Saturday, 26 August 2023 19:58

ሲልከን ቫሊ ኮሌጅ ከ350 በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
ሲልከን ቫሊ ኮሌጅ ከ350 በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ
• በላቀ ውጤት ለተመረቁ ተማሪዎች፣ ነጻ የትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸዋል
• በዋንጫና ሜዳልያ የተንበሸበሸችው ተመራቂ፣ በዛሬው ዕለት ጋብቻዋን ፈጽማለች
ሲልከን ቫሊ ኮሌጅ፤ በማስተርስ ድግሪና በመጀመሪያ ድግሪ ደረጃ እንዲሁም በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ዘርፎች፣ በቀንና በማታው መርሃግብር፣ ከ350 በላይ ተማሪዎችን ዛሬ ጠዋት በሃገር ፍቅር ቴአትር አዳራሽ አስመርቋል፡፡
ከተመራቂዎቹ መካከል 49 በመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸው ተነግሯል፡፡
የምርቃት ሥነሥርዓቱን በም/ጠቅላይ ሚኒስትርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የጽ/ቤት ሃላፊ ረ/ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን የቦርድ አባልና የዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር መሳይ ገ/ማርያም እንዲሁም በተመድ የፋኦ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶ/ር ተፈራ ዳርጌ በክብር እንግድነት ታድመውታል፡፡
ለተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሲልከን ቫሊ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ቴዎድሮስ አበበ፣ ባደረጉት ንግግር፤ ኮሌጁ በማስተርስ ድግሪ ደረጃ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን፤ በመጀመሪያ ድግሪ ደረጃ በአካውንቲንግና ፋይናንስ፤ በማኔጅመንትና በ7 የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና መስኮች ከሚመለከተው የመንግስት አካል ሙሉ ዕውቅና ማግኘቱን ጠቁመዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዶች፣ ከየትምህርት ዘርፉ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የሠርተፊኬት፣ የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማቶችን አበርክተዋል፡፡
ኮሌጁ ባለፉት ዓመታት ከፍለው መማር ላልቻሉ ዜጎች የነጻ ትምህርት ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ያስታወሱት የኮሌጁ ዲን፤ በዛሬው ዕለት በላቀ ማዕረግ ለተመረቁ ተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል በማስተርስ ድግሪ ደረጃና የሥራ ዕድል እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡
በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ሜዳልያና ዋንጫን ጨምሮ በሁሉም ሽልማቶች የተንበሸበሸችው የማርኬቲንግ ትምህርት ክፍል ተመራቂዋ ናዝራዊት መስፍን እሸቱ፣ በዛሬው ዕለት የጋብቻ ሥነስርዓቷን የፈጸመች ሲሆን፤ ሽልማቶቿን በተወካይዋ በኩል ወስዳለች፡፡
በም/ጠቅላይ ሚኒስትርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የጽ/ቤት ሃላፊና የዕለቱ የክብር እንግዳ፣ ረ/ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ባደረጉት ንግግር፤ “እንደ ሴት ልጅ አባትነቴ ብዙ ሴት የማስተርስ ድግሪ ተመራቂዎች በማየቴ ደስ ብሎኛል፤” ብለዋል፡፡
አክለውም ፤“ዛሬ የተመረቃችሁ ሴቶች፣ የዛሬ 5 ዓመት በሦስት ዓመት ውስጥ ሁለት የማስተርስ ድግሪዋን የሰራችውን እናቴን አስታውሳችሁኛል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“እየተማራችሁ በሄዳችሁ ቁጥር ከሰፈርና ከመንደር አስተሳሰብ ወጥታችሁ የበለጠ አገራችሁን የምታገለግሉ መሆን አለባችሁ” ያሉት ረ/ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ፤ “ሲሆን ሲሆን ኢትዮጵያን በዓለም ዙሪያ የምታስተዋውቁ ለመሆን ያብቃችሁ፡፡” ሲሉ የዕለቱን ተመራቂዎች መርቀዋል፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
 
Read 1845 times