Saturday, 05 August 2023 11:28

ጭንቀት…. የረዥም እና የአጭር ጊዜ.. አለው፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

ማንኛውም ሰው በተለያየ ምክንያት ለጭንቀት እንደሚጋለጥ የተረጋገጠ ነው፡፡ ሴቶች ደግሞ ለየት የሚያደርጋቸው በተለይ በእርግዝናና በወሊድ ጊዜ ለጭንቀት ሊጋለጡ የሚችሉ መሆናቸው ነው። በተለይም በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች ለጭንቀት የሚዳረጉባቸው ምክንያቶችን ምንነት ለእናንተ ለአድማጮቻችን ለማጋራት ስንል ከባለሙያ አስተያየት ተቀብዬ ለንባብ ብያለሁ፡፡ ባለሙያዋ ዶ/ር ኢትዮጵያ ቁምላቸው ይባላሉ፡፡ ዶ/ር ኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ህክምና እስፔሻሊስት ሲሆኑ የሚሰሩት በኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል ነው፡፡
ዶ/ር ኢትዮጵያን ለማግኘት ወደ ኢትዮ ጠቢብ ሆስፒታል ባመራንበት ወቅት የታዘብኩት ነገር አለ። ቦታው ምርመራ የሚያደርጉ ሐኪሞች ያሉበት ሲሆን ብዙ እርጉዝ ሴቶች በየሐኪሞቻቸው ለመቅረብና ለመታየት ተራ እየጠበቁ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ማለት በሚያስችል ደረጃ ፈገግታ በፊታቸው ላይ አይታይም፡፡ ሴቶቹ በዝምታ ቁጭ ብለዋል። ወንዶቹም በዝምታ አጠገባቸው ቆመዋል፡፡ አንዳንዶች ከባለቤታቸው ጋር ከሚያደርጉት የእርስ በእርስ ውይይት ባለፈ እንደ ሳቅ ያለ ነገር አይታይም። ሁሉም ማትም ባልም ሚስትም በሚያሰኝ ደረጃ እውን … እርግ ዝናው በሰላም አብቅቶ ልጄን አቅፍ ይሆን ብለው የሚያስቡ ይመስላሉ፡፡ ይህ በእርግዝና ጊዜ በየቤተሰቡ የሚገጥም አስተሳሰብ ነው፡፡
ተመርማሪ የምርመራ ክፍሉን ስትለቅ ወደ ጽንስና ማህጸን ሐኪምዋ ዶ/ር ኢትዮጵያ ምርመራ ክፍል አመራሁ፡፡ ጥያቄም ሰነዘርኩ፡፡
ጥ፤- በእርግዝና ጊዜ ጭንቀት ለምን ይከሰታል?
ዶ/ር፤- እርጉዝ ሴቶች በተለያየ ምክንያት ሊጨነቁ ይችላሉ፡፡ እራሱ እርግዝናው ከባህርይ እና ከሆርሞን ለውጦች ጀምሮ የሚያመጣው ጭንቀትም ሊኖር ይችላል፡፡ ሌላው ደግሞ በእርግዝና ጊዜ የሚከሰተው ጭንቀት እርጉዝዋ ሴት ያለችበት አካባቢ፤ የስራዋ ሁኔታ፤ እርግዝናው ያልተቀደ ከሆነ፤ እርግዝናው ላይ እያለች የተለያዩ አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎች ይደረግላታል ወይ? የሚለውን ሁሉ የሚመለከት ይሆናል፡፡ ጭንቀት የረዥም ጊዜና የአጭር ጊዜ ተብሎ ይከፈላል፡፡ ይህም ድንገት የሚከሰት የጭንቀት መንስኤ ለምሳሌ (በቤተሰብ ውስጥ የሚያጋጥም ሞት…. እስር…. ሕመም የመሳሰሉ) እና በሂደት መለመድ የሚያቅታቸው የጭንቀት ምክንያቶች ሊገጥሙአት ይችላሉ፡፡ የረዥም ጊዜው ደግሞ ከአኑዋኑዋር፤ ከቤተሰበብ፤ ከስራ ከመሳሰሉት ነገሮች ጋር ሊያያዝ አብሮ የቆየ ሊባል የሚችል ይችላል፡፡   
ጥ፡- አንዲት እርጉዝ ሴት በጭንቀት መያዝዋን በተለይም አብሮአት የሚኖሩ ሰዎች እንዴት ሊያውቁ ይችላሉ፤-
