Saturday, 29 July 2023 12:49

ፍጹም ጀርባ መስጠት የታለ? - (ወግ)

Written by  ድረስ ጋሹ
Rate this item
(4 votes)

      ቅጠሎች  ቢለመልሙ በቅርንጫፍ ላይ፣ ቅርንጫፍ ቅጠል ሊሸከም ቢችል በግንድ ላይ፣ ግንድ ቅርንጫፎችን ሊይዝ ቢችል በሥር ላይ ነው።
እኔስ በማን ትከሻ ላይ ነኝ?
ምጣድ ባወጣው እንጀራ እጆች ይፈረጥማሉ። ዳሩ ሲፈረጥሙ ይሰብሩታል። ”መሬት  ችላን በተቀመጠች አትደብድባት” ይለኝና አጎቴ... ሲያርሳት ሲያደማት ይውላል። ውለታና ባለውለታ የት ገቡ? በቁና ለሰጡት ውለታ፣ አጀዲ ሙሉ ግፍ መቀበሉ አስመረራቸው ይሆን?_ምጽ! አመድ አፋሾች።
የትል መብራት ምግቧ ምንድን ነው? ትበራለች..ማታ ማታ። ጨለማ ውስጥ ብርኀን መሆንን ማን አስተማራት? ከቤታችን ያለውን ተገግ ያለ የአምፖል ብርሃን አይታ ያልተሳቀቀች ምን ዓይነት ልብ ቢኖራት ነው? እንደ አቅም መኖርን ማን ሰበካት?_እንጃ። ለመሆኑ ብርሃኗን ለምን ነው የምትጠቀመው? ለአደን፣ ለመንገዷ ወይስ ለምን?_አላውቅም። ራሷን ካሳያት ግን ምን አነሳት። ለራሳችን እንኳ መታያ ብርሃን ለምን አጣን?
እኔስ፣ ብርሃን ውስጥ እንድጨልም ማን ገፋኝ?
ዕርፈት የላትም ጉንዳን። የተሠጣ አይቀራት፣ በዛች አቅሟ ስንዴ ይዛ ቱስ ቱስ ማለት ታበዛለች። ቋቷን (ጎተራዋን) ሞልታ ክረምትን ልትጠብቅ? ለልጅ ልጆቿ ልታወርስ? አቅሟ ሲደክም ሃብቷ እንዲጦራት አስባ?...
ይታወቀኛል፣ ወጣትነቴን ተጭኘዋለሁ። በትራስ አፍኜ እንዳልገድለው ሃግ የሚል ሰው ያሻኛል። ክንዶቼ ድንጋይ እንደተጫነው ሣር ቢጫ ሆነዋል። ፀሐይ ሲነካኝ እንደ ቅቤ እቀልጣለኹ፣ ብርድ ሲሆንም እኮማተራለሁ። ሥራ ማንን ገደለ? ኃይሌ ገብረ ሥላሤን?_ኧረ በፍጹም።
ማለዳ ይነሳል ንስር። ክንፎቹን ግራ ቀኝ ሊያፀዳ ፤ለውሎውም ሊያዘጋጃቸው። ከሩቅ ሲወረወር፣ ከፍ ብሎ ሲበር፣ ድብቁን ሲመዝ_ሊውል።
የታል ዝግጅቴ? ማንን ነው በጠዋት አመስግኜ የማውቀው? ሲያመኝ የምኼድበትን ቤተ-እምነት ደህና ሆኜ ለምን ሸሸሁት? እጅግም ስለት ቢሾልክ ከአፎት፣ አንዳንዱም ጥበብ ቢያቃርብ ለሞት፣ በኔ የባሰ ዕዳ እንዳለ ማን ቀርቦ አይቶት?
ሣሮች ጠዋት ይነቃሉ። እንባ እንባ ቋጥረው። ሰው ሁሉ የሞተ መስሏቸው። ግን እኮ ሰውን እንቅልፍ ነበር አስተኝቶ ያሳደረው። አደግ አደግ ያሉት ሣሮች የቋጠሩት የእንባ ዘለላ ልብ ይነካል። እነቃለሁ በፋንታዬ፤ ብርድ ልብሴን ለብሼ፣ ጤዛ (እንባ) የቋጠሩ ሣሮችን አያለሁ። ሞቅ ሲል ፈገግ ይላሉ ።ተስፋ ስለሚያደርጉ አይደለም? አልሞቱም...አሉ...ያኗኑሩናል ብለውም አይደል?
