እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጦሰኛው ዓመት ከእነጦሱም ይሁን ጦሱን አራግፎ ባይታወቅም ሊወጣ ዳር፣ ዳር እያለ ነው፡፡ ‘ሂሳብ ሊወራረድላቸው የሚገቡ ነገሮችን ሂሳብ የማናወራርድሳ!
ስሙኝማ… ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…አንድ የታክሲ ላይ ጥቅስ ምን ትላለች መሰላችሁ… “ከሩቅ ጮማ የቅርብ ቆሎ ይሻላል…” አሪፍ ነች፣ አይደል! ግን ምን መሰላችሁ ይቺ ጥቅስ ‘አፕግሬድ’ መደረግ አለባት፡፡ አሀ… የዘንድሮ የቆሎን ዋጋ እያወቁ እንዲች አይነት ጥቅስ… አለ አይደል…እንደ ቀሺም የሳይንስ ፊክሽን ‘ሾርት ስቶሪ’ ነገር ልትታይ ትችላለቻ!
አንድ እፍኝ ቆሎ ቁርጥም ያደርግና
አንድ ጣሳ ውሀ ግጥም ያደርግና
ተመስገን ይለዋል ኑሮ ተባለና፣
የምትለዋ ስንኝም ‘ኤዲት’ ትደረግልን፡፡ ልክ ነዋ…“አንድ እፍኝ ቆሎ…” የምትለዋ ከዘመኑ ጋር ስለማትገጥም ወይ ትተካ፣ ወይ በ‘ክፍት ቦታነት’ ትታለፍልን፡፡ ውሃም ቢሆን ልጄ ስቶሪው ተቀይሯል፡፡ ሬስቱራንት፣ ምግብ ቤት ገብታችሁ ምግብ ከቀረበ በኋላ “የሚጠጣ ምን ይምጣ!” ስትባሉ…አለ አይደል… ከቧንቧ ስጪኝ ለማለት፣ “አንድ ብርጭቆ የእግዜር ውሀ ትላላችሁ፡፡ ምን መልስ ቢሰጣችሁ ጥሩ ነው፣ “የታሸገ ውሀ ብቻ ነው ያለው፡፡” እናማ…“አንድ ጣሳ ውሀ…” የሚለውም ይስተካከልን፡፡
ታዲያላችሁ፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ዓመቱ ጥርግ ብሎ ሲወጣ…አለ አይደል… ከተቻለ አንዳንድ ነገሮች ላይ የሂሳብ ማወራራድ ነገር ቢኖር፡፡
የጉልበተኝነት ሂሳብ ይወራረድልን፡፡ የምር እኮ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…በፊት እኮ “በእንትን ሰፈር እንዳታልፉ፡፡ እዛ ያሉ ጎረምሶች የለየላቸው ጉልቤዎች ናቸው፡፡”
“ምን እንዳያመጡ ነው!”
“በል በዛ አልፋለሁ ብለህ ሞክራቸው፡፡ አስራ ምናምን ቲዝህን አሳቅፈውህ ነው የሚልኩህ!” ወይ ደግሞ “ስማ ፒያሳ የምን ግርግር ነው አለ የሚሉት?”
“እባክህ ቻይና ግሩፖች መጥተው ፒያሳን በአናቷ ነው ያቆሟት!”
ታዲያላችሁ…ጉልቤዎች ይታወቁ ነበር። አሁን እኮ ግራ ግብት ያለው በየቀኑ አዳዲስ ጉልቤዎች እየተፈለፈሉብን ነው ግራ የገባን። ደግሞላችሁ… እኮ የጉልቤዎች ብቻ ሳይሆን የጉልቤነቱ አይነት መብዛት፡፡ በፊት ኤኮ ኮሌታን ጨምድዶ ይዞ “እንትንህን አውጥቼልህ አንገትህ ላይ እንደከረባት እንዳላሰርልህ!” አይነት ጉልቤነት ነበር፡፡ (ስሙኝማ… ይሄ ነገር ትንሽ ሂዩማኒቲ ምናምን አለው እንዴ! አሀ…እንትን ያለውን ነገር አውጥቶ እኮ… አለ አይዶል… “የውሻና የድመት ቀለብ አደርገዋለሁ!” አላለም፣ እንደከረባት አንጠለጥልሀለሁ እንጂ! ማን ያውቃል ‘እኛ የዋሆቹ እኮ… “አጅሬው ዛሬ የዘመኑ ፋሽን ከረባት አድርጎ ነው እንዴ የመጣው፣” ልንል እንችላለን፡፡
“ያ እንትና የሚሉት ቦዲቢልደር ሰፈራችንን አመሰው እኮ! ፍራንካችንን ተነጥቀን፡ ገርልዬዎቻችንን ተነጥቀን ለእሱ ብለን ሀገር ጥለን መሄድ አለብን እንዴ!” ምናምን እንባባል ነበር፡፡ ለአፋችን ነው እንጂ ለእሱ ብለን አገር ጥለን አንሄድም ነበር፡፡ ዘንድሮ ነው እንጂ “ሀገር ጥላችሁ ጥፉ፣ ጥፉ!” የሚያሰኙ ጉልቤዎች የበዙብን፡፡ አሀ…ኮሚክ ነገር እኮ ነው! አንዳንዶች እኮ “በጉልቤነት የሥራ መስክ ደረጃ ሀሌታው ሀ የንግድ ፈቃድ ያወጡ ነው የሚመስሉት፡፡ አሀ… የሆነ ‘የንግድም ሆነ የግንድ’ ፈቃድ ሲኖር ነዋ ያለከልካይ እንደ ልብ ጉልቤ መሆን የሚቻለው!