ዶ/ር፤ እንደሁኔታው ሊታወቅ ይችላል። በተለያዩ ጥናቶች እንደተመለከተው ለጊዜው በእኛ ሀገር ተግባራዊ ባይደረግም ጭንቀቱ የሚለካበት መሳሪያ አለ፡፡ እንደጭንቀቱ ሁኔታ የሚያመጣውም ተጽእኖ ሊለያይ ይችላል፡፡ለምሳሌ ጊዜዋን ጠብቃ በስነስርአቱ ምግብ ላትበላ ትችላለች፤ እንደጭንቀቱ ደረጃ የምግብ ፍላጎትዋ ሊቀንስ ይችላል፡፡  መሰረታዊ የሆነው ጭንቀቱን ያመጣው ምክንያት ምንነት የሚወስነው ይሆናል። እንደዚህ ያለ ነገር የገጠማቸው እርጉዞች እራስን መጠበቅ ሊጠሉ ይችላሉ፤ የህክምና ክትትላቸውን ማድረግ አይፈልጉም፤ ይህ ምግብ ይሻለኛል ብለው አይመርጡም፤ አንዳንዶቹ እንዲያውም መመገብ አይፈልጉም፡፡ ጭንቀቱ የሚመጣበት ምክንያት ደረጃውን የሚወስነው ሲሆን ቤተሰብ እንደዚህ ያሉ ነገሮችን ሲመለከት በቅርብ ሊረዳ ይገባል፡፡
በእርግዝና ላይ የተስተዋለ ጭንቀት በብዙዎች ዘንድ የሚወሳ ሲሆን አንዳንዶችን እናስታውስ፡፡
…….አንዲት በስራ አለም የማውቃት እርጉዝ ሴት ልጅዋን በሰላም ተገላገለች ሲባል አብረዋት የነበሩ ጉዋደኞችዋ…. ተመስገን…. አረ እኛነን የተገላገልነው…. ነበር ያሉት፡፡ እናም መልካም ምኞትን ለመግለጽ ለመጎብኘት የስራ ባልደረቦቿ በአንድ ላይ ወደ ቤትዋ ተጉዋዙ፡፡ በወሬ መካከል በእርግዝናዋ ወቅት ጥሩ እንዳልነበረችና በጣም ትነጫነጭ እንደነበር በተለይ የሚቀርባት ሰው ደፍሮ ተናገረ፡፡ እስዋም በጣም ብዙ ነገሮች ይረብሹኝ ነበር፡፡ በተለይም እከሊት ጸጉርዋን የምትሰራበት ዊግ ሳየው በጣም ነበር የሚረብሸኝ፡፡ አልወደውም ነበር፡፡ በጣም ያበሳጨኝ ነበር አለች፡፡
ጥ፤- እንግዲህ እርጉዝዋ ሴት ከእስዋ ፈቃድና ቁጥጥር ውጭ የሆነው ነገር ሁሉ ሊረብሻት የሚችል ከሆነ እንዴት ልትሸሸው ትችላለች? ልታስወግደው የማትችለው ነገር እንድት ጨነቅ የሚያደርጋት ከሆነ የጭንቀቱ ውጤት ምን ይሆናል፤
ዶ/ር፤- በእርግዝና ላይ ሴቶች አጠቃላይ ውሎ አዳራቸው የተለየ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አንዳንዶች በፍጹም ሰው ከአጠገባቸው እንዲለይ የማይፈልጉ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ሰው ካጠገባቸው እንዲደርስ ላይፈልጉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ከሰዎች ጋር ማህበራዊ ግንኙነትን ለማድረግ ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ እንደ ቡና ከሰዎች ጋር አብሮ መጠጣት የመሳሰሉትን ነገሮች አይፈጽሙም፡፡ ባጠቃላይም ቀደም ሲል ትወደውና ታደርገው የነበረው ልምድ ላይ ፍላጎት አታሳይም። የጭንቀቱ ደረጃ ቀለል ያለ ከሆነ ደግሞ መልኩን ይለውጣል፡፡ ለምሳሌ በማህበራዊ ግንኙነትዋ ከሰዎች ባትሸሽም ግን በቀጣይነት ወይንም በትእግስት ስትጨርሰው አትታይም፡፡ በሰዎች መካከል ሆና በሚደረጉት ጨዋታዎች አለመሳተፍ፤ እራስን መርሳት፤ እራስን መጣል የመሳሰሉ ልምዶች ሊታዩባት ይችላል፡፡
ጥ፡- አንዳድ ጥናቶች ጭንቀትን ከጽንስ ክብደት ማነስ ጋር ያገናኙታል፡፡ ይህ እንዴት ይገለጻል?