ይገርመኛል። ስንቱ በቁማችን አለቀሰልን። ”ሰውን ማመን ቀብሮ ነው” ያለች ቀበሮ ምን አይታብን ነው? ማንም ለኛ የሚያስብ ያለ አይመስልም_ከአለቀሱልን በቀር። አህያ እንኳ ”ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ነው ብሂሏ።
ስለ ሰርዶ አውቃለሁ።
አርባ አንጓ ያለው ሰርዶ ቀንጥሰን። አድርቀን። የበሬ ቁስል የምትበላዋን ወፍ ገድለን...አድርቀን። ደቁሰን ደቋቁሰን። የምንወዳት ልጅ መንገድ ላይ ሸንታ ስትነሳ (እንዳኹኑ ሽንት ቤት ሳይበዛ) ሽንቷ ላይ ጨምረን። እንደምታፍቀረን አምነን፣ እሺታዋን እንጠብቅ ነበር። ማን ያውቃል ለአህያ ይህ ምስጢር ተገለጠላት ይሆን? ሊጠቀሙ ነው ብላ ይሆን?
ቅናት በእሷ አልተጀመረ።
የተለመደውን ሐበሻን የሚያሸማቅቁበትን ተረት ላንሳው?
እግዚአብሔር ወደ ምድር መጥቶ ጠየቀ። ለአንተ አንድ መኪና ከሰጠሁህ ለጎረቤትህ ሁለት እሰጣለኹ፡፡ ለአንተ መቶ በሬ ከሰጠሁ ለጎረቤትህ ሁለት መቶ እሰጣለሁ። ምን አለፋህ ለአንተ የሆነው ለጎረቤትህ እጥፍ ይሆናል። ስለዚህ...
”ለአንተ ምን ላድርግልህ?” ቢለው እግዚአብሔር
”አንድ ዓይኔን አጥፋልኝ” ነበር ያለው።
በዚህ መች አበቃ...
ሌላም ሰፈር ኼዶ ”ለሰዎች ሥጦታ ሳድል ዋልኩ፤ ለእናንተ ምን ልስጣችሁ?” ሲላቸው፤ ”ለእነገሌ ምን ሰጠሃቸው?” ነበር ያሉት።
ብቻ...ሆድ ይፍጀው።
ዓይኖቼ ይነቃሉ_ለቅኝት። ሜዳ ጉብሱን፣ ጓያና ገብሱን፣ አዝማራ ተክሉን እቃኛለሁ። አራቱ ዘሮች ከአእምሮዬ ጠፍተው አያውቁም። በመልካም መሬት ላይ ስለበቀሉት (ስለበቀልነው) ግን የበለጠ አስባለሁ።
በመልካም መሬት ላይ በቀልን። አፈራን። በቃ?
ምን ዓይነት አፈራር አፈራን ያለ የለም።
አዝዕርቶቹና አትክልቶቹ ግን ይመልሱታል። ሁሎቹም የበቀሉት በመልካም መሬት ላይ ነው፤አፈራራቸው ግን ለየቅል።
ካሮት በምኑ ያፈራል?_በሥሩ።
በቆሎ በምኑ ያፈራል?_በጎኑ።
ጤፍ በምኑ ያፈራል?_በጫፉ።
የእኛስ ፍሬ በየቱ ነው? በልጅነት? በወጣትነት? ወይስ በስተእርጅና?...
ስለመብቀሉ መሰበክ ይብቃ፤ ስለፍሬው እናስብ።
የቱ ጋ ነኝ? ጣቴን ወደራሴ ልሰብስብ፣ ስጠቁም ወደ’ኔ የቀሩት ሦስቱ ጣቶች ፋታ ነሱኝ። የሌሎችን ጉድፍ ለማውጣት የራስ መጥራት አለበት ይላል፤ ቅዱስ መጽሐፍ፣ ቀጥሎ የቻይናው ኮንፊሽየስ።
ከፍ ብዬ ታየሁ እንዴ?_የደገፈኝ ይኖራል።
ጨልሜ ታየሁ ይሆን?_በእፍታ የፈጠረኝ በእፍታ አጥፍቶኝ ይሆናል፤አልያም ራሴው ለራሴው ፀር ሆኜው ይሆናል...
ብዙ ተኛሁ ?_ምናልባት ብቆም የሚጥለኝ በዝቶ ይሆናል...
ጤዞች የሚያለቅሱት ለ’ኔም ነው?_ሰው አይደለሁ...
መች ይሆን ከቦታዬ የምታጡኝ?_እቀና ብል...
መገን።
ፍሬዬ በስሎ ያውቃል_ድንጋዮች አረገፉኝ እንጅ። ለፍሬ ያበቃኝም እጅ የቀጠፈኝም እጅ። በአንድ አፍ ሁለት ምላስ ብቻ አይበቃም፤ በአንድ እጅ ሁለት ሥራም እንጅ። የሳመው ይሁዳ የተሸጠውም ጌታ። እራት ለመጨረሻ ጊዜ ከማን ጋር በላሁ? ...ክርስቶስ በወደዳቸው ተሰቀለ ?...ሳምሶን በሚወዳት ኃይሉን አጣ...ማንስ ነው በሚወደው የተጠቀመ ? ዓለምን አብዝተው ቢወዱ ሊጠፉባት፣ አብዝተው ቢደሰቱባት ትዝታን ሊያበዙባት አይደለምን? ማንስ ነው ዘላለማዊ ደስታን የታደለ?፣ ደራሲው «ሰው ኢየሱስ ያድናል እያለ ያብዳል»ብሎ ነበር...ማበጃችን በውዴታችን በኩል አይበዛም?...
