Sunday, 09 July 2023 17:36

«ከጂ’ራትም የለው»

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(4 votes)

 ጠባብ የመተላለፊያ መንገዱ ጠመዝማዛና ዘላለማዊ ይመስላል። በመተላለፊያው ውስጥ የሚያስተጋባውን ደካማ የውሃ ድምፅ እሰማለሁ።
ድምጹን ተከትዬ ወደ አንድ ትንሽ የከርሰ ምድር ወንዝ ደረስኩ።.ከመሬት በታች ወደሆነው ወንዝ ዘልቄ በመግባት ፈጣን ጅረት ወደ ታች እንዲወስደኝ ፈቀድኩ። ወንዙ በዋሻው ግድግዳ ላይ አልፎ አልፎ የተሰቀሉ ችቦዎች እየበሩለት በቀጥታ መስመር ሲፈስ ሰው ሰራሽ ይመስላል።
በድንገት ወንዙ በከፍተኛ ሁኔታ ወድቆ ወደ ቁልቁል ፏፏቴ ስነጉድ ራሴን አገኘሁ።

         ከእንቅልፌ በነቃሁ ጊዜ አካሌን እስር ቤት ውስጥ  አገኘሁት።ኹለት የነተቡ ፍራሾች ቁራጭ ብርድልብስ ለብሰው ጥግ ላይ ተጋድመዋል። ብልጭ ድርግም የሚል መብራት ክፍሉ ውስጥ አለ። ከውጭ፣ አንዴ የሚደምቅ አንዴ የሚቀዘቅዝ ድምፅ ይሰማኛል። የእግር ዳናዎች እና የሚቀባበሉ ጥይቶች ድምፅ በጀርባዬ በኩል ይከናወናሉ። ፀጉሬ ቆመ። እደርስበት የለኝም። እዚህ እንዴት እንደደረስኩ ለማሰብ ስሞክር ፍርሃት እና ጭንቀት አላሰናዝርህ አለኝ። ብቻዬን ነኝ። በስተሰሜን  በኩል ካለችዋ ክፍት ጠባብ ክፍል በቀር የብርኀን ዘንግ ያለፈበት የለም። ግድግዳዎቹ ቀለም አልባ እና የተሰነጣጠቁ ድንጋዮች ናቸው። ወለሉ ከበረት የሚለየው እኔ ስለዋልኩበት ነው። ወጥመድ ውስጥ እንደገባሁ ተሰማኝ። ማን አምጥቶ አኖረኝ? መቼስ ነው ወደዚህ ኩነኔ የገባሁት? ሲዖልስ ከዚህ ትከፋለች?... ሕይወት እሳት ላይ ካልተጣደች የማትበስል(የማትጥም) ሽንብራ...
አሐዱ ቅዠት ፡
ወንጀል ሥሰራ አብረኸኝ ያልቆምክለታ፣ ፍርድ ሳጓድል ለምን ያልክ እንደሁ አይማረኝ አልምርህም። ከመኖር እቀንስሃለሁ አልያም ስቃይህን አበላሃለሁ። የያዙኩት ድንጋይ ይታይሃል? አሁንስ ከእኔ የሚበልጥብህ ማነው ?...ዓይንህ ወደ ሌላ ቢያማትር፣በሐሳብህ፣ ሽባ ሐሳቤን ብትተረትር ወዮልህ! ፀጥ ለጥ ብሎ መኖርን የመሰለ ነገር እያለልህ መንገድ መጋፋትን እንዳትመርጥ። ሴት ልጅ ብትደፈር ዝም በል ፣ሕግ ቢጓደልም እንዲሁ። ከእኔ በላይ ልታውቅ አትችልምና፣ አቅምህም አያዋጣህምና፣ ሁሉም በእጄ ሁሉም በደጄ ነውና _እንዳትጋፈጠኝ። ጓደኝነታችን ይቀጥል ፤ውሸት ስናገር አጨብጭብ ፣ሳጭበረብርም ባላየ እለፍ ።
