Sunday, 09 July 2023 17:33

አላዛር

Written by  ሶስና ሰይፉ
Rate this item
(8 votes)

 ከመጋረጃዉ ዉስጥ ህይወት ያለ አይመስልም። እሱን ቦታ እፈራዋለሁ። በልጅነቴ ምሽት ከሆነ በኋላ ከእንቅልፍ መዘግየት አይፈቀድልኝም ነበር። ማለዳ ስነቃ በጭስ ይሁን በእንቅልፍ እጦት ወይም ሌላ ለእኔና ለልጅነት ልቦናዬ ባልተገለጠ ምክንያት የእናቴን ፊት እዚህና እዚያ ተዘባርቆ አገኘዋለሁ። ከወትሮው ፈጥኜ ከተነሳሁ ሌላም ሌላም አያለሁ። የወንድ መታጠቂያ ቆዳው የነተበ ቀበቶ፣ አንድ እግሩ በወለቀው ገዳዳ ወንበር ላይ ተንጠልጥሎ አያለሁ። የቆሻሻውና የእርጅናው መጠን ከውሎውና ከረገጠባቸው የህይወት ዳናዎቹ የተረፉ የሚመስሉ ብዙ ምልክቶችን የያዘ ጫማ (የእኔም የእናኑም ያልሆነ) በቤታችን ደጃፍ ተቀምጦ አያለሁ። ቀን ቀን ስንቸገር እናኑ አትበላም ጠግቤያለሁ ትላለች። አንባሻዉን ወደ ፊቴ ትገፋለች። ስትበላ አይቻት ስለማላውቅ በኩርፊያ ከንፈሬን ስጥለው፣
“ጥጋበኛ!” ትለኛለች። “እየኖርኩ አይደለም እየሞትኩ ነዉ ያጠገብኩህ!” ትጨምርበታለች።
ሰው እንዴት እየሞተ ያጠግባል? እንድትበላ እፈልጋለሁ። ፀጉሯን እንድታበጥር፣ እንደ አብዲ እናት ራሂማ ሰዎች ደንግጠው ሰላም እንዲሏት፣ እንደ ጋሽ ተፈሪ ጊዮርጊስን እንድትሳለም፣ ሌላም እናኑ በህይወቷ አድርጋቸዉ የማታውቅ የሚመስለኝን ሁሉ ግን እሱዋ ቀድሞውንም ማለዳ ነቅቼ ስመለከታት ትቆጣለች። ሁሌም በእኔ ላይ እንደተናደደች ነው።
እየደጋገመች “አንተን ወልጄ ነው ልጅነቴን ያጣሁት” ትላለች። ደግሞ የእሷ ልጅነት እንደምን ያለ ነዉ? እነ አብዲን የመሰሉ ጓደኞች ነበሩዋት? ከሎሚ ትከሻ እንደማይጠፋው ድመት የምታዝለው መጫወቻስ? እና እነዚህን ሁሉ በምን ሰበብ እኔ አሳጣሁዋት?
ሥጋዬን ሸጬ የምኖረው አንተን ለማሳደግ ነዉ! ትለኛለች። ይሄንን ንግግሩዋን ስሰማው እናቴ የውሸታሞች ሁሉ ውሸታሟ ትመስለኛለች። ሥጋ ሸጦ የሚኖር ሰው እንዴት አንድ ቀን እንኩዋን ሥጋ አይበላም? ሎሚን ጠየኩዋት፤ ዶሮ ማነቂያ ብዙ ሥጋ መሸጫ ቤቶች አሉ፣ ነገር ግን አንዱም የእናትህ አይደለም ስትዋሽ ነው፣ አለችኝ። አፈርኩባት። ከእኩዮቼ ጋር እንድጫወት አትፈቅድም። ዳሩ እሱዋ ሀጃዋን ሞልታ የተመለከተችኝ ቀን ብትፈቅድ የእነሱ ወላጆች ልጆቻቸውን ከእኔ ያሸሻሉ። ብቻዬን ስሆን ስለ እናኑ በየቀኑ ስለሚበቅሉ ምልክቶች አስባለሁ። ሌሊት ስለሰማሁት መቃተትና የአንዳንድ የገንዘብ የሚመስሉ ድምፆች እንዲሁም ከመጋረጃው ጀርባ ስላለው የእናኑ መኝታ ስለ ሁሉም አስባለሁ።
እሷ እና እኔ የማይቀሩ ትዕዛዛት አሉን፡፡
ሀ/ አላዛር በጠዋት እንዳትነሳ!
