Saturday, 15 July 2023 20:46

በሎሚና በፌጦ የተፈተፈተች!

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(1 Vote)

 ላንቲካ አይደለም፤ እግዚሔር ወደ ምድር የወረደው ሊያስተምር አልነበረም። ጣኦስን በሎሚና በፌጦ ሊፈተፍት እንደሆነ የሚያውቅ አልነበረም፤ ማንም ዓለም በማሰችለት ቦይ ይገማሸራልና እንዲያ፣ እንዲያ ያለ ነገር ላንቲካ ሊመስለው ይችላል…
…ጣኦስ በዓለም ሳንባ የምትኖር አስተማሪ ነች። ሰውነቷ አደይ ተነስንሷል፤ አፍዋ የጣዝማ በር ነው፤ ከምታፈልቀው ቃል (ከንቦቹ ጋር ጣፋጩን እየተሻማ) ሊያወጋት የሚያቆበቁብ መልከ ብዙ ነበር፤ ስታወራ ታዲያ ቁርባን የምታድል ትመስላለች፤ ከአፍዋ ዘቢብ እየዘነበ ዓይነት፤ የዘቢብ ዶፍ ከአፍዋ ዘንቦ ሕዝቡ በጣፋጭ ጎርፍ እንዲጥለቀለቅ የተደረገች የእግዚሔር ሸር፤ ትኩስ ርጥብ እንፋሎት ከአፍዋ ይወጣና ወደ ሰማይ ይምዘገዘጋል፤ ከዚያ የጳጉሜን ሩፋኤል ሲደርስ ዝናብ ሆኖ ምድርን ያረሰርሳል፤ ዕጽዋት በአናታቸው ገብቶ ትን እስኪላቸው ይምግ፣ ይምጉትና ቀጣዩ ሩፋኤል እስኪደርስ በጉጉት ይጠባበቃሉ።
እግሮችዋን አመሳቅላ በተቀመጠችበት እጆቹን የኋሊት ገንዞ የሚታዘዝ አታጣም ይሆናል። በነዚያ በውብ ከንፈሮቿና በውብ ብርጭቆ መካከል ትቦ ሰግስጋ ማንጎ መምጠጥ ያምራት ይሆናል፤ ምናልባት አይስ ክሬም የመግመጥ ሕልሟ ምዋቲዎችን በማስተማር ስለ በለጠባት…
…እተማሪ ቤት የኩታራ ፈስ ቢገኝ ነው፤ በምንም መሀል ግን የነፍሷን ጥያቄ መመለስ ብታልምስ? ስለ ሙያ ታወጋለች፤ ቢያንስ የኤሌክትሪክ ማብሪያና ማጥፊያ ስለ መግጠም፤ የሰው ልጅ መሸመትን ወዲያ ጥሎ በትንሹ ጎመን ተክሎ መብላት አለበት፤ የበር ቁልፍ መግጠም የሚችል እጁን ያውጣ? ብላ ጠይቃ ምላሽ ታጣና ወደ ተግባር ሥራ ትተማለች።
የምታወጋቸው ማቲዎች እስር፣ ስርዋ እየተንጦለጦሉ፣ እገባችበት እየገቡ፣ ቡራኬ እንደሚቀበል ሰው ከበዋት፣ የምታቅማቸው አሹቅ በሒሳብ የዞረ ናላቸውን እያሰከነ፣ እያልራቋት… እረፍት የሚመስላት ከአንድ ሥራ ወደ ሌላ መሸጋገር ሆነና፣ በእረፍት ሰዓት ከመማሪያ ክፍል ጀርባ በአራት መደብ የተገጠገጠውን አትክልት እያረመች ሳለ፡-