የዛ ሰው ትዕዛዝ አቃጨለብኝ።
አእምሮዬ በሐሳብ ይጣደፋል። እጄን አጎንብሼ ባይ ካቴና ውስጥ፣ እግሬም የቆመው ቀዝቃዛ የድንጋይ ወለል ላይ ነው። ምን ላድርግ?...ካቴናውን ለማላቀቅ መሞከር፣ በክፍሉ ዙሪያ ዓይኔን ማንቀዋለል አልያም ለእርዳታ መጮህ ምርጫዎቼ ነበሩ።
የክፍሉን ዙሪያ አማትር ገባሁ።
ክፍሉን ዞር ብዬ ስመለከት የብረት መጋዝ በስተቀኝ ካለው የድንጋይ ግድግዳ ላይ አየሁ። በቀዝቃዛና ቆሻሻው ወለል ላይ ድምፄን አጥፍቼ ተረማምጄ የእጄን ካቴና ስለቷን ዘቅዝቃ (ተዘጋጅታ)በተቀመጠችው መጋዝ ቆረጥኩት(ምናልባት ቀደሞኝ ሌላም ታሰሪ አድርጎታል)። እየመገዝኩ ሳለ በሬ ይንኳኳ ነበር። የከስክስ ጫማ ድምፅ በቤቱ ዙሪያ በርክቶም ነበር። የእጄ ነፃ መውጣት አልደነቀኝም አካሌን ከዚህ  የቆሻሻ ወለል፣ እና ከላይ ትንሽ የታሸገ መስኮት ያለው ከባድ የብረት በር እንዴት ላርቀው? ነበር ፍላጎቴ። የፊት የፊቱን እንዲል ጓያ ነቃይ ፤እኔም እንዳደረግኩት።
 ለክፍሉ ደብዛዛ ብርሃን የሚለግስ  በሩ አጠገብ ባለው የዛገ ቅንፍ ላይ የተሰቀለ ብልጭ ድርግም የሚል ችቦ እና የመስኮቷ ጨረር ነው። ወለሉ ላይ የቀደሙት እስረኞች ድንጋዩን ወይም ቆሻሻውን የቧጨሩበት እና አንዳንድ ምልክቶች ከድፍድፍ ካርታ ጋር የሚመሳሰሉ ምልክቶችን ማየት ቻልኩ። የብረት በሩን ልፈትሽ? ችቦውን ልፈትሽ? ወይስ ወለሉ ላይ የጭረት ምልክቶችን ልፈትሽ?
የጭረት ምልክቶች የእስር ቤቱ ካርታ መሆኑን ልብ አልኩ። ዋናውን የወህኒ ቤት አካባቢ እና ሌሎች በርካታ ሴሎች አቀማመጥ ያሳያል። ነገር ግን፣ ከወህኒ ቤቱ ባሻገር ተጨማሪ የነጻነት መንገድ ያለ ይመስላል። ማንዴላ የደረሳት ነፃነት ፣ሮዛ ፓርክ የቀመሰቻት ጽዋ ለእኔ ራቀች። ከፈረስ ጭራ የቀጠነች መንገድ (ነፃነት) ካርታው ላይ እያየሁ ልራመድ ፈራሁ። አፈ-ሙዞች ሰው አይመርጡም ፤ቃታ ሳቢዎችም አስተሳሰብ አያዩም። በዚህ ግሳንግስ ዓለም ውስጥ መኖር መረገም እስኪመስለኝ አሰብኩ። ከሐሳቤ ስነቃ በካርታው ላይ ያሉትን ምልክቶች ልፈትሽ?  ለማምለጥ ልሞክር? ወይስ  ሰው እንዲያድነኝ ልጠብቅ እያልኩ ተጨነቅኩ።
ዓይኔን ወደ ምልክቶቹ ቀሰርኩ።
ምልክቶቹ በማይገባኝ ቋንቋ እንደተጻፉ ተገነዘብኩ። ጥቂት ቀስቶች፣ አንዳንድ ክበቦች እና ኮከቦች አሉ፣ ነገር ግን ምንም ትርጉም ላለመስጠት ሁሉም ነገር ግልጽ ያልሆነ ይመስላል። በመንገዱ ላይ ወጥመድን ወይም መሰናክልን የሚያመለክት አንድ ምልክት እንዳለ ግን አወቅኩ።