ለ/ አላዛር መጋረጃውን እንዳትከፍት!
ሐ/ አላዛር እዚህ ቤት የሚመጣን ሰው ምንም መጠየቅ አይፈቀድም!
መ/ አላዛር ወተት ግዛ!
ይህንን ወተት እንዳፈላ አዛኝ ከሄደችበት እስክትመለስ ቀልቤ በተከለከልኩት ጨዋታ ይሰረቅና ትንሽ እንኳን በውስጡ እንዳይቀር ሆኖ ይገነፍላል። መጠጥ ትጠጣለች። ለእኔ ግን ይሄ የሰይጣን ጠበል ነዉ ትለኛለች። አምናታለሁ። ሰኢድን ብዙ ጊዜ “የሰይጣን ጠበል ስጠኝ” ብዬው አውቃለሁ፡፡
የተላኩት ምን እንደሆነ ያውቃል። ለእኔ የሚያዝን ብቸኛ የመንደራችን ባለ ሱቅ ነው ሰኢድ፡፡
“እውነትም ሰይጣን ይላል” ብዙ ጊዜ ተቸግረንና የምንበላዉ አጥተን ታለቅሳለች። ታድያ አንድ ቀን ገና እንቅልፍ እንደጀመረኝ የእናቴ መተኛ ከሆነው መጋረጃ ውስጥ የሚያጣጥር ድምፅ ሰማሁ። እናኑ እንደዚህ ጮሀ አታለቅስም። ልከፍተው ፈለግሁ።
“አላዛር መጋረጃዉን እንዳትከፍት!” ተዉኩት፡፡
እንዳልሰማሁ ሁሉ የነተበ አንሶላዬ ውስጥ ተወሸቅኩ። በፍርሀት ክንብንቤ ውስጥ እንቅልፍ ወሰደኝ። ጠዋት እንደነጋ ባውቅም እናኑ ድምፁዋን እስክታሰማ መነሳት አልችልም።
“አላዛር” አለችኝ። ከክንብንቤ ተንፏቅቄ ወጣሁ፤ ዛሬም ሌላ ምልክት ዐየሁ። ዐይኖቼ በበለዙ አንገቷ ዙሪያ በተቀመጡ የጣት ምልክቶች ጀርባ ይንከራተታሉ። እንዲህ በማያልቁ ጥያቄዎችና በስስት ሳያት ታውቅብኛለች።
“ወተት ግዛ ዳቦም ጨምር፣ ዛሬ እንደፈለክ መጫወት ትችላለህ፣ ሎሚንና አብዲን ጥራቸውና ሜዳ ሂዱ አሞኛል፤ እኔን አትቀስቅሰኝ” ብላ መጋረጃ ዉስጥ ተመልሳ ገባች።
ያኔውኑ  መሄድ አስጠላኝ። ተከልክዬው ያናወዘኝ ጨዋታ አልስብ አለኝ። ይህን የእናኑን ፊትና ፀጉር አንገቷን ጨምሮ አይቼው እንደማላውቅ ሁሉ ዛሬ ምን ተገኝቶ ነው፣ ከታሰርኩበት ብፈታ በነፃነት ብረር ብባል እንቢኝ ያስባለኝ? ደግሞስ እኩዮቼ ከእኔ ጋር ሲጫወቱ ቢታይ እንደሚቆነጠጡ እያወቀች እናኑስ ምን ሆና ነው? መላሽ እና ሰሚ ባይኖራቸውም ጥያቄዎቼ ከወትሮው እየጨመሩ ነው።
ወደ ሰኢድ ሱቅ ሄድኩ። ... ለመሮጥ እንደሚንደረደር ሰው አንዴ ወደ ፊት አንዴ ወደ ኋላ በቄንጥ ስራመድ የዝርዝር ሳንቲሞቹ ጫጫታ ከመዳፌ ውስጥ ይሰማል። ሰኢድ ሱቁ ውስጥ አጎንብሶ እንቁላል ሲቆጥር ደረስኩ እንዳየኝ ጀርባውን ሰጥቶኝ ማቀዝቀዣውን ከፈተና ሾላ ወተት ሰጠኝ። ምንም አልተናገርኩም። ቆሜ እመለከተዋለሁ።