ዶ/ር፡- ጭንቀት በእርግዝና ወቅት ካለጊዜው ምጥ እንዲመጣ ወይንም ልጅ እንዲወለድ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል መሆኑን አንዳንድ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ እርግዝናው ከሰላሳ ሰባት ሳምንት ሳይደርስ ምጥ የሚመጣ እና ልጁ እንዲወለድ መንገድ የሚከፍት ከሆነ ኪሎው ብቁ ያልሆነ ልጅን መገላገል ግድ ይሆናል፡፡ ስለዚህም ከክብደት በታች መወለድ የሚባለው አንድ ልጅ አሟልቶ እንዲወለድ የሚገባውን ክብደት ሳያሟላ በዝቅተና ደረጃ፤ በመካከለኛና እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ደረጃ ሊወለዱ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ህጻን ሲወለድ ከ2.5 ኪሎ በታች ካልሆነ ትክክለኛውን ክብደት ይዞአል ማለት ነው፡፡ ከ2.5 ኪሎ በታች ሲሆን ዝቅተኛ የክብደት መጠን ይሆናል፡፡ ከ1.4 ኪሎ በታች ሲሆን ደግም በጣም ዝቅተኛ ክብደት ከሚባለው ደረጃ ይመደባል፡፡ ከአንድ ኪሎ በታች ከሆነ ደግሞ እጅግ በጣም ዝቅተኛ በሚለው ይመደባል፡፡ ክብደታቸው ባነሰ ቁጥር ልጆች ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ በጣም ከባድ ነው፡፡ ለምሳሌ ሰባት ወር ላይ መውለድ ስምንት ወር ላይ ከመውለድ ጋር አይነጻጸርም፡፡ በዘጠኝ ወር መውለድም እንዲሁ የራሱ መስፈርት አለው፡፡ በህክምና እርዳታ የሚያድጉ የመኖራቸውን ያህል ወዲያውኑ ሲወለዱ የሚሞቱም ይኖራሉ፡፡ እንግዲህ እናትየው በእርግዝና ላይ እያለች በሚገጥማት ጭንቀት ምክንያት ከክብደት በታች የሆነ ልጅ መውለድ ከተከሰተ እንደገናም ከተወለደ በሁዋላ በማሳደጉ ረገድ ከባድ ጭንቀት ሊገጥማት ይችላል፡፡ ስለዚህ ጭንቀትን አስቀድሞውኑ ማስወገድ አስፈላጊ ይሆናል፡፡  
ከክብደት በታች ስለሚወለዱ ልጆች የአለም የጤና ድርጅት በ2022 እንዳወጣው መረጃ ከሆነ ትልቁ ትኩረትን የሚሻ የጤና ችግር ነው።
እንደ ዩኒሴፍ (2019) መረጃ በአለም አቀፍ ደረጃ በጠቅላላው ከሚወለዱ ከ15-20% የሚሆኑ ልጆች ከክብደት በታች የሚሆኑ ሲሆን ይህም በየአመቱ ቁጥራቸው ከ20 ሚሊዮን የማያንስ መሆኑን ያሳያል፡፡ በየአመቱ እንደተወለዱ ከሚሞቱ ጨቅላዎች ከ60-80% የሚሆኑት ከክብደት በታች የሚወለዱ ናቸው። እንደ ዩኒሴፍ መረጃ፡፡  
ገቢያቸው በዝቅተኛና በመካከለኛ ደረጃ ያሉ ሀገራት ከ90% በላይ ከክብደት በታች ያሉ ጽንሶች የሚወለዱባቸው ሲሆን ይህም በኤሽያ 72% በአፍሪካ ደግሞ 22% ይሆናል እንደ የአለም የጤና ድርጅት (2004) መረጃ፡፡
እንደ ውጭው አቆጣጠር በ2015 የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው በኢትዮጵያ በየአመቱ ወደ 27.587 ጨቅላዎች ከክብደት በታች በመወለዳቸው የሚያልፉ ሲሆን ከአጠቃላዩ የጨቅላዎች ሞት ውስጥም ወደ 4.5% የሚሆነውን ቁጥር ይይዛል፡፡
ዶ/ር ኢትዮጵያ በስተመጨረሻ እንዳብራሩት እርግዝና ትልቅ የህይወት ለውጥ ነው፡፡ ጽንስ ከተፈጠረ ጀምሮ የእርግዝናውን ጊዜ በሰላም ጨርሶ ከዚያም ተወልዶ እስኪያድግ ድረስ ትልቅ ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው፡፡ ስለዚህ እርግዝና ድንገት መጣ ሳይባል አስቀድሞ አቅዶ፤ ተመካ ክሮ፤ ተዘጋጅቶ፤ ከእርግዝና በፊት ምርመራን አድርጎ እርግዝናውን በጸጋ የመቀበል ሁኔታ ካለ በእርግዝናው ጊዜ ሊከሰቱ የሚችሉትን ነገሮች ሁሉ በክትትል በጊዜ በምክር አገልግሎት አማካኝነት በጸጋ መቀበል ይቻላል፡፡ አንዲት ሴት ልጅ እወልዳለሁ ብላ ስታቅድ ለዘጠኝ ወር ያህል ከአካላዊ ቁመናዋ ጀምሮ ሁለመናዋ ለውጥ የሚኖረው ስለሆነ ይህንን ስትወልደው የምትደሰትበትን ልጅ በጤናማ ሁኔታ ለማሳደግ ለመብቃት አስቀድማ እራስዋን መንከባከብ፤ ከሕክምና ባለሙያዎች አለመራቅ፤ከባለቤትዋ እንዲሁም  ከቤተሰብዋ ጋር በቅርበት በመመካከር የእርግዝና ጊዜዋን ልትጨርስ እና ልጅዋን ልታቅፍ ይገባታል፡፡ ስለ ዚህም ይህንን ከባድ ለውጥ እና የተፈጥሮ ጸጋን በደስታ ለመቀበል ባለትዳሮች በጋራ በመ ሆን ሊዘጋጁበት ይገባል፡፡ 

Read 635 times