ምልክቶችን ዲኮድ ማድረግ ጀመርኩ።
 ምልክቶች ለማጥናት የተወሰነ ጊዜ ወስጄ ትርጉማቸውን ለመረዳት ሞከርኩ። አንዳንድ መሰረታዊ ንድፎችን ማወቅና የተወሰኑ ቅርጾችን ሊሆኑ ከሚችሉ ትርጉሞች ጋር ማያያዝ ጀመርኩ። ካርታው በኃያላን ፍጡራንና በጠመዝማዛ ዋሻዎች ወደተጠበቀው መውጫ የሚመራ ይመስላል። ምልክቶቹ በበለጠ ማሰስ እንዳለብኝና አንዳንድ ሚስጥሮችን እንደያዙ ተሰማኝ። ነገር ግን «ማምለጥ» ይሉት ግዙፍ ግብ ተጭኖኛል። ተነስቼ  ከሴሉ የማመልጥበትን መንገድ ለመፈለግ ወደ ብረቱ በር ሄድኩ። ወደ በሩ ስጠጋ፣ በእስር ቤቱ ውስጥ የሚያስተጋባ የእግረኛ ድምፅ ተሰማኝ። ዱካዎቹ ጮክ ብለው ያድጋሉ። ከበሩም ስንጥቅ በታች ጥላ ይታያል። ፈራሁ።
 ተረጋግቼ  የሚመጣው ሰው እስኪገባ ድረስ ጠበቅኩ።
 እግሮቹ ከበሩ ውጭ ቆሙ። በመቆለፊያውም ውስጥ ቁልፍ ሲዞር ሰማሁ። ከባዱን፣ ዝገቱን በር ከፍቶ በጨለማ ካባ የለበሱ ምስሎች ከፊቴ ተከሰቱ። ፊታቸውን በግልፅ ማየት አልቻልኩም። ነገር ግን አንዱ «ተከተለኝ» ሲለኝ ተከተልኳቸው። ካለሁበት ክፍል የሚያስወጣ ትንሽ ድብቅ መተላለፊያ መንገድ ሰጠኝ ።
ክልኤቱ ቅዠት፡
ግዛቴን ኃይል ይጠብቃታል። ጉልበቴም ተገዳዳሪዎችን ይጥላል። ደሃ ቢጮህ ጉሮሮውን ከማንቃት ውጭ አልሰማውም። አንተም ስለ ድሆች እጮሃለሁ ካልክ የድሃ ደሃ አደርግሃለሁ። «ና» ሲሉህ መምጣት «ሂድ»ሲሉህ መሄድን ምረጥ። የአካልም የአእምሮም እስረኛ ላደርግህ አቅም አለኝ። እንባዎች ሲፈሱ ዝም በል ፤አጠራቅመን ክላሽ እንወለውልባቸዋለን። ዋይታዎች ቢበራከቱም በቸልታ እለፍ በጃዝ ምትክ ይደመጣሉ። ኔሮን ቄሳር ትዝ አለህ? ከተሞችን እያቃጠለ ክራር የሚያደምጠው። ያቺስ ሴቷ ትዝ አለችህ? በሴቶች ጡት ጦር ሰድዳ የምትደሰተው። በቃ እንደዛ መሆን ያምረኛል። አንተ አፍ አውጥተህ የተናገርክ እንደሁ አይማረኝ አልምርህም። ቀዝቃዛ ወለል ምንጣፍህ ፣ጨለማ ጣሪያ ልብስህ ፣ሐሳብ ምግብህ ፣ቆሻሻ ሽታ አየርህ ይሆናል።
የዛ ሰው ዛቻ ሰቅዞ ያዘኝ።
ስጠራጠር እና ፀጉሬ ሲቆም ተመለስኩ_በእስር ቤቱ ውስጥ ልቆይ።
