Saturday, 08 July 2023 00:00

ተወርዋሪ ኮከብ

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(0 votes)

ይኼ የሆነው ባለ አንባሻ ቅርጽዋ - የዚያድ ባሬ ሶማሌ ልትወርረን ስትቃጣ ነበር፤ ቤታችን ቡና እየተቀቀለ ስለነበር ‹የትም እንዳትሄድ› ስለተባልኩ ታዛ ላይ ቁሜ ውጭ-ውጭውን አያለሁ። ካፊያ ቢጤ ይስተዋላል። እግዚሔር በሰው ልጆች ክንድ ላይ የተደረተውን ንቅሳት ተጠይፎ በግማሽ ክብ ቅርጽ ባለ ሰባት ቀለም ንቅሳቱን ሰማይ ላይ አትሟል። ጸሐይ ሙሉ-ለሙሉ አልጠለቀችም…
…‹ጸሐይና ዝናብ በአንድነት ከተስተዋሉ ጅብ ትወልዳለች› የሚል ሀገርኛ ብሒል ውል አለኝ። ገራገር ነጎድጓድ ይሰማል፤ ወደ ሰማይ አንጋጥጬ ሳለሁ የእሣት አሎሎ የሚያኽል ኮከብ እየተድበለበለ ወረደ። ፈሪ ነኝ። ብቅብቅ። ልቤ ተተረተረች። ሊያደባየኝ የተላከብኝ ስለመሰለኝ ሮጬ ቤት ገባሁ፤ በተመሳሳይ ሰዓት እናቴ ሮጣ ወጣች። የቆላችው ቡና ከልባሽዋ ጋር ተዋህዶ ተከትሏት ወጣ፡-
‹‹አየኼው! አየኼው!›› ፈገግ ብላ በኩራት ወደ ኮከቡ አቅጣጫ እየጠቆመች
‹‹ኮከቡን?››
‹‹ገልቱ›› ቱግ አለች ‹‹አባትህ እኮ ነው፤ አባትህ፣ የእኔ ጀግና!››
‹‹እ…?››    ‹‹አ - ዎ! አባትህ፤ ኮኮብ ተመስሎ!›› እንባ ተናነቃት
*  *  *
ሁኔታዋ ስላጠራጠረኝ ትክ ብዬ እያየኋት ተጠጋኋት። መጠን ባጣ ደስታ ውስጥ ስለነበረች ገጽዋ እንደ ጸደይ ሰማይ ወከክ ብሏል። ውስጥዋ ጎጆውን የቀለሰ ናፍቆት አለ - እሳት ያዳፈነ - ተወርዋሪውን ኮከብ ባየች ቅጽበት የተዳፈነው እሳት ተቆስቁሶ ነፍስዋ አስተረየች። ልቦናዋ ላይ የተቀባበለው የሰው ጥማት ተተኩሶ ተባራሪ አረር ፈጃት…
…እጆቹዋን በብቅል ሰቃይ ስልት ወደ ሰማይ አንገርብባ የማይሰማ ድምጽ ታነበንባለች። ከኀሊ አምላኳን ታወድሳለች። ለጋስ አድባሯን ትሸልማለች፤ አባቴ ከተለየን ረጅም ጊዜ ሆኖታል። እኔ ከተወለለግክወድኩ ጊዜ አንስቶ አንደበቱን የተነጠቀ ይመስል በዝምታ ኑሮ በዝምታ ሞተ፤ በዚህች ምድር ላይ የአባቴ የቅርብ ወዳጅ ‹ዝምታ› ብቻ ነበር። ማዕድ የሚቆርሰው ከዝምታ ጋር ነበር። ጣመንና እርካታውን ለዝምታ ያካፍላል። ከዝምታ ጋር ይመክራል። ትንባሆ ውል ሲለው ፍራንክ ከዝምታ ይቀበላል። እሱቅ ወጥቶ ሲገዛ አይታይም - ነገር ግን ያጤሳል። ከአምላኩ ጋር በዝምታ የመቀጣጣት ጸብ ሳይኖረው አይቀርም ዘወትር ተለጉሞ ይኖራል። ሻሂ አብዝቶ ይጠጣል። ሲጋራ ይምጋል፤ እናቴ ለአመል፣ ወላ ተስቷት ‹ይኼ ሲጋራ ቢቀርብህ ጥሩ ነበር፤ ለጤናህ ጠንቅ ነው› ብላው አታውቅም፤ ከእናቴ ጋር ቋንቋ ሲገበያዩ ሰምቼና አይቼ አላውቅም። ጥንት ከሚሠራበት ቦታ ሸር ሸርበው ከቀነሱት በኋላ የአንድ ድርጅት ዘብ ሆኖ ይሠራ እንደነበር አውቄአለሁ። ታዲያ ዘብ ሲያድር ወስላታ ገጥሞት እንደሆነ ‹ገለል በል› የሚል አይመስለኝም፤ የዕድሜውን ሰማንያ በመቶ የፈጀው ከፊት-ለፊቱ የነበረውን ባዶ ግድግዳ ትክ ብሎ በማየት ነበር፤ እናቴ ውብ ነች። ያውም እንደ ቆቅ መረቅ ውድ ሴት። እሷን ሲያይ ድምጽ ማውጫው ረግፎ ይሆን? እና ምን ብሎ አገባት? እሺ ማግባቱንስ ያግባት፣ ቃል የማይወጣው ከሆነ ለምን አልፈታችውም? እንዴት አብረው ዘለቁ? ወላ ከመጋረጃ በስተጀርባም ይሁን በአደባባይ በትዳር ዓለም ውስጥ ሚስቱን ከማያሽኮረምምና ከማያሞጋግስ ባል ጋር መዝለቅ ይቻላል?            
*  *  *
ፋታ ሳትወስድ ውዳሴዋን ታንበለብላለች። እሱ ልጓም ቢሆንም አባቴን ትወደዋለች። መድኅንዋ ነው። ለእኔ ትርጉም ባይሰጠኝም የጥድቅ መንገድዋ አድርጋ ስላዋለች። ሥሙን ሳታነሳ አትውልም። ስትፈጭ፣ ስትነጭ፣ ስትቀረድድ፣ ስታሻምድ፣ ስትቀቅል፣ ስትፈትል፣ ስትቀዳ፣ ስታጸዳ፣ ስትከትፍ፣ ስትቀረጥፍ፣ ስትጠብስ፣ ስታምስ፣ ስታጥብ፣ ስትገርብ፣ ስትከካና ስታቦካ የአባቴን ሥም በተራዳኢነት ትጠራለች…
…ታዲያ ያኔ ‹አባቴ ከመልአክት ወገን ይሆን?› እላለሁ። መልአክት ሲጋራ ያጤሳሉ? ዝምታስ ግብራቸው ነውን? እኔ‘ጃ! ወንድ አያቴን ልጠይቀው እልና እተዋለሁ፤ እሱም የእናቴ ቢጤ ነው ዞሮ። ቅን ስላይደለ ከቀጥተኛ ይልቅ ጉግማንጉግ ምላሽ መስጠት ይቀናዋል፤ አድክም ነው፤ ብዙ ጊዜ ብዙ ዓይነት ለጆሮ ሸክም የሆኑ ንግግሮችን አውግቶኝ ያውቃል፤ ደጋግሞ ነው ታዲያ፤ ሲበዛ ጮሌ ነው እንደሰለቸኝ ሲያውቅ ‹ልጅነት ያሉትን መስማት ነው› ይሉት አሳሪ ንግግር ያስከትላል። የራሱ ጉዳይ ነው ግን። ምን በወጣኝ… ጦስ ጥንቡሳሱን ይዤ ፍግም አልልም፤ ለምሳሌ ከሁለት ቀን በፊት አንድ ተዐብ አይሉት ተዐምር በጆሮዬ አፍስሶአል። ይህቺ እናቴ ናት ‹‹ከመጡ ቆዩ፤ ኑ ቡና ጠጡ በላቸው ስሞትልህ›› ብላኝ ጠራኋቸው፤ ምግብ የምትቀቅልላቸውን አረንጌ አስከትለው መጡ፤
