Saturday, 29 July 2023 12:28

ቄሱ እና የሚሞተው ሰው

Written by  ደራሲ፡- ማርኪ ዴ. ታድ ትርጉም፡- በኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(14 votes)

 ቄስ፡- አሁን የቅዠትህን አለም ሸፍኖት ያለው መጋረጃ ተቀዶ እስከዛሬ ስትሰራው ከነበረው የሀጥያት አዘቅጥህ ጋር ፊትለፊት ሊያገናኝህ ከፊትህ ሞት እጆቹ ተዘርግተዋል። እንግዲያውስ የኔ ልጅ… የተሸከምከው ድክመትህና ሀጥያትህ ይቅር እንዲባልልህ ንስሀ ለመግባት ዝግጁ ነህ?
የሚሞት ሰው፡- አዎ…ንስሀ እገባለሁ፡፡
ቄስ፡- ባለህ አጭር ጊዜ ውስጥ ይቅር ባይነትህንና ሽንፈትህን በመለየት ይቅር እንድትባል እድሉን መጠቀም አለብህ፡፡ ይህን ስታደርግ …. ምኞትህን ወዳሻኸው አላማህ የሚለውጥልህ ማንም የማይመረምረው ለሁሉም ስነ ፍጥረት እረፍትን የሚሰጠው አንድ ሀያልና ዘላለማዊ አምላክ እንዳለህ በማመን ነው።
የሚሞት ሰው፡- አንተ ከተረዳኸኝ በላይ ነው እየተረዳሁህ ያለሁት፡፡
ቄስ፡- ምን ማለትህ ነው?
የሚሞት ሰው፡- ንስሀ ገብቻለሁ ብዬሀለሁ እኮ፡፡
ቄስ፡- እኔም ሰምቼህ ነበር፡፡
የሚሞት ሰው፡- አዎ ሰምተኸኛል፡፡ ነገር ግን ምን ለማለት እንደፈለኩኝ አልተረዳኸኝም፡፡
ቄስ፡- ሌላ ምን አይነት ትርጉም ሊኖረው ይችላል?
የሚሞት ሰው፡- እንግዲያውስ ከዚህ በኋላ የምልህን ከልብህ ሆነህ ስማኝ፡፡ የተፈጠርኩት በተፈጥሮ ፍፁም ፈቃድና ጠንካራ ስሜት ውስጥ ነው፡፡ ወደ ምድርም ስታመጣኝ በተፈጥሮ ውስጥ ያሉትን ነገራቶች በሙሉ እንዳከብራቸውና እንድንበረከክላቸውም በማሰብ ነው፡፡ እነዚህም ፍጡራን የኔ የተፈጠረው ማንነት አካላት ናቸው እንጂ ተፈጥሮ አላማዋን የምታከናውንባቸው መገልገያ መሳሪያዎቿ ብቻ አይደሉም፡፡
እናም ንስሀ የምገባው የተፈጥሮን ፍፁም ሉዓላዊነት ባለማመኔ ነው እንጂ ባንተ አይኖች ውስጥ ሀጥያት እያልክ የመዘገብካቸውና ለኔ ምናልባትም እንደ ፅድቅና የምቆጥራቸውን፣ ብሎም ተፈጥሮ እንድገለገልባቸው ለሰጠችኝ  ሰብዕናዎች አይደለም፡፡   
አንዳንዴ ተፈጥሮን እጋፋታለሁ… ልፈትናትም ይቃጣኛል፤ ለዛም ከልቤ ይቅርታ ልጠይቃት እፈልጋለሁ፡፡ ባለንተ ቅዥቢ የአምልኮ ስርዓት ታውሬ በውስጤ ሲንቀለቀል የነበረውን የውስጤን ስሜት እንደ ልቤ ሳልተገብረውና ተፈጥሮዬ ላይ በማመፄ እጅግ አድርጎ ይፀፅተኛል፡፡ ስፍሩ የማይታወቅ ሰብል መሰብሰብ እየቻልኩ የአንዲት አበባን ውበት ብቻ በማድነቅ ነው ጊዜዬን የገደልኩት። ይህን ሀሳብ ነው እንግዲህ የተፀፀትኩበት፡፡ የምታከብረኝም ከሆነ  የምልህን ከፍርድ ውጭ ሆነህ አድምጠኝ፡፡
ቄስ፡- እንዴት አድርገህ ነው ስህተትህን ማጣጣም የተመኘኸው፡፡  ሶሳኒያኒዝም ፍልስፍና ውስጥ ሆነህ በእንዴት አይነት መልኩ ነው መንገድህን የሳትከው፡፡ ፍፁምና ሉዓላዊ ባልካት የተሳሳተች የተፈጥሮ ትርጓሜ ውስጥ ሆነህ ምን ያህል ንስሀ መግቢያ እድልህን እያጣህ መሆኑን ተገንዝበሀል?
የሚሞት ሰው፡- እንደማየው ከሆነ የምታቀርበው ምክንያት ልክ እንደ ጭንቅላትህ ባዶ መሆኑን ነው፡፡ ጥርት ባለ ምክንያታዊነት ውስጥ ሆነህ ብታወራኝ ፍፁም ፍላጎቴ ነበር፤ ነገር ግን ይህን የማታደርግ ከሆነ ከእነ ሰላሜ ጥለኸኝ ብትሄድ ምኞቴ ነው። ምን ለማለት ፈልገህ ነው ፈጣሪ ስትል? የተሳሳተ ተፈጥሮስ ስትል ምን ተረድተህ ነው?
ቄስ፡- ፈጣሪ ማለት የምታየውን የሁለንታ አለም የፈጠረው ነው፡፡ ሁሉም የምታያቸው ነገሮች በሙሉ የተፈጠሩት በሱ እጅ ነው። ይህም የፈጣሪነቱን ግርማ አንድና ብቸኛው ሉዓላዊ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡
የሚሞት ሰው፡- እንግዲያውስ ይህ የምትለኝ ሰው እጅግ ታላቅ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ንገረኝ….ይህ ሰው እንዴት አድርጎ ነው ፍፁም የሆነ ተፈጥሮን የሰጠን?
ቄስ፡- ፈጣሪ ነፃ ፍቃድን ካልሰጠው የሰው ልጅ ጥቅም ምኑ ላይ ነው? በምድር ላይስ የሰው ልጅ ሲኖር መልካሙን ከመጥፎው መለየት ካልቻለ ምኑን ሰው ሆነው?
የሚሞት ሰው፡- ስለዚህ ፈጣሪ አለምን ቀጥ ያለ የማይለዋወጥ አድርጎ ሲፈጥር በቀላሉ  የሰው ልጅን ሊፈትን ነው ማለት ነው? ይህ ማለት የፈጠረውን ፍጥረት በቅጡ አያውቀውም ማለት ነው? ወይም ደግሞ ቀጥሎ ሊመጣ የሚመጣውን ነገር አያውቀውም ማለት ነው፡፡
ቄስ፡- በእርግጥም የፈጠረውን ፍጥረት ያውቀዋል፡፡ በተጨማሪም ግን በእውቀትና በጥበብ ውስጥ ሆኖ ያሻውን እንዲመርጥ እድሉን ሰጥቶታል፡፡
የሚሞት ሰው፡- ለምን ብሎ… የፈጠረው ፍጥረት ቀጥሎ ምን ሊመርጥ እንደሚችል ቀድሞ ያውቀዋል፡፡ አንተም ብትሆን ሀይል ሁሉ የሱ ነው ብለኸኛል …እንግዲያውስ በዚህ ሀያል አቅሙ ውስጥ እኔም ብሆን የፈጣሪን ምርጫ ራሱ ትክክል መሆኑን ማወቅ እፈልጋለሁ?
ቄስ፡- ይህን ሰፊና ዘላለማዊ የሆነውን ፈጣሪ ለሰው ልጅ ያሰበለትን ምክንያት ማንስ ሊረዳው ይችላል? የሚታዩትን ነገራት በሙሉ በአንድ ጊዜ ሊረዳስ የሚችል የሰው ልጅ እንዴትስ ሊገኝ ይችላል?
የሚሞት ሰው፡- ማን መሰለህ የምትላቸውን ሚስጥራቶች መርምሮ መረዳት የሚችለው… ማንኛውም ነገራትን በቀላሉ መመልከት የሚችል ሰው፡፡ በተለይ ደግሞ በግልፅ የሚታዩ የተፈጥሮ ውጤቶችን ተመልክቶ በቀላሉ መረዳትን እንጂ የሚያየውን ሁሉ ሚስጥራዊና የተደበቀ ግኝት አድርጎ የማይመለከት ሰው ነው፡፡ መጀመሪያ ተረዳሁት ያልከውን በግልፅ ማስረዳት ሳትችል እንዴት አድርገህ ሁለተኛውን መመለስ ይቻልሀል፡፡ አንተ ፈጣሪዬ ነው የፈጠረው ያልከውን ተፈጥሮ በራሷ ማድረግና ማግኘት ከቻለች ስለምን የተለየ ምትሀታዊ እጅ እንዲመጣና ስራዋን እንዲሰራላት ትፈልጋለህ? ልታስረዳው ያልቻልከው ታላቅ ሚስጥር የምትለው ነገር ምናልባትም የመጨረሻው ግልፅና ቀላል እውቀት ሊሆን ይችላል፡፡ ፊዚክስ አጥና… በዛም ተፈጥሮን በተሻለ ለመረዳት ይቻልሀል፣ ጥርት አድርገህ ለማሰብ ብዙ አጥና፣ ብዙ አሰላስል….ከዚህ በፊት ጎትተህ ያመጣኸው እውቀትህን ወዲያ አሽቀንጥረው፤ በዛም ፈጣሪዬ የምትለው አምላክህ ምንም እንደማያስፈልግህ ትረዳለህ፡፡
ቄስ፡- የማትረባ መናፍቅ፡፡ ከሀጥያትህ የማትናብል ፍፁም ሀጣን መሆንህን ስለተረዳሁ ነው ልዋጋህ ከነ መሳሪያዬ የመጣሁት፡፡ ነገር ግን አሁን አላማኝ መሆንህንና እስካሁን ድረስ በየቀኑ መኖሩን በተፈጥሮ ውስጥ እየሰበከህ ያለውን ፈጣሪህን መመልከት ያቃተህ ደካማ መሆንህን ስለተረዳሁ ከዚህ በኋላ ምንም ነገር ባወራህ ትርጉም እንደሌለው ተረድቻለሁ፡፡ አይኑ ለማያይ ሰው ብርሀን ሊገለፅለት አይቻለውም፡፡
የሚሞት ሰው፡-  አንድ ነገር እርግጠኛ ሁንልኝ፡፡ አንድ ሰው ታወረ የምንለው በአይኑ ላይ ሽፋን ያደረገውን እንጂ ያወለቀውን አይደለምን? ምክንያቶችን ለራስህ በሚመች መልኩ ታስተካክላለህ ትፈጥራለህ፡፡ አንተ ትርጉሞችን ታባዛቸዋለህ፤ እኔ ግን አወድማቸውና ወደ ቀላል መረዳት አወርዳቸዋለሁ፡፡ አንተ በስህተት ላይ ስህተት ትደራርባለህ፤ እኔ ደግሞ ሁሉንም ስህተቶች እገዳደራቸዋለሁ፤ እፈትናቸዋለሁ፡፡ እንግዲያውስ ከኔና ካንተ እውሩ ማነው?
ቄስ፡- ስለዚህ በፈጣሪ አታምንም ማለት ነው?
የሚሞተው ሰው፡- አዎ በፈጣሪ አላምንም፤  ይህንንም ስል በአንድ ቀላል ምክንያት ነው፡፡ ይህም አንድ ሰው ሊረዳው የማይችለውን ነገር ሊያምንበት አይገባም የሚል ነው፡፡ በመረዳትና በማመን መካከል ግልፅ የሆነ ግንኙነት መገንባት አለበት፡፡ መረዳት የእምነት መሰረቱ ነው፡፡ ፍፁም መረዳት በሌለበት እምነት ይሞታል፤ እነዛም ስለጉዳዩ ምንም መረዳት የሌላቸው ሰዎች፣ ነገር ግን አምኛለሁ የሚሉት ግብዞች ናቸው፡፡
በየቀኑ የምትዘምርለትንና የምታመልከውን ፈጣሪህን በህይወት መገኘቱን ማስረዳት ባለመቻልህና  ተፈጥሮውን ለማስረዳት አቅም ያለህ ስላልሆንክ እቃወምሀለሁ፡፡ አዎ… ፈጠረኝ የምትለው አምላክህን ሳታውቀው ነው ትርጉም በማይሰጡ ምክንያቶች ልታጥበኝ የምትመኘው። ይህም ማለት ከሰው ልጅ አቅም በላይ የሆነ ነገር ወይ ቅዠት ነው ወይ ደግሞ ደረቅ ህልም ነው፡፡  በዚህም ያንተ ፈጣሪ ከሁለቱ አንዱ መሆኑ ካልቀረ እኔም ብሆን ይህንን በማመኔ እንደ እብድ ነው ልታይ የሚገባኝ፡፡ ቁስ አካል የማይነቃነቅ መሆኑን አስረዳንና እኔም ፈጣሪውን እሰጥሀለሁ፡፡ ተፈጥሮ በራሷ ሙሉ አለመሆኗን አስረዳኝና እኔም በደስታ አለቃዋን ፈልገህ እንድትሰጣት እድሉን እሰጥሀለሁ። ይህን ማድረግ እስካልቻልክ ድረስ ከእምነቴ ፈቀቅ አልልልህም፡፡ በማስረጃ የተደገፈን ነገር አምናለሁ፤ የማምንበትም መሳሪያዬ የስሜት ህዋሳቴ ብቻ ነው፡፡ ከነዚህም የስሜት ህዋሳቶቼ ውጭ ያለን መረዳት ለማመን ምንም አይነት ሀይል እንደሌለኝ አምናለሁ፡፡ ፀሀይ መኖሯን የማምነው ስለማያት ነው፡፡ ለምድርና ለፅንፉ አለማት ዘላለማዊ ብርሀን እንደምትሰጥ ባምንም የሁልጊዜ ስራዋን እያየሁ የተለየ መደመም ውስጥ አልገባም፡፡  ይህ የፊዚክስ ግኝት ነው፤ ምናልባትም ከኤሌክትሪሲቲ አሰራር ጋር ቢመሳሰል እንጂ የተለየ ጥበብ በውስጡ የለም። ከዚህም በላይ ልጨምርልህ… የራስህን ፈጣሪ አበጃጅተህ ከሁሉም የተፈጥሮ ግኝቶች በላይ አድርገኸዋል… ታዲያ ይህን በማድረግህ እኔን ወደ ፊት እንድሄድ ያደርገኛል? የሚገርመው ቅዠትህን ከፊቴ መገተርህ ለኔ ምንም የሚሰጠኝ አገልግሎት የለውም፡፡  እጅግ ግራ ከመጋባትህ የተነሳ ላንተ የምሰጥህ ጥላቻን እንጂ ምንም አይነት አድናቆት የለኝም፡፡ ያንተ አምላክ የውስጥ ስሜትህን ልትሰብክበትና ልትፈፅምበት ያበጀኸው መሳሪያህ ነው፡፡