ከምስጢራዊው ምስል እና ወደአልታወቀ መንገድ ከሚመራው ነገር ሁሉ ተቆጥቤ በጨለማ ክፍል ውስጥ ለመቆየት ወሰንኩ። ምሥጢራዊው ምስል ተከትሎኝ መጥቶ ለአፍታ የሚያመነታ ይመስላል። ከዚያም ከክፍሌ ወጥቶ ሲሄድ የማይታይ እጁ በሩን ከፍ ባለ ድምፅ እንዲዘጋ ያስችለዋል። ሌሎቹም ግብረአበሮቹ ተከታትለው ሲወጡ  የእግራቸው ኮቴ  ሲደበዝዝ ይሰማኛል። ብቻዬን ሲተውኝ  እንደገና ወጥመድ ውስጥ ገባሁ።ሌላ መንገድ የማግኘት ሙከራዬ ቀጠለ።አካባቢዬን ለመተንተን እና ሌላ መውጫ ለመፈለግ ከመዞሬ በፊት ጥልቅ ትንፋሽ ወሰድኩ። አንድ ሰው ማሳለፍ የሚያስችል ትልቅ መጠን ያለው የአየር ማስገቢያ ቱቦ በፍጥነት አስተዋልኩ። የአየር ማናፈሻው በብረታ ብረቶች የተሸፈነ ነው።
 የአየር ማናፈሻ ቱቦውን ሽፋን አስወገድኩ።በተወሰነ ጥረት የቱቦውን ሽፋን አስወግጄ ወደ ውስጥ ተሳብኩ። ቱቦው ጠባብ እና ጨለማ ነው።
በእሱ ውስጥ እየተሳብኩ ትንሽ የብርሃን ስንጥቅ አያለሁ። ብርሃኑ የሚመነጨው በሰርጡ በኩል ካለው ትንሽ ፍርግርግ ነው። እንዲህ እንዲያ እያልኩ ወደ ሌላ ደብዛዛ ብርሃን ወዳለው ክፍል ውስጥ ወረድኩ።
በሌላኛው ክፍል ላይ ያለውን የብርሃን ምንጭ መመርመር ቀጠልኩ።
ወደ ብርሃኑ ምንጭ በጥንቃቄ ኼድኩ። ስጠጋ ያገኘሁት ሐቅ ቅስም ይሰብራል። ክፍሉ በመደርደሪያዎች እና በጠረጴዛዎች የተሞላ ነው። ከዚህ በፊት አይቻቸው በማላውቃቸው ጥንታዊ ቅርሶችና ሚስጥራዊ ነገሮች የተሞላ ነው።
 ክፍሉን ለቅቄው ማምለጫ ፍለጋዬ ቀጥሏል።
ጠባብ የመተላለፊያ መንገዱ ጠመዝማዛና ዘላለማዊ ይመስላል። በመተላለፊያው ውስጥ የሚያስተጋባውን ደካማ የውሃ ድምፅ እሰማለሁ። ድምጹን ተከትዬ ወደ አንድ ትንሽ የከርሰ ምድር ወንዝ ደረስኩ።.ከመሬት በታች ወደሆነው ወንዝ ዘልቄ በመግባት ፈጣን ጅረት ወደ ታች እንዲወስደኝ ፈቀድኩ። ወንዙ በዋሻው ግድግዳ ላይ አልፎ አልፎ የተሰቀሉ ችቦዎች እየበሩለት በቀጥታ መስመር ሲፈስ ሰው ሰራሽ ይመስላል። በድንገት ወንዙ በከፍተኛ ሁኔታ ወድቆ ወደ ቁልቁል ፏፏቴ ስነጉድ ራሴን አገኘሁ። ከፍ ያለ የጉልላት ጣሪያ ያለው ትልቅ የመሬት ውስጥ ክፍል ላይ ወጣሁ። በክፍሉ መሃል ላይ አንድ ትልቅ የድንጋይ ምሰሶ ወደ ጣሪያው ተዘርግቷል። ወደ ምሰሶው ስዋኝ ቀደም ብዬ ካገኘሁት ካርታ ላይ ካሉት ምልክቶች ጋር በሚመሳሰሉ በሚያንጸባርቁ ምልክቶች ያጌጠ መሆኑን ተመለከትኩ።
አሁንም በአዕማዱ ላይ ያሉትን ምልክቶቹን በበለጠ ዝርዝር ለማጥናት በመጓጓት ወደ ድንጋይ ምሰሶው ዋኘሁ። በቅርበት ስመረምር፣ ምልክቶቹ ካርታ የሚመስል ንድፍ ሲፈጥሩ አያለሁ። ምልክቶቹን ካጠናሁ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ ካርታው ወደ ሚስጥራዊ መውጫ እንደሚመራ ተገነዘብኩ። ይህ ቦታ ትኬቴ ሊሆን ይችላል።
