Saturday, 22 July 2023 12:50

ክፋትና ጥፋት ‘ኖርማላይዝ’ ሲደረጉ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

 “ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... የጉድጓድ ነገር ካነሳን አይቀር በመንገዶች ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉ ነገር ሳንጠብቃቸው ወይም ሳንጠረጥራቸው ድንቅር የሚሉ ጉድጓዶች በዙብንሳ፡፡ የባህሪይ ጉድጓዶች፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድጓዶች፣ የማን አህሎኝነት ጉድጓዶች፣
የ“ዕድሜ ለታላቅ ወንድሜ!” አይነት ጉድጓዶች፣ የ“ዘመድ ከዘመዱ” አይነት ጉድጓዶች... ምን አለፋችሁ ጉድጓድ በጉድጓድ ሆነናል፡፡--”
              

          እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ...እኛ ሌሊት እንቅልፋችንን ስንለጥጥ ወይ ለመለጠጥ ስንሞከር ዶማ ይዞ ከተማ የሚዞር አለ እንዴ! አሀ... ጉድጓድ ሲበዛብን ምን እንበል! ለጥ ባለው ‘አስፋልት’ ወይም ንጣፍ መንገድ፣ በየአምስት ደቂቃው እንቅፋት በሚመታን ምድር ጉድጓድ ተጨምሮ በምን አንጀት ይቻል! ደግሞ ክዳን ኖሯቸው በሆነ ክፍል ከተከፈቱ በኋላ እንደዛው የሚተዉ ጉድጓዶች ነገር ግርም አይላችሁም! ፈረንጅ ቢሆን ኖሮ “አይ አም ኤ ታክስፔየር!” ብሎ ቀውጢ ይፈጥር ነበር፡፡ እሱን ነገር አንዳንድ ዜጎች ሞካከሩትና ጭርሱን ሲሳቅባቸው ሁላችንም ጭጭ አልን መሰለኝ፡፡ እናላችሁ...የሆኑ ጉድጓዶች ይቆፈራሉ፣ አፈሩ ወጥቶ ይከመራል፣ ዝናብ ሆዬ ዘንቦ የማያውቀውን ያህል ያወርደዋል፣ ...እና ማን መከራውን ቢያይ ጥሩ ነው... የፈረደበት እግረኛ! ግን ደግሞ በጉድጓዶችና በ‘አስፋልት’ ላይ እንቅፋቶች መነጫነጭ (“ዝም ብላችሁ አትነጫነጩ!” የሚሉን ወይ ሊሉን የሚችሉ ስላሉ ነው!) አሁን፣ አሁን አቆምን ወይ ቀነስን መሰለኝ!
‘ኖርማላይዝ’ አደረግነዋ!
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... የጉድጓድ ነገር ካነሳን አይቀር በመንገዶች ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉ ነገር ሳንጠብቃቸው ወይም ሳንጠረጥራቸው ድንቅር የሚሉ ጉድጓዶች በዙብንሳ፡፡ የባህሪይ ጉድጓዶች፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድጓዶች፣ የማን አህሎኝነት ጉድጓዶች፣ የ“ዕድሜ ለታላቅ ወንድሜ!” አይነት ጉድጓዶች፣ የ“ዘመድ ከዘመዱ” አይነት ጉድጓዶች... ምን አለፋችሁ ጉድጓድ በጉድጓድ ሆነናል፡፡ ግርም የሚል ነው እኮ!
ሌላ ደግሞ በንግግሮችም፣ በመግለጫና በመሳሰሉ ጽሁፎችም ሙልጭ እያደረጉ ‘ያኛውን ወገን’ ወይም ያኛው ወገን ነው ተብሎ የሚታሰበውን እንትን የነካው እንትን ማስመሰል ‘ኮምፐልሰሪ ቦተሊካ’ ምናምን ነገር መስሎላችኋል፡፡ እኛም መደነቁንና “ጉድ! ጉድ!” ማለቱን እየተውነው ነው፡፡  “ስማ ትናንት ማታ ያ እንትና የሚሉት ሰውዬ በቴሌቪዥን ሙልጭ ያደረገንን ሰማኸው?” መባባል መተዋችንን ለማሳወቅ ያህል ነው፡፡ አሀ..ሲበዛብንስ!
ተለቅ፣ ተለቅ ካሉ መድረኮች እንኳን “ወዮልህ/ወዮልሽ!” “አንተን/አንቺን አያድርገኝ!” አይነት ቃና ያላቸው ነገሮችንም ለመድናቸው መሰለኝ፡፡ እንበልና የሆነች ሴትዮ እስኪበቃት ቴረር ምናም የሚመስል ነገር ከለቀቀችባችሁ ከሦስትና አራት ሳምንት በኋላ እኮ ነው... “አንተ ያቺ ሴትዮ እስከዶቃ ማሰሪያ ነገረችን የሚባለው ማን አይዞሽ ብሏት ነው!” የምንባባለው! ያውም ትዝ ካለን፡፡
እግረ መንገዴን... “ሶሪ ቱ ሴይ ኢት!” እንዲል ፈረንጅ እኛም እንዋስና ሶሪ ቱ ሴይ ኢት ግን ለምንድነው አብዛኞቹ ቦተሊከኞቻችንና ‘ሶ-ኮልድ’ አክቲቪስቶቻችን (ፈረንጂኛውን አዘነብኩት አይደል!) ለስድብና ለዘለፋ የተፈጠሩ የሚመስሉት! የቦለቲከኞች፣ የእክቲቪስቶች ምናምን ዲ.ኤን.ኤ. ይታይልንማ። አሀ... ለሳይንስ አዲስ ግኝት እናበረክት ይሆናል!  
ነገሮችን ሊያሰጋና ሊያሳሰብ በሚችልና በሚገባውም ሁኔታ ‘ኖርማላይዝ’ እየተደረጉ ነው!
በየቀኑ ብቻ ሳይሆን አንዳንዴም በየሰዓቱ ከሀገራችን የተለያዩ ክፍሎች የምንሰማቸው ዜናዎች እየከበዱ የሄዱ ነው የመሰለው፡፡ ቀደም ሲል በዚህ ደረጃ፣ በዚህ ጥልቀትና ስፋት ሀገሪቱ መሰል መከራዎች ይገጥሟታል እንል የነበርን ካለን ምናልባትም ‘ነቢይ’ መሆን ነበረብን፣ እስካሁን ካልሆንን ማለት ነው፡፡ (“ዛትስ ሁዌር ዘ መኒ ኢዝ!” እንዲል ፈረንጅ፡፡) በእርግጥ የሰማነውንና የተነገረንን ሁሉ እናምናለን ማለት አይደለም፡፡ ሆኖም አመንንም አላመንንም እንደነዚሀ አይነት የሚረብሹና እንቅልፍን ብቻ ሳይሆን ጤናንም የሚያዛቡ ነገሮች ደጋግመን ከመስማታችን የተነሳ ከማሰብ፣ ከመጨነቅና ስለ መፍትሄዎች ከመምከር ይልቅ “ምን ታደርገዋለህ!” ወደመባባል ስንገባ ‘ኖርማላይዝ’ እያደረግነው ነው ማለት ነው፡፡ ለሀገር ደግሞ ከዚህ የባሰ አደጋ አይመጣበትም!
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሰው የለ... “የሚሸሹበት አምባ ሲሸሽ ተገኘ፣” የምትል አባባል አለች፡፡ አንዳንድ ጊዜ እኮ “ከዚህስ የትም፣ የትም ቦታ በሄድኩ!” አይነት ስሜት ያድርባችሁ የለ! (በአሁኑ ሰዓት እንደዚህ አይነት ስሜት ያላቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብ  ወላ ጨለምተኝነት፣ ወላ ‘ፔሲሚዝም’ የሚባሉት ነገሮች ይገልጹት፣ አይገልጹት እንደሁ ባለሙያዎች መርምረው ይንገሩንማ! እንደዛ የምናስብ ቁጥራችን እየጨመረ ስለሆነ ነው፡፡) እናላችሁ... በእግር ወደ ሞንጎሊያና ወደ ባራባዶስ ምናምን አናስነካው ነገር እነ ክላውስ ሽዋብ ዓይን እንዳንገባ እንሰጋለን፣ (ቂ...ቂ...ቂ...) አሀ... የምንሸሽባቸው አምባዎች እንዳንሸሽባቸው አይነት እየሆኑብን ያሉት የእነሱ እጅ ቢኖርበት ሊሆን ይችላላ! እኔ የምለው...ጋሽ ሽዋብ፣ ጋሽ ሶሮስ፣ ጋሽ ጌትስ... በአንድ ትጠቀላላችሁ (“ትጨፈለቃላችሁ” ላለማለት ነው፣) ያላችሁን በ2030 አይደለም እንዴ! ታዲያ አሁን፣ አሁን ምንድነው እንዲህ ያጣደፋችሁ! አንድ የዓለም መንግሥት፣ አንድ የዓለም ኤኮኖሚ ስርአት፣ አንድ የዓለም ሃይማኖት ትርክቶች ከመደጋገማቸው የተነሳ ነገሬ ሳንለው፣ “ይሄ ነገር እንዴት ነው?” ጆሯችን እየለመዳቸው ይሆን እንዴ!
ነገሮች በፍጥነት ‘ኖርማላይዝ’ እየተደረጉ ነዋ!
ስሙኝማ... ፀሀይ ‘አማሪካኖችን’ እንዴት ብትቆጣቸው ነው ሰሞኑን የቃጠሎ መአቱን እያወረደችባቸው ያለው! ለምሳሌ ፊኒክስ በምትባለው ግዛት ለሀያ ምናምን ቀናት የሙቀት መጠኑ 110 እና ከ110 ዲግሪ ፋረንሀይት በላይ ሆኖ ነው የሰነበተው፣ 43 ዲግሪ ሴልሲየስ ማለት ነው፡፡ አውሮፓም እንደ አሜሪካ በሙቀት ማዕበል እየታመሰች ነው፡፡ በሌላ በኩል ህንድና ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ከባድ ጎርፍ ህይወት እያጠፋና ንብረትም እያወደመ ነው፡፡ ግን መሰል ክስተቶች ነገና ከነገ ወዲያ በዚችኛዋ ዓለማችን ጥግ ሊከሰቱ የማይችሉበት ምክንያት የለም በሚል የሞቀንም፣ የቀዘቀዘንም አይመስልም፡፡
በሩስያና በዩክሬይን ጦርነት ደግሞ ከዕለት ወደ ዕለት ነገሩ እየባሰ፣ የሚያሰጋው አሁን እያካሄዱ ያሉት ውጊያ ነገና ከነገ ወዲያ ሊፈጠር የሚችለው እየሆነ ነው፡፡ ወደ ውጊያው ሜዳ በተለይ ሩስያን በተመለከተ “ናው ኦር ኔቨር!” የሚል የፑቲንን አገር አፈር ድሜ የማስጋጥ እንቅስቃሴ ላይ ያሉ ከሚመስሉት ከምዕራባውያኑ ለዩክሬይን እየተላኩ ያሉት ዘመናዊ የጦር መሳሪዎች አውዳሚነታቸው እጅግ የከፋ መሆናቸው፣ ሩስያ በበኩሏ ሸሸግ አድርጋ ያቆየቻቸውን መሳሪያዎች ብቅ፣ ብቅ እያደረገች ነው መባሉ ቀደም ሲል ትርክት ማሳመሪያ ነገር ብቻ የነበረው ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ይበልጡኑ እያቀረበው ነው ይባላል። እናላችሁ... እነኚህ ሁሉ ነገሮች ይህች ዓለም ወደምን አይነት ጥፋት እየሄደች እንደሆነ ማሳያ ናቸው በሚባልበት ጊዜ ነገሮች ‘ኖርማላይዝ!’ እየተደረጉ መሆናቸው ሊያሰጋ ይገባል፡፡
የጦርነት ዝግጅት ነገር ካነሳን በዛኛው የዓለም ጫፍ ደግሞ በኮሪያ ልሳነምድር ጦርነት የማይቀር ከሆነና ድንገትም ከሰሜን ኮሪያ የኑክሌየር ጦርነት ፍልሚያ በሚል ሰሞኑን አማሪካኖቹና ደቡብ ኮሪያዎች የጦርነት እቅድ እያወጡ ሰንብተዋል ነው የሚባለው፡፡ ከእኛ እይታ ውጪ ከመጋረጃ ጀርባ ነገሮች አስጊ ደረጃ ባይደርሱ ኖሮ እንዲህ በአደባባይ እስኪነገር ድረስ ስለኑክሌር ጦርነት እቅድ ባያወሩም ነበር። በሌላ በኩል ከሌሎች ዓለማት ስለሚመጡ ያልታወቁ በራሪ አካላትና የሌላ ዓለም ፍጡራን አሁን፣ አሁን ዝም ብሎ ወሬ ከመሆን አልፎ ለበርካታ አስርት ዓመታት ተደብቀው የቆዩ ምስጢሮች እየወጡ ነው! ግን ደግሞ ብዙ ነገሮች ‘ኖርማላይዝ’ እየተደረጉ ያለበት ዓለም ስለሆነ ብዙዎቻችን “ኬሬዳሽ!” አይነት ነገር ውስጥ ነን፡፡ የክፋትና የመጠፋፋት ወሬዎች፣ እኩይና አውዳሚ አስተሳሰቦች፣ ሰይጣናዊ የሆኑ ትርከቶችና ተግባራት ‘ኖርማላይዝ’ የተደረጉበት አስከፊ ዘመን፡፡
ስሙኝማ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...አሁን ደግሞ የትዊተሩና የቴስላ ጌታ ኤለን መስክ ሴት ሮቦቶችን እያመረተላችሁ ነው። (ግዴላችሁም... የጉድ ዘመን ውስጥ እንዳለን አትጠራጠሩ፡፡) በሁለትና በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ለገበያ ይቀርባሉ ነው የሚባለው፡፡ እናላችሁ ሮቦቷ እንትናዬ ቻርጅ እየተደረገች ነው የምትሠራው አሉ፡፡ በተከታታይ ለሦስት ቀናት ያህል ቻርጅ ትደረግና አንድ ወር ሙሉ ሁሉም ሙሉ፣ ሁሉም ዝግጁ ይሆናል ነው የሚባለው። በተለይ በዚህ ዘመን ‘ሂ’ እና ‘ሺ’ን በተመለከተ (ቂ...ቂ...ቂ...) አዲስ ነገር በመጣ ቁጥር “ይህ ነገርማ እንዴት ያመልጠናል! ምርኩዝ ይዘንም ቢሆን...” ምናምን የምትሉ የ‘የስተርዴይ’ አራዶች ተረጋጋጉማ... የነርቭና የአጥንት ህክምና ውድ ነው፡፡ (ቂ...ቂ...ቂ...)
አንተ የጓሮ ፍየል ብትስል ብታነጥስ
ዛሬ ባል ነውና ቅጠልም አልበጥስ
በሚል “እሰይ ብል ባከረባብት” ሌላ የሮቦት እንትናዬ ሌላ!
እናላችሁ...ክፉ፣ ክፉ ነገሮች ሁሉ ‘ኖርማላይዝ’ እየተደረጉ ነገሬ ሳንለው ከሀዲዱ እያስወጡን ሊሆን ይችላልና ልቡናው ከተገኘ ነቃ ማለት ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1332 times