“ዳቦ የለም አርፍጄ ስለተነሳሁ አልተሰለፍኩም” አለኝ።
እናኑ የሰጠችኝኝ አሮጌ ሳንቲሞች በሙሉ አስቀመጥኩ። የዳቦውን መለወጫ ወደ ፊቴ ገፋልኝ። ወተቱንና ቀሪ ገንዘቤን ይዤ ከሰኢድ ፊት ጠፋሁ። በመጣሁበት አኩሃን ወደ እናኑ ሄድኩ።
“ኮቴ የለህም እንዴ?! አንተ ዲቃላ!?” አፈጠጠችብኝ።
ልክ አንድ ነገር ስትሰራ እንደነበር ሁሉ በመግባቴ በረገገች። ዐይኖቿ ውስጥ አሁን ድረስ ስም ያልሰጠሁት ማጣት ዐየሁ። የልጅነት የዐይኖቼ መዳፎች የፊቷን ቆዳዎች ከነወዛም ቀዳዳቸው ሳያዩ ተአምር በሚመስል ፍጥነት ይስሏቸዋል። አዉቃታለሁ።
“ተቀመጥ! እና ብላ”! አለችኝ።
የወተቱን ማሸጊያ ከፍቼ አንከርፍፌው እመለከታት ጀመር። ይገባታል።
“ዳቦ የለም?” አለችኝ። መልሴን ሳትጠብቅ ተቆናጥራ ከመጋረጃውና ከአልጋው ወጣች። ትሸታለች። ይሄን ሽታ ሜዳ ኳስ እና አባሮሽ ስንራገጥ ከውስጤ የሚወጣው የልጅነት ወዝ ካገነነውና እኩዮቼ ከሸተታቸዉ “ሴት ሴት ይላል” በማለት ያውካኩብኛል። የከርቤና በከተማው እጅግ ርካሽ ሽቶ ቃና። የእናኑ ግን የብዙ ሰዎች ወዝ አለበት። የዳቦ ቤቱ፣ የእንጨት ሰራተኛው፣ የተራ አስከባሪው፣ የታክሲ ሹፌሩ፣...
ከአልጋው ግርጌ የበላንበትን ቀኑንና ሰአቱን የማላስታውሰው መጥበሻ ከፈተች፤ ሁለት ባል እና ሚስት በረሮዎች ወጡ፡፡ ምንም አይነት ነፍሳት ሁለት ሆነዉ ሲሄዱ ካየች ባልና ሚስት እምትላቸዉ ሎሚ ናት። እኔ ለምን አልኩ? አንደኛው በረሮ (ይመስለኛል ባልየው) ከመጥበሻው ሲሮጥ ወጥቶ ወደ አልጋው ስር ገባ። ይታየኛል እዛ ምን እንደሚያገኝ፣ የእናኑ አይጦች መሀሉን የበሉት የውስጥ ሱሪ፣  እናኑ ጓደኛዋ እንደሰጣት የነገረችኝ ትንሽዬ ኳስ (የእኔ ነው። በቅጣት ሳልቀማ በፊት ድሮ ድሮ..) መቼ አድርጋቸው እንዳረጁ የማይገቡኝ ውብ እና ውድ እንደነበሩ የሚያሳብቁ አሮጌ ጫማዎች፣... ብዙ ጊዜ እንደ ፊኛ ስነፋው አግኝታኝ በርበሬ የታጠንኩባቸው ወዛም ላስቲኮች (የእነዚህ ላስቲኮች ማሸጊያ ትንሽ ካርቶን ላይ የተቃቀፉ ወንድና ሴት አሉ። ደመ ነፍሴ ሴቷ እናኑን ትመስላለች ይለኛል... እንደውም እናኑን እራሷ ናት። ግን እሷ እንደዚህች ሴት ፊቷ አያምርም፣ ፀጉሯ አልተበጠረም የሚያቅፋትም የለም። እንጃ ለምን እናኑን እንደመሰለችኝ። ለምን ሎሚን አልመሰለችኝም? ለምን እትዬ ራህማን አልመሰለችኝም? የተቃቀፉት ሰዎች ለምን በፊኛው ላስቲክ ላይ እንዳሉ አስባለሁ...) ሌላኛዋ (ሚስት በረሮ) ዘግይታ ከፊቴ ጠፋች። ከመጥበሻው ውስጥ የሰነበተ ቁራሽ ዳቦ ሰጠችኝ። ደስ አለኝ። አሁንም አያታለሁ።
“አታፍጥ! እኔ አልበላም ብላና በሩን ዘግተህ ውጣ!! አሞኛል” ብላ መጋረጃዉ ውስጥ ተወረወረች።
ትንሽ ደቂቃ ዝም ብዬ ተጎለትኩና መብላት ጀመርኩ። የዳቦዉ ቃና ስም ልሰጠው የማልችለው ነው። ግን ልምድ አለን። ተስማምተናል። በሰኢድ ወተት እያማግኩ መብላት ጀመርኩ። “አታጨብጭብብኝ!”... (ሰው እንዴት በአፉና በምግብ ያጨበጭባል?)
ከእናኑ ንጭንጭ ጋር ተላምጄያለሁ። ዳቦውን እንዳልራበኝ ሁሉ አፌ ውስጥ አንቀዋልለው ጀመርኩ። ድንገት ዞር ብላ ዐየቺኝ። ከውስጤ የምትፈልገው ነገር ያለ ይመስል በዐይኖቿ መረመረችኝ። አጎነበስኩ። በቀስታ ተጠጋችኝ፡፡
“የወተቱስና የዳቦው መልስስ አንተ?” አፈጠጠች።
“ጭራሽ ኪስህ አርገህ ዝም ማለት ጀመርክ? እኔ ነኝና ልጅት!”...ከአልጋው ወረደች።
ለኩርኩም በታጨ ጭብጦ መዳፏ አናቴን አንዴ አነደደችው። ከአፌ የታኘከ እና ያልታኘከ ወጣ። አጎነበስኩ
“ቀና ብለህ እየኝ እስቲ ቀና?” ፊቴን አየችኝ።
እንደ ጣረ ሞት እፈራታለሁ። ጥለኸዉ ነው? የምንግባባዉ እንደዚህ ነው። አንዳንዴ ይህቺ ሴት እናቴ ልላት ሲቸግረኝ ግን ደግሞ ይሄን ይሄን መረዳቷን ሳስተውል አምላኬ ልላት ይቃጣኛል።
“ምን ስታደርግ ነው የጣልከው?” እንዲህ ዐይን ዐይኔን ስታየኝ ፊቴን አሸሻለሁ፡፡
“ወይኔ አምላኬ ምን አርጌህ ነው ይሄን የጣልክብኝ?” ወደ አልጋዉ ዉስጥ ተመለሰች። ስትናፈጥ እሰማታለሁ (በአንሶላ ነው፣ አልያም በመጋረጃዉ... በሌላም በሌላም)። ዳቦውን ከእጄ አራግፌ ወተቱን አስቀመጥኩና የንፉቅቄን ወደ መዝጊያው ሄድኩ ከፍቼ ስወጣ እናኑ ድምፁዋን ከፍ አደረገች። ለቅሶዋ ነው። ወጥቼ ለእኔ ብቻ ከሚበቃው የቤታችን የውኃ መከላከያ (ተከላክሎልን ባያውቅም፣... እንደውም እናኑ ባለፈው ክረምት “እዚህ ቤት ውስጥ ከመሆን ጎዳና መውጣት ይሻላል!” ስትል ነበረ። የገባው ውኃ የሚጠቅመውንም የማይጠቅመውንም አበላሽቶብን ይሄዳል። ዳሩ እዚህ የሚጠቅም የለንም።) ደፉ ላይ ተቀመጥኩ። ትንንሽ አይበሉባዎቼን በአንገቴ ግራና ቀኝ አድርጌ አንዴ ደግሞ በመዳፌ እየቀያየርኩ የሜዳውን ህይወት ማየት ጀመርኩ።