በዚህ ሰዓት ደካማዋ ነፍሴ ሰላምንና ፍልስፍናን ነው የምትሻው፡፡ ታዲያ ይህች ነፍሴን  በዚህ ሰበካህ ጭንቀትህንና ድንጋጤን ከመፍጠር ውጭ ወዳንተ መንገድ የምታመጣበት አካሄድ አልታየኝም፡፡ በማረጋጋት ፋንታ ነፍሴን ማቃጠሉን ነው የመረጥከው፤ የኔ ነፍስ ተፈጥሮ የመረጠችላትን ነው የምትሆነው፡፡ ተፈጥሮን ከህጎቿ በላይ ለመረዳት አትሞክር፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ አዕምሮ ቋሚ ህልውና ስለሌለው ነውና፡፡ ተፈጥሮንም ለማስረዳት የምትሞክር ከሆነ ከፍቃድዋና ከፍላጎትዋ ውጭ ላለመመልከት ሞክር፡፡
ቄስ፡- እናስ በአለም ላይ ያለው ነገር በሙሉ ጥቅም አለው እያልከኝ ነው?
የሚሞት ሰው፡- እርግጥም እንደዛ ነው፡፡
ቄስ፡- ነገር ግን ሁሉም ነገር የሚያስፈልግ ከሆነ፣ በያንዳንዱ ነገር ውስጥ ስርዓት አለ ማለት ነው?
የሚሞት ሰው፡- ማነው ስርዓት የለም ያለው?
ቄስ፡- ነገር ግን ይህን ሁሉ ስርዓት፣ ሁሉን አዋቂና ሀያል እጅ ካሆነ በስተቀር ማንስ ሊገነባው ይቻለዋል?
የሚሞት ሰው፡- የጥይት ባሩድ በክብሪት ሲለኮስ  አይፈነዳምን?
ቄስ፡- አዎን ይፈነዳል፡፡
የሚሞት ሰው፡- በዚህ ውስጥ ምን ጥበብ ተመለከትክ?
ቄስ፡- ነገሩ ግልፅ ነው፡፡ ምንም አይነት ጥበብ የለበትም፡፡
የሚሞት ሰው፡- ስለዚህ በጣም ሊጠቅሙ የሚችሉ ነገሮች በጥበብ ያልተሰሩ ነገራት እንዳይደሉ የተረዳህ ይመስለኛል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በመጀመሪያው ምክንያት የተፈጠሩ ነገሮች ምናልባትም ምክንያትም ሆነ ጥበብ ላይገኝባቸው የሚችልበት መንገድም እንዳለም መረዳት አለብህ፡፡
ቄስ፡- ወደ የት ነው ሀሳብህን እየወሰድከው ያለኸው?
የሚሞት ሰው፡- ሁሉም ነገር ባለበት ቀላልና ግልፅ እንደሆነ ላረጋግጥልህ እወዳለሁ። በተፈጥሮ ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ አካላት ያለ ምንም ተጨማሪ ሀይል ስርዓታቸውን ጠብቀው መሄድ ይችላሉ፤ ያንተንም ፈጣሪ ፈቃድም ሆነ ህግ አያስፈልጋቸውም፡፡ በዚህም መንገድ ፈጣሪህ ምንም አይነት ጥቅም ስለሌለው ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡
ቄስ፡- ይህ ከሆነ ያንተ አመለካከት… ስለ ሀይማኖት ላዋራህ የምችልበት ምንም አይነት ምክንያት፡፡
የሚሞት ሰው፡- የሰው ልጅ በሀይማኖት ሰበብ ምን ያህል ቅዥቢነትንና የእውቀት ማነስን መለማመድ ውስጥ እንደገባ ሳስብ መዝናናት ውስጥ ነው የምገባው፡፡ ግልፅ አድርገህ መልስልኝ…ከሁሉም በላይ ከራስህ አስተሳሰብና ፍላጎት ውጭ ሆነህ መልስልኝ፡፡ ምናልባት ያንተን ግራ የገባው አምልኮህን አምኜልህ አምላክህን ማምለክ ብጀምር የትኛውን አይነት የአምልኮ ስርዓት ተከትዬ ነው እንዳመልከው የምትፈልገው? የኮንፊሺየስን ደረቅ እብደት እንድከተለው ታደርገኛለህ ወይስ የብራህማንን ባዶነት? የኔግሮ ታላቅ ዘንዶ ፊት ልንበርከክ፣ የፔሩቪያንን ጨረቃንና ከዋክብት ላምልክ ወይስ የሙሴ ተዋጊዎች አምላክ ለሆነው? የትኛውን  ነው እንድከተል የምትመርጥልኝ? ወይስ የትኛው የክርስትና አስተሳሰብ ነው ከሌሎቹ በላይ ጎልቶ ሊታይ የሚችለው? ከመመለስህ በፊት ተጠንቅቀህ አስብ?
