴር ታትመው ከወደሙትና ለተረፈው ብቸኛ “Morted Arthur” ለተሰኘ መጽሐፍ ድርጅቱ 42,800 ዶላሮችን አውጥቷል፡፡ ቀደምት አብያተ መጻሕፍት በአብዛኛው በግብፅ፣ በአሶር እና በባቢሎን የሚገኙ ነበሩ፡፡ መጻሕፍቶቹ ጥንታውያን ከመሆናቸው ባሻገር ከወረቀት በፊት የሚጠቀሙበት በፓፒረስ የተሰጡ ጥቅሎች ከመሆናቸው ባለፈ፣ አንድም ከእጥረታቸው አንድም ከእድሜ ባለጠግነታቸው ጋር ተያይዞ ለዋጋቸው አለቅጥ መናርና መወደድ በተመራማሪያኑ እንደምክንያት ይጠቀሳል፡፡
 ወደ አገራችን መለስ ብለን ደግሞ እንይ፡፡ ስለ መጻሕፍት ሕትመት ሲወሳ በአቢይነት ሶስት ዘርፎች ያሉ መሆናቸውን እቁጥር ውስጥ ማስገባት ያሻል፡፡ እነርሱም የመማርያ መጻሕፍት፣ የሥነጽሁፍና ጠቅላላ እውቀት ናቸው፡፡ በአጥኚዎች ዘንድ ተደጋግሞ እንደሚነገረው፤ የአፍሪካ የመጻሕፍት ሕትመት ዘጠና ከመቶ ያህሉ በመማሪያ መጻሕፍት ወይም በትምህርታዊ ሕትመት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በኢትዮጵያም የሚታየው ይኸው ነው፡፡ ይህም ከሥነጽሑፍ፣ ከጠቅላላ እውቀት፣ ከጋዜጣና መጽሔቶች በላቀ ሀገራቱ ለትምህርት ቅድሚያ የሚሰጡ መሆናቸውን ያመላክታል፡፡ ይህ ትኩረት አይቀሬና ሁሌም የሚኖር መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ይሁንና የሕትመቱ ኢንዱስትሪ በዚህ ላይ ብቻ ተወስኖ ሲያተኩር፣ የሌሎች መጻሕፍትን ሕትመት ያቀጭጫልም-ያዳክማልም ተብሎ በአጥኚዎች ዘንድ ይሰጋል፡፡ ተባባሪ ኘሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው በጉዳዩ ላይ ከፃፉ አጥኚዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡ የስነጽሑፍ ምሁሩ “ከበአሉ ግርማ እስከ አዳም ረታ” በተሰኘ መጽሐፋቸው፤ “የኢትዮጵያ የመጻሕፍት ሕትመት የደረሰበት የእድገት ደረጃ፣ የታዩ ችግሮች እና መፍትሔዎች” በሚል ንዑስ ርዕስ ስር ባሰፈሩት ጥናታዊ ሀተታቸው  ለአገራችን ስጋቶች ናቸው ያሏቸውን በሶስት ከፍለው እንደሚከተለው አስቀምጠዋል፡፡…“የሕትመት እንዱስትሪው በአብዛኛው በመንግስት በጀት ላይ ብቻ ይወድቃል፡፡ አልፎ-አልፎ በእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ወይም አገሮች በጎ ፍቃድ ይሆንና ዘላቂነቱ ያጠያይቃል፡፡ የሀገሩ መንግስት በሚያወጣው ስርዓተ ትምህርት ላይ መጻሕፍቱ ስለሚመሰረቱ የደራሲዎቻችንና የአሳታሚዎችን የፈጠራ አቅም ይገድባል፡፡ የመጻሕፍት ንግዱ በሀገሩ ላይ ብቻ ተወሰኖ ይቀርና የገበያ ስፋት እንዳይኖር ያደርጋል”፡፡(ገጽ.137)
በእርግጥ ወደ አገራችን መለስ ብለን ስናጤን ከነዚህ ስጋቶች በላይ አያሌ ችግሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ደራሲዎቻችንም ዘወትር የሚያማርሩበት ዋነኛ ተግዳሮት መሆኑ እሙን ነው፡፡ ምንም እንኳን የመማሪያ መጻሕፍት ሕትመት በዓለም ደረጃ ከፍ ያለ ቢሆንም፣ በዚያው መጠን በበለፀጉ አገሮች ያሉ አሳታሚዎች የመማሪያ መጻሕፍት ሕትመት ዋና መሰረታቸውም ሆነ ጉዳያቸው እንዳልሆነ ይጠቀሳል፡፡ ዛሬ-ዛሬ የመጻሕፍት ሕትመት ዋጋው ሰማይ ነው፡፡ ከሌሎች የኢኮኖሚ መሰረቶች አንፃር ሲታይ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ትልቅ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ለዜጎች የአእምሮ ብልጽግና አስፈላጊነቱ ብሎም ያለው ጉልህ አስተዋጽኦ በጣሙን ላቅ ያለ ነው፡፡ ሀገር የተማረ እና በልቶ የሚያድር ዜጋ ብቻ ሳይሆን ያነበበና ማሰብ የሚችል ትውልድም ያስፈልጋታል፡፡ እንዲህ ያሉ ዜጎች የሚፈጠሩት ደግሞ መንግስት ከመማሪያ መጻሕፍት በላቀ በሌሎች ህትመቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ሲችል ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ከሕትመት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለማቃለል ወይም ለማስቀረት በአጥኚዎች በዋነኛነት ከተሰጡ የመፍትሔ ሀሳቦች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡ የአሳታሚዎች  ማህበራት በማቋቋም ችግሮችን በጋራ መፍታት፣ የመጻሕፍት ፖሊሲ መቅረጽ፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተና በባለሙያዎች የተደገፈ የሕትመት ስራ መስራት፣ ደራሲዎችንና አታሚዎችን፣አከፋፋዮችንና ሻጮችን…አቀራርቦ ማነጋገር የመሳሰሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከታሪካዊ ዳራ አንፃር ስንመለከተው አገራችን ከሌሎች የአፍሪቃ አገሮች የተሻለች እንደነበረች ጉዳዩን ያጠኑ ተመራማሪያን ጽፈዋል፡፡ ለምሳሌ አልበርት ዤራርድ በአገርኛ ቋንቋ የፈጠራ ስራዎችን በማሳተም ረገድ ከሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ጋር ስትነፃፀር ኢትዮጵያ በተለየ ላቅ ያለ ደረጃ ላይ ናት ብለው ጽፈዋል፡፡ ይህን ያሉት ከዛሬ 41 ዓመት በፊት ነው፡፡ ይህ አነጋገር በአገር ቋንቋ የማሳተም ስራ ምን ያህል በተፈለገው ደረጃ እያደገ መጥቷል ? የሚል ጥያቄ እንዲጠየቅ ያሳስባል፡፡ የምስራቅ አፍሪካ ባህልና ታሪክ ላይ በርካታ ጥናታዊ ወረቀቶችንና መጻሕፍትን እንዳሳተሙ የሚነገርላቸው የሶሾሎጂ ምሁር የሆኑት ዶናልድ ሌቪን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሚያስተምሩበት ወቅት ኢትዮጵያን የተመለከቱ ሁለት መጻሕፍት አሳትመዋል፡፡ ከነዚህ ሁለት መጻሕፍቶቻቸው በ“Wax & Gold” (በደሳለኝ ስዩም ሰምና ወርቅ በሚል ወደ አማርኛም ተመልሷል) ውስጥ በኢትዮጵያ የህትመት ጉዳይ ላይ የታዘቡትን እንደሚከተለው አስፍረው ነበር፡፡…”መጻሕፍትን ጽፎ ማሳተም በኢትዮጵያ ዘመናዊ ምሁራን ዘንድ እንደጠቃሚ ነገር የሚታይ አይደለም፡፡ በአማርኛ የሚጻፉ ወጥ መጻሕፍት ቁጥር በአመት ከ50 አይበልጡም፡፡   በእርግጥ የህትመት ዋጋ ውድነት፣ ያልተደራጀ የገበያ እጦት፣ እንዲሁም የአሳታሚ አለመኖር ለዚህ እንደ ምክንያት ይጠቀሳል፡፡ የመጽሐፍ ንባብ ባህል ያለማድረጉ ልማድ በእርግጥ ዝም ብሎ የተፈጠረ አይደለም፡፡ የአንባብያን የግንዛቤ (የትምህርት ደረጃ) ዝቅተኛ መሆን ፣ የሂስ መድረክ አለመኖር፤ ከዚህ ቀደም የነበረው ዘመናዊ የስነጽሁፍ ታሪክና የሕትመት ሁኔታ ደካማ መሆን ጠንካራ የስነጽሁፍ ጉዞ እንዳይኖር አድርጓል፡፡ (ሰምና ወርቅ-ሌቪን IV)     በዚህ በክፍል ሁለት ጽሁፌ ከፍ ሲል በምሁራን የተጠቀሱትንና የተጠቆሙትን ሌሎችም ችግሮችን መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራባቸው ዘንድ ሀተታዬ ጥቂት መንገርና ማመላከት ከቻለ በቂ ነው፡፡ አዎ፣ በኛ አገር መጻሕፍት ለጥቂቶች ካልሆነ በስተቀር መሰረታዊ ፍላጎት አይደሉም፡፡ ለኑሮ ወሳኝና አስፈላጊ ግብአትም ሆነው አይካተቱም፡፡ ቢሆኑም እንኳን ዛሬ-ዛሬ በዋጋቸው መናር ሳቢያ ቅንጦት መሆናቸው አልቀረም፡፡ በሩቁ የሚታዩ እንጂ የማይበሉ የአይምሮ የነጠሩ ፍሬዎች መሆናቸው ገሀድ ነው፡፡
 ከእንግዲህ የውጥንቅጡን አለም ማምለጫዎቻችን፣ አንብበን የምንረካባቸው፣ የምናሰላስልባቸው፣ ወደ ነፍሳችን አስጠግተን የምናቅፋቸው ሰናይ መጻሕፍት ላይኖሩን ይችላሉ፡፡ ከሞላ ጎደል ከሰዎች ለሰዎች መሆኑ ቀርቶ፣ ህዝብ ጋ በቀላሉ የሚደርሱበት ዘመን አብቅቶ… በውድ ዋጋ ተገዝተው ለሳሎን ጌጥ ብቻ እሚሆኑበት ጊዜ ሩቅ አይመስልም፡፡ መንግስት በህትመትና ወረቀት  ጉዳይ ላይ እጁን ካላስረዘመ በስተቀር ህዝብ በሀገር ጉዳይ የሚቀነስ እንጂ የሚደመር ትውልድ አይሆንም፡፡ እንዲሆን መጠበቅ አንድም ታሪክን ጠንቅቆ አለማወቅ አሊያም ከታሪክ አለመማር ነው፡፡    

Read 859 times