Saturday, 19 August 2023 20:00

የማይሰለቸኝ ዘመዴ ድንጋዩ ነበር፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እ.ኢ.አ በ2023 31ኛውን አመታዊ ጉባኤ ማካሄዱ ይታወሳል፡፡ ማህሩ በየአመቱ ጉባኤውን ሲያካሂድ በማህጸንና ጽንስ ህክምና ዙሪያ በጎ አስተዋጽኦ ላበረከቱና ረዥም አመት ላገለገሉ ሽልማትን ያበረክታል፡፡ ከዘንድሮዎቹ ተሸላሚዎች መካከል ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል አንዱዋ ነበሩ፡፡
ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል የጽንስ ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና በተለይም በፊስቱላ ህክምና ከሀያ አምስት አመታት በላይ ያገለገሉ እና ዛሬም በቀዶ ሕክምናው ስራ በተጠሩበት ሁሉ እየሄዱ አገልግሎት የሚሰጡ አንጋፋ እና የተከበሩ ባለሙያ ናቸው፡፡
ፊስቱላ በወሊድ ጊዜ በሚደርስ የምጥ መራዘም ምክንያት በሴቶች ላይ ሊከሰት የሚችል በማህጸንና በአካባቢው የሚከሰት የሰውነት መቀደድ የጤና ችግር ነው፡፡ በእርግጥ በሌላም የውስጥ አካል የሚደርስ መቀደድ ካለ እና ከሌላ ሰውነት ጋር መገናኘት ከአጋጠመ ይህም ፊስቱላ ይባላል፡፡ ነገር ግን የተለመደው በተለይም ወጣት ሴቶች ላይ የሚከሰተው ሲሆን ይህም የተለየ ትኩረትን የሚሻ ሆኖ ቆይቶአል፡፡
በአገራችን በተለይም በአዲስ አበባ ሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል የተቋቋመበት እና ይህም ችግሩን ለመፍታት አቅሙ ውስን እንዳይሆን በሚል በተወሰኑ ክልሎች ባሉ ሆስፒታሎች ስራው በመሰራት ላይ መሆኑም እሙን ነው፡፡
ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል ከፊስቱላ ጋር በተያያዘ Hope of light የተሰኘ አገር አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅት አቋቁመዋል፡፡ ባጠቃላይም የፌስቱላን ስራ በሚመለከት በዘርፉ ለረጅም አመታት አገልግሎት የሰጡ አንጋፋ ባለሙያ በመሆናቸው ያለፉባቸውን ትውስታዎች እንዲያጋሩን እና የተሸላሚነታቸውን ምክንያት እንዲያብራሩልን የአምዱ እንግዳ አድርገን ጋብዘናቸዋል፡፡
የዶ/ር አምባዬን ማብራሪያ ከማቅረባችን በፊት ግን ከአሁን በፊት የፊስቱላ ህክምና አገል ግሎት በሚሰጥባቸው በተለያዩ ሆስፒታሎች ያነጋገርናቸው ታካሚዎች የሰጡንን ሀሳብ ቀንጨብ ቀንጨብ እያደረግን እናስነብባችሁ፡፡