እናላችሁ…የዘንድሮ ጉልቤነት ነገር…አለ አይደል… “ማን አለኝ ከልካይ!” አይነት ነገር የሆነ አይመስላችሁም! እናማ… የ‘ቦስ’ ጉልቤ አለላችሁ፡፡ ከ‘ቦስ’ ከቦስ ጉልቤማ ይሰውራችሁ። ልክ ነዋ… በተለይም ከፍሬሽና የወንበሩ ላስቲክ ገና ሳይለቅ ናቡከደናጾር ምናምን ሊሆንባችሁ ከሚሞክርና በባዶ ስታዲየም ‘ቦስ’ ነኝ ብሎ ከሚያስብ ጉልቤ ይሰውራችሁ፡፡
እናማ… የጉልቤነት ሂሳብ ይወራረድልንማ!
ከህግ ማስከበር ጉልቤ፣ ከሆነ የደንብ ልብሽ ለባስ ጉልቤ፣ ከድጋፍ ሰጪ ምናምን ጉልቤ፣ ከጥበቃ ጉልቤ፣ ከተራ አስከባሪ ጉልቤ፣ ከታክሲ ረዳት ጉልቤና አዛዥ ናዛዥ የሌላቸው ከሚመስሉ ጉልቤዎች ይሰውራችሁማ! (ስሙኝማ… ይቺ በቋሚ፣ በወጣ ገባ፣ በ“ፉርሽ ባትሉኝ፣” በተለዋዋጭና በተገለባባጭ (ቂ…ቂ…ቂ…) ቦተሊከኞች አካባቢ በ‘ኢንተርቪው’ መሀል፣ በ‘ስፒች’ መሀል፣ በአክቲቪስቶች ቦተሊካዊ ትንተና መሀል (‘ትንተና’ የሚለው ‘ብተና’ ከሚለው ቀድሞ እንደመንደርደሪያ የሚመጣ ቃል የሚመስለኝ ነገርዬው እንዴት ነው!) ጣል የምትደረግ የጉልቤነት ቃልና ሀረግን ተዉንማ! እንዴ የሆነ ለአንድ ዕቁብ እንኳን የምትበዛ መድረክ ላይ የወጣን ሁሉ፣ የተሻለ ሰው ስለጠፋም ይሁን በ“አምቻ ምናምን…” (ቂ…ቂ…ቂ…) ማይክ ፊት የቀረብን ሁሉ ጉልቤነት እየቃጣን የጉልቤነት ‘ዩኒክ’ ትርጉም እየተዛበ ስለሆነ ዲክሽነሪ የምታዘጋጁ አንድ በሉንማ!
እናማ…የጉልቤነት ሂሳብ ይወራረድልንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እናላችሁ ቤት ውስጥ አባት፣ እናት፣ ልጆችና የእንጀራ ልጆች አሉ እንበል፡፡ እናማ…ስለ አንዳንድ ክፉ የእንጀራ እናቶች በታሪክም በተረትም የምንሰማቸው፣ ሁላችንም ባንሆን አጋጣሚው ደርሶን ክፉ የሚባሉ እንጀራ እናቶችን ድርጊቶች ‘ላይቭ’ ያየን…አለ አይደል…“ማን ተፈላስፎ ማን ይቀራል!” አይነት ነገር ሽው ይልብናል፡፡ እናም… “እንጀራ እናት የሚለው ስም ውስጥ ካልጠፋ ቃል እንጀራ የሚለው ቃል ለምን ገባ!” ብንል እኮ አይፈረደብንም፡፡ አሀ… የእንጀራ ልጁ “ሽቅብ፣ ሽቅብ” ሳይል ሊበላ የሚችል እንጀራ የማግኘት ዕድሉ ‘ኖንቼ!’ ነዋ!
እናማ… የእንጀራ እናት ልጆች ሸሮ በቅቤያቸውን ግጥም አድርገው፣ ለእንጀራ ልጅ እሳቸው ሠራተኛቸውን “ስሚ የበቀደሙ ምስር ወጥ አልቋል እንዴ?” ይሏታል፡፡
“እትዬ፣ ሳምንት አልፎታል እኮ!”