ርኢክዋ፣አእምርክዋ፣አፈቀርክዋ ለዓለም።
አየኋት፤ ወደድኳት፤ አፈቀርኳት_ዓለምን። እሷ ግን ማር ባቀበልኩበት ዕቃ መርዟን ጋተችኝ። ብን ብዬ እጠፋ ዘንድ ከብናኝ ማነስ ነበረብኝ። ዓይኗን ላለማየት ጀርባ መስጠት ግዴታዬ ነበር።
ለዓለም ጀርባ ሰጠኋት ።
ለመሆኑ ሰው ለምሥራቅ ጀርባውን ቢሰጥ ለምዕራብ ፊቱን አይሰጥም? ፍጹም ጀርባ መስጠት አለ ወይ? በዓለም ውስጥስ የማይቻለው ይኼ አይደለም? ለዛች ጀርባ ሲሰጡ ለዚች ፊት ነው የሚሰጠው። ሰሜንን ላለማየት ቢሹ ደቡብ ነው የሚጠብቅ፤ ቀና ለማለት ቢጠሉ ሲያዘቀዝቁ ምድር አለች።
ጀርባ መስጠት የታለ?
እማ ዘነቡ ጨንቋት ”ይኼን መንግሥት እንዴት ልረፈው?” ትላለች። እስቃለሁ። ጀርባ ልትሰጠው መሆኑ ነው፤ ለመጪው ፊት መስጠቷ አልገባትም። ወይም ከአሁን በፊት ለነበረው መንግሥት ጀርባ ሰጥተን ለዚህኛው ፊት መስጠታችን ተዘንግቷታል_ምጽ!
ለሥራ ጀርባ ሥሰጥ - ለስንፍና ፊት መስጠቴን
ለኑሮ ጀርባ ስሰጥ -ለሞት ፊት መስጠቴን
የተረዳሁ ዘግይቼ ነው። እንደ ፊት መስጠት ከባድ ነገር የለም። ለውሻ ከሮጡለት ይነክሳል፤ ለልጅም ከሳቁለት ይማታል። ፀሐይ እንኳ ግዑዟ ፊት ልትሰጥ አይገባትም። ልብን ከመታች ስልት ታስይዛለች።
”ሥራ እንዴት ነው ?” ያሉት ልብስ ሰፊ
”ችግር ነው” ነው መልሱ። ለሁለት እግር መሹለኪያ ሲያበጅ፣ ለቀበቶ ማስገቢያ ሲዘመዝም፣ ሲቆርጥ ሲቀጥል ስለሚውል።
ቆርጠን እንቀጥል።
እግዚአብሔር እኛን ማየት አቁሟል ካልን፣ እኛስ ለመታየት የሚያበቃ ቦታ ላይ ነን ወይ?
በዓለም ላይ መልካም ነገር የለም ካልን፣ መጥፎ ያልነው በምን አንፅረን ነው?
ለጥያቄዎች ጀርባ መስጠት ያምረኛል፤ ለመልስ ፊት መስጠት ባይኖረው። እፍታ ውስጥ የተካተተው ስለ አፄ ቴዎድሮስ የተጻፈው ሐሳብ ይምጣ። ”ኢየሱስ ክርስቶስ ለአይሁዳዊያን እጅ ሰጥቶ ዓለምን ማዳኑን እያወቅክ ለምን ቴዎድሮስ እጅህን አልሰጠህም ነበር? በሞትህ ምን አተረፍክ?” ይለዋል። ቴዎድሮስ ለሽንፈት ጀርባ ሰጠ፤ ለሞት ግን ፊቱን። ለሞት ጀርባውን ቢሰጥ፤ ፊቱ ለሽንፈት ነበር። ይኼ ነው ጥያቄውን የሚያከብደው ...ፍጹም ጀርባ መስጠት አለ ወይ?
አህያ ከሞተች ሰርዶ ቢበቅል...
የበሬ ጀርባም ቢቆስል ...
ወፏም ብትኖር ...ገድለን...አደራርቀን ...ቀጣቅጠን፣ ሕይወት ያረፈችበት ቦታ ላይ ሁሉ ነስንሰን በፍቅር ማንበርከክ። ብዙ ሰዎች ለእሷ ጀርባ፣ ለሞት ፊት ይሰጣሉ። ለእሷ ፊት መስጠት ነው ጥሩ። የራስ ፀጉር የሚያድግበትን ቀን ለይቶ የሚያውቅ አለ? ሲያድግስ ያየ አለ?..አድጎ ግን እናያለን። አምናለሁ!...ደስ የሚሉ ስሜቶች አድገው፣ ፈርጥመው እንደማይ። አዎ...ፍጹም ጀርባ መስጠት የለማ።

Read 617 times