‹‹እትዪ፤ እግዚአብሔር የት ነው ያለው?›› ብሎ ለጠየቃት ምዋቲ፣ በጣዝማ ሽንቁር አፍዋ ፈገግ ብላ፡- ‹‹በልባችን ውስጥ›› ብላለች፤ ጸጉራቸውን እያባበሰች ከአትክልቶቹ በፊትና በኋላ የሕጻናቶቹንም ጠባይ ሳትታክት አርማለች።
መሬታቸውን ሰቅስቀው የሚያርሱ ትጉህ ገበሬዎች፣ እህል ሲያጭዱ ተባብራ አጭዳለች፤ ያጨዱትንም ከምራለች። አራሽ ጎበዛዝት አበክሮዋ መለኪያ አጥቶ ውል ስላሳታቸው የትጋትዋን ዋጋ ላለማርከስ ሲሉ ዝምታን መርጠዋል። ወላ ሥራ ወዳድነት ‹ንብ› አስብሏት፣ ከያኢ ኤሌክትሮኒክስ ጎን ያለው ንብ ባንክ ፎቶግራፍዋን በቀኝ በኩል ሰቅሏል፤ ገድለኛ ነችና፣ የግብጽ ሕጻናትን ስለ ዓባይ እንደ መምከር ያለ ትምህርት ተለገሰ ቀዬው።
‹‹ጅረትና ጅራፍ›› በሚል መጻሕፍዋ፤ ዓባይ ‹ቀለበት ካላሰርን ወደ ግብጽ መፍሰሴን አቆማለሁ› እያለ ሲማጠናት የሚጠቁም ሃቲት ተርካለች። በመጻሕፉ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሳለ ዑራኤል ከጎኑ ደም በዋንጫ ይቀዳና ወደ ሰማይ ይነጠቃል። ከዚያ በማስከተል ወደ ኢትዮጵያ ይረጫል፤ (እንዲህ ባዩ ሃቲቱ ነው ታዲያ)።
የእግዚሔር ነገር ግልጥ አይደለምና ከሰማይ ወደ ምድር የተደፋው ደም መልኩን ለውጦ፣ ውኃ ወይ ሰማያዊ መስሎ በግሽ ዓባይ እንብርት በኩል ሽቅብ ይፍለቀለቃል (አሁንም ያ መዘዘኛ መጻሕፍ ነው፤ ይኼን ያለው)…
…ተፍለቅልቆም አያበቃም፤ ኢትዮጵያ የተባለችዋን፣ ብዙ ብሔር ያላት (ምናልባት ለችግር ጊዜዋ ከኬኒያ ወይም ከሩዋንዳ አንድ ሁለት አራት ብሔሮችን የምትበደር) ሀገር ከጭንቅላት እስከ ጥፍሯ ዘልቆ ሲያረሰርሳት፣ መብራት ሆኖ ሲያፈካት፣ ወላ ውላጅ ሆኖ ሲጦራት ይገኛል። ተዐብ ይመስላል። ታላቁ መጻሕፍ ገነት በምሥራቅ በኩል እንደሚገኝ በገደምዳሜ ይናገራልና፣ ከፈጣሪዋ በኮረጀቺው ገደምዳሜ ልሳን ተመልታ ስታበቃ በዓባይ የረሰረሰች ሀገርዋን በገነት ትወክላለች፤ ባሻ አዳሪነት ይመስላል ግን…
*  *  *
‹በዓባይ የወዛሽ - ሀገሬ፣
የጥድቅ በር - ገነት፣ ኢትዮጵያ ክብሬ፤›
