ክፉ ፍርሃት
ጨለማ እኮ…!
በድቅድቁ - ምሽቱ ላይ ጥቁር
ሌሊት መቀለሙ
ጽልመቱ ውስጥ - ተስፋ አርግዞ
- ሊነጋ ነው መጨለሙ፡፡
ብርሃን ግን…
ካድማሱ ጥግ ‘ብቅ‘ ብሎ - ፀሐይ
ክንፉን ሚዘረጋው፣
የመከነ ተስፋ ይዞ - ሊጨልም
ነው የሚነጋው፡፡
***
የሚሊኒየሙ አናፂ
አብዮት ፈንድቶ - ጥርስ ቀን ወጣለት፣
የተነቃነቀው - ድጋፍ ታሰረለት፡፡
ሸራፋው ሊጠገን - መጠኑ ተለካ፣
ያረጀው ተነቅሎ - በአዲሱ ተተካ፡፡
የተቦረቦረው - ተጠቅጥቆ ሞላ፣
ዱልዱሙ ክራንቻ - ተሞረደ ሰላ፡፡
አዬ የኛ ነገር…
ማኘኪያችን ሾለ - ገንዘብ ጠላት ገዛ፣
የምንበላው የለን - ጥርስ አዳሹ በዛ፡፡
(ሲሳይ ዘ-ለገሃሬ)
***
የውዴ መዓዛ
አልሄድም ፍለጋ አሪቲና አደስ
ከርቤስ ምን ሊሆነኝ አልሻም ናርዶስ
ዕጣኑ፣ ብርጉዱ ሉባንጃው ወዲያልኝ
ዝባድና ሽቱ በጭራሽ ይቅሩብኝ
አልበልጥብህ አሉኝ ከውዴ መዓዛ
ልቤን ከሰወረው ከጠረንሽ ለዛ፡፡
(አበራ ኃ/ማርያም)
Published in
የግጥም ጥግ