Saturday, 29 July 2023 12:50

ከማህበራዊ ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


                           ጥበበኛው ሽማግሌ ስለ ስኬት


       በጥበበኛነቱ ወደሚታወቅ አንድ ሽማግሌ ዘንድ አንድ ወጣት መጣና፤ “በህይወቴ ስኬታማ መሆን እፈልጋለሁኝና ምን ማድረግ እንዳለብኝ ንገረኝ” አለው፡፡ ጥበበኛው ሽማግሌም የወጣቱን ዓይኖች ትኩር ብሎ ሲመለከታቸው ስኬትን ለማግኘት ያለውን ቁርጠኛነትን ተረዳና እንዲህ ሲል ጠየቀው፤ “በህይወትህ በጣም የምትወደው ምግብ ምንድነው?” ወጣቱም ምንም ሳያመነታ፤ “እናቴ ጋግራ የምታበላኝን ዳቦ ነው አብልጬ የምወደው” በማለት መለሰ፡፡
ጥበበኛው ሽማግሌ አሁንም የወጣቱን አይኖች ትኩር ብሎ እየተመለከታቸው፤ “እሺ አሳ ለማጥመድ ፈልገህ ወደ ሀይቅ ዳር ብትሄድ አሳውን ለማጥመድ ማጥመጃው ጫፍ ላይ ምን አይነት ምግብ ታደርጋለህ?” ሲል ጠየቀ፡፡ ወጣቱም ፈጣን በሆነ ምላሽ፤ “ትላትሎችን አደርጋለሁኝ!” በማለት መለሰ፡፡ በዚህ ጊዜ ጥበበኛው ሽማግሌ ለወጣቱ ልጅ፤ “ለምን? አንተ የምትወደው ምግብ እናትህ የጋገረችውን ጣፋጭ ዳቦ ነው፡፡ ለምንድነው አንተ የምትወደውን ዳቦ ትተህ ለአሳው ትላትል የምትወስድለት?” በማለት መስቀለኛ ጥያቄን አቀረበለት፡፡ ልጁም ትንሽ አሰብ አደረገና፤ “አሳውን ለማጥመድ ስሄድ ማሰብ ያለብኝ እኔ ስለምወደውና ስለምፈልገው ምግብ ሳይሆን አሳው ስለሚወደውና ስለሚፈልገው ምግብ ነው!” በማለት ተናገረ፡፡ በዚህን ጊዜ ጥበበኛው ሽማግሌ ፈገግ ብሎ ወደ ወጣቱ ልጅ እየተመለከተ፤ “በል እንግዲህ ልጄ! ስኬትን የማግኛው ምስጢርም አሁን አንተ የተናገርከው ነገር ነው፡፡ እኛ የምንፈልገውና የምንወደው ነገር እንዳለ ሁሉ ስኬትም የሚፈልገውና የሚወደው ነገር አለ፡፡ ስለዚህ ስኬትን ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ አንተ የምትወደውንና የምትፈልገውን ነገር ከማድረግ ይልቅ ስኬት የሚፈልገውን  ነገር ተግብር!” በማለት ምክሩን ለግሶት ጉዞውን ቀጠለ፡፡
በህይወታችን ማሳካት የምንፈልጋቸውን ነገሮች ከግብ ለማድረስ የምንሻ ከሆነ፡ ነፍስያችን የምትፈልገውንና የምትወደውን ነገር ገታ በማድረግ ማግኘት የምንፈልገው ስኬት የሚፈልገውንና የሚወደውን ተግባር መፈጸም  አለብን፡፡ ይህ ነው የአጭሩ ታሪክ ትልቅ መልዕክት!
ያማረ ስኬት ለሁላችን!
(መፅሐፈ ሬድዋን)



Read 780 times