Friday, 04 August 2023 20:41

አርቲስት አብርሃም ወልዴ፣ 1.9 ሚሊዮን ብር ለበጎ አድራጎት ተቋማት ለገሰ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
አርቲስት አብርሃም ወልዴ፣ ለሰርጉ ወጪ በሚል በጎፈንድሚ እና በተለያየ መንገድ ከሰበሰበው ከ2.2 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ውስጥ 1.9 ሚሊዮን ብር በደቡብ ጉራጌ፣ በሰሜን ሸዋ ፍቼ ከተማ፣ በሰቆጣና በደብረብርሃን ለሚገኙ አራት የበጎ አድራጎት ተቋማት ለገሰ።
ገንዘቡ የተበረከተው ለጋበር የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ ለፍቅር የተቀናጀ የማህበረሰብ ልማት ማህበር፣ በደብረብርሃን ለሚገኙ ተፈናቃዮችና በሰቆጣ 3 ወረዳዎች ለሚገኙ ከ30 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ነው፡፡
አርቲስት አብርሃም ወልዴና ባለቤቱ ወ/ሮ ማክዳ ኃ/ሚካኤል፤ ለጋበር በጎ አድራጎት 250 ሺ ብር፣ ለፍቅር የተቀናጀ የበጎ አድራጎት ማህበር 250 ሺ ብር፣ ለደብረብርሃን ተፈናቃዮች 400 ሺ ብር እንዲሁም በአበርገሌ በሳግብጂና በሰቆጣ ወረዳ ለሚገኙ ተፈናቃዮች 1 ሚሊዮን ብር፤ በድምሩ 1.9 ማሊዮን ብር ለግሰዋል፡፡
ሙሽሮቹ ከዚህ ቀደም ከዚሁ ለሰርግ ስጦታ ከወዳጅ ዘመድ ከተሰበሰበው ገንዘብ ላይ 300 ሺ ብር ለሜቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል መለገሳቸው ይታወቃል።
አርቲስት አብርሃምና ባለቤቱ ማክዳ ለሰርጋቸው ከሰበሰቡት 2 ሚሊዮን 266 ሺህ 205 ብር ከ56 ሳንቲም ውስጥ በጎፈንድሚ የተሰበሰበው 31 ሺ 935 .20 ዶላር ሲሆን፤ ቀሪው ገንዘብ በብር የተሰበሰበ መሆኑ ታውቋል፡፡
ዛሬ ቀትር 7 ሰዓት ተኩል ላይ የገንዘብ ድጋፉን በደሳለኝ ሆቴል በተካሄደ ሥነስርዓት ላይ የተረከቡት የየተቋማቱ ተወካዮች፣ አርቲስት አብርሃምንና ባለቤቱን ወ/ሮ ማክዳን አመስግነው፣ ጥንዶቹ ትዳራቸው ፍሬያማ እንዲሆንላቸውም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 1079 times