ብሎ ቁራጭ ወረቀት ሰደደላት፤ ኃጎስ መጻሕፍዋን ጨርሶ አንብቦ። ይኼን ሲያደርግ በልበ ሙሉነት ነው ታዲያ፤ ዓባይ ዕድሜ ልኩን ግንድ ይዞ ሲዞር ለምን አንተን እንደረሳህ አልገባኝም እንደማትለው ያምናል። ሂድ መውደድህ አድኖሃል የተባለ ይመስል አጥብቆ ይወዳታል፤ በጺም የተወረረ ቀይ ዳማ ፊቱ ወዝቶ ነበር ይኼንን ሲል የነበረው። እንደ ኮሪያ ወታደር ደረቱ ድረስ የታጠቀውን ሱሪ ኪስና ቀበቶውን እየደባበሰ ይንጠረበባል። ኃጎስ አንባሻ ይወዳል። ጣኦስንም ይወዳል፤ የኃጎሱ ምንጭ ናት ለኃጎስ። ቀልድ ሊመስልህ ይችላል፤ ሀገሬንም እወዳለሁ ይላል አዘወትሮ ሀገር ያወቀ፣ ጠሐይ የሞቀ ፈገግታውን እየፈገገ። ለምን አንባሻ አዘወትሮ እንደሚበላ ሲጠየቅ፣ ማዕዘናቱን ከጣኦስ እያስተያየ ይተነትናል፤ አንዱ ጫፍ ስል አዕምሮዋ፣ ሌላው ምንትስዋ… እያለ ብዙ ዓይነት ማምታቻዎችን እያፈራረቀ፤ ማር ያደለው ምላስ ጣዕም እንደማያጣ ሥሟን ከስሜት ሕዋሳቶቹ ነጥሎ አያውቅም፤ ለምሳሌ ከምላሱና ከእጁ ላይ። ሕይወቱ በቀጠሮ የታጠረች ናት፤ አንዱ ፈረቃ እሷ።
ለሰንደቅ ዓላማ መዝሙር የተከነዳ እጅ ለማቀፍ ይከነዳልና… መተኛት በመንቃት እንደሚከተል በድርጊያዎቹ ሁሉ ቀጠሮ አስይዟታል። ምናልባት የእግዚሔርን ሕገ-ደንብ የሚጥስ፣ ከእራስ በላይ ሌላን መውደድ፤ አማዞን ጫካ መሀል ግዙፍ የአምልኮ ሥፍራ ገንብቶ፣ ግስላ አላምዶ ወይ ከርከሮ አልቦ መስዋዕት ቢያቀርብላት፤ ወይም ስምንት ሺ ኪሎ ሜትር የሚፈስ ዓባይ ውኃዊ መልኩን ለውጦ የጥቁር አዝሙድ ዘይት የፈሰሰበት ብልቃጥ መሳይ ገጽዋን ቢፈስ ወላ ከኤደን ገነት መግቢያ አፍዋ የሚፎን ሳቅዋን እየፎነነ የሱዳኖቹን የማሽላ ማሳ፣ የግብጾቹን ናስር ቢያቋርጥ፤ እና አንድ ሀገር በወር አራት ቀን ያብዳልና ቡርኪናፋሶ በጠረኗ ተነክታ በውል ብትወበራ… ገነቱ ቀርቶበት ጭንጫ ልቡን ያረሰረሰች ዓባዩ ነች…
…በ1514ቱ የአህመድ ግራኝ ወረራ ወቅት በአጼ ልብነድንግል በኩል ተሰልፋ ተዋግታለች። ጣዕመኛ ወጥ ቀቃይም ነበረች። ታዲያ ሽምብራኩሬ የመሸገው የወገንዋ ጦር ሥጋ ጠብሶ እንዳይበላ ጭሱን ተከትሎ የጠላት ጦር እንዳያደበየው በሠጋበት ወቅት፣ ይህቺ ሴት ቄንጠኛ ብልሃት ቀመመች፤ ለመሆኑ ምን አደረገች? እናገራለሁ…
…መጥበሱን ችላ ብለው ጥሬውን የሚበሉበትን ዘዴ እንካችሁ ማለት… እና ከዚያስ?