ቄስ፡- መልሴ ላይ ምንስ አይነት ጥርጣሬ ሊኖር ነው?
የሚሞት ሰው፡ ያም ሆኖ ከራስ ፍላጎት ተነስቶ የሚመለስ መልስ ሊሆን ይችላል፡፡
ቄስ፡- በፍፁም እንደዛ ሊሆን አይችልም፡፡ የኔን እምነት ላንተ ስሰብክህ ራሴን ከምወደው በላይ አንተን እንደምወድህ ነው የሚናገረው፡፡
የሚሞት ሰው፡- እነዚህን ስህተቶችህን በማዳመጤ ለሁለታችንም ያነሰ ፍቅር እንዳለህ ነው የምረዳው፡፡
ቄስ፡- ቤዛ የሆነው መለኮታዊ ፈጣሪያችን የሚሰራውን ተዓምር ለማየት እውር መሆን የሚችል ማን ይኖራል?
የሚሞት ሰው፡- ልክ እንደ አምላኩ አጭበርባሪ መሆኑን የሚረዳ ሰው፡፡
ቄስ፡- ፈጣሪዬ ሆይ…አንተ የልብ አዋቂ የሆንከው እባክህን አንደበትህን በመብረቅ ነጎድጉዋድ አትግለፀው።
የሚሞት ሰው፡- ዝም በል፡፡ ስትጠብቀው የነበረው ድምፅ ያልመጣው በቀላል ምክንያት ነው… የመጀመሪያው የምትለው ፈጣሪ መስማት አይችልም ወይም በጣም አስተዋይ ስለሆነ ነው ወይም ሌላ ምክንያት ይኖረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ልመነው እንኳን ብል በሀዘኔታና ከመልካም አስተሳሰብ አንፃር ብቻ ሊሆን ነው የሚችለው፡፡
ቄስ፡- ሆኖም ስለ ነብያቶች፣ ተዓምራቶችና ሰማዕታት ምን አመለካከት አለህ? እነዚህ ነገሮች ማረጋገጫ መሆን አይችሉም?
የሚሞት ሰው፡- በራሱ ብቻውን ተረጋግጦ ያላለቀን ነገር እንዴት አድርገህ እንደ ማረጋገጫ ትጠቀምበታለህ? የአንድን ትንቢት እርግጠኝነት ለማወቅ በመጀመሪያ የተባለው ትንቢት ተፈፅሟል ወይ የሚለውን እርግጠኛ መሆን አለብኝ፡፡ ትንቢት ምናምን የምትለው ነገር በታሪካውያን የተተረከ ነገር ነው፤ ይህም የሆነው ከግል ፍላጎታቸው የተነሳ ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህም እውቀት ባለቤት በመሆኔ የመጠራጠር መብቴ የተጠበቀ ነው የሚሆነው፡፡ ማንስ ነው ሊነግረኝ የሚችለው ትንቢት እያልክ የምታወራው ነገር የተተነበየው ታሪኩ ከተፈፀመ በኋላ አለመሆኑን? ስለዚህ ፈጥነህ ትንቢቶች መለኮታዊ ግኝት ስለመሆናቸው ለማስረዳት ትንቢትን እንደማረጋገጫ ከመስጠትህ በፊት ራሱኑ ትንቢቱን ለመመርመር ትጋ፡፡
ተዓምራት ላልከው ነገር ደግሞ…እውነት ለመናገር ከትንቢቶች በላይ ተዓምራቶች ያስደንቁኛል፡፡ ሁሉም አጭበርባሪዎች ተዓምራት ይሰራሉ፤ መሀይማን ደግሞ ይከተሏቸዋል፡፡ ይህን ተዓምራት እያልክ የምትጠራውን ነገር እንዳምንልህ ከፈለክ ከተፈጥሮ ህግ ውጭ እየሆነ ያለ ነገር ስለመኖሩ አንድ ላይ እንድታስረዳኝ እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም ከተፈጥሮ ስርዓት ውጭ የሆነ ነገር እንደ ተዓምር ስለሚታይ፡፡ ሆኖም ስማኝ፤ የትኛው የሰው ፍጥረት ነው የተፈጥሮን ሚስጥር ጠንቅቆ የተረዳ? ማነው የተፈጥሮን ጅማሮና ፍፃሜን በድፍረት