‹‹…..ታካሚዋ እራስዋ እንደነገረችኝ እድሜዋ 17 አመት ነው፡፡ ቀይ፤ጸጉርዋ እጅግ ጥቁር እና ዞማ፤ የምታ ምር ልጅ ናት፡፡ አይንዋ ከብለል ከብለል ሲል ያሳዝናል፡፡ ላነጋግራት ጠጋ ስል አ..አ..ይ.. አትጠጊኝ አለችኝ፡፡ ለምን አልኩአት፡፡ አይሄይሄ….አሁን ታከሚ ብለው ከሰው ቀላቀሉኝ እንጂ እኔስ ድንጋይ ነበር ዘመዴ አለች፡፡ ምን ማለት ነው የሚል ጥያቄ አነሳሁ፡፡ ያው ቤተሰብ ከገፋኝ ቆየሁ። በምወልድበት ጊዜ እንዲሁ ሽንቴን መቆጣጠር ስላቃተኝ…በቃ… ባለቤቴም ወዲያውኑ ወደቤተሰቤ መለሰኝ፡፡ በቤተሰቤም ከሰውም እንዳልቀላቀል ተደረግሁ… በቃ…. ጠዋት ከእንቅልፌ ተነስቼ ወጥቼ ከጉዋሮ ካለችው ድንጋይ ላይ ቁጭ እላለሁ፡፡ ድንጋይዋ ብቻ አትሰለቸኝም፡፡ ሽንት ሲበዛባት ውሀ እያመጣሁ አጥባታለሁ፡፡ ፀሐይ እስኪያደርቃት ጠብቄ ከእስዋው  ላይ ተቀምጬ በሽንቴ ሳበሰብሳት እውላለሁ፡፡ ማታ ለጠዋት ውሀ አደርግባታለሁ፡፡ ለራሴ ስል ነው፡፡ ቤተሰቦቼም እናቴ ወይንም እህቶቼ ምግቤን ከደጃ ፋቸው ያስቀምጡና ይጣራሉ፡፡ እኔ ሰማሁም አልሰማሁም ሳያረጋግጡ ወደቤት ይገባሉ። እኔ ግን ስለሚርበኝ ያንን ጥሪ ጠዋትም፤ በሰአትም እጠብቀዋለሁ። አመሻሹ ላይ ደግሞ ከማድርበት ከከብቶቹ ቤት አጠገብ ያስቀምጡልኛል፡፡ ተነስቼ እበላለሁ፡፡ በቃ። እናቴ ብዙ ጊዜ የለችም ትባላለች። የእኔን በሽታ ለማዳን በየአዋቂው ቤት ትሄዳለች። እስዋ ተለክፋ ነው…ሰይጣን ይዞአት ነው ብላ ነው የምታምነው። ቅጠላ ቅጠሉን ፤ስራ ስሩን ይዛ ትመጣለች፡፡ እኔ ግን ምንም ለውጥ አላመጣም፡፡ እናቴ ብቻ ነበረች ሁኔ ታዬን በቅርብ የምትከታተል። እግዚሐር እኮ እኔን ተቆጥቶኝ ነው …እሱዋማ ምን አደረገች…ህጻን ነች….ትላለች፡፡ እንግዲህ አሁን ከሆነልኝ ወደሐኪም በመከራ ደርሻለሁ፡፡ እግዚአብሔር ከረዳኝ እጠብቃለሁ፡፡ ነበር ያለችው፡፡ ይህችን ታማሚ ከሶስት ወር በሁዋላ ጎብኝተናት ነበር፡፡ በጣም በተሸለ ሁኔታ ላይ ድና ነበር ያገኘ ናት፡፡ በጣም ደስ የሚል ለውጥ ነበር፡፡
አሁን የዶ/ር አምባዬን ማብራሪያ እናስከትል። ዶ/ር አምባዬ ወ/ሚካኤል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና በፊስቱላ እስፔሻላይዝድ ያደረጉ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ፊስቱላ የሚባለው የጤና ችግር በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት ሲሆን በእኛ ሀገር ግን ወደ 95% የሚሆነው በምጥ መራዘም ምክንያት የሚከሰት ነው፡፡ በዚህ ስራ ወደ ሀያ አምስት አመት ያገለገልኩ ሲሆን መጀመሪያ በአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል ከዚያ በሁዋላ ደግሞ women & health alliance በሚባለው አለም አቀፍ ድርጅት በፊስቱላ የተጠቁ ሴቶችን ባሉበት ማለትም በየገጠሩ የማከም ስራ ላይ ተሰማርቼ ነበር፡፡ ያ ድርጅት ፕሮጀክቱን ሲዘጋ እኔ በስራው ማለትም  በፊስቱላ የተጎዱትን የማገልገል ስራዬን ለመቀጠል ስል ይህንን አገር አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት Hope of light በሚል ስያሜ አቋቁሜ በመስራት ላይ እገኛለሁ፡፡ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በየአመቱ ለህብረተሰቡ ጠቃሚ አገልግሎት ላበረከቱ የሚሰጠውን ሽልማት የመቀበሌም ምክንያት ይህ አገልግሎቴ ነው ብለዋል፡፡
የፌስቱላ ሕክምናን የሚሰራ ባለሙያ ስራውን በተጉዋዳኝ ነው የሚሰራው፡፡ ባለሙያው የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ሆኖ በተጨማሪነት የፊስቱላ ቀዶ ሕክምናንም ይሰራል፡፡ የፊስቱላን ሕክምና በሚመለከት ሙሉ በሙሉ ስራዬ ብለን የምንሰራው ሐኪሞች በጣም ጥቂት ነበርን ማለት ይቻላል፡፡ እኔ እንደተመረቅሁ በፊስቱላ ሐኪም ቤት በመመደቤ እና ህክምናው እጅግ በጣም አስፈላጊ፤የብዙ ሴቶችን ሕይወት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ሌላ አማራጭ የማይታይበት በመሆኑ እራሴን አሳምኜ ሙሉ በሙሉ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሳላይ እነዚያን ሴቶች የማከም ስራዬን ተያያዝኩት። በዚህም ምን ያክል ሴቶችን እንደአ ከምኩ ጊዜው እንዲሁም ቤቱ ይቁጠረው ብለዋል ዶ/ር አምባዬ፡፡
የፊስቱላ ታካሚ ሴቶች ወደ ህክምናው በሚመጡበት ጊዜ በምን አይነት አቋምና ጉዳት ሲሰቃዩ እንደነበር ምንም ምስክር ሰያሻውም፡፡ ሲታዩ ያስታውቃሉ፡፡ አንድ ሰው ሐኪም ብቻ ስለሆነ ሳይሆን ሰው በመሆኑ ብቻ እነዚህን ሴቶች ለማዳን ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ እንደሚገባው ምንም አያጠራጥርም፡፡ ስለዚህ ይህ ህክምና በሐምሊን ፊስቱላ ባሉ ውስን ሐኪሞች ብቻ ተሰርቶ የሚያልቅ እንዳልሆነ ግልጽ ነበር፡፡ ስለዚህ ሌሎች የጽንስና ማህጸን ሐኪሞችንም በፊስቱላ ቀዶ ሕክምና ዙሪያ ስልጠና መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት የስልጠና ስራው እንዲቀጥል ተደረገ፡፡ ስለዚህም በጊዜው የነበርነው አራት ሐኪሞች ስራውን ከመስራት በተጨማሪ ሌሎች ሐኪሞችንም ማሰልጠኑን ተያያዝነው፡፡ ከጠቅላላ ሐኪምነት ወደ ጽንስ እና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትነት ደረጃቸውን ከፍ የሚያደርጉ ሁሉ በአዲስ አበባ ሐምሊን ፊስቱላ ሐኪም ቤት እየመጡ ስልጠናውን እንዲወስዱ በመደረጉ እነዚያ ሐኪሞች በሚመደቡበት ሆስፒታል ችግሩ ሲያጋጥማቸው የቻሉትን እየሰሩ ያልቻሉትን ደግሞ ወደ ሐምሊን ይልኩ ነበር በሚል ዶ/ር አምባዬ ትውስታቸውን አጋርተውናል፡፡
