Sunday, 06 August 2023 00:00

ፐርፐዝ ብላክ የ2ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን "ከሚሊዮኖች ወደ ቢሊዮኖች" በሚል አከበረ

Written by 
Rate this item
(2 votes)
• ካፒታሉን ከ1 ሚሊዮን ብር ወደ 2 ቢሊዮን . ብር አሳድጓል
• የኩባንያው ቴሌቪዥን ጣቢያ በይፋ ሥርጭት ጀምሯል
ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ፣ የተመሰረተበትን የ2ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን፣ "ከሚሊዮኖች ወደ ቢሊዮኖች - ቃል በተግባር" በሚል ዛሬ ተሲያት ከ8 ሰዓት ተኩል ጀምሮ፣ በተለያዩ ዝግጅቶች በሚሊኒየም አዳራሽ አክብሯል፡፡
በ1 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሰረተው ኩባንያው፤ በ2 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ካፒታሉን ወደ 2 ቢሊዮን ብር ማሳደግ መቻሉን የፐርፐዝ ብላክ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ፍስሃ እሸቱ በክብረ በዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር አስታውቀዋል፡፡
“ከገበሬው ቲቪ” (ኬቲቪ) የተሰኘው የኩባንያው ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ በዛሬው ዕለት የሙከራ ሥርጭቱን በይፋ እንደጀመረ ያበሰሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ጣቢያው ትኩረቱን በግብርናና ኢኮኖሚ ላይ አድርጎ ለ24 ሰዓት እንደሚሰራጭም ጠቁመዋል፡፡
እስካሁን በ10ሺ የሚሰሉ አርሶአደሮችና ሌሎች ኢትዮጵያውያን፣ የፐርፐዝብላክ ባለአክሲዮኖች መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ ኩባንያው ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል ምርቶችን በቀጥታ ከገበሬው በማምጣት፣ለተጠቃሚው ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ሲያከፋፍል ቆይቷል፡፡
ፐርፐዝብላክ፣ በከተማዋ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የመኖርያ ቤት ችግር ለማቅለል በማለምም፣ በቅርቡ ፊቱን ወደ ሪልእስቴት ግንባታ ያዞረ ሲሆን፤ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ መኖሪያ ቤት የሚያገኙበት ፕሮጀክት እንደሆነም ተነግሯል፡፡
የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም፣ የዩኒቲ ኮሌጅ መሥራችና ባለቤት በነበሩት ዶ/ር ፍስሃ እሸቱ፣ጠንሳሽነት የተቋቋመው ብላክፐርፐዝ ኢትዮጵያ፤ የጥቁርን ህዝብ የኢኮኖሚ የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በሥራ ለማዋል እየተጋ የሚገኝ ኩባንያ ሲሆን፤ በቅርቡ አዲስ ሁለገብ የበይነመረብ መገበያያ መድረክ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
Read 964 times