አውቀዋለሁ ብሎ ማስረዳት የሚችለው? በቅድሚያ ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ተዓምር ነገር ነው ለማለት ተፈጥሮን ጠንቅቀን አውቀናታል? ምርጥ ተዓምራት ለመባል ሁለት ነገሮች ያስፈልጉናል…አንደኛው እውቀት የሌለው ባለመድሀኒትና የጀርባ አጥንት የሌላቸው ተመልካቾች ናቸው፡፡ እስከዛሬ ተዓምር ፈጣሪዎች ነን ያሉት ሀይማኖት ፈጣሪዎች፣ በባህሪያቸው እንግዳ የሆኑና የሚሰሩት የሚናገሩት በሙሉ ተዓምራትን ብቻ እንደሆነ ለተከታዮቻቸው ይነግራሉ፡፡ የታያናው አፖሎኒየስ ካንተ እየሱስ የተሻለ ብዙ ተዓምራትን ሰርቷል፤ ሆኖም እኔ አምላክ ነኝ የሚለውን ሀሳብ የትኛውም የሰው ጭንቅላት ውስጥ ለማስገባት አልሞከረም፡፡
ሰማዕታት ላልከው ነገር ደግሞ…እስካሁን በምድር ላይ ስኖር እንደነሱ ያለ ደካማ ፍጥረት አይቼ አላውቅም፡፡ ሰማዕት ለመባል ቅንዓት እና ግትርነት ብቻቸውን በቂ ናቸው፡፡
ስማኝማ ወዳጄ…አምላኬ እያልክ የምትሰብከው ፈጣሪህ ግዛቱን ለማስፋፋት ተዓምራትን፣ ሰማዕታትንና ትንቢቶችን የሚፈልግ ይመስልሀል?  አንተም እንዳልከው ከሆነ የሰው ልጅ ልብ የፈጣሪው እጅ ስራ ከሆነና የሰው ልጅ ልብ ግን የሚገነባው ራሱ ፈቅዶ ባወጣው ህጉ ከሆነ ነገሩ እንዴት ነው የሚሆነው? የምርም ይህ ሁሉንም የሰው ልጆች በተመሳሳይ ጸጋ የፈጠረ ፈጣሪ ካለ፣ ሁላችንም ፍጥረታት ውስጥ ተመሳሳይ ፀጋው ነው መገኘት ያለበት፡፡  ሁሉም የሰው ልጅ ተመሳሳይ የአስተሳሰብ መርህን ተከትሎ እንዲሄድ በአምላኩ መልክ ከተፈጠረ ሁሉም ሰው ፈጣሪውን የሚያመልክበትና የሚያይበት ተመሳሳይ መንገድ መፈጠር ነው የነበረበት። በዚህም ምክንያት ሁላችንም ፈጣሪያችንን በተመሳሳይ መልኩ ነው ልንወደው፣ ልናደንቀውና ልናመልከው የሚገባው፡፡ ሆኖም አሁን በአለማት ላይ ብመላለስ ምንድን ነው ላገኝ የምችለው? በትውልድ ብዛት ልክ የበዙ አማልክቶችን እና የማሰብ ርቀታችን እስከተጓዘው ድረስና እስከምንዋለደው ብዛት ልክ የፈጣሪ የአምልኮ ስርዓቶችም እንዲሁ በዝተው ነው የማገኛቸው፡፡
እንግዲያውስ ንገረኝ ልምረጥ ብል እንኳን እድሜዬ የማይበቃኝ የሀይማኖት ብዛትን ስመለከት እውነት ይሄ የፈጣሪ እጅ ስራ ነው ብዬ ማመን አለብኝ? አይሆንም የኔ ሰባኪ…በዚህ አይነት ብርሀን ልታሳየኝ የመረጥከው አምላክህ ራሱ  የሚበሳጭብህ ይመስለኛል፡፡ እመነኝ እኔ የእሱን መኖር ከካድኩት በላይ ያንተ ውሸት የተቀባና እውቀት ያነሰው ሰበካህ በበለጠ ያበሳጨዋል፡፡ አስብ የኔ ሰባኪ…ያንተ እየሱስ ከመሀመድ የተሻለ አይደለም…ሙሀመድም ከሙሴ የተሻለ አይደለም…እነዚህም ሶስቱ ሀያላን በአንድ ላይ ሆነው ከኮንፊሽየስ በላይ መሆን አይችሉም፡፡ ሆኖም ኮንፊሽየስ ምርጥ የሆኑ በቁጥር ተለቅመው የተፃፉ መመሪያዎችን ሲያስቀምጥ ሌሎቹ ግን እንቶ ፈንቶ የሆነ ወሬ አውርተው ነው የሄዱት፡፡