ለወትሮም ቢሆን ጥያቄዎቼ ብቻዬን ካገኙኝ ይበዛሉ። እናኑ ለምን ታለቅሳለች? እሷም የሚመታትና የሚቆጣት አለ? ደግሞ ሁሌም ሳንቲም ታገኛለች? ሳንቲም ስል የወተቴ መልስ ትዝ አለኝ። መሬቱ ላይ አቀርቅሬ በሰኢድ ሱቅ አቅጣጫ ልፈልገው ተነሳሁ፣ መሬቱን እያሰስኩ ከነጋ እንዳልተመላለስኩበት ሁሉ በትናንሽ የውኃ ርክፍክፎችና ጭቃ መሆን ባቃው አፈር መሀል ብዙ ዱካዎችን ዐየሁ። ከዱካዎቹ ውስጥ የወተቴን መልስ በዐይኖቼ እያሰስኩ አዘገምኩ፡፡ የህፃናት ዱካ (ምናልባት የዳቦ ሳንቲማቸውን በርሀብ የፍጥነት ሩጫ ከመንገድ የጣሉ...) የኮረዶች እና የልጅ አገረዶች ዱካ (ወጪት ሰብረው ከቀለም ቤትና ከእናት ቁንጥጫ የኮበለሉ፣... ዶሮ ማነቂያን ግራና ቀኝ የከበቡ....) የጎልማሶች እና የወይዘሮዎች ዱካ (ከእነሎሚ ጋር ስጫወት “አንተ የሸቃላ ልጅ! ከልጆቼ ጋር እንዳላይህ!” እያሉ ቀንዴን የሚሰብሩኝ) የወጣቶችና የአዋቂዎች ዱካ (ተማር እና እናትህን አግዛት ጎረምሳው መንገድ ላይ አትዋል፣... ለእሷም አልጠቀማት!!!) እያሉ ሲላቸው ጆሮዬን በቁንጥጫ የሚያነዱኝ፣ ሲላቸው ፀጉሬን የሚደባብሱኝ (ልክ እናኑ ከወሩ በስንተኛው ወር፣ ከዓመቱ በየትኛው ዓመት፣ ከሳምንቱ በስንተኛው ሳምንት፣ ከቀኑ በየትኛው ቀን እንደሆነ በማላውቀው እንደዳበሰችኝ ሁሉ) ሌሎች የህፃናት ዱካ (ከአቡበከር እስከ አብዲ ከሎሚ እስከ አስኒ የተመላለሱበት)፣….. ሲልም ባለ ከረባቱ፣ ባለ ጎሚስታው፣ ባለ መታወቂያው፣  ባለ ቁንቡራው፣ ባለ አተላው፣ አንዴ ሽቁጥቁጡ፣ አንዴ ባለትፋቱ፣...
በዚህኛው ጎዳና ማን ያልሄደ አለ? ደግሞስ አብዛኛው መድረሻው ለምንድነው ከእናኑ ደጅ የሆነው? አሁንም አስተውያቸው በማላቃቸው ከመንደሬ በተሳሉት የእግር ፊርማዎች ውስጥ አጎንብሼ ስሙኒዬን እፈልጋለሁ። የዳቦ ነዋ! ሥጋ ተሽጦ የሚገኝ የዳቦ ዋጋ፡፡ ሳገኘው ለእናኑ እሰጣታለሁ።
ፈገግ ትል ይሆን?
2012



Read 1187 times