እግራቸው ደጁን እንዳለፈ የአባቴን ሥም እያነሱ መነፋረቅ ያዙ፤ እጃቸውን አንገርብበው ‹አንድያዬ፣ ውላጄ› እያሉ፤ ድርጊታቸውንም ቃሉንም አይቀይሩም ግን። ቢሆንም ከፊታቸው አንዳች ጥርኝ እንባ አጣሁባቸው፤ እናቴም ደቀ መዝሙራቸው ናትና ተከትላ እንባዋን ዘራች፤ ስስ የእንባ ጅረት በጠወለጉ ጉንጮቿ ቁልቁል ተንከላወሰ። በአይበሉባዋ እያበሰች አያቴን ስማ አስቀመጠቻቸው። አረንጌም አያቴም ሳሙኝ፤ አያቴ ቡና ሳቀብለው ጸጉሬን ደባብሶ ‹‹እደግ›› አለኝ፤ ወዲያው ሲለው ‹‹እንደው አባቱን እኮ ነው›› የሚል ሐረግ አከለ። ለመሆኑ አባቴን እመስላለሁን ወይስ አባቴ ይመስለኛል? እንጃ እኔ፤ ቡናው ከማክተሙ አስቀድሞ ስኒ የያዘ እጄን ትክ ብሎ እያየ፡-
‹‹በልጅነት የቡና ጠኔያም ሆንክ?›› አለኝ
‹‹ጠኔ ምንድነው?››
‹‹ሱስ ማለት ነው››
‹‹እ-ሺ››
‹‹የካሊ አዲ አምላክ እ-ሺ ይበልህ››
‹‹ካሊ አዲ ማነው?››
‹‹ተው እንጂ አትመራመር›› አረንጌ ጣልቃ ሆነች
አያቴ ችላ ብሏት ቀጠለ፡- ‹‹በ9ነኛው ክፍለ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ቡናን ያገኘ ወጣት ነው፤ እረኛ ነበር እንግዲህ። ግና አንዳንድ የታሪክ አተሎችና ወስላቶች ‹ሥሙ ካልዲስ ነው› ይላሉ፤ ትክክለኛው ሥም ግን ካሊ አዲ እንደሆነ አፈታሪክ እማኝ ነው››
‹‹ምን ማለት ነው?››
‹‹ጥሩ፤ ‹ካሊ› ማለት በካፋ ሕዝቦች በተለይ በገጠራማ አካባቢዎች የሚዘወተር የወንድ ጾታ ሥም ነው፤ ቀልጣፋ ወይም ከተፎ ማለት ሲሆን ‹አዲ› ደግሞ ‹እረኛ፤ ከብት ጠባቂ› እንደማለት ነው››    
እናቴ በረካ እየጣደች ዝግ ባለ ድምጽ ታንጎራጉራለች። ከሂሩት በቀለ ዘፈኖች አንዱን እንደምትዘፍን አውቄአለሁ፤ በአባቴ ፍቅር ስትረግፍ የሂሩት በቀለ ዘፈኖች ያጽናኗት ነበርና ውለታቸው አለባት አሉ። እንደው ይህቺ ሴት መክሊቷ ማዜም ሳለ በከንቱ ቡና መቀቀል ላይ ጥሏት ይሆን? ከሆነም እግዚሔር ሆይ እግዚሔር ይይልህ… መለስ ብላ አንድ እፍኝ ሙሉ ዕጣን ዘግና ከተንደረከከ የእሳት ላንቃ ውስጥ ዶለች። በመሀል፡-
‹‹አሁን ለዚህ ገልቱ ቢነግሩት ከቁምነገር ይጥፋል ብለው ነው?›› አፍዋን ጠመም አድርጋ ወረፈቺኝ፤
አረንጌ በተባባሪነት አንገቷን ትወዘውዛለች፤ ጭንቅላቷ እስኪወልቅ ድረስ። እዚህ ሀገር (ይቅርታ እዚህ ቤት) ከወጊው ይልቅ ጩቤ ቀቅሎ አቀባዩ ይበዛል፤ ኧረ እግዚሔር የወጊው፣ የአስወጊውና የተወጊውን ቁጥር አመጣጥን በአላህ። አረንጌ የሥራ ፍቃድ ያላት አብጠልጣይ ናት፤ ወላ ግብር ከፋይ። ዳፍንታም ናትና የእኔ ነገር አይጥማትም…
‹‹ልጄማ ብርቱ ነው፤ ቆፍጣና›› የአያቴ ይባስ!