ቄስ፡- ምን ማለትህ ነው… ከአራቱማ አንዱ ብቻ ነው ፍፁም መሆን የሚችለው፡፡
የሚሞት ሰው፡- አዎ…የሚገባው አንዱ የሚገባውን ያገኛል፡፡ እሱም ቢሆን በደንብ አድርጎ እያማለለ መሸወድ የሚችለው፣ የውሸት ምስክሮችን ሰብስቦ የሚያስመሰክረውና ለማመን የሚከብዱ የሀሰት ተዓምራትን የሚፈፅመውን ነው። እንደዚህ አይነት ሰዎች ባላምናቸውም ቀልቤን ይስቡታል፡፡ ሆኖም እነዚህን በመከተል ጊዜዬን አላጠፋም፡፡ የማምነውና ክብር የምሰጣቸው ንጉሶችንና ንግስናቸውን ብቻ ነው፡፡ ሀገሩንና ንጉሱን የማይወድ ሰው በምድር ላይ ሊኖር አይገባውም እላለሁ፡፡
ቄስ፡- ሆኖም ከዚህ ህይወት በኋላ የሆነ ነገር እንዳለ አምነህልኝ አልነበር?  እንግዲያው ይህን አስረዳኝ፡፡ በምንፍቅና ህይወት ውስጥ የሚኖር ሰው ቅጣት እንደሚጠብቀውና መልካምን ህይወት የመራው ደግሞ የዘላለም ስጦታ እንደሚሰጠው የሚገልፀው ሀሳብ ላይ ምን አስተያየት አለህ?
የሚሞት ሰው፡- ለምን ወዳጄ። የምንምነት ፍልስፍና አስፈርቶኝ አያውቅም፡፡ ለኔ የምትለው ነገር ቀላል  አድርጌ ነው የምወስደው፡፡ ሌላ መልስ ብመልስልህ መልሱ የመጣው ከግል ኩራት ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም እኔ የምመልስልህ ጥርት ካለ ምክንያታዊነት ተነስቼ ነው። ለማንኛውም ምንምነት ፍፁም የሆነ ነገር አይደለም፡፡ በእርግጥም የተፈጥሮን የማያልቅ የትውልዶች መወላለድንና መወዳደምን እንድመለከትላት ከፊቴ እንደ መፅሀፍ የተገለጠች አይደለችምን? ምንም ነገር አይጠፋም…ምንም በምድር ላይ ያለ ነገር ወድሞ አያልቅም፡፡ ዛሬ ሰው ትሆናለህ ነገ ወደ ትልነት ትቀየራለህ፤ ከዛን ቀን ስትለጥቅ ወደ በራሪ ነፍሳት ትቀየራለህ…ይህ አይደል ታዲያ ዘላለማዊ ህይወት ማለት? ታዲያ ይጠቅማል ብዬ ባላሰብኩት ነገር የምሸለምና ልቆጣጠረው በማልችለው ወንጀል የምቀጣ አይነት ሰው መሆኔን ለምን ማመኑን መረጥክ… ፈጣሪዬ እኔን ለመቅጣት ብቻና በዛም ለመዝናናት አስቦ ሊፈጥረኝ ይችላል ወይስ መልካሙን ባለመምረጤ ክዶኝ የስህተት ምርጫዬን እያሰበ ነው የሚቀጣኝ?
ቄስ፡- ነገር ግን እኮ አንተ የመምረጥ ነፃነት አለህ፡፡
የሚሞት ሰው፡- አዎን የመምረጥ ነፃነት አለኝ፡፡ ሆኖም የነፃ ፍቃድ ፍልስፍና የተጣመመ መቅድመ ልባዌህን ከፈጣሪህ መለኮታዊ ክብርና መርህ ጋር ለማጋባት የተፈጠረ መላ ብቻ ነው። የሚቀጣውን ቅጣት ቆሞ እየተመለከተ በፍቃዱ ብቻ ወንጀልን ለመስራት የሚፈልግ ሰው አለ? የለም፡፡ ተፈጥሮም ብትሆን መልካም ነገርንና ጥፋትን በእኩልዮሽ የምታስኬድበት የራስዋ  መንገድ አላት፡፡ እውነትስ ተፈጥሯችን በምትመራን መንገድ በመሄዳችን ወንጀለኞች ልንባል እንችል ይሆን?
ቄስ፡- ስለዚህ እጅግ አፀያፊ የምትለው ወንጀልን እንኳን ብንፈፅም ምንም ልንፈራው የሚገባ ነገር የለም ነው የምትለኝ?