የፌስቱላ ስራ አድካሚና ለጥቅም ወይንም ለትርፍ የሚሰራ ስራ አይደለም፡፡ የነጻ አገልግሎ ነው። ነገር ግን ይህንን ስራ መስራት ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ የውስጥ ደስታን ይሰጣል፡፡ አንዲት ሴት ታክማ፤ ድና እና ከነበረችበት የተሳቀቀ፤ ከሞቱት በላይ ከቆሙት በታች እንደሚ ባለው አይነት ሕይወት በመላቀቅዋ ከሆስፒታሉ ስትሸኝ የሚሰማት ደስታ ሲታይ አገልግ ሎቱን ለሰጡ ባለሙያዎች የሚሰጠውን እርካታ መግለጽ አይቻልም፡፡ ስለዚህ የፌስቱላ ህክምና ዋጋው ወይንም ክፍያው ህይወትን ማዳን፤ አንዲትን ሴት ያጣችውን ህይወት መልሶ መስጠት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል መጥተው የሚታከሙት እነማን ናቸው? ሌሎች መምጣት ያልቻሉ በየአካባያቸው አይኖሩምን? የሚለው ዶ/ር አምባዬን ጥርጣሬ ላይ የጣለ ሌላው የፌስቱላ ህክምና አገልግሎት ፍተሻ መንገድ ነበር፡፡ የፌስቱላ ታማሚዎቹ በየገጠሩ ብዙ እንደሚኖሩና ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ግን አቅሙም ፤የሚረዳቸው አካልም እደማይ ኖራቸው እና መታከም እንደሚችሉ እውቀቱም እንደማይኖራቸው መጠርጠር ግድ ነበር፡፡ እዚህ ላይ በትግራይ ፊስቱል ህክምና ላይ ያገኘናቸው ሴት ያሉትን ልናስታውስ እንወዳለን፡፡
‹‹….እኔስ ድኜ…ከቤተ ክርስቲያን ሄጄ…በሞትኩ…አሉ ፡፡ ለምንድነው አልኩ ዋቸው፡፡ እኔ ዛሬ ትልቅ ሴት ነኝ በእድሜዬ ወደ ስድሳው ተጠግቻለሁ። የሁለት ልጆች እናት ነኝ፡፡ በሶስተኛው ልጅ ነው እንዲህ የሆንኩት፡፡ ላለፉት ሰላሳ አመታት ሰው አልቀብር….እድር አልሄድ…ቤተክርስቲያን አልሄድ…ባለሁበት የፈታኝ ባሌ ሌላ ሚስት ቢያገባም ….እግዜር ይስጠውና ከአጥር ጥግ ኩቺና መሰል ሰርቶ ከዋናው ቤት ብቻ አወጣኝ፡፡ ባለሁባት ኩቺና ምግብ ሰርቼ …ቡናዬን አፍልቼ ልጆቼን እያየሁ ለእራሴ እመገባለሁ እንጂ አጠገቤ አይደርሱም። ብቻ እግዜር አልጨከነብኝም፡፡ ልጆቼ ሁሌ ይጠይቁኛል፡፡ የባለቤቴ ሚስትም ቡናው ንም ምግቡንም ትሰነዝራለች፡፡አትጨክንም፡፡ደግ ናት፡፡ አሁን ከዚህ ያመጡኝም እነዚህ በየሰ ፈሩ የሚጎበኙ ሐኪሞች ናቸው፡፡ ካለዚያማ ከዚህ በሁዋላ ምን ያህል ልኖር? እንዲያው እን ደተበላሸሁ መሞቴ ነበር፡፡  እኔ አሁን ምንም አልፈልግ፡፡ እን ዲያው…. ድኜ ….እንደሰው ቤተክርስቲያን ሄጄ ከአንድ ገዳም ገብቼ ከሰው በተቀላቀልኩ፡፡ …ይህንን በጎ ስራ ለሚሰሩም ጸሎት እና ክፉ እንዳይነካቸው…እንደእኔ ለተበላሹ መድህን እንዲሆኑ ፈጣሪ እድሜና ጤና እንዲሰጣቸው በለመንኩ ›› ነበር ያሉት…››፡፡ በቀጣይ እትም እንመለስበ ታለን፡፡

Read 561 times