አምልጦኝ ሊሆን የሚችል ሌላ ፍንጭ ወይም ንጥል ካለ ለማየት በጓዳው ውስጥ ለመጨረሻ ጊዜ ተመለከትኩ። ስዋኝ ያገኘሁት ድንጋይ  ሲገፋ የተደበቀ መሿለኪያ የሚገልጥ ትልቅ ዓለት ነው።
ዋሻው ጨለማ እና ጠመዝማዛ ነው፣ ነገር ግን ወደ ላይ እንደሚመራ ማየት ቻልኩ።  አካባቢዬን ፈትሼ  ደህንነቱ የተጠበቀ መሆኑን አረጋገጥኩ። መሿለኪያው የተተወ ይመስላል፣በአካባቢው ምንም ዓይነት የህይወት ምልክት የለም። አንድ ብኩን እንስሳት ብቻ ከፊቴ ነበር። እጅ እግር ቀርቶ ጅራትም የሌለው።
ሰልስቱ ቅዠት ፡
ሳታውቀው አዲስ ቦታ ላይ ትነቃለህ። የሚገርፍህ ባልክብህ እንኳ ቦታው ብቻውን ስቃይህን ያበላሃል። ከጂ’ራትም የለው ትለውን ግጥም ታነበንበዋለህ። አዎ የምታገኘው እንስሳ ጅራት አይኖረውም _የምትደርስበት ቦታ ስለሚርቅ። ከጂህ (የከዳህ) ግን እንዴት እራት አይኖረውም ብለህ ታስባለህ። አንተን በጨለማ ክፍል አጉሬ ሁለት እራት እንደምበላ ዘነጋህ? ወይስ ሐቁን መቀበል ተሳነህ?...
የዛ ሰው ትንቢት ደረሰ።
በነቃሁባት ሌላ ምድር ፣ኩርትም ብዬ ስውል ሳድር የነካኝ አውሬ እንኳ አልነበረም። ጆርጅ ኦርዌል «እንስሳት ቢጤያቸውን አይገድሉም» ያለው ምሬት የተገለጠለኝ ያኔ ነው። ግርም ድንቅ ቢለኝ...
«ክፉ ሰው ለምን አይሞትም?» አልኳት ነፍሴን
«በክፋት ላይ ክፋት እንዲጨምር» ብላ አሳረፈችኝ።
አሐዱ እውን፡
«ወደ እኔ ፈጥኖ የመጣውን አልበላውም »ብሎ አንበሳ ለጫካ እንስሳቶች መልዕክት ማስተላለፍ። ሁሉም እንስሳት ተሯሩጠው አጠገቡ መገኘት። ኤሊ በፋንታዋ መንቀራፈፍ። አንበሳው በዚህ ድርጊቷ መናደድ።
«ለምን ዘገየሽ?»
«በጫካው ውስጥ ከ’ኔ በላይ አለቃ የለም ብሎ አስቁሞኝ ሌላ አንበሳ»
«እንኺድ አሳይኝ ...እገድለዋለሁ..»
አብረው መኼድ። ባሕር ዳር ሲደርሱ ኤሊዋ የራሱን ጥላ ከባሕሩ ውስጥ መጠቆም። አንቄ ያዝኩት ብሎ ወደ ባሕሩ መግባት እና በዛው መሞት»
የዛ ሰው የተጠራቀመ ግፍ ጎርፍ ሆነ። ከስቃይ አገግሜ ሳገኘው ወደ ጎርፉ ወሰድኩት። ባጠራቀመው ግፍ እንዲዋኝ ራሱን ጠቆምኩት። ክፉ ለራሱም አይራራምና ፣ተቀናቀኙን አይወድምና የሆነው ሆነ። የጠቆምኩት  አምሳሉ ከጂ’ራትም የለው።
  የ«አስፈሪ ቃላት»ን ሐሳብ ...ለሐሳቤ ማወራረጃ ተጠቅሜያለሁ።

Read 681 times