የሚሞት ሰው፡- እኔ እንደዛ አላልኩም። የምንሰራውን በደል ለማስቆም ምድር ላይ ያለ ህግና የፍትህ ሰይፍ ያስፈልገናል፡፡ ንስሀ መግባት ግን ከነዚህ ነገሮች ሁሉ አያድነንም። ይቅር በሉን ማለት ትርጉም የሌለው ነገርና በቀጣይ የምንሰራቸውን ወንጀሎች የማስቆም ሀይል የለውም፡፡ ሆኖም ወንጀል መስራትን እያበረታታሁ እንዳልሆነም በዚሁ እንድትረዳኝ እፈልጋለሁ። እርግጥ ነው ሁላችንም ወንጀልን መከላከልም ማስቆምም ይገባናል፡፡  ሆኖም ስናስቆማቸው ጥርት ባለ ምክንያታዊነት ላይ መሰረት አድርገን እንጂ ወደየትም የማይወስደውን የማይጨበጥ ፍርሀት ላይ መሰረት አድርገን መሆን የለበትም። ምክንያታዊነት …አዎ ምክንያታዊነት ብቻ ነው  በሌሎች ላይ ጥፋትን ማድረስ ደስተኞች ሊያደርገን እንደማይችልና ሌሎችን ስናስደስት በዛውም ደስታችን ደስታቸው ውስጥ እንደሚገኝ ተፈጥሮ በራሷ መንገድ የሰበከችን መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ የሁሉም የሰው ልጅ ሞራል በነዚህ ቃላቶች ውስጥ ሊገለፅ ይችላል…እራስህን እንደምታስደስት አድርገህ ሌሎችንም አስደስት…አንተን የሚያሳምምህን ነገር ሌሎች ላይ ከመተግበር ተቆጠብ የሚሉትን ሁለት ህጎች ብቻ ነው የህይወታችን መመሪያ ልናደርጋቸው የሚገባን፡፡ እነዚህን ለማድረግ ምንም አይነት ሀይማኖትም ሆነ ፈጣሪ አያስፈልገንም፤ እነዚህን መመሪያዎች ተግባር ላይ ለማዋል የሚጠቅመን ጥሩ ልብ ብቻ ነው፡፡  
ሆኖም የኔ ሰባኪ….አሁን ጥንካሬ እየራቀኝ ነው፡፡ ፍርዶችህን ወደዚያ አድርገህ ሰው ሁን …ወንድ ሁን …ፍርሀትህንና ተስፋህን ከውስጥህ አውጣ። መለኮታዊ እውቀትህንና ህግጋቶቹን ከውስጥህ አፅዳ… እስካሁንም ሃሳብህን እንደልብህ እንዳትናገር አድርገውሀልና፡፡ ምድር ላይ በሰው ልጅ ከተፈፀሙ ጦርነቶች በላቀ በነዚህ አስከፊ አማልዕክቶችና  እምነቶች ሰበብ የፈሰሰው ደም ይበልጣል። አሁን ካለህበት አለም ውጭ ሌሎች አለማቶች አሉ የሚለውንም ሀሳብ እርሳው፤ ምክንያቱም ምንም ነገር የለምና። ሆኖም ለግልህ ጥልቅ ፍላጎት ጀርባህን ሳትሰጥ ራስህንና በአቅራቢያህ ያሉትን ሰዎች ለማስደሰት ሞክር፡፡ ለህይወት ያለህን ጉልበት እንድታጠነክር ተፈጥሮ ልትሰጥህ የምትችለው ፀጋ ይሄን ብቻ ነውና፡፡ ወዳጄ ሆይ…  ካለኝ ንብረት በላይ የምኮራበት ሀብቴ የግሌ ጥልቅ ፍላጎቴ ነው። መላው ህይወቴን ያሳለፍኩት ለፍላጎቴ  ስሰግድና በእሱ ትከሻ ላይ እስከ ህይወቴ ማብቂያ ድረስ ለመሰንበት ነው። ጊዜዬ እየደረሰ ነው፡፡ ስድስት ሴቶች ምድርን ከምታሞቃት ፀሀይ በላይ የተዋቡ ናቸው። ለዚህ ቅፅበት ብዬ አዘጋጅቼያቸዋለሁ። ሂድና ተቀራመታቸው …ከደረታቸውም ላይ ራስህን አድርገህ እረፍትን እረፋት…እኔ እንዳደረኩት ሁሉን ነገር ለመርሳት ሞክር፡፡
የሚሞተው ሰው ካጠገቡ ያለውን ደውል ሲደውል ስድስት ሴቶች ወደ ክፍሉ ዘለቁ፡፡ በትከሻቸው ውስጥም የሰመጠው ቄስ በተፈጥሮ የሳተ ሰው ሆኖ ራሱን አገኘው…ይህ ሁሉ የሆነው ቄሱ የተሳሳተና መናፍቅነት ያጠቃው ተፈጥሮ ምን ማለት እንደሆነ ማስረዳት ስላቃተው ብቻ ነው፡፡  

Read 742 times