… ልብነድንግል ልቡ እስኪወልቅ ድረስ ተደነቀ፤ በአፉ ሙዳ ሥጋ እያንከላወሰ፣ የልቡ ድንግልና ተገረሰሰ። በደስታ ብዛት በዓይኑ እንባ ከትሮ፣ ጦሩን ሽቅብ ወድሮ የወርቅ ብዕር ሸለማት፤ ወታደሩም ወጥቶ ማደሩን መረቀ፣ ሻኛና ሽንጥ እየሰለቀ፤ ሦስት ቀንና መዓልት ኃይለኛ ጭፈራ ሆነ፤ ወታደሮች ብዙ አቧራ አስነሱ፤ የግራኝ ጦር በሚንገዋለለው አቧራ እየተመራ ደረሰባቸው፤ በመደመም አጮልቆ ሲያይ ጥሬ ያነክታሉ፤ መጠቃቃት ጋብ ብሎ ጦሩ ተቀላቀለ፤ በደምሳሳው አንድ መአድ ቀረቡ፤ አህመድ ግራኝ ጥሬ አበላል አልተካነምና ቀኙን ትቶ በግራ እጁ እየቆረጠ ይጎርሳል፤ አህመድ ነበር ሥሙ፤ በግራው ስለሚቆርጥ ‹‹ግራኝ›› የሚል ተጨመረለት፤ በኋላ ጥሬ ሥጋው ሲያልቅ ውጊያ ላይ እንደነበሩ ትዝ አላቸው፤ ውጊያውን ቀጠሉ።         
መቀመጫውን የዓለም ሳንባ ያደረገው ‹‹ካቶጵያ ጋዜጣ›› ሁኔታውን ለዓለም አበሰረ፤ ፖርቱጋሎች ቀድመው ሰምተው ኖረው ጥሬ ሥጋ አቅምሱን ብለው መልዕክተኛ ሰደዱ፤ ልብነድንግል ልቡ ሩኅሩህ ነውና አልነፈጋቸውም ነበር፤ ምናምን ሺ ያህል ሰው ተግተልትሎ መጣና ተቃመሰ፤ ሀገር ቤት ልኮም አስቀመሰ፤ ለዚህ ውለታና ጥሬውን ሥጋ ጥሎ ለመሄድ መቁረጥ ያቃተው በላተኛ፣ የአህመድ ግራኝን ጦር መዋጋት ተያያዘ፤ ጥሬ ሥጋ ሰንቆ ነበር ታዲያ፤ ለእሷና ለአህመድ ግራኝ ምስጋና ይግባቸው፣ የኢትዮጵያዊያን የአመጋገብ ሥርዐት ላይ አሻራ አኑረዋልና…
…ሐሮኔ ሆቴል ጥሬ ሥጋ ጋብዟት ጥሬ ቧልት ያንበለብላል፤ ስለ መጻሕፍዋ፣ ስለ ሌላ ሌላ… ጎበዝ እንደሆንኩ የማውቀው ስለ ጉብዝናዬ ሲነግሩኝ ነው እንደሚሉ ድኩሞች ስላይደለች፣ ሙገሳውን ታክካ ምጥን ማብራሪያ ትነሰንሳለች፤ እንዲያ ስትሆን ኃጎስ ቢራቢሮ እንደሚያድን ማቲ መዝለል ይቃጣዋል። ወይ ከአፍዋ የዘቢብና ናና ጥቃቅን ኳሶች በሕቡዕ ይዘንቡ ነበርን? ስታወራ ሆዱ ባባ፤ መስከረሙ እንዲጠባ በልቡ የምትፈነዳ አበባ፤  
*  *  *
ኩርማን አንጀት ስጪኝ፤
ከሆድሽ አኑሪኝ፤
ከማግኘት ወደ አለማግኘት ወላ ከማወቅ ወደ አለማወቅ ዘሞ ተፈጥሯልና፣ በጊዜ ሂደት የፈረቃ ኮረጆውን ሳያምታታ እንደሚሞላ አንጣር-በአንጣር መክሯል፤ ለምሳሌ ገና ዱቄት ያልተጨመረበት ግን በጀበና እየፈላ ያለ ውኃ ‹ቡና አለ› እንዳይባል፣ ከእነ ዱቄቱ ፈልቶ ያልሰከነ፣ ደግሞ ‹ቡና የለም› ላለማለት እየፈላ ያለ ዓይነት አወራካቢ ሕልዮት ሲዘበዝብ ይኖራል… ሌጣ ነፍስን ማስጨነቅ ነው ይኼ…     
…የሣር ፍራሹ ላይ ተጋድሞ ሣር እያመነዠከ ያቃጀውን ዘባተሎ ሀሳብ በሙሉ፣ ከወሳሰደው ስሜት ተንሸራቶ ሲመለስ በሣር መልክ ፕላስተር የተለበጠ ማስታወሻው ላይ ይከትባል። እያስታወሰ ሊኖር፤ እየኖረ ሊቀርብ፤ ድከም ያለው ነውና ደክሞ ሊያደክማት ይሆናል፤ ሁናቴው አላምጦ ያልዋጡት ዕውቀት እንደሚያቅር ዓይነት ነገር… ቃራም ነው ግን። እና ካሴት ነው፤ የሚጣምኑ ነገሮችን የሚያመሰኳ። ብቻ ውላቸው ያልለየላቸው ብዙ፣ ብዙ ደባች ነገሮችን እያግተለተለ…
*  *  *
የአተር ክክ በአልጫው ቀቅለው ይጠሯታል። ክኩ ትላልቅ ነው ሁሌም፤ አንዱ ትሪ ስለሚያህል ሌሎቹንም እዚያ ላይ አስቀምጠው መብላት ይችላሉ፤ ዓሉም አክዋክ አብረዋት ሲበሉ እህሉ እንጂ የእሷ ነገር አይዋጥላቸውም፤ አከራይዋ ቢሆኑም ቧልት ዘብዛቢ፣ ጅስም አንገብጋቢ ናቸው…
ምጽዋት ባትለምን፣ ተርፎን ባንደግፋት፣ጎጆዋ ለቻላት፣ ምን ነበር ባንገፋት፤
ብዙ ጊዜ ደጋግመው ትብታብ ክታብ ለደብተራም እንዳልበጀ አዟዙረው ይወርፋሉ። አፋቸው ጤፍ ይቆላልና፣ ወይ ታክቶ አታካች ስለሆኑ መጻሕፍ የማገላበጥ መጨረሻው ዓይን ከማድከም የዘለለ ሌላ ፋይዳ እንደማይኖረው ይገረግራሉ፤ ደጋግመው ነው ደሞ፤ ጥሬ ጨው ያነሰው አልጫ ወጥና ዝብዝብ ስለሚያቀርቡላት አይጥማትም። ቢከፋትም አትናገርም። ላሽቆ ሊያላሽቋት። ነገረ ግብርዋ አዋጭ ስላይደለ ውስልትናን ያሰለጥንዋታል፤ አንዳንዴ ብሶባት፡-
‹‹እግዚሔር ይመስገን›› ስትላቸው እምር ብለው…
‹‹ቡና ያለስኳር ብጠጣ የማይገዛልኝ ለምን ይመስገን? ኧረ ጥድቁ ቀርቶብኝ… ‹ቡና አጣጣኝ› ብለው ‹እ-ሺ› ብሎ ብቸኝነቴን ያስረሳኝ ኖሯል?›› ሲኒውን እንደማሽቀንጠር ይሠራራቸዋል…
…ጸጉሯን አምሥት ወይ ሦስት ቦታ አሽማ በላዩ ላይ ለጋ ቅቤ ያልደነባች ሴት ኪሳራ ትመስላቸዋለች። በዚህ አያበቁም፤ ‹ምጥ ቢጠና ደራሽ ጎረቤት ነውና ወጣ እያልሽ በርበሬ ተቃመሺ› ይላሉ፤ እንዲያ ካላደረገች የቤት ኪራይ እንደማይቀበልዋት ተናግረው ያውቃሉ፤ አንዳንዴ ዛቻ ይመስላል። ይቀበላሉ ግን። ከተቀበሉ በኋላ መልሰው ይሸነግላሉ ደግሞ። ምናልባት የክፍያው ጊዜ መቃረቡን እያስታወሷት ይሆናል…
…ያደቆነ አቃቅርና መንገላጀጃቸው ሳያቀስ አይተውምና፣ ዘባተሎ መጣጥፍዋን ጉድጓድ ከታ፣ ጓዳ ከትማ ሲጠሯት ከእጅዋ ላይ ሊጥ እየሞጨለፈች ‹አቤት› ብላ እንድታስተናግዳቸው ይከጅላሉ። ጮሌ ናቸው፤ እሷ እንጂ እግዚሔር ቡና አያጣጣቸውምና ለጥቅማቸው ያደላ ንድፈ ሀሳብ እየቀመሙ ይወተውትዋታል…   
*  *  *
ማያ አድጋለች፤ የፊትዋ አቀማመጥ እንደ እናቷ ልከኛ ነው፤ ለክብ ያደላ ዘቢብ። እልህ ግልጥ ጠባይዋ ሆነ፤ የፈለጉትን የመንካትም ሆነ የመውሰድ ተጋድሎና መቅበጥበጥ፤ ትጋትዋ ከእናትዋ የተወረሰ እንደሆነ ኃጎስ ደንግጓል። ከትምህርት ቤት በጊዜ ይመልሳታል፤ ዘቢብ አረንጓዴ ፊትዋን እያሻሸ፤ ወይን ቀንጥቦ ለሚስቱ እያጎረሰ ይስማቸዋል ሁለቱንም። በእናቷ ዝምታና በአባቷ ኩርኮራ እየተምነሸነሸች የሕጻን ምግብዋን ታጎርሳለች ለሁለቱም፤ ቢጣፍጥ ባይጣፍጣቸው ግድ አይሰጣትም፤ ከምትጽፍበት ጠረጼዛ ተነስታ እንድታቅፋት ታንባርቃለች እናቷ ላይ፤ ከዚያ አባቷ ያቅፋታል። ወላ ገሸሽ እንዲል ትጮኸለች፤ የእናት ፈረቃ ነውና…
…ኃጎስ ቡና እየቀቀለ ለምትጽፍ ሚስቱ ያቀብላል፤ ፈንታውን ፉት እያለ። ማያ ሀገር ይያዝልኝ ብላ ቡና ታስቀዳለች፤ እናቷ ትክ ብላ ታስተውላለች፤ ኃጎስ ደሞ ሆድዋን ይተከትካል። በብር ላስቲክ የታሰረ ጸጉርዋ እስኪፈታ ትስቃለች፤ እየሸሸች ትመለሳለች።
ብዙ ጊዜ የትምህርት ቤት ገድልዋን እየተረከች፣ የታች ከንፈርዋን በላይኛው ጥርሷ እየነከሰች፤ ወላ በቀኝ እጅዋ ጭብጥ የግራ እጅዋን መዳፍ እየተመተመች…   
…ዓሉም ስኳር ድንች ስለሚሰጥዋት ቤታቸው ታዘወትራለች። እንብርትዋን ስለ ቆረጡ ደሞ የባለውለታነት ነገር ይጎበኛቸዋል። ከኃሳዊ ንግግራቸው ማያ በሌለችበት የጠጡት ቡና ከራስ ምታት ሊያስጥላቸው ይሰንፋል፤ ምናልባት የእናቷ ተቃራኒ ስለ ሆነች በወሬ ስለምትጠምዳቸው ይሆናል የወደዷት፤ ሰው በተሰበሰበበት፡-
ለምንድነው እጅሽ እንደ ላስቲክ የተሰበሰበው?
ስኳር ድንችሽ ይጣፍጣል
እናቴ እኮ ታነባለች
ብላ ታውቃለች ሳትፈራ
የልጅ ማሽንክ
የእናቷ ተጻራሪ
ተናግሮ አናጋሪ
ብለዋት ያውቃሉ፤ አንዳንዴ ሳቅ ብለው ወይ ቆጣ ብለው…
…የፈረቃ ሕልዮት አንቡጦ ያበባት ምዋቲ፤ ያለፈ በረኸማ ውሎና አዳሩን በጽጌያት የተካች እርብትብት፤ በፈረቃ የደለደለውን እንቶፈንቶ መልሷል ኃጎስ፤ እሳት በውኃ እንዲጠፋ ሆኖአልና… ዝብዝብ ኑረቱን በእየፉርጎው እየደለደለ ይከርማል፤ በሕይወቱ ያካፋ ጣመን እርካታ እንዲያዘንብ ዕሙን ሆነና ተስፋ መቁረጡን ተስፋ አደረገ፤ የልቡ ላይ አደይ የጽገሬዳ አበባ ፈንድታ መስከረሙ ጠባ።



Read 584 times