Saturday, 22 July 2023 12:38

“ከእትብት ጋር የወጣ አመል፣ ከከፈን ጋር ይቀበራል”

Written by 
Rate this item
(6 votes)

   የአንድ ቅኔ ት/ቤት ተማሪዎች ቅኔ የሚዘርፉበት ዕለት ነው፡፡ ከየደብሩ፣ ከየቅኔ ት/ቤቱ ሁሉ አንቱ የተባሉ ሊቆች ተጠርተው መጥተዋል፡፡ ተማሪዎች ምን ያህል እንደተማሩና እንደረቀቁ ለማዳመጥና ለመመዘን፣ እግረ-መንገዳቸውንም የእነሱ ዘመነኛ የሆኑት የቅኔ መምህር ምን ያህል እንዳስተማሩ በማየት ከራሳቸው ጋር ሊያነፃፅሩ ነው፡፡ በተማሪዎቹ መካከል ፉክክር እንዳለ ሁሉ በመምህራኑም መካከል የእኔ እሻል እኔ እሻል ውድድር አለ፡፡ በጥንቱ የቅኔ ትምህርት ይትባህል አለቃ እገሌ ዘንድ የተማረ፣ መምህር እገሌ ዘንድ ቅኔ የዘረፈ መባል ብዙ ስምና ክብር አለው፡፡ (በዘመናችን ሲታሰብ ዶክተር እከሌ የተባለ፣ ፕሮፌሰር ጋር ነው ያጠናሁት እንደማለት ነው፡፡ ወይም ዛሬ “የዚህ School of thought “ ተከታይ ነኝ እንደሚባለው፣ “የዚህ ደብር ተከታይ ነኝ” እንደማለትም ይሆናል)
ከተማሪዎቹ መካከል አንድ ኃይለኛ ተማሪ አለ፡፡ መምህሩ ሳይቀሩ ይፈሩታል፡፡ ታዲያ የዚያን ዕለት መምህሩ በበኩላቸው፣ ችሎታቸውን ለማሳየት ያህል ቅኔውን ሲዘርፉት፣ አንድ ላላ ተደርጎ ሳይረገጥ መነበብ ያለበት “ታምሪሃ” (የተዓምር ድርጊት) የሚል ቃል፣ የኔታ እርግጥ አድርገው ‘ታምሪሃ!’ ብለው ያነባሉ፡፡ ይሄኔ ያ ጎበዝ ተማሪ “የኔታ ልመልስዎት” ይላቸዋል፡፡ የኔታ አፍረውም ተናደውም ቢሆን፣ ምሬታቸውን ዋጥ አድርገው ሲያበቁ፣ “እሺ የእኔ ልጅ፤ መልሰኝ” አሉ፡፡ “‘ታምሪሃ’ አይጠብቅም ያላሉት” ይላቸዋል፡፡ የኔታም አላልተው በድጋሚ ይወርዱታል፡፡
በነዚያ ሁሉ ታዋቂ መምህራን ፊት ተማሪያቸው ስህተት ስላገኘባቸው በጣም ተናደዋል፡፡ ስነሥርዓቱ ሁሉ አለቀና እንግዶቹ ሁሉ ተሸኙ፡፡
የየኔታ ቤት አፋፍ ላይ ነው፡፡ የጎበዙ ተማሪ ቤት ታች ሜዳው ላይ ነው፡፡ ለተማሪው የየኔታ ቤት ቁልጭ ብሎ ካፋፍ ይታየዋል፡፡ የኔታ ጠዋት ማለዳ ተነስተው እደጃቸው ካለው የወይራ ዛፍ ቅርንጫፍ ቆርጠው አርጩሜ መልምለው፣ በጋቢያቸው ሸፍነው ይዘው ቁልቁል ሲወርዱ ተሜ ያስተውላቸዋል፡፡
ት/ቤት እንደተለመደው የኔታ ተማሪዎቹ ቅኔ እንዲዘርፉ ሲመሩ፤ ሳያውቁ ያሉት አስመስለው የትላንትናውን “ታምሪሃ” የሚል ስህተት በመድገም ረግጠው አነበነቡት፡፡ ተሜ ግን እንደ ትላንቱ “ልመልስዎት” ሳይላቸው ጭጭ አለ፡፡ የኔታ ትንሽ እንደመናደድ ብለው አሁንም ያችን “ታምሪሃ” ረገጥ አድርገው ተናገሯት፡፡ ተሜ አሁንም ጭጭ! የኔታ በጣም ተናደዱና ጮክ ብለውና በጣም ረግጠው “ኧረ ታምሪሃ”! አሉ፡፡ ተሜ አቀርቅሮ እረጭ፡፡ የኔታ ትዕግሥታቸውን ጨርሰው፤
“አንተ፤ አትመልሰኝም እንዴ?” ሲሉ ጠየቁት በኃይለ-ቃል፡፡
ተማሪው ሲመልስ፤
“አይ የኔታ፤ ይቺ እንኳ ውስጠ-ወይራ ናት!” አላቸው፡፡
ውስጠ-ወይራ ታሪካዊ አመጣጧ ይሄ ነው፡፡
***
በረዥም ጊዜ ታሪካችን ውስጥ በሀገራችን የሚካሄድ ብዙ ውስጠ-ወይራ ነገር አለ፡፡ ስህተት የሚሰራ ሞልቷል፡፡ ስህተት እያየ ውስጠ-ወይራ ናት ብሎ ጭጭ የሚልም አንድ አገር ነው፡፡ የትላንቱን ቂም ለመወጣት እንደየኔታ አውቀው ተሳስተው “አትመልሰኝም ወይ?” የሚሉም አያሌ ናቸው፡፡ በስህተት ከማፈርና መናደድ፤ ብሎም ለአርጩሜ ከመዘጋጀት ይልቅ፣ ስህተትን ለማረም ዝግጁ መሆን ቢችሉ፣ አገራችን ከስንት ህመም በዳነች ነበር፡፡ ይህ ድክመት በሁሉም የህይወት መስክ ሲንፀባረቅ ይታያል፡፡ በተለይ ግን በፖለቲካው መድረክ ላይ ተሰማርተው የተንቀሳቀሱም ሆኑ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ፓርቲዎች ዕድሜያቸው ለአካለ- ትግል ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ የሚታይባቸው መሰረታዊ የድክመት ጠባይ አለ፡- ፖለቲካዊ ሸፍጥ፣ ስቶ ማሳሳት (Disinformation)፣ አድርባይነት፣ አስመሳይነት (Hypocracy)፣ ባዶ ሜዳ ዛቻ፣ ዕብጠት፣ ፖለቲካዊ አክራሪነት፣ መቻቻልን ከሽንፈት መቁጠር፣ እኔ የሌለሁበት ማሕበር ጥንቅር ብሎ ይቅር ማለት፣ ማጋለጥ፣ ማጋፈጥ፣ ለጠላት አሳብቆ ማስመታት፣ ታክቲካል ግንኙነትንና ጡት-መጣባትን አለመለየት፣ ህጋዊ ትግል፣ ዲፕሎማሲንና ህቡዕ ትግልን (Clandestine struggle) ወይ አጥርቶ አለማወቅ፣ አሊያም አንዱን ከአንዱ ጋር ማምታታት፣ እርስ በርስ  እየተሻኮቱ አገርንና ህዝብን እርግፍ አድርጎ መርሳት፣ መሸመቅ፣ ያታግላል በሚል ምክንያት ብቻ አዲስ መፈክር ማውጣት ወዘተ…
እንግዲህ ከነዚህ በአንዱ፣ በጥቂቱ ወይም በሁሉም የተነሳ እስካሁን የሚታየው የትግል ስልት ሁሉ ውስጠ-ወይራ አለበት፡፡ “ጠጅ የለመደች ገንቦ፣ ያለ ጠላ አታድርም” እንዲሉ መልኩ ይለዋወጥ እንጂ በውስጠ-ወይራ የማያምን ፓርቲ፣ ማህበር፣ ድርጅት፣ መሪ፣ ካድሬ፣ ታጋይ የለም ለማለት ያስደፍራል፡፡ እርግጥ መጠቅለያው ይለያያል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን በማህበራዊ ግንኙነታችን ውስጥ “ውስጠ-ወይራ” እንደማይጠፋ ሁሉ በየፓርቲው ፕሮግራም፣ በየቡድኑ ታክቲክና ስትራቴጂ፣ በየስምምነት ፊርማው፣ በየጋራ ግንባር ውይይት ውስጥ ሁሉ በገዛ ወገን ላይ ሳይቀር “ውስጠ-ወይራ” አለች፡፡
ብዙ ህይወት የጠፋባቸው፣ ብዙ ቁርሾ የተፈራባቸው፣ ለዘመናት የማይሽሩ የሚባሉ ቁስሎች የተፈጠሩባቸው፤ አመታትን አይተናል፡፡ በነዚህ ውስጥ “ከሰራነው ስህተት እራሳችንን ለማረም የቻልን ስንቶች ነን?” ብሎ የጠየቀ ሰው የሚያገኘው መልስ ግን  እጅግ መንማና ቁጥር ነው፡፡ ወደ አለፉት ስህተቶቻችን መለስ ብለን እንድናይ የሚያግዘን አንድ ፍቱን መሳሪያ አለ፡፡ ታሪክን በፅሁፍ ማስቀመጥ፡፡ ትንሽም ይሁን ትልቅ ታሪክ ፅፎ ማስቀመጥ፡፡ ሁሉ በሚዋሃድበት ጊዜ የሚጣረሰው ተዋዶ፣ የተሳሳተው ታርሞ አንድ ቀን ሙሉ ታሪካችን አደባባይ ይወጣል፡፡
ቶማስ ኤዲሰን “ከሰራኋቸው ኤክስፔሪመንቶች ሁሉ ውጤት አግኝቻለሁ! ሁሉም ስህተት ናቸው፡፡ ይህ ግን ትልቅ ድል ነው፡፡ እስካሁን ድረስ እንኳን 138 እኔ ባሰብኩት መንገድ የማይሰሩ መንገዶች መኖራቸውን ተምሬአለሁ፡፡” ይለናል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ድክመቶች እስካሉ ድረስ ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን እጣ-ፈንታ ከወዲሁ መናገር የሚያዳግት አይሆንም፡፡ ጊዜያዊ  አሸናፊ ብቅ ይላል፡፡ ይኸው አሸናፊ አንድ ሰሞን ያለፈውን ሲረግም፣ አንድ ሰሞን መጪውን እቅዱን ሲያስተዋውቅ ይከርማል፡፡ ከዚያ “ብቻውን የሚሮጥ የሚቀድመው የለ፣ ብቻውን የሚሟገት የሚረታው የለ” እንደተባለው ተረት ይሆናል ነገሩ ሁሉ፡፡ ከዚያ ስለእኔ ተሰብሰቡ፣ “በእኔ እመኑ” “እኔ ቀናዒ” (እኔ ቀናተኛ አምላክ ነኝ) እያለ ሰውን ሲያፈጋ ይቆያል፡፡ ሰነባብቶ የአሸናፊነት ሰንጠረዥ ላይ ያለው ጠቋሚ-መስመር እንደገና ማሽቆልቆል ይጀምራል፡፡ ሌላው ባለ ጊዜ ደግሞ ለሌላ ጊዜያዊ አሸናፊነት፣ ያንኑ ማንነቱን፣ ያንኑ ውስጠ-ወይራውን እንደያዘ መድረኩ ላይ ብቅ ይላል፡፡ ቀለበታዊ ሂደቱ ይቀጥላል፡፡ “እራሱን የማይገዛ፣ አገር አይገዛ” የሚባለው ተረት የዋዛ አይደለም፡፡ እራስን መመርመር፣ ማረም፣ ስህተትን መቀበል፣ መሳሳትን በሰው ፊት ማመን፣ በጋቢው የተሸሸገውን ወይራ ለመስበርም ሆነ፣ ወደፊትም ከነጭራሹ ከዛፉ ተቆርጦ እንዳይመለመል ለማድረግ፣ ወሳኙ እርምጃ ነው፡፡ አለበለዚያ “ከእትብት ጋር የወጣ አመል፤ ከከፈን ጋር ይቀበራል” ማለት ብቻ ይሆናል ቋንቋችን፡፡

Read 1846 times