Saturday, 02 September 2023 00:00

የኑሮ ውድነቱን ያባባሰው የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

 - በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ በነዳጅ ዋጋ ላይ 55 በመቶ ጭማሪ ተደርጓል
          - የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በኑሮ ውድነቱ ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ ነው ተብሏል
          - በየእለቱ 2.5 ሚሊ. ሊትር ቤንዚንና 8 ሚሊ. ሊትር ናፍጣ ጥቅም ላይ ይውላል
            
       የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ በነዳጅ ምርቶች ላይ ከነሐሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ቢኒዚን በሊትር 74.85 ናፍጣ 76.34 እንዲሁም ኬሮሲን 76.34 ሳቲም እንዲሸጡ የችርቻሮ ዋጋ አውጥቷል፡፡ ይህም የነዳጅ ዋጋ ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ከነበረበት 47 ብር 83 ከሳንቲም፣  የ27 ብር ጭማሪ ማሳየቱን ያመለክታል፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ምክንያቱ፣ ከሐምሌ ወር ጀምሮ የአለም የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየቱ እንደሆነ አመልክቷል፡፡
በአገሪቱ ለነዳጅ ሲደረግ የነበረውን ድጎማ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው ተከታታይ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት ማስቀጠል ባለመቻሉ፣ ድጎማውን ቀስ በቀስና  በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችን በማይጎዳ ሁኔታ ለማስቀረት እንደሚሰራ ከአንድ ዓመት በፊት ገልፆ የነበረው የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር፤ የነዳጅ ድጎማውን በየሶስት ወሩ ሲያነሳ ቆይቷል፡፡
በአገሪቱ ባለፉት ወራት ጭማሪው ያለማቋረጥ የቀጠለ ሲሆን፤ ካለፈው አመት ሐምሌ ወር ጀምሮ እስከ አሁኑ ጭማሪ ድረስ በቤንዚን፣ ነጭ ናፍጣ እና ኬሮሲን ላይ የ55 በመቶ ጭማሪ ተደርጓል፡፡
ጭማሪው የአለም የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን መሰረት በማድረግ የሚቀጥል እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ይህ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ የሚታየውን የኑሮ ውድነት ይበልጥ የሚያባብስ እንደሆነ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በአገሪቱ የተከሰተው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ዘላቂ መፍትሄ ባላገኘበት ሁኔታ በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚደረገው የዋጋ ጭማሪ በእሳት ላይ ቤንዝን እንደማርከፍከፍ ይቆጠራል ያሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ቴዎድሮስ ተመስገን፤ መንግስት ሁኔታውን ቆም ብሎ ሊያስብበትና አካሄዱን ሊያስተካክል ይገባል ብለዋል፡፡
አገሪቱ አሁን ያለችበት አዙሪትና አገራዊ ቀውስ ባልተሻሻለበትና ጦርነት፣ የምርት መቀነስና፣ የስራ አጥነት ችግር በተባባሰበትና የብር የመግዛት አቅም በእጅጉ በወረደበት በዚህ ወቅት፤ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ መፍትሄዎችን መፈለግና የኑሮ ወድነቱንና የዋጋ ግሽበቱን ለማረጋጋት መሞከር ሲገባ፣ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑን ባለሙያው ይናገራሉ፡፡
መንግስት የነዳጅ ድጎማን በአንድ አመት ውስጥ በየምዕራፉ ሙሉ በሙሉ የማንሳት  ውሳኔው ከሶስት ወራት በፊት ባደረገው ጭማሪ መጠናቀቅ ነበረበት የሚሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ በአራት ምዕራፍ የድጎማ ማንሳቱ ተግባር ተፈፃሚ እንደሚሆን ተናግሮ የነበረ ቢሆንም፣ የዋጋ ጭማሪው ግን አሁንም ቀጥሏል ብለዋል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ውሳኔ መንግስት በተደጋጋሚ በሚያካሂደው ጦርነት ሳቢያ የሚያጋጥመውን የኢኮኖሚ ድቀት ለማቻቻል የሚደርገው ጥረት መሆኑን የሚያመለክቱት የጠቆሙት ባለሙያው፤ የዋጋ ጭማሪው የእያንዳንዱን ዜጋ የኑሮ ሁኔታ የሚነካና በአገሪቱ የሚታየውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነት የሚያባብስ አጉል ውሳኔ ነው ሲሉ ተችተውታል፡፡
የኑሮ ወድነት የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ደጃፍ ማንኳኳት ከጀመረ አመታት ቢቆጠሩም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአገሪቷ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሽቅብ ወጥቷል ያሉት ሌላው የምጣኔ ሃብት ምሁሩ አቶ ታረቀኝ ደጀኔ፤ በተለይም መንግስት የነዳጅ ድጎማን አንስቻለሁ ካለበት ጊዜ ወዲህ የኑሮ ውድነቱ መባባሱንና የብር የመግዛት አቅሙም በእጅጉ ማሽቆልቆሉን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት አመታት አገሪቱ ጦርነት ውስጥ መቆየቷ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን አባብሶት ቆይቷል ያሉት ምሁሩ፤ ከዚህ ቀደም የፍጆታ እቃዎችን ከውጪ ለማስገባት ይውል የነበረው የውጭ ምንዛሬ ለመከላከያና ደህንነት ተግባር መዋሉ አይቀሬ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
በሀገራችን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እንጂ ቅናሽ ሲያደርግ ታይቶ አይታወቅም ያሉት አቶ ታረቀኝ፤ የኮሮና ቫይረስ በተከሰተ ሰሞን የዓለም ነዳጅ ዋጋ እንዲያ በወደቀበትና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከዜሮ ዶላር በታች ይሸጥ በነበረበት ጊዜ እንኳን ምንም አይነት የዋጋ ማስተካከያ ሳይደረግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉ ከአገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም አንፃር አግባብ ሊሆን ብችልም፣ በዚህ የዋጋ ንረቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት፣ የህዝቡ ኑሮን የማሸነፍ አቅም ፈተና ላይ በወደቀበትና ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ ሊያጋጥም ይችላል የሚል ስጋት ባጠላበት ወቅት መደረጉ ግን ተገቢ አለመሆኑንም፣ መንግስት የዋጋ ግሽበቱ እንዳይባባስ የሚያደርጉና የኑሮ ውድነቱን ለማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎች ላይ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባው ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
በዓለም ዙሪያ ባሉ አገራት ውስጥ የነዳጅ መሸጫ ዋጋን የሚያቀርበው ስታስቲክስ ታይምስ ከአራት ወራት በፊት ባወጣው መረጃ መሰረት፣ ኢትዮጵያ ነዳጅ አምራች ከሆኑት አንጎላ ናይጄሪያና አልጀሪያ በመቀጠል በአፍሪካ ውስጥ በአነስተኛ ዋጋ የነዳጅ ምርቶችን ለህዝቧ የምታቀርብ አገር ናት፡፡


Read 1746 times