“ቱሪናፋ! እሱን ማን ንገሪኝ አለሽ? አልቋል ወይ ነው ያልኩሽ፡፡”
“ድስቱን የጠራረጉባትን ትንሽዬ እንጀራ ለድርቆሽ ትሆናለች ብዬ አስቀምጫታለሁ፡፡”
“በይ እሱን ምሳውን ስጪው፡፡”
“እትዬ ሳምንቱን ሙሉ እኮ እንዲሁ ክፍቱን ነው የከረመው!”
“አይ እንግዲህ ሰይጣኔናን አታምጪው! ስጪው አልኩሽ ስጪው!”
(እግረ መንገዴን የሆነ ነገር ትዝ ብሎኝ ነው… የሆነ ነገር ባልን ቁጥር ፊት ለፊት አፍ አውጥታችሁም ባይሆን እንዲሁ በ‘ሾርኒ’ “ሰይጣኔን አታምጡብኝ!” አይነት ምልክቶችን የምታሳዩን ሰዎች እንዴት ነው ነገሩ! አሀ…እንኳን ሰይጣኖቻችሁ ተጨምረው እናንተ ከአቅማችን በላይ ሆናችሁብናል እኮ!)
እናማ…በየቦታው፣ በየአገልግሎት መስጫው፣ በየምናምኑ ትንፋሻችንን እያሳጠሩት ያሉት የልጅና የእንጀራ ልጅ አይነት ነገሮች ሂሳብ ይወራረድልናማ!
ደግሞላችሁ እኮ ያው መቼም የራስ ልጆችም ባይወልዱትም ሊያሳድጉት የወሰዱት የእንጀራ ልጅም አንድ አይደሉም እንዴ! “የመንደራችን ሰዎች…” የሚባሉትን አይነቶች እንሁን፣ ፈልሰውም ይሁን እንጀራ ፍለጋም ይሁን “ከማዶ የመጡ ናቸው…” የሚባሉትን አይነቶች እንሁን፤ ያው ሁሉም ዜጋ እኩል ዜጋ አይደለም እንዴ! የምር እኮ “ከልጅ ልጅ ቢለዩ ዓመትም አይቆዩ!” የምትል አባባል አለች፡፡ ስለመብት ነው እያወራን ያለነው፡፡ እንደ ዜግነታችን ማግኘት የሚገቡንን አገልግሎቶች ‘ዲስክሪሚኔሽን’ ሳይደረግብን ተገቢውን አገልግሎት ማቅረብ ያለባቸው ክፍሎች እዛ ማዶና እዚህ ማዶ ሆነው ሳይጠቃቀሱብንና ሳይጠራሩብን ሊያገለግሉን ይገባል ስንል ስለ መብታችን ነው እያወራን ያለነው፡፡ (ስሙኝማ… “ዊ አር ታክሰ ፔየርስ!” ብዬ በፈረንጅ አፍ ልደሰኩር ዳዳኝና ዝም አልኩላችሁ፡፡ አሀ…በአንድ ወቅት የሆነ መሥሪያ ቤት አንድ በአገልግሎት አሰጣጥ የተበሳጩ ሰው (‘አምልጧቸው’ ሳይሆን አይቀርም) “አይ አም ኤ ታክስ ፔየር!” ሲሉ ተሳቀባቸው የተባለውን ነገር በቀላሉ አንረሳማ!)
የምር ግን…አለ አይደል… አሁን አሁን እኮ አንዳንድ ቦታዎች ፍጥጥ ያለ ‘ዲስክሪሚኔሽን’ ነው የምታዩት፡፡ ‘ፌይር’ አይደለማ! አገልግሎት ያለመድልዎ ለማግኘት የግድ “የእኛ ሰው…የእነኛዎቹ ሰው” አይነት የቡድንና የቡድን አባቶች ድልድል ውስጥ መካተት አለብን እንዴ! አሀ… “የእኛ ሀገር ልጅ፣” “አበ ልጃችን፣” “የቦተሊካ አጣጪያችን፣” ምናምነን መባባል አለብን እንዴ!
እናማ… የልጅና የእንጀራ ልጅ አይነት አገልግሎት አሰጣጥ ሂሳብ ይወራረድልንማ!
ብዙ በጣም ብዙ እንዲወራረዱልን የምንፈልጋቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ዝርዝሩ የሚያበዛ ሳይሆን የሚያሳንሰውን ተአምር ያውርድልንማ! ሁሉንም ነገር ለእሱ የሰጠ፣ የመጨረሻውንም መፍትሄ ከእሱ የሚጠብቅ ህዝባችን ብዙ፣ እጅግ ብዙ ነውና!
ደህና ሰንብቱልኝማ!
Sunday, 27 August 2023 19:41
ሂሳብ ይወራረድልንማ!
Written by ኤፍሬም እንዳለ
Published in
ባህል