Saturday, 22 July 2023 20:38

“የኔ መንገድ“ - በጊዮን ግሮቭ ጋርደን በድምቀት ተመረቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

•  የኮሎኔሉ ታሪክ - ከመጽሐፍ አዟሪነት እስከ  የጦር አዛዥነት

ከአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን አንስቶ በአራት መንግሥታት ውስጥ ያለፉትና ከመጻህፍት አዟሪነት እስከ ከፍተኛ የጦር አዛዥነት የደረሱት ኮሎኔል ፈቃደ ገብረየሱስ የጻፉት “የኔ መንገድ“ የተሰኘ ግለ-ታሪክ (ኦቶባዮግራፊ)፣ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በግዮን ሆቴል ግሮቭ ጋርደን ተመርቋል፡፡


በ653 ገጾች የተቀነበበው መጽሐፉ የተመረቀው፣ የኮሎኔሉ የቀድሞ አለቆችና የደርግ ዘመን ከፍተኛ የጦር አዛዦች፣ ቤተሰቦችና ወዳጆች እንዲሁም የሚዲያ ባለሙያዎች በታደሙበት ደማቅ  ሥነስርዓት ነው፡፡


የመጽሐፍ አዟሪነት ዘመናቸውን በምረቃው ሥነሥርዓት ላይ ያወሱት ኮሎኔል ፈቃደ፤ “እኔ መጽሐፍ ስነግድ እነሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስን፣ አቤ ጉበኛን፣ ክቡር ደራሲ ሚካኤል ከበደን በአካል አውቃቸው ነበር፡፡” ብለዋል፡፡

ከአጼ ኃይለሥላሴ ጋር ድንገት መንገድ ላይ ተገናኝተውም መጽሐፍ እንደሸጡላቸው ደራሲው በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ አስታውሰዋል፡፡

“የኔ መንገድ“ የተሰኘውን የኮሎኔል ፈቃደ ገብረየስ ግለታሪክ መጽሐፍ፣ የአርትኦት ሥራ ያከናወኑት ታዋቂው ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላና ጸሃፊና የሥነጽሁፍ ባለሙያ የሆነው ባዩልኝ አያሌው ሲሆኑ፤ ሁለቱም ስለመጽሐፉ አጫጭር ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል - በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ፡፡

የኮሎኔል ፈቃደ የቀድሞ አለቃ የነበሩትና የደርግ ዘመን ከፍተኛ የጦር አዛዥ ብርጋዴር ጀነራል ካሣዬ ጨመዳና ሌሎችም በመድረኩ ላይ ስለ ባለታሪኩ የሚያውቁትን ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡


ኮሎኔል ፈቃደ ከዚህ ቀደም አራት ያህል መጻሕፍት ለንባብ አብቅተዋል፡፡  አምስተኛውንና አዲሱን  “የኔ መንገድ“ የተሰኘ ግለታሪክ ለምንና እንዴት እንደጻፉት በመጽሐፉ መግቢያው ላይ እንዲህ ያስረዳሉ፡-

“አንዳንድ ወዳጆቼ “ለምን የህይወት ታሪክህን አትጽፍም?“ ሲሉኝ፣ “እኔ ምን ታሪክ አለኝ?“ እያልኩ ነገሩን ጉዳዬም ሳልለው ቆየሁ፡፡ አንድ ቀን ጠዋት አንደኛው ልጄ ብስራት ፈቃደ በጨዋታ መሃል ድንገት “ጋሼ የህይወት ታሪክህን ግን ለምን አትጽፍም? በሕይወት እያሉ እኮ ታሪካቸውን የሚጽፉ ጥቂቶችና የታደሉ ናቸው፡፡ ሌሎቹ እኮ ልጆቻቸው ናቸው የሚጽፉላቸው“ አለኝ፡፡ እኔም “ምን ታሪክ አለኝና እጽፋለሁ? ልጻፍ ብልስ አስር ገጽስ መጻፍ እችላለሁ እንዴ?“ ብዬ መለስኩለት፡፡ “ግለ ታሪክህን ስትጽፍ እኮ ያንተን ታሪክ ብቻ አይደለም የምትጽፈው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች ያገኘሃቸውን ሰዎችንና ድርጊቶች እንዲሁም ገጠመኞች ጭምር እንጂ፡፡  አንተ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ስታጫውተን ልብ እንዳልኩት ብዙ ህይወት አሳልፈሃል፡፡ በዚህ ሂደትም ከብዙ ሰዎች ጋር ተገናኝተሃል፡፡ የሚገራርሙ ገጠመኞችም አሉህ፡፡ ብዙ ሰውም የሚጽፈው  እኮ ይህንኑ ነው፡፡ ለማሳተም እንኳን ብትቸገር አዘጋጅቶ ማስቀመጡ አንድ ነገር ነው፡፡“ ብሎ የምመልሰውን ለመስማት በአንክሮ ተመለከተኝ፡፡ የምመልሰው ባጣ “እስቲ ላስብበት“ ብዬው ጨዋታችንን ቋጨን፡፡--” በዚህ መንገድ ነው በዛሬው ዕለት ለምርቃት የበቃው መጽሐፍ የተወለደው፡፡