‹‹ኡኡቴ!›› ለሁለት፤
አያቴ ማብሸቃቸውን እንደ መጥፎ ልማድ እያየ ይበሽቃል፤ በጣም ይበሽቃል። ለመሆኑ ለሚያበሽቅ ሰው መብሸቅ የመልስ ምት ይሆናል? እኔ እንጃ… ኮናኝ ልማዳቸውን እንደመኮነን ዓይነት መሳይ አስተያየት አይቶአቸው ሲያበቃ ሚጢጢዬ ቅቤ መሳይ ነገር ከዓይኖቹ ጠራርጎ ቀጠለ፡-
 ‹‹ታዲያ ካሊ አዲ ከሚያግዳቸው የቤት እንስሳዎች መካከል በአንድ ምሽት አንዲት ፍየል እንቅልፍ አጥታ ስትጮኽ፣ በጎረኖ ስትሯሯጥና ስትቁነጠነጥ አደረች››   
‹‹ቦታው ጠቧት ነው?››
‹‹የለም፤ አድምጠኝማ! የዚያን ምሽት ፍየሏ ባሳየቺው እንግዳና ያልተለመደ ጠባይ ግራ የተጋባው ካሊ አንድ ብልሃት አበጀ…››
‹‹አረዳት?››
‹‹አይደለም፤ በነጋታው መንጋዎቹን ለግጦሽ በሚያሰማራበት ጊዜ፣ የፍየሏን እንቅስቃሴ በተጠንቀቅ መሰለል ጀመረ፤ ትክ ብሎ ሲያያት አንድ ዓይነት ተክል እየቀረደደች ዋለች። ተክሉ ያማረ ፍሬ ያለውና ቅጠሎቹ ደግሞ ወዛም ናቸው። ግንዱ አመዳም ዓይነት ነጭ፤ ካሊ በተጠንቀቅ ሲፈትሽ ከሌሎች ተክሎች ይለያል…››
እናቴና አረንጌ እኔን መንቀፋቸውን ገትተው ወደ አያቴ አስግገዋል። አረንጌ ከቡናው ዕኩል ታሪክ ፉት እያለች ነበር፤ በጠባቡ የተከፈቱ ዓይኖቿ ግራ በተጋባ ሥሜት ውስጥ እንዳለች ያሳብቃሉ፤ ያንን መከረኛ አናቷን በአድናቆት ላይ ታች ትመታለች፤ ከዚህች ቁንጽል አድናቆት ጀርባ ያደባ ሰማይ-ጠቀስ ጥርጣሬ ወላ ፌዝ እንዳለ ጠርጥሬአለሁ
‹‹ታዲያ ተክሉን ቆረጠው?››
‹‹የምን መቁረጥ አመጣህ? ይልቅ ያ ተክል ፍየሏን ያነቃቃት ሊሆን እንደሚችል ስለገመተ ጥቂት ቅጠል ቀርድዶ ቃመ፤ ለአፉ ቢመረውም ከትንሽ ደቂቃዎች በኋላ ካሊ ብርታት አገኘ። መላ ሰውነቱ ስለተነቃቃና ሐሴት ስለወረረው ጫካ ውስጥ መደነስ ተያያዘ። አልፎ ተርፎ ሌሊቱን በሙሉ ቅንጣት ታህል የድካምና የእንቅልፍ ሥሜት ሳይሰማው ንቁ እንደሆነ አደረ..››
አያቴ ለንጥሻ ዕድሜ እንኳን ትረካውን ሳያስተጓጉል ስኒ እንዳሳልፍ ሰጠኝ፤ ትኩረት ሰጥቶ ስለሚተርክ ትንታ እንኳን እንደማይፈታተነው አውቃለሁ። አያቴ ጮሌ ነው፤ ይህን ሁሉ ሲተርክ ትን እንዳይለው፣ ትን የሚስብሉ ቃላትን ትቶ ትን የማያስብሉትን ብቻ እየመረጠ ለትረካ ተጠቅሞ ይሆናል። ለአረንጌ አቀበልኳት። ቅዝቅዝ ሆናለች፤ በንውዘት ውልብታ ተቀበለቺኝ…  
‹‹እናም በቀጣይ ቀን ከተክሉ ቅጠል ገንጥሎና ፍሬ ለቅሞ በቅርብ ካለ ገዳም ገስግሶ ለአንድ መነኩሴ ሰጣቸው፤ ቅጠሉ በፍየሏና በእሱ ላይ የፈጠረውን ተጽዕኖ ጨምሮ አስረዳቸው። ይኼኔ መነኩሴው ባዕድ አምልኮ ስለመሰላቸው በብስጭት የተቀበሉትን ሁሉ ከእሳት ጣሉ…››
‹‹ጀበና የላቸውም?››
‹‹በካሊ ተበሳጭተው ነው የወረወሩት፤ እንኳንም ተበሳጩ… ካሊ ዕድለኛ ነበርና አፍታ ሳይቆይ ከእሳት የተጣለው ቅጠልና ፍሬ ግሩም መዓዛ ማፍለቅ ጀመረ። መነኩሴው ከብርጉድ ውጭ እንዲያ ያለ ሰላማዊ ሽታ ያለው ነገር አያውቁምና ተደመሙ። ፈጠን ብለው የምሥራቹን ለሌሎች መነኩሳትም አበሰሯቸው። ከዚያ በኋላ በእሳት የተለበለበውን ቅጠልና ፍሬ ቃሙ፤ የግኝቱ ተቋዳሾች እንደ ካሊና ፍየሉ መነቃቃትንና መበርታትን ስለሸመቱ ሌሊቱን ድካም አልባ ጸሎት ሲያደርጉ ብዙ ቆዩ፤ እያለ እያለ ያ ተዐምረኛ ተክል መነኩሳቱን በምስጋና፣ በንባብ፣ በጸሎትና በማኅሌት ወቅት እያበረታቸውና እያነቃቸው ስለሄደ ፍሬውን በወጉ ቆልተው በመፍጨት እያፈሉ መጠጣትን ልማድ አደረጉ። በኋላ በሌሎች አድባራት ለሚያገለግሉ መነኩሳትም ላኩላቸው…››
‹‹ፍየሏን ነው? ተሸወዱ››
‹‹ብርታትና ንቃት የሰጣቸውን ተክልና ተዋጽኦውን እንጂ! ቀጥሎ ተዐምረኛው ተክል ሥያሜ እንዲያገኝ ብዙ መከሩ፤ አውጥተው አውርደው በመጨረሻ በተገኘበት ሥፍራ እንዲሠየም ቆረጡ፤ ካሊ ተክሉን ያገኘው ‹ማኪራ› ከተባለ ሥፍራ፣ ልዩ ቦታው ‹ቡኒ› ስለሆነ ‹ቡና› ተብሎ ተሰየመ፤ በጊዜው ለንግድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የመናዊ ነጋዴዎች ቡናን ወደ የመን፣ ቱርክ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና አውሮፓ ነግደው ለዓለም አስተዋወቁ። አንዳንድ ሥሞች ከግለሰቡ፣ ከአካሉና ከግኝቱ ቅርብ ካለ ነገር ወይም ከተገኘበት ሥፍራ፣ ከሚያወጣው ድምጽና ሌላም ምክንያቶች ተያያዥነት በመነሳት ሊሠየሙ ይችላሉ፤ ቆይ ለምሳሌ ከከፍታ የሚምዘገዘግ ውኃ ‹ፏፏቴ› የተባለው ከሚያወጣው ድምጽ በመነሳት እንደሆነ ዓይነት ማለት ነው…››
‹‹እና ምን ይጠበስ?›› ምሣሌው ስለተሳከረብኝ በሸቅሁ፤
‹‹ምንም አይጠበስ›› ብሎ ቀጠለ ‹‹…ተክሉ ከቡኒ፣ ማኪራ፣ ካፋ መገኘቱን ያረጋገጡ ነጮች ደግሞ ‹ኮፊ› በማለት ይጠራሉ። የሚገርመው አረቦቹ በነገዱ የኢትዮጵያ ቡና ‹ኮፊ አረቢካ› የሚል ሥም ተሰጠው። ትክክለኛው የቡና መገኛ ቡኒ፣ ማኪራ፣ ካፋ መሆኑንና ሥሙ ደግሞ ‹‹ኮፊ-ካፋ›› እንደሆነ የሚያረጋግጥ ጥናት አለ፤ ‹‹Intimacy among Coffee and Kaffa: A Brief Contemplation on the Origin of Coffee›› የሚል ርዕስ ያለው። ለዚያውም በልጄ፣ ባንተ አባት የተሠራ›› ይኼን ብሎ እጄን ስቦ ጉያው አሳረፈኝ፤ ጸጉሬን ዳብሶ ሳመኝና ላይ ታቹን ሰልሎ (የምናወራ ሰዎች ወሬ አድማጭ እንቋምጣለንና)፡- ‹‹በሉ ቡና ስጡት›› አለ፤
‹‹በዚህ ዕድሜው ቡና አንቃሮ ሃሜተኛ እንዲሆን ነው?›› አረንጌ፤
‹‹ቡና የሚጠጣ ሃሜተኛ ነው ያለው ማነው?››
‹‹ኧረ ስቀልድ ነው››
አያቴ ከዚህ በፊት በፊቱ ተቆጥቶ አያውቅም። ዓይኖቹ ይልጣሉ። አረንጌ እየተርበተበተች ቀድታ አቀበለቺኝ፤ አሹቅ ቃም አድርጎ ማርሽ አስገባ፡- ‹‹ቡና የሚጠጣው ተሰብስቦ ለማማት ሳይሆን ተሰብስቦ ለመምከር ነው፤ ደካሞች ናቸው ግብራቸውን ቡና ላይ ያላከኩት። ቡና ሳይጠጡ ማማት አይቻልም? ለነገሩ ከታሪክ አተላ ጋር በአንድ ጣሪያ ማደር ከባድ ነው። የሆነው ሆኖ ቡና ጥልቅ ኢትዮጵያዊ ሚስጥር ያለው ሀብታችን ነው። ልብ ብሎ የሚያጤን የለም እንጂ፣ ቡና ገና ሲያፈራ ደማቅ አረንጓዴ ቀለም ያለው ሲሆን፤ በሚጎመራበት ወቅት ደግሞ ቢጫ ነው፤ በመጨረሻ ተለቅሞ ለመጠጣት ሲደርስ ቀለሙ ቀይ ይሆናል። አየሽ የተከበረ ሠንደቅ-ዓላማችን ማለት ነው ቡና። ሠንደቅ-ዓላማችን ከቡና ሚስጥር ጋር የተሳሰረ ነው። አናርኪ ሁላ መች ይኼ ይገባዋል? እናም ዳተኞችና ወሮበሎች ያበጃጁትን የቸከ ተረት ነጋ ጠባ እያመሰኳሽ ተላላ አትሁኚ። ቡና የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን መተሳሰሪያ ገመድ ነው፤ የመሰብሰቢያ ምክንያት ነው። ቡና የሚጠጣ ደግሞ ጀግና ብቻ ነው፤ ስለ ሠንደቅ-ዓላማው ፍቅርና ክብር ራሱን ለመሰዋት የተዘጋጀ፣ ወገኑን ወዳድ…›› ይኼንን ብሎ ቡናውን ፉት አደረገና ቀጠለ…
‹‹ውሽልሽል ሥነ-ልቡና ያላቸው ግን አንዴ ‹ቡና የሃሜተኛ ነው› ሌላ ጊዜ ‹ቡናን የፈጠረው ሰይጣን ነው› ይሉሻል፤ ሰይጣን ፈጣሪ ሳይሆን ተፈጣሪ መሆኑን ማን በነገራቸው? ለነገሩ ዳፍንት ነው ጋርዶባቸው ዓይነት። አባቶቻችን ቡና በመጠጣት ሽፋን ተሰብስበው ስለ ሠላም ይመክራሉ፣ ስለ መተሳሰብ ያውጠነጥናሉ፣ ስለ ደግነት ይገስጻሉ፤ አንቺ ያልሺው ግን መናኛና ክብረ-ነክ የሆነ ቧልት ነው›› ዳግም አሹቅ ዘገነ፤ ስለደከመው ማርሽ ሊቀይር ነው ማለት ነው፤ ግራ ግብትብት አለኝ፤
‹‹ያልኩት ገብቶሃል?›› ከአፉ የመነጨ የአሹቅ ጠረን ወጋኝ፤ ለአያቴ ጥያቄ አረንጌ መልሴን ራስ በመነቅነቅ ትርኢት ለውሳ መለሰች፤ አልተቀየምኳትም ከእሷ ኮርጄ ራሴን ነቀነኩ፤ ግን የተባለው ገብቶኝ ነበርን? ያቺ አረንጌስ? እኔ እንጃ፤       
*  *  *
የወበራች እናቴን ተጠጋኋት። ብጠጋትም አላናግራትም ግን። ያልለየለት የተስፋ ቅኝት ብትት-ብትት ያደርጋታል። ሁኔታዋ ፈጽሞ እንግዳ ሆነብኝ። ፍርሃት እንደ ሻህላ ይቧጥጠኛል። ድንገት እምር ብላ፡- ‹‹አምላኬን አየህልኝ! አባትህን ሲልክብኝ!›› በድንጋጤ ልቤ ጫማዬ ውስጥ ገባች፤ እጄን ሃፈፍ አድርጋ እውስጥ ገባን። ማጀት ገብታ ቡናውን አከታልፋ ሳሎን አወጣች። የስንዴ ዳቦ በትልቅ ገበቴ ሞልታ አቀረበች። አምላኳን ማመስገንዋ ነው፤
‹‹አንት አረንዛ ሆድ፣ በአባትህ መመለስ አልተደሰትክም?››
ከእጇ ተቀብዬ ፉት ለማለት ወደ አፌ ያስጠጋሁት ስኒ መሬት ወርዶ ፍንችር አለ። ምን ይዤ ልደሰት! የቤታችን መንፈስ በቅዠት እጅ ይውደቅ ወይ በእውን ዓለም ስላልገባኝ ዘርፈ-ብዙ ውርክብ ተወራከብኩ… አንዴ እዚህ ጋ የቅዠትና የእውን ዓለም የሚለያዩበት ትክክለኛ መስመር የት ጋር እንደሆነ ተንትኖ የተረዳ ማነው? ሁለቱን ዓለማት በትክክል የምንረዳው በምክንያታዊነት ላይ ተመሥርተን ከሆነ መለኪያቸው ወይም መስፈሪያቸው ምንድ ነው? ታከተኝ…                   
‹‹አባትህ ሰው ሆኖ ሞቶ ኮከብ ሆኖ መጣ እያልሺኝ ነው?››
‹‹መጠርጠሩስ!›› ረገጥ አድርጋ፤
የቆረሰቺውን የዳቦ ሙዳ ወደ አፍዋ ከሰደደች በኋላ፡-
‹‹ግና አመጣጡ እንኳን ለወሬ ፍጆታ እንዳልሆነ አውቃለሁ›› ብላ የመኮፈስ ስሜት ጎበኛት…
‹ወይ ጉጉጉድ!› ለራሴ
‹‹እና?›› ለእሷ
ጥቂት ተንጠርብባ… ‹‹ከሰው መርጠው ለሹመት፤ ከእንጨት መርጠው ለታቦት ነውና ብሒሉ የአባትህ አመጣጥ ጥንቃቄ የታከለበት ምርጫን ተከትሎ ነው። አመጣጡ…›› በሽኩክና ብልሃት ወደ ጆሮዬ ተጠግታ፡-
‹‹የእኔ ጀግና የመጣውማ ከዚያች የማሽላ ቂጣ ከምታሻምድ አመዳም… ሥሟን ቄስ ይጥራው…›› የንቀት አንገረገበች
በዪ ሲላት፡-
‹‹ከዚያድ ባሬ - ሶማሌ ነጻ ሊያወጣን ነው!›› ብላኝ አረፈች
‹‹እንዴት?››
‹‹እንዴት ማለት ሸጋ! ይኼውልህ የእኔ ልጅ፣ ከጥንቱ ጀምሬ ባወሳህ የሚሻል ይመስለኛል›› ቡናዋን ፉት አደረገች፤ ጥቂት አሰብ አድርጋ ደግሞ፡-
‹‹በአጤ ምኒልክ ዘመን ማን ወረረን? ያ-ሶላቶ!›› ራሷ ጠይቃ ምላሽ ሰጠች፤ ቀጥላ፡-
‹‹ታዲያ ሶላቶው ጥሊያን ሲወረንና አፈር ልሶ አፈር ሲያስልሰን በማን ተራዳዕነት ነበር ያቸነፍነው? በአራዳው ጊዎርጊስ ነዋ! ካሕናት ታቦት ተሸክመው አድዋ ዘመቱ፤ ምንም እንኳን ጥሊያኖቹ ግሳንግስ መሣሪያ አግተልትለው ሊወርሩን ቢቃጡም ጊዎርጊስ በአፍጥማቸው ደፈቃቸው። ሀገሬም ድል አደረገች። እግዚሔር ያሳይህ… አሁን ደግሞ ያቺ ችጋራም ሶማሌ በተራዋ ልትወርረን ቃጣች። ነገሩ ‹ላታመልጪኝ አታሯሩጪኝ› ነውና እስከ አጥንታቸው ድረስ የሚዘልቅ ውርደት መከናነባቸው ላይቀር ጦርነት ከሚከጅሉ የዘንጋዳ ቂጣቸውን ጠፍጥፈው ቢበሉ ይሻላቸው ነበር ባይ ነኝ፤ እነዚህ አመዳሞች!...››
‹‹መወረፉን ተዪና ንገሪኝ›› ማለት ቃትቶኝ ዋጥኩት፤
‹‹የሆነው ሆኖ ሶማሌ ወረረችን፤ በጥሊያኖቹ ጊዜ ረድቶ የነበረው ጊዎርጊስ አልነበር! አሁን ደግሞ አባትህ ታጨ! ያው በአባትህ ኃይል የሶማሌ አንገት ሊሰበር ነው!›› ብላ እልልታዋን አቀለጠች፤ በማመንና ባለማመን ቅርቃር ውስጥ ተሰነቀርኩ፤
*  *  *
እርሾ ልትወስድ ቤታችን እየመጣች የነበረች አረንጌ እልልታው ልብ ነስቷት ቱር ብላ ገባች። የእልልታውን ምንጭ በመለየት ፈንታ እናቴን አጀበች፤ ከዕጣኑ ጭስ ጋር ተደምሮ ቤታችን ታቦት የወጣበት ቤተ-መቅደስ መስሏል፤ አረንጌ ከእናቴ እጅ ጀበናውን ተቀብላ በረካ ጣደች። ወዲያው ደግሞ ቂጧን ከበርጩማ ጥዳ ወሬ ማንገዋለል ጀመሩ፤ በእነዚህ ሴቶች ዘንድ የጀግንነት ዓይነት ስንት ቦታ ሊከታተፍ ነውን? ምን ዶለኝ? ችላ ብያቸው ስብ ቡናዬን አጣጥማለሁ…
…ወዛም ላት መሳይ ቡና የጎበኘኝን ብርድ እያበራየ በጉሮሮዬ ይንከላወሳል፤ የጥቁር ስንዴ ዳቦ በግራ እጄ ተጭኖ ደረቴ ላይ ተጋድሟል። መብረቁ ደጋግሞ ሰማዩን ያርሳል፤ እውጭ ስመለከት ነጫጭ የዝናብ እንክብሎች ይረግፋሉ፤ ሁለቱ ሴቶች በየመሀሉ ከንፈር ይመጣሉ፤ ከሰል ማንደጃው በሰፊ አፉ የተንደረከከ ፍም ያላምጣል፤ ስቡ የበዛ ቡናዬን እያላመጥኩ አለሁ፤ ገድላ ገድል ይንበለበላል፤
ቆይቶ፣ ቆይቶ አረንጌ እርሾ ይዛ ሄደች፤ በዝናቡ አሻግሬ እያየኋት እየቀጠነች እናቴን ለትረካና መወድስ፣ እኔን ለተተራኪነት ጥላን፤ እናቴ አቅፋኝ ትፍነከነካለች። ሰውነቷ ሞቆ ደስታዋ አላባራም። ሳቅ የተከለው ደስታ ውስጥ ሆና ራሴን ትነካካለች። በዕውኑ የደስታ ምንጯ የሚያስደስት ነበርን? የአባቴ ‹ጀግና ነው› መባል ስለምን አልተዋጠልኝም? የደስታዋ ተቋዳሽ ያልሆንኩት ልቡናዬ ጭንጫ ስለነበር ነውን? ከምሶሶአችን ሥር ያደባው ሕቡዕ ሚስጥር ግራ መጋባት ውስጥ እንደሰነቀረኝ ኖርኩ…    

Read 1923 times