የራሳቸውን ታሪክና ከህይወታቸው ጋር የተገናኙ የሌሎች ሰዎችን እንዲሁም ገጠመኞችን ታሪኮች ያካተቱበትን ይህን መጽሐፍ ለምን “የኔ መንገድ“ እንዳሉት ሲገልጹም፤

 “--ሁሉም ሰው የራሱ የተለየ ታሪክ አለው፡፡ እያንዳንዱ ሰው የተጓዘበት የህይወት ልምዱ የአንዱ ከሌላው ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ልክ እንደ እጃችን አሻራ ያንዱ ከሌላው ጋር በምንም አይመሳሰልም፡፡ አሁን ላይ የዕድሜዬ ቆጣሪው 69ኛው ዓመት ላይ ያሳያል፡፡ በዚህ ረጅም ዓመታት እኔ የተጓዝኩበትና የመጣሁበት መንገድ፣ የኖርኩበትና ያለፍኩበትም የህይወት ልምድ እንዲሁ ከሌላው የተለየ ነው፡፡ ለዚህም ነው የመጽሐፌን ርዕስ ”የኔ መንገድ” በማለት የሰየምኩት፡፡--” ብለዋል፡፡

ከመጽሐፉ አርታኢዎች አንዱ የሆነውና የቀድሞው የአዲስ አድማስ የረዥም ጊዜ ጸሐፊ በምረቃው ሥነስርዓት ላይ በሰጠው ሙያዊ አስተያየት፣ የምዕራፎቹ ስያሜዎች ጠሪ ናቸው ብሏል፡፡ ጥቂቶቹን ለማሳያ ያህል፡- “ከኢህአፓ ጋር መርካቶ ተዋወቅን“፣ “ባድመ ግንባር ላይ ያገኘሁት ጎረቤቴ“፣ “አይ ጨበራ ጩርጩራ ፓርክ“፣ “የሞስኮ ጎረምሶች አንቆራጠጡን“፣ “የባዳ ዘመዳችን - መወለድ ቋንቋ ነው“፣ “አባባ ጃንሆይን መንገድ ላይ አገኘኋቸው”፣ “የተነፋው ጎማ ተነፈሰ” ወዘተ ይገኙባቸዋል፡፡ አርታኢው እውነት ብሏል፤ጠሪ ናቸው፡፡

“የኔ መንገድ“ ግለታሪክ መጽሐፍ ለአገር ውስጥ በ600 ብር፣ ለውጭ አገራት በ25 ዶላር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡

ዘገባዬን ደራሲው በመጽሐፉ መግቢያ ላይ በተጠቀሙበት የሲ.ሲ. ኮልተን አባባል ልቋጭ፡፡ እንዲህ ይላል፡-

 “ደራሲ መሆን ሦስት ችግሮች አሉት፡፡ ለህትመት የሚመጥን ጽሁፍ መጻፍ ፤የሚያሳትሙ ቅን ሰዎች መፈለግ፤ የሚያነቡትን አስተዋይ ሰዎች ማግኘት